
28 ሀምሌ 2023, 14:47 EAT
ተሻሽሏል 28 ሀምሌ 2023, 14:47 EAT
የሞሪታኒያ ባለሥልጣናት አንዲት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በፈተና ወረቀቷ ላይ የእስልምና ሃይማኖት ላይ በመሳለቅ አንቋሻለች በሚል በሞት ሊያስቀጣ የሚችል ክስ ተመሠረተባት።
ተማሪዋ በቁጥጥር ስር የዋለችው ከሳምንት በፊት ሲሆን፣ ድርጊቷም የእስልምና እምነት መሥራች በሆኑት በነቢዩ መሐመድ ላይ ማሾፍ እንደሆነ ተገልጿል።
ተማሪዋ ፈጽማለች ተብላ በተከሰሰችበት ድርጊት ጥፋተኛ ሆና ከተገኘች፣ ይግባኝ በለው የሞት ፍርድ ቅጣት ሊበየንባት እንደሚችል ተነግሯል።
ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ሞሪታኒያ እስልምናን የሚያንቋሽሽ ድርጊት በፈጸሙ ሰዎች ላይ የሚተላለፈውን ቅጣት በተመለከተ የነበራትን ሕግ የበለጠ ያጠናከረችው በቅርብ ዓመታት ውስጥ ነው።
ቀደም ሲል በነበረው ሕግ በእስልምና ላይ የተሳለቁ ወይም የማንቋሸሽ ድርጊት የፈጸሙ ሰዎች ጥፋታቸውን አምነው ከተጸጸቱ የሞት ቅጣት አይጣልባቸውም ነበር።
ነገር ግን ባለፉት 30 ዓመታት በላይ ባለው ጊዜ ውስጥ በተመሳሳይ ጥፋት የሞት ፍርድ የተፈጸመበት ሰው አልነበረም። ።
- የኒጀር መፈንቅለ መንግሥት መሪ፤ የፕሬዝደንቱ ክብር ዘብ መሪ የሆኑት ጀኔራል ሆነው ተገኙ28 ሀምሌ 2023
- የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስቴር በስህተት ምስጢራዊ ኢሜይሎችን ለማሊ ላከ28 ሀምሌ 2023
- ‘ዩፎ’ እና ባዕድ ፍጡራን የተከፋፈለውን የአሜሪካ ምክር ቤት አንድ አድርገውታል28 ሀምሌ 2023
በነቢዩ መሐመድ ላይ አሹፋላች ተብላ የተከሰሰችው ተማሪ በሞሪታኒያ ሰሜን ምዕራብ ግዛት ውስጥ አታር በተባለች ከተማ ውስጥ ከ10 ቀናት በፊት ነበር በሕግ አስከባሪዎች ቁጥጥር ስር የዋለችው።
በባለሥልጣናት የቀረበባት ክስም “በነቢዩ መሐመድ ላይ ማሾፍ እና ተገቢውን አክብሮት አለመስጠት” የሚል እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ “የእስልምናን ቅዱስ ዕሴቶችን ማጣጣል” መሆኑን በዋና ከተማዋ ንዋክሾት ውስጥ የሚገኙ አንድ የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግለፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ተናግረዋል።
ነገር ግን ተማሪዋ እንድትከሰስ ያደረጋት እና በፈተናዋ ወረቀት ላይ ጽፋዋለች የተባለውን ጉዳይ በተመለከተ ምንም አይነት ዝርዝር መረጃ አልተሰጠም።
የተማሪዋን መያዝ ተከትሎ ቤተሰቧ ለአንድ ጋዜጣ በጻፉት መግለጫ ላይ፣ ልጃቸው አእምሮ ጤና ችግር እንዳለባት በመግለጽ ምህረት እንዲደረግላት ጠይቀዋል።
ሌላ የአረብኛ ጋዜጣ ጉዳዩን አስመልክቶ እንደዘገበው፣ የተከሰሰችው ተማሪ ቤተሰቦች ሃራቲን የተባለው እና ከሰሃራ በታች ካለ የአፍሪካ ክፍል የፈለሱ ጎሳ አባላት ናቸው ብሏል።
ተማሪዋ በቁጥጥር ስር መዋሏ ይፋ የሆነው የሞሪታኒያ የሃይማኖት ባለሥልጣናት፣ ነቢዩ ሞሐመድን የሰደቡ ሰዎች የሞት ቅጣት ይገባቸዋል በማለት ከወጁ በኋላ ነው።
የሞሪታኒያ እስላማዊ ምሁራን ይህንን ሃይማኖታዊ ውሳኔ ባለፈው ሳምንት ያሳለፉት፣ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሚሐመድ ኡልድ ጋዡኒ የእምነቱ መሪዎች እስልምናን የሚያንቋሽሹ ሰዎችን በተመለከተ ያላቸውን አቋም ግልጽ እንዲያደርጉ ከጠየቁ በኋላ ነው።
እምነቱን በማንቋሸሽ ጥፋተና የሆኑ ሰዎች የሞት ቅጣት እንዲጣልባቸው ከመጠየቃቸው በተጨማሪ፣ በሌሎች ሃይማኖቱን በተመለተ ዝቅ ያሉ ጥፋቶችን የፈጸሙ ሰዎች ደግሞ አስከ ሁለት ዓመታት የሚደርስ እስር እና የገንዘብ ቅጣት ይጣልባቸዋል ተብሏል።