
ከ 7 ሰአት በፊት
ቬትናም በኮቪድ-19 ወረርሽ ወቅት ወደ አገራቸው የሚመለሱ ዜጎችን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ከፍተኛ ጉቦ በመጠየቅ ሙስና ፈጽመዋል ያለቻቸውን ከፍተኛ ባለስልጣናት አሰረች።
የሃገሪቱ የቀድሞ ሚኒስትርና ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ 54 ግለሰቦችን ከፍተኛ ሙስና በመፈጸም ወንጀለኛ ናቸው ሲልም የቬትናም ፍርድ ቤት ብያኔ አስተላልፏል።
ባለስልጣናቱ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ወደ አገራቸው መመመለስ ከሚፈልጉ የቬትናም ዜጎችን ገንዘብ መመዝበራቸውንም ዳኛዎቹ ተናግረዋል።
አንድ የቀድሞ ሚኒስትር ከ900 ሺህ ዶላር በላይ ጉቦ በመቀበል የ16 ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ መንግሥት በአስተዳደሩ ላይ የታየውን ሙስና ለማስወገድ የከፈተው ዘመቻንም ተከትሎ ነው።
ከሁለት ሳምንታት በላይ በፈጀው የፍርድ ሂደት የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ጨምሮ በርካታ የቀድሞ ባለስልጣናት፣ ከፍተኛ ዲፕሎማት ጉቦ በመቀበል፣ በማጭበርበር እና ስልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።
ባለስልጣናቱ፣ ዲፕሎማቱና ተባባሪዎቻቸው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የንግድ በረራዎች መከልከላቸውን ተከትሎም ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉ የቬትናም ዜጎች ከፍተኛ ገንዘብ በመቀበልም መልሰዋቸዋል ተብሏል።
ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ “ከባድ ቅጣት ሊጣልባቸው ይገባል” ብሏል።
የመንግሥት ጋዜጣ የሆነው ቪቲሲ እንደዘገበው 25 የመንግሥት ባለስልጣናት በድምሩ 7.4 ሚሊዮን ዶላር ጉቦ በመቀበል ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።
- አሜሪካ በመፈንቅለ መንግሥት የተወገዱት የኒጀር መሪን እንደምትደግፍ ገለጸች29 ሀምሌ 2023
- https://www.bbc.com/amharic/articles/clkvj4lv77ko
- https://www.bbc.com/amharic/articles/czrg0npvxz1o
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በጤና እና የህዝብ ደህንነበት ሚኒስቴር ውስጥ ባሉ በአራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይም የእድሜ ልክ እስርም ተበይኖባቸዋል። በዚህም ጉቦና ሙስና ላይ ነጋዴዎችና ግለሰቦችም ተባባሪ ነበሩ ተብሏል።
የአገሪቱ የቀድሞ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ጸሃፊ ፋም ትሩንግ ኪን እንዲሁም የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ቶ አንሀእ ዱንግ ከዚህ ሙስና ጋር ተያይዞ ስማቸው በከፍተኛ ሁኔታም ሲነሳ ነበር። በ11 ወራት ጊዜ ውስጥ 253 ጉቦዎችን በመቀበል በድምሩ 1.8 ሚሊዮን ዶላር አግኝተዋል በተባሉት ጸሃፊው ፋም ላይ አቃቤ ህግ የሞት ቅጣት እንዲፈረድባቸው ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ የዕድሜ ልክ እስር በይኖባቸዋል።
በጎሮጎሳውያኑ 2020 ቬትናም ድንበሯን ከዘጋችበትና ከሌሎች አገሮች ለሚመለሱ ዜጎች ብቻ ጉዞን በፈቀደችበት ወቅት መንግሥት 800 በራራዎችን አዘጋጅቶ ነበር።
ማህበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ ሌሎች ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ተመላሾች ወደ ቬትናም ለመግባት ውድ የበረራ ዋጋን ጨምሮ በርካታ ውስብሰብ ሂደቶች እንዳጋጠማቸው ነው።
አንዲት እናት ልጃቸውን ከአውሮፓ ወደ ቬትናም ለማምጣት 12 ሺህ ዶላር መክፈል እንደነበረባቸው ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።