ሮበርት ኦፕንሃይመር

29 ሀምሌ 2023, 07:43 EAT

ሆሊውድ አሉኝ ከምትላቸው ዳይሬክተሮች አንዱ ክሪስቶፈር ኖላን “የአቶሚክ ቦምብ አባት” እያሉ ስለሚጠሩት ኦፕንሃይመር የሕይወት ታሪክ አንድ አስደናቂ ፊልም ሠርቷል።

ይህ በሲኒማ ወዳጆች ዘንድ ዕውቅና እያተረፈ ያለ ፊልም በመላው ዓለም በሰልፍ እየታየ ነው።

ነገር ግን ይህ ፊልም ሕንዳውያንን ለሁለት የከፈለ ይመስላል። ምክንያቱ ደግሞ ባጋቫድ ጊታ ነው። ከሒንዱ እምነት ቅዱስ መጽሐፍት መካከል አንዱ።

ሮበርት ኦፕንሃይመር በፊልሙ እንደሚታየው ከአንዲት ሴት ጋር አንሶላ ከተጋፈፈ በኋላ ይህን መጽሐፍ ያነባል።

ኦፕንሃይመር እጅግ ከሚወዳቸው መጽሐፍት መካከል አንዱ በጥንታዊው ሳንስክሪት ቋንቋ የተፃፈው ባጋቫድ ጊታ ነው።

ሐምሌ 1945 (እአአ) የመጀመሪያው አቶሚክ ቦምብ ሙከራ በአሜሪካዋ ኒው ሜክሲኮ በረሃ ሊካሄድ ሁለት ቀናት ሲቀሩት ሮበርት ኦፕንሃይመር ከባጋቫድ ጊታ መጽሐፍ መስመሮች እየመዘዘ ያነበንባል።

የፊዚክስ ንድፈ-ሐሳብ ሊቅ የሆነው ኦፕንሃይመር የሕንድ ጥንታዊ ቋንቋ የሆነውን ሳንስክሪት ያጠናው በበርክሌይ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ሳለ ነው።

ባጋቫድ ጊታ አሊያም የአምላክ ሙዚቃ የተሰኘው መጽሐፍ ከሒንዱ እምነት ታላቅ መጽሐፍት አንዱ ተደርጎ ይቆጠራል።

የዓለምን ታሪክ ከቀየሩ ክስተቶች መካከል አንዱ አቶሚክ ቦምብ ነው። እነሆ “የአቶሚክ ቦምብ አባት” ቦምቡን ከማፈንዳቱ በፊት እንዲህ ሲል አነበነበ [ግርድፍ ትርጉም]፡

በአውድማ፣ በጫካ፣ በተራራ መሐል፣ ድንጋይ በወረረው

ጨለማ በዋጠው ሐይቅ፤ በቀስቶቹ መካከል እሣት በጎረሰው

በእንቅልፍ ሰመመን፣ ግራ በመጋባት፣ ጥልቅ ሐፍረት በዋጠው

የሰው ልጅ ቀድሞ ለፈፀመው መልካም ነገር ሁሉ ብርታትን ሆነው።

ካይ በርድና ማርቲን ሼርዊን በፈርንጆቹ 2005 በፃፉት ‘አሜሪካን ፕሮሚቲየስ’ የተሰኘ የሮበርት ኦፕንሃይመር ግለ ታሪክ፤ ኦፕንሃይመር በካሊፎርኒያው በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ ሳለ ከሳንስክሪት እንደተዋወቀ ያወሳሉ።

በወቅቱ የ25 ዓመት ወጣት የነበረው ኦፕንሃይመር፣ ረዳት ፕሮፌሰር ሆኖ ነው ወደ ዩኒቨርሲቲው ገብቶ የነበረው።

በወቅቱም ወጣቱ የፊዚክስ ምሁር የሳንስክሪት ፕሮፌሰር ከሆኑት ሪፐብሊካኑ አርተር ራይደር ጋር ለመተዋወቅ ችሏል።

ኖላን በሠራው አዲሱ ፊልም ተዋናይ ሲሊያን መርፊ፣ ኦፕንሃይመርን ሆኖ ይጫወታል። በዚህ ፊልም ላይ ኦፕንሃይመር የሳንስክሪት ፕሮፌሰር የሆኑት ራይደርን በዘመናት አንድ ጊዜ ብልጭ ከሚሉ ሰዎች መካከል አድርጎ ይቆጥራቸዋል።

እኒህ በኦፕንሃይመር ዐይን እጅግ የተከበሩ ምሁር ሐሙስ ሐሙስ ምሽት ለወጣቱ የፊዚክስ ሰው የሳንስክሪት ቋንቋ ያስተምሩት ይጀምራሉ።

“ሳንስክሪት መማር ጀምሪያለሁ” ሲል ኦፕንሃይመር ለወንድሙ ፍራንክ ደብዳቤ ይጽፋል፤ “እጅግ በደስታ ነው እየተማርኩ ያለሁት ይገርምሃል” ብሎ አስፍሯል።

በርካታ ጓደኞቹ ይህ ሰው ጥንታዊ የሕንድ ቋንቋ ለመማር መቁረጡ ግራ ሆኖባቸው ነበር። ከእነዚህ መካከል አንዱ ሃሮልድ ቸርኒስ ግን ይህ አልገረመውም። ኦፕንሃይመር እና ፕሮፌሰሩን ያስተዋወቃቸው እሱ ነውና።

ለዚህ ነው የክሪስቶፈር ኖላን፣ ኦፕንሃይመር እና ጊታን ለይቶ ፊልም መሥራት እንደማይቻል ያወቀው።

ነገር ግን አንዳንድ ቀኝ ዘመም የሒንዱ እምነት ተከታዮች በለተይ ደግሞ ከፍቅረኛው ጂን ታትሎክ ጋር ወሲብ ከፈፀመ በኋላ ጊታን ማነብነቡ ሃይማኖቱ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው ይህ ክፍል ተቆርጦ ይውጣ ሲሉ እየጠየቁ ነው።

ቢሆንም የሕንድ የፊልም ሐያሲያን ግን ፊልሙ ምንም ችግር የለበትም ብለዋል። ፊልሙም ሕንድ ውስጥ እጅግ ተወዳጅ ሆኖ ከሁሉ ልቆ እየመራ ይገኛል።

አልበርት አይንስታይንና ሮበርት ኦፕንሃይመር
የምስሉ መግለጫ,አልበርት አይንስታይንና ሮበርት ኦፕንሃይመር ቀኑ ባልተጠቀሰ ፎቶ

ኦፕንሃይመር እጅግ ያነበበ ሰው መሆኑ የተደበቀ አይደለም። የፍልስፍና ትምህርት ወስዷል፤ ስለፈረንሳይ ሥነ-ጽሑፍ አጥንቷል፤ እንግሊዝኛ ተምሯል፤ ታሪክ መርምሯል።

አልፎም ሥነ-ሕንፃ ለመማር ከጫፍ ደርሶም እንደነበር ይነገራል። ሠዓሊ አሊያም ገጣሚ የመሆን ፍላጎትም ነበረው። ብቸኝነት እና ሐዘንን የሚቃኙ ግጥሞችን ጽፏል።

ለቋንቋ ትልቅ ክብር ያለው ሳይንቲስቱ ግሪክኛ፣ ላቲን፣ ፈረንሳይኛ እና ጀርመንኛ ያጠና ሲሆን፣ የደች ቋንቋን ለማወቅ ስድስት ሳምንታት ነው የወሰዱበት።

ከዚያ ወደ ባጋቫድ ጊታ አቀና። “እጅግ ቀላል እና አስደናቂ” ሆኖ እንዳገኘው ለጓደኞቹ መናገሩን ግለ-ታሪኩ ይጠቅሳል።

“በየትኛውም ቋንቋ ከተፃፉ ሙዚቃዎች እጅግ ማራኪ የፍልፍስና ሙዚቃ ነው” ሲል ጊታን የሚያሞጋግሰው ኦፕንሃይመር፣ የመጽሐፍ መደርደሪያው ላይ ሮዝ ቀለም ያለው ከራይደር የተበረከተለት የጊታ መጽሐፍ ይታያል።

በ1933 (እአአ) አባቱ ክራይስለር የተሰኘ ቅንጡ መኪና ሲገዙለት በሒንዱ እምነት ግዙፏ የወፍ አምላክ በምትባለው ጋሩዳ ስም ሰይሟታል ነበር።

በዚያው ዓመት ለወንድሙ በጻፈው ደብዳቤ በምሥራቁ ዓለም ፍልስፍና እጅግ መማረኩን ያስረዳል።

ኦፕንሃይመር ብቻ ሳይሆን ሄንሪ ዴቪድ ቶራው፣ ይትስ እና አሊየት የተሰኙት ታላላቅ ገጣሚያንም በጊታ ይማረካሉ። የናዚ ፓርቲ አባል የነበረው ሃይንሪኽ ሃይምለርም የእምነቱ አድናቂ ነበር። ማሐትማ ጋንዲ ፅኑ ተከታይ ነበሩ።

ኦፕንሃይመር የአቶሚክ ቦምብ ሙከራውን ሲያደርግ ሰማይ ላይ የተመለከተው ግዙፍ የእንጉዳይ ቅርፅ ያለው ብርቱካናማ እሣት እና ጭስ ወደ ጊታ እንዲመለስ ገፋፉት።

በሁለተኛው ዓለም ጦርነት በጃፓን የሂሮሽማ እና ናጋሳኪ ከተሞች የፈንዱት አቶሚክ ቦምቦች በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድለዋል።

“ዓለም በለመደችው መንገድ እንደማትቀጥል እናውቃለን። ጥቂቶች ሳቁ፤ ጥቂቶች አለቀሱ። ብዙዎቹ ግን ዝም አሉ” ሲል በ1965 (እአአ) ኤንቢሲ ለሠራው ዘጋቢ ፊልም ተናግሮ ነበር።

ኦፕንሃይመር ቦምቡ ሲፈነዳ ካነበነባቸው የጊታ ቃላት መካከል እጅግ ታዋቂው “እነሆ አሁን እኔ ሞት ሆኛለሁ። ዓለማትን የማጠፋ” የሚለው የሚታወስ ነው።