
ከ 7 ሰአት በፊት
በምስራቃዊ ዩክሬን በምትገኘው ዲኒፕሮ ከተማ ትናንት ሌሊት [አርብ] ሩሲያ የሚሳኤል ጥቃት ፈጽማለች። በጥቃቱ የጋራ መኖሪያ ቤት እና አንድ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ሕንጻ ኢላማ ተደርገዋል።
የከተማዋ ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት በጥቃቱ ቢያንስ 9 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ሁለቱ ሕጻናት መሆናቸው ታውቋል።
የቢቢሲ የዘገባ ቡድን በስፍራው ተገኝቶ እንዳረጋገጠው የጋራ መኖሪያ ቤት ጣሪያ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተደርምሷል።
ንብረትነቱ የዩክሬን የደኅንነት መሥሪያ ቤት የሆነ ግዙፍ ሕንጻም የጥቃቱ ሰለባ ሆኗል
ጥቃቱን የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ “የሩሲያ የሚሳኤል ሽብር” ብለውታል።
ዘሌንስኪ ከተደረመሰው ሕንጻ የሚወጣን ጭስ እና በጎዳና ላይ የሚንቦገቦግ የእሳት ነበልባልን በቴሌግራም ገጽ አጋርተዋል።
ክስተቱን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ የአካባቢው ባለስልጣናትንና የተመረጡ የካቢኔ አባላትን በመጥራት ለአስቸኳይ ስብሰባ መቀመጣቸውን ገልጸዋል።
- አነቃቂ ንግግሮች ወዴት ያደርሱናል? ወደ የማይጨበጥ ተስፋ ወይስ ወደ ስኬት?29 ሀምሌ 2023
- ዩክሬን ከሩሲያ ትውፊቶች ራሷን ለማራቅ የገና በዓልን ዕለት ቀየረችከ 9 ሰአት በፊት
- ሩሲያ የዩክሬንን እህል የመላክ ስምምነት እንድታከብር የግብጹ መሪ አሳሰቡከ 9 ሰአት በፊት
የአከካባቢው አስተዳዳሪ የሆኑት ሰርኺ ሊሳክ በጥቃቱ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል የ14 እና የ17 ዓመት ታዳጊዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል።
እስካሁን በጥቃቱ ከደረሰው ጉዳት ውጭ የተመዘገበ የሞት መጠን አለመኖሩን አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
የከተማዋ ከንቲባ ቦሪስ ፊላቶቭ እንደገለጹት ደግሞ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ሕንጻ ኢላማ ሲደረግ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።
ሁለቱ ሕንጻዎች በአብዛኛው ክፍት የነበሩ ሲሆን የጋራ መኖሪያ ቤትም በቅርቡ ተጠናቆ ለኪራይ ዝግጁ በሚሆንበት ወቅት ይህ ጥቃት መፈጸሙን ከንቲባው ተናግረዋል።
ይህ ጥቃት የተፈጸመው ሩሲያ ትናንት [አርብ] ከዩክሬን የተተኮሱ ሚሳኤሎችን ሮስቶቭ ክልል አካባቢ ማክሸፏን ከገለጸች በኋላ ነው። በዚህ ሂደትም ከከሸፈው ሚሳኤል በወደቀው ስብርባሪ ቢያንስ 15 ሰዎች መጎዳታቸውን ሞስኮ ገልጻ ነበር።
የሩሲያ የመከላከያ ሚንስትር እንደገለጹት የመጀመሪያው ሚሳኤል ኢላማ አድርጎ የነበረው 250 ሺህ ሕዝብ በሚገኝባት ከተማ የመኖሪያ ሰፈርን ነው።
ሚንስትሩ ከዚህ በተጨማሪም ወዲያውኑ ሌላ ሚሳኤል መትተው መጣላቸውን ያስታወቁ ሲሆን፣ ስብርባሪውም ባዶ መሬት ላይ ማረፉን ገልጸዋል።
የሮስቶቭ ክልል አስተዳዳሪ ቫሲሊ ጎሉቤቭ እንደገለጹት ታጋንሮግ በተባለው አካባቢ 15 ሰዎች በከሸፈው ሚሳኤል ስብርባሪ መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ታጋንሮግ ከዩክሬን ድንበር በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አዞዝ ተብሎ በሚጠራው የባሕር ዳርቻ አካባቢ የምትገኝ ስፍራ ነች።
ከተማዋ ወደ ማሪዮፖል የወደብ ከተማ የመሄጃ መንገድ ላይ የምትገኝ ነች። ስትራቴጂኳ ከተማ ማሪዮፖል ባለፈው በነበረው ጦርነት በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት ደርሶባታል።