July 28, 2023

በሃሚድ አወል
ገዢው ብልጽግና ፓርቲ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በሚደረገው ውይይት ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ “እንደገና መልሶ እንደሚያጤነው” የፓርቲው የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዛዲግ አብርሃ ተናገሩ። አቶ ዛዲግ ይህን ያሉት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ እና ምርጫ ነክ ጉዳዮች ላይ ባደረጓቸው ተከታታይ ውይይቶች ወቅት ብልጽግና ፓርቲን የተመለከቱ ጠንከር ያሉ ትችቶች መቅረባቸውን ተከትሎ ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ውይይት እና ምክክሮችን ማድረግ የጀመሩት ካለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ጀምሮ ነው። ፓርቲዎች ውይይት ከሚያደርጉባቸው ጉዳዮች መካከል “ምርጫ እና ምርጫ ነክ ጉዳዮችን” የተመለከተው ይገኝበታል። በዚህ አጀንዳ ላይ ዛሬ አርብ ሐምሌ 21፤ 2015 ፓርቲዎቹ ለሁለተኛ ጊዜ ውይይት አካሄደዋል።
በአዲስ አበባው ኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል በተካሄደው በዛሬው መርሃ ግብር፤ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አፈጻጸምን፣ የምርጫ ስነ ስርዓትን እና የአካባቢያዊ ምርጫዎችን በተመለከተ ለሁለት ሰዓታት ገደማ የቡድን ውይይት አድርገዋል። የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮቹ ከቡድን ውይይቱ በኋላ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ተስተውለዋል ያሏቸውን “ተግዳሮቶች” ዘርዝረዋል።
ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ “የገዢው ፓርቲ ተጽዕኖ ነበረበት” ከሚለው አንስቶ፤ ሂደቱ “ነጻ እና ገለልተኛ አልነበረም” እስከሚለው ድረስ በተግዳሮትነት ተነስተዋል። ምርጫው “በብዙ አካባቢዎች አልተካሄደም” የሚለው አስተያየትም ሌላው በችግርነት የተነሳ ነው። የሲዳማ አንድነት ፓርቲ ጸሐፊ አቶ መንክር ኃይለሚካኤል፤ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ “በካድሬዎች እና በታጣቂዎች የተጠለፈ፤ በተጽዕኖ ስር የወደቀ ምርጫ ነበር” ሲሉ ጠንከር ያለ ትችት ሰንዝረዋል።
የምርጫው ውጤት “ጦርነትን ያዋለደ የነበረ ነው” ያሉት አቶ መንክር፤ በሀገራዊ ምርጫው “የተሳካለት ብልጽግና እና ተከታዮቹ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል። ለዚህ የአቶ መንክር ገለጻ የተወሰኑ የውይይቱ ተሳታፊዎች ድጋፋቸውን በጭብጨባ ገልጸዋል። የተቃዋሚ ፓርቲው ተወካይ ስለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ያቀረቧቸው ትችቶች፤ የብልጽግናው አቶ ዛዲግ አብርሃን “የአካሄድ ጥያቄ” እንዲያነሱ አድርጓቸዋል።
አቶ ዛዲግ “dialogue ከሆነ ውይይት እንደዚህ ነው ወይ የሚመራው?” ሲሉ የውይይቱ አካሄድ ላይ ጥያቄ ሰንዝረዋል። በእንዲህ አይነት ውይይቶች በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ምክክር የሚደረግባቸው ሊሆኑ እንደሚገባ ያመለከቱት የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊ፤ “ስለ እኛ ብዙ ይወራል…ለመሰዳደብ ነው የምንገናኘው ወይስ ውይይት ነው?” ሲሉ በአጽንኦት ጠይቀዋል። ብልጽግና ፓርቲን ወክለው በፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ላይ የሚገኙት አቶ ዛዲግ፤ “እኛ ይሄን ውይይት የምናስብበት ይሆናል። መልሰን እናጤነዋለን” ሲሉ ገዢው ፓርቲ በመሰል ውይይቶች ያለውን ተሳትፎ ላይቀጥል እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል።

ከአቶ ዛዲግ በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በውይይቱ ላይ የሚያቀርቧቸው ሀሳቦች የመወያያ ጉዳዩ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባው አስገንዝበዋል። በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ውይይት “አላሰራ ያሉ ህጎች እና አላሰራ ያሉ ፖሊሲዎች የሚቀየሩበት፤ መመሪያዎች የሚሻሻሉበትን ሁኔታ የመምከር እና ትልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለውጥ ለማምጣት [የሚደረግ] የልሂቃን ውይይት ነው” ሲሉ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ፋይዳውን አስታውሰዋል።
በፓርቲዎች ውይይት ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ለሀገራዊ ምክክሩ ግብዓት መሆን እንዳለባቸው የጠቆሙት አቶ ውብሸት፤ “እያንዳንዱ የምሰማው ነገር የአቋም መግለጫ ይመስላል” ሲሉ ተችተዋል። “ይህን ውይይት የአቋም መግለጫ የብሶት መድረክ [እና] የጉልበት መፈታተኛ አናድርገው” ሲሉም ለፓለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)