July 29, 2023 – BBC Amharic 

OUTIN AND AL SISIS

ከ 8 ሰአት በፊት

የሩሲያው ፕሬዛዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባስተናገዱት የሩሲያ አፍሪካ ስብሰባ ላይ የግብጹ ፕሬዛዳንት ጠንከር ያለ ሃሳብ አንስተዋል።

ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ዩክሬን እህል ወደ ውጭ እንድትልክ የሚያስችለው ስምምነት በፍጥነት እንዲታደስ የሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲንን በብርቱ አሳስበዋል።

ስምምነቱ “ወሳኝ” ነው ያሉት አብድል ፈታህ አል ሲሲ፣ ችግሩ በፍጥነት ተቀርፎ ድሃ አፍሪካውያን መፍትሄ ሊያገኙ ይገባል ብለዋል።

ሩሲያ ከስምምነቱ የወጣችው ባለፈው ሳምንት ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የጥቁር ባሕር ወደብን በቦምብ እያጋየችው ነው።

ለማሳሰቢያው ምላሽ የሰጡት ፕሬዝዳንት ፑቲን፣ ምዕራባውያን የመደራደሪያ ነጥቦችን ባለማክበራቸው ስምምነቱ መፍረሱን ጠቅሰው፣ ለአፍሪካውያን ግን ከራሳቸው ካዝና እህል እንደሚልኩ ገልጸዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜም ስድስት የአፍሪካ አገራት የዚሁ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርገዋል።

ሩሲያ እህሉን በነጻ እንደምትሰጥም ተናግረዋል።

ግብጽ በጥቁር ባሕር በኩል በሚደረገው የዩክሬን የእህል ሽያጭ ዋነኛ ተዋናይ ነች።

በዚህም ምክንያት በጥቁር ባሕር ያለው የእህል ገበያ ሲዘጋ ግብጽ ከፍተኛ የምግብ ቀውስ ውስጥ ትገባለች።

ከጦርነቱ በፊትም የእህል ዋጋን መጨመር በምዕራባውያን በኩል የተስተዋለ የፖሊሲ ችግር እንደነበርም ፕሬዝዳንት ፑቲን አንስተዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ የዓለምን የምግብ ቀውስ ችግር እልባት ለመስጠት ሩሲያ የራሷን እህል እንደምትልክ ፕሬዝዳንት ፑቲን አረጋግጠዋል።

ሩሲያ በሚቀጥሉት ሦስት እና አራት ወራት ለቡርኪና ፋሶ፣ ዚምባብዌ፣ ማሊ፣ ሶማሊያ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ እና ኤርትራ ለእንዳንዳቸው ከ25 እስከ 50 ሺህ ቶን ስንዴ ለመለገስ ቃል ገብታለች።

የእህል እርዳታው በቀዳሚነት የተደረገላቸው ስድስቱ የአፍሪካ አገራት ከሶማሊያ በስተቀር የሩሲያ አጋር ናቸው። በሌላ በኩል እነዚሁ አገራት በሰብዓዊ ቀውስ የሚታመሱም ናቸው።

ሩሲያ ከስምምነቱ ከወጣች ጊዜ ጀምሮ የጥቁር ባሕር ወደብን እያጋየችው ሲሆን ብዙ መጋዘኖችና በብዙ ሺህ ቶን የሚቆጠር እህልን አውድማለች።

ከእህል ግብይት በተጨማሪ የአፍሪካ መሪዎች በሁለተኛ ቀን ውሏቸው ስለ ሰላምም ተወያይተዋል።

መሪዎቹ በዩክሬን ላይ የተጀመረው ጦርነት እንዲያበቃ በአፍሪካውያን ዘንድ የቀረበውን የመነሻ ሃሳብ እንዲቀበሉም ፕሬዝነዳት ፑቲንን ጠይቀዋል።

ያቀረቡት የመደራደሪያ ሃሳብ የሩሲያ እና የዩክሬን ሉዓላዊነት እውቅና እንዲሰጠው፣ በፍጥነት የሰላም ውይይት እንዲጀመር እና ያልተገደበ እህልን ለውጭ ገበያ የመላክ ሂደት እንዲፈጠር ማድረግ ነው።

የኮንጎ ብራዛቪሉ ፕሬዝዳንት ዴኒስ ሳሱ ንጉኤሱ ይህ ሃሳብ ችላ ሊባል የማይገባው መሆኑን ገልጸዋል።

በእርግጥ ፕሬዝዳንት ፑቲን ሃሳቡን እንደሚያጤኑት ተናግረዋል።

ነገር ግን የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ሩሲያ ከያዘቻቸው ግዛቶች እስካልወጣች ድረስ ሃሳቡ ዋጋ ቢስ መሆኑን አስረግጠዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ያደረገችው ጦርነት የአገሪቱን ጥቁር ባሕር ወደብ ዘግቶታል። ይህ ደግሞ ወደ ውጭ ሊላክ የነበረ 20 ሚሊዮን ቶን እህል እንዲስተጓጎል አድርጓል።

ይህም በዓለም የምግብ ዋጋ መናር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳረፈ ሲሆን በተለይ በአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያስከትላል የሚል ስጋትን ደቅኗል።

ሰሞኑን ሩሲያ ያፈረሰችው ስምምነት ባለፈው ዓመት በቱርክ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አሸማጋይነት የተደረገ ሲሆን ይህም ዩክሬን ነጻ መሬት ተሰጥቷት እህል ወደ ውጭ የምትልክበት ዕድል የፈጠረ ነበር።

ዩክሬን እንደ ገብስ፣ ስንዴ እና በቆሎ የመሳሰሉትን እህሎች ወደ ውጭ በመላክ በዓለም ቀዳሚ ከሆኑ አገራት መካከል ነች።