ምላጭ የያዘ እጅ

28 ሀምሌ 2023, 13:24 EAT

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ደደር ወረዳ፣ ልጆቻቸውን ያስገረዙ ሦስት እናቶች እና ግርዛቱን የፈጸመች ግለሰብ የእስር ቅጣት ተፈረደባቸው።

የወረዳው ዐቃቤ ሕግ ግርዛቱ በታዳጊ ሕጻናቱ ላይ በተለያዩ ጊዜያት መከናወኑን ለፍርድ ቤት አስረድቶ ነው በፈጻሚዎቹ ላይ የተለያዩ የእርስ ጊዜ የተፈረደባቸው።

ራሷን የባህል ሐኪም በማለት የምትጠራው ተከሳሽ ምስኪ መሐመድ ግርዛት ከፈጸመችባቸው ልጆች መካከል አንደኛዋ ያለ ቤተሰቧ ፈቃድ መገረዟን ዐቃቤ ሕግ ለቢቢሲ ገልጿል።

ዋና ተከሳሽ የሆነችው ምስኪ ግንቦት 19/2015 ዓ.ም. ልጅቷን ወደ ጎረቤት በመውሰድ ድርጊቱን ያለ ቤተሰቧ ፈቃድ እንደፈጸመች የደደር ወረዳ እና ከተማ አስተዳደር ዐቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ፈሬስ አራጎ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ምስኪ መሐመድ ከግንቦት ወር ወዲህ ብቻ አራት ሴት ሕጻናት ላይ ግርዛት መፈጸሟን የዐቃቤ ሕግ መዝገብ ያሳያል።

አቶ ፈሬስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ተከሳሿ የደደር ወረዳ ነዋሪ ስትሆን፣ ይህንን ወንጀል የፈጸመችውም በምትኖርበት ወረዳ ሙሚቻ ቀበሌ ውስጥ ነው።

ከተገረዙት ታዳጊ ሴቶች መካከል አንደኛዋ እድሜዋ 12 ሲሆን የተቀሩት ሦስቱ ደግሞ15 መሆናቸው ታውቋል።

ተከሳሽ ምስኪ መሐመድ ግርዛት የፈጸመችባቸው ታዳጊ ሴቶች ባለፈው ሳምንት ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም መሆኑ ተገልጿል።

ሁለቱን ልጆች ከእነዚያ ውስጥ የአንዷ እናት ወደ ሆነችው ወ/ሮ ኑርያ አሊዬ ሐሰን ቤት በመውሰድ እና የእርሷን ልጅ በመጨመር ግርዛቱ መፈፀሙን ዐቃቤ ሕጉ አስረድተዋል።

ድርጊቱ በዕለቱ ከጠዋቱ ከሦስት ሰዓት እስከ አራት ሰዓት ባለው ጊዜ በታዳጊ ሕጻናቱ ላይ የተፈጸመ ሲሆን፣ የባሕል ሐኪም ነኝ የምትለዋ ግለሰብ ግርዛቱን እንድታከናውን ሦስቱ እናቶች ከማገዛቸው በተጨማሪ ልጆቹ እንዳያስቸግሩ እናቶቹ ከእንጨት ጋር አስረዋቸው እንደነበር አቶ ፈሬስ ገልጸዋል።

ይህ ወንጀል ሲፈጸም ያዩ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ማመልከታቸውን አቃቤ ሕጉ ያስረዳሉ።

“እነዚህ ግለሰቦች ለመደበቅ ሞክረው ነበር። ነገር ግን የፀጥታ አካላት እና የቀበሌ መዋቅር ከሕብረተሰቡ ጋር በመሆን ከተደበቁበት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርገዋል ” ይላሉ አቶ ፈሬስ።

ዐቃቤ ሕጉ አክለውም በግርዛቱ ጉዳት የደረሰባቸው ታዳጊዎች በፍጥነት ወደ ደደር ሆስፒታል ተወስደው ሕክምና እንዲያገኙ ተደርገዋል።

ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ ሕጻናቱን ለማሳከም ደደር ሆስፒታል ሄደው እንደነበር የሚናገሩት አቶ ፈሬስ “ልጆቹ በጣም ተጎድተው እንደነበር ባለሙያዎች ሲናገሩ ነበር። ከዚህ ውጪም ልጆቹ ይህ ድርጊት እነደተፈጸመባቸው አረጋግጠዋል” ብለዋል።

እነዚህ ተከሳሾች ፖሊስ በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ ድርጊቱን አጣርቶ በደደር ወረዳ ፍርድ ቤት ክስ መስርቷል።

“የባሕል ሐኪሟ” ምስኪ መሐመድ በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 565 ስር ክስ ሲመሠረትባት፣ የሦስቱ ልጆች እናቶች ደግሞ በአንቀጽ 569 ክስ እንደተመሠረተባቸው የዐቃቤ ሕጉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አራቱ ተከሳሾች ወንጀሉን መፈጸማቸውን ለፍርድ ቤቱ በማመናቸው፣ ከዚህ በፊት የወንጀል ክስ መዝገብ ስለሌለባቸው እና የቤተሰብ ኃላፊ መሆናቸው መሆኑ ከግምት ገብቶ በቅጣት ማቅለያነት ተይዞላቸዋል።

በዚህም ፍርድ ቤቱ ሐምሌ 19/2015 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ተከሳሽ ምስኪ መሐመድ የስድስት ወራት ቀላል እስራት ሲፈረድባት፣ የሦስቱ ልጆች እናት የሆኑት ዘሃራ ሼኹ አልየ፣ አልፊያ ጣሂር እና ኑርያ ሐሰን አልዬ ደግሞ እያንዳንዳቸው የሁለት ወራት እስራት ተፈርዶባቸዋል።

በደደር ወረዳ ይህ ጉዳት የሚያስከትለው የግርዛት ድርጊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም፣ አሁንም አልፎ አልፎ የሚከሰት መሆኑን ኃላፊው ይናገራሉ።

በዚህ ዓመት ውስጥ ብቻ አራት የግርዛት ወንጀል መዝገቦችን መክፈታቸውን የሚናገሩት አቶ ፈሬስ አራጎ፣ ጽህፈት ቤታቸው በየጊዜው ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንደሚሰጡ ገልጸዋል።