የኒጀር ፕሬዚዳንት መሃመድ ባዙም

ከ 9 ሰአት በፊት

አሜሪካ በመፈንቅለ መንግሥት ለተወገዱት የኒጀር ፕሬዚዳንት መሃመድ ባዙም “ያላሰለሰ ድጋፍ” እንደምታደርግ ገለጸች።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት መሃመድ ባዙም በክቡር ዘብ መሪያቸው ጄነራል አብዱራህማኔ ቺያኒ ወይም በተለምዶ ኦማር ቺያኒ በተመራ መፈንቅለ መንግሥት ከስልጣናቸው ተነስተዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን መሪውን መሃመድ ባዙምን በቁጥጥር ስር ላዋሏቸው ግለሰቦች ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል።

ለአገሪቱ የሚደረገው “በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር እርዳታ”ንም አደጋ ውስጥ እንደሚከተው ነው የተናገሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።

የቀድሞው የፕሬዚዳንቱ ክቡር ዘብ መሪ የኒጀር አዲሱ መሪ መሆናቸውን አውጀዋል።

ፕሬዚዳንት መሃመድ ባዙም ኒጀር ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት በጎሮጎሳውያኑ 1960 ነጻ ከወጣች በኋላ የአገሪቷን መሪ እንዲተኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጡ መሪ ናቸው።

በአካባቢው ከሚገኙ ጽንፈኛ ታጣቂዎች ጋር በሚደረገው ውጊያም ምዕራባውያኑ እንደ ቁልፍ አጋር ይቆጥሯቸዋል።

በራሳቸው ጠባቂዎች ታግተው የሚገኙት ፕሬዚዳንቱ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙም ይታሰባል።

ብሊንከን ፕሬዚዳንቱን ለሁለተኛ ጊዜ በስልክ ያናገሯቸው ሲሆን አሜሪካ “በኒጀር ህገ መንግሥታዊ ስርዓቱ ሙሉ በሙሉ ወደቀደመ ሁኔታ እንዲመለስ እና ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርን ለማረጋገጥ” ትሰራለች ብለዋል።

ከፕሬዚዳንት መሃመድ በፊት የኒጀር መሪ የነበሩትን ማሃማዱ ኢሶፉን ብሊንከን ያናገሯቸው ሲሆን “መሃመድ ባዙምን በቁጥጥር ስር ያዋሉ ግለሰቦች ለዓመታት የተደረገውን የተሳካ ትብብር እና በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እርዳታን አደጋ ላይ መጣላቸው ያሳዝናል” ሲሉም መናገራቸውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ቢሮ ቃለ አቀባይ ማት ሚለር ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንቱ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል።

ምክር ቤቱ በተጨማሪም “ህጋዊ መንግሥትን ኢ-ህገመንግሥታዊ በሆነ መልኩ ለመቀየር የሚደረግን ጥረት” አውግዟል።

የቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ በበኩሏ መፈንቅለ መንግሥቱን ላካሄዱ መሪዎች እውቅና እንደማትሰጥ እና የፕሬዚዳንት መሃመድ ባዞምን አስተዳደር ብቻ እንደምትቀበል ተናግራለች።

በቡርኪናፋሶ እና ማሊ ተመሳሳይ መፈንቅለ መንግሥት መደረጉ የሚታወስ ሲሆን በኒጀርም ተመሳሳይ ሁነት መከናወኑ የሳህልን ቀጠና የበለጠ አደጋ ውስጥ ከቶታል።

መፈንቅለ መንግሥቱ በአፍሪካ ህብረት፣ የምዕራብ አፍሪካ ቀጠናዊ ቡድን (ኢኮዋስ)፣ የአውሮፓ ህብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ በአለም አቀፍ አካላት ሙሉ በሙሉ ተወግዟል።