የተሰበሰቡ ሰዎች

27 ሀምሌ 2022

ተሻሽሏል 29 ሀምሌ 2023

*መካሪና ሰባኪ በዝቷል። ከመገናኛ እስከ ኢኒስታግራም፤ ከዩትዩብ እስከ ድልብ መጻሕፍት፣ ከመድረክ እስከ ታክሲ፤ በተለይ አራተኛ ወንበር ላይ።

የሁሉም መልዕክት አንድ ነው፤ ‘የብልጽግና ባቡር ቀርባለችና ተሳፈሩ’ የሚል።

በየዓመቱ መቶ ሺዎች እየተመረቁ ሥራ ያጣሉ። ‘የሥራ ፍጠሩ’ ሰባኪዎች ይቀበሏቸዋል።

በስንት ደጅ ጥናት የተገኘን ሥራ ‘ጥላችሁ ውጡ’ ይላሉ። ዛሬውኑ የራሳችሁ አለቃ ሁኑ እያሉ ያስጎመዣሉ።

ከእጅ ወደ አፍ ቀርቶ፣ እንደ ወፍ – ከአፍ ወደ አፍ በሆነ የዛሬ ኑሮ፣ ‘ከቆጠባችሁ ከነገ ወዲያ ሚሊዮነር ትሆናላችሁ’ ይላል።

አነቃቂ መጻሕፍት ሕይወት ይለውጣሉ? የመድረክ ዲስኩሮች ያበለጽጋሉ?

አንዳንዶች ‘አዎና! እኛን ነው ማየት!’ ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ በአነቃቂ መጻሕፍት የሚለወጥ ሕይወት ካለ የደራሲው እና የዲስኩረኛው ብቻ ነው ብለው ያፌዛሉ።

በሁለቱም ጎራ የካበተ ልምድ ያላቸውን አሰልፈን ጉዳዩን ብናብላላውስ?

ዶ/ር ወሮታው፡ “የአንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ሕይወት ለመለወጥ እየሠራሁ ነው”

በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ግንኙነት ሦስተኛ ዲግሪ አላቸው። የእርሳቸው ሥራ ግን የሰዎችን አእምሮ ከብልጽግና ጋር ማዋደድ ነው። ወጣቶችን ወደ ሃብት ማማ ማውጣት።

የትኛውንም አእምሮ በመግራት ስኬት እና ልዕልናን ማጎናጸፍ ይቻላል ብለው ያምናሉ።

እንደተመረቁ የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት ተቀጠሩ፣ ከዚያም ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ አስተማሪ ሆኑ።

ከዕለታት አንድ ቀን “ሕይወቴን የሚለውጥ አጋጣሚ ተፈጠረ” ይላሉ ዶ/ር ወሮታው።

ቀን እና ወሩን ሁሉ አይረሱትም። በ1992 ዓ.ም. ነሐሴ ወር ከዩኒቨርስቲው ከጋና በመጡ አሠልጣኞቹ በሚሰጥ ሥልጠና ላይ እንዲሳተፉ ተላኩ።

ሥልጠናውን ሲጨርሱ ከባድ የአስተሳሰብ ነውጥ ገጠማቸው። የአስተሳሰብ ነውጡ፣ የሕይወት ለውጥን አስከተለ።

“በዚያች ቅጽበት የራሴን ነጻነት አወጅኩ፤ ከዚያ በኋላ በጭራሽ አልተቀጠርኩም፤ በጭራሽ!” ይላሉ።

“ተቀጥሮ መሥራት አንገሽግሾዎት ስለነበር ነው ዶ/ር?”

“አይደለም፤ በዚያች ቅጽበት የምኖርለትን ሕልሜን ስላገኘሁ ነው።”

“የሚኖሩለት ሕልም ምንድን ነበር?”

“ማሠልጠን፤ ባለጸጎችን ለኢትዮጵያ ማፍራት።”

“የምር ይሳካል ብለው ያምናሉ?”

“ያለጥርጥር! አንድ ሚሊዮን ባለጸጎችን ለኢትዮጵያ እናፈራለን።”

“መቼ ነው ይህን ሁሉ ሰው ባለጸጋ የሚያደርጉት?”

“የዛሬ 20 ዓመት፤ በነሐሴ 2023 ዓ.ም።”

ዶ/ር ወሮታው ይህን የሚሉበት እርግጠኝነት የእምነታቸውን ጥንካሬ ያሳብቃል። እንዴት ያለ ሥልጠና ቢሆን ነው?

“…በዚያ ሥልጠና ወሮታው ላይ ሳቅኩበት፤ ወሮታውን ነጻ አወጣሁት። ለሕልሜ ታማኝ እንድሆን፣ ሃብቴ አስተሳሰቤ እንደሆነ፣ የማምንበትን እየሠራሁ እንድኖር ያደረገኝ አጋጣሚ ነበር።”

የእሳቸው ሕይወት በአንድ ሥልጠና ከተለወጠ የሌሎች ሕይወት ለምን አይለወጥም?

ናትናኤል ፋንታ፡ “የሞቲቬሽን ሥልጠና በብድር መደሰት ማለት ነው”

‘ናትናኤል ሜሞሪ’ በሚለው የንግድ ስሙ በርካቶች ያውቁት ይሆናል።

የሕይወቱን እኩሌታ በአእምሮ ሥልጠና ላይ አሳልፏል።

ናትናኤል በተለይ በማስታወስ ጥበቡ በ90ዎቹ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ እየቀረበ ብዙ ሰዎችን ሲያስደምም አንዳንዶች ዛሬም ድረስ ያስታውሱታል።

ናትናኤል ከማስታወስ ጥበብ በኋላ በቀጥታ ወደ ‘ሞቲቬሽን’ [ማነቃቃት] ተሸጋገረ።

ብቻ በጥቅሉ ባለፉት በ21 ዓመታት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ከአእምሮ ጋር በተያያዘ አሠልጥኗል።

የእሱን ልብ አንጠልጣይ ‘ሞቲቬሽን’ ቃል ለመስማት ብዙዎች አዲስ አበባ 22 አካባቢ ደጅ ጠንተዋል።

እሱም ያንን ዘመን በመለስተኛ ፀፀት እያስታወሰ፣ “…ሙሉ ጉባኤ ቁጭ ብድግ አስደርግ ነበር” ይላል።

አሁን ግን ፍጹም በተቃራኒው ቆሟል። የአነቃቂ ንግግሮች አድናቂ አይደለም። እንዲያውም ‘ሞቲቬሽን’ አይሠራም ሲል አውጇል።

“ከዚህ ሁሉ ዘመን በኋላ ያረጋገጥኩት አንድ ነገር ቢኖር፣ የሰዎችን ሕይወት ለመለወጥ ትክክለኛው መንገድ ያ እንዳልነበረ ነው” ይላል።

ለምን? በ21 ዓመት ውስጥ ምን ተፈጠረ? ትክክለኛው መንገድ ያ ካልሆነ ታዲያ የቱ ነው?

በዓመታት ጥናት ደረስኩበት የሚለውን ይነግረናል።

የአነቃቂ መጻሕፍት አጭር የሕይወት ታሪክ

ራስ አገዝ መጻሕፍት፣ የይቻላል ዲስኩሮች እና መሰሎቻቸው በጅምላው ‘ሰልፍ ዴቨሎፕመንት ኢንዱስትሪ’ ውስጥ ይካተታሉ።

በአሜሪካ በአንድ ወቅት ከሙዚቃ ኢንዱስትሪው ቀጥሎ ሚሊዮን ዶላር የሚያንቀሳቅስ ዘርፍ ነበር። በተለይ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ወዲህ።

የአነቃቂ መጻሕት አባት የሚባለው ቻርልስ ሃናል ነው።

ኋላ የመጡት ገናናዎች የእርሱ ደቀ መዛሙርት ናቸው።

በዘመኑ የጻፈው ነገር አእምሮን የሚያሸፍት ነበር።

“…ኋላ ላይ እንዲያውም ቤተ ክርስቲያን መጽሐፎቹን ለቅማ አቃጥላበታለች” ይላል ናትናኤል።

ከእርሱ በኋላ አብረሃም ማስሎው መጣ። “አእምሮን በመግራት ማንም ሰው ምንም መሆን ይችላል” ብሎ ተነሳ።

ቀስ በቀስ ሞቲቬሽን ከቤት እና ከቢሮ ወጥቶ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ሰተት ብሎ ገባ።

የይቻላል መንፈስ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንቀጾች ጋር ስምም ተደርጎ በሰባኪዎች አንደበት ተነገረ።

ሚሊዮኖች በተስፋ ራሳቸውን ሳቱ። ያለስስት ጥሪታቸውን ለሰባኪያን ሸለሙ።

ከአፋቸው ማር ጠብ የሚልልላቸው ሰባኪያን መቅደስ ጠበባቸው። በቲቪ መስኮት መጡ።

‘ቴሌቫንጀሊስቶች’ ተወለዱ። በስብከት ጉባኤ መዋጮ የግል ጄት ገዙ። ምዕመናን የታክሲ እያጡ፣ እየነጡ መጡ።

ካፒታሊዝም ፋፋ። የገበያ ትንቅንቅ ተፈጠረ።

‘ሞቲቬሽን’ ሽያጭን የሚያስመነድግ ሁነኛ መሣሪያ እንደሆነ ተደረሰበት።

ሰዎች የስቶክ ማርኬት የድርሻ ገበያ እንዲገዙ ማሳመን ፈተና ሆኖ ነበር።

ለዚያም ነው በሞቲቬሽን አእምሯቸውን ማጦዝ፣ በተስፋ ካውያ ማጋል አስፈላጊ ሆኖ የተገኘው።

እንዲህ፣ እንዲያ እያለ በ80ዎቹ እና በ90ዎቹ የሞቲቬሽን ኢንዱስትሪ ጣሪያ ነካ። ደራሲያን መጻሕፍትን በሚሊዮኖች ቅጂ መሸጥ ጀመሩ።

በእኛም አገር ‘ኔትዎርክ ማርኬቲንግ’ በስፋት ዘልቆ ገባ።

የ’ጎልድ ኩዌስት’ ዘመን፣ የፒራሚድ ገበያን ለማሳለጥ ሁነኛ የ’ሴልስ’ ስትራቴጂ ኾኖ አገለገለ።

ሐኪሞች ሆስፒታልን፣ መምህራን አስኳላን ጥለው ወጡ፤ ወደ ሀብት ይወስዳል የተባለው አውራ ጎዳና በሕዝብ ታመቀ፣ ተጨነቀ።

ብዙዎች “አይቤን ማን ወሰደው”ን እያነበቡ አይባቸውን ፍለጋ ባዘኑ። አንዳንዶች አገኙት። ብዙዎች አጡት።

ናትናኤል ያን ዘመን የነበረውን አስደማሚ መነቃቃት ሲያስታውስ፣ “አዳራሽ ውስጥ ‘I believe I can fly’ የሚል ሙዚቃ ተከፍቶ ሰዎች በተስፋ ብቻ ሲያለቅሱ አይቻለሁ” ይላል።

ይህን ነው እሱ “የብድር ደስታ” የሚለው። ምን ማለቱ እንደሆነ ቆየት ብሎ ያስረዳናል።

የዴል ካርኒጌ ዘመን

እርግጥ በእኛ አገር ብቻም ሳይሆን አሜሪካ ገበያ እነ ዴል ካርንጌ፣ እነ ናፖሊዮን ሒል የጻፏቸው መጻሕፍት ከባድ የአስተሳሰብ አብዮት አስነስተዋል።

በተለይ ናፖሊዮን ሒል ለ25 ዓመታት 500 የሚሆኑ እጅግ የናጠጡ ባለጸጎች ላይ ጥናት ሠርቶ “Think and Grow Rich” የሚለውን መጽሐፉን ከጻፈ በኋላ ምድረ አሜሪካ በ‘ይቻላል’ ተነቃንቋል።

ከዚያ ወዲያ ‘ሞቲቬሽን ዘርፍ’ ሳይከስም እየጎመራ ነው የቆየው።

በርካታ በዓለም ዙሪያ የተሰራጩ የማነቃቂያ መጻሕፍት ታትመው ሚሊዮኖች ጋር ደርሰዋል።

ዛሬ ደግሞ ለቲክቶክ ዘመን በሚስማማ መልኩ በሚጻፉ፣ ቶሎ ተጥደው፣ ቶሎ በሚገነፍሉ፣ ቶሎ ተነበው ቶሎ የሚጣሉ (Use and throw) መጻሕፍት ብቅ ብለዋል።

ገበያ የሚወዳቸው ሞቲቬሽኖች

የሚገርመው በዓለም የገነኑት የማነቃቂያ መጻሕፍት አብዛኞቹ በሚሊዮኖች ቅጂ የታተሙ ናቸው።

ከየትኛውም የመጻሕፍት ዘውግ (Genre) ባልተናነሰ ሁኔታም ወደ አማርኛ ተመልሰዋል።

በኢትዮጵያ ገበያ ሌሎች መጻሕፍት 3 ሺህ ቅጂን ለማለፍ ፍዳቸውን በሚያዩበት ጊዜ፣ እነሱ እንደዋዛ በ20 እና 30 ሺህ ቅጂ ይታተሙም ነበር።

አሁን ግን መጻሕፍቱ በመድረክ ዲስኩሮች እየተተኩ ይመስላል።

ፋይዳቸው ዘላቂ ነው? ብለን ብንጠይቅ አልዘገየንም ለማለት ነው።

እውን ናትናኤል እንደሚለው ሞቲቬሽኖች ‘የብድር ደስታ’ መፈልፈያ ፋብሪካዎች ናቸው? ወይስ ዶ/ር ወሮታው እንደሚሉት ሰዎችን ወደላቀ ልዕልና የሚያደርሱ አውራ ጎዳናዎች?

በሙግቱ ትንሽ እንግፋበት እና እናገባድ።

የተሰበሰቡ ሰዎች

“በስድስት ዓመት ውስጥ ራሴን አፍርሼ ሠራሁት”

ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ያመቻቸላቸው ሥልጠና አዲስ የብርሃን ዘመን የከፈተላቸው ዶ/ር ወሮታው፣ ከዚያ ወዲያ የሞቲቬሽን መጻሕፍትን እያሳደዱ ማንበብ ጀመሩ።

እሳቸው ወጣት ሳሉ የቭላድሚር ሌኒን እንጂ የናፖሊዮን ሒል መጻሕፍት አልነበሩም።

ስለ ግል ቢዝነስ ማሰብም ነውር ነበር።

የወላጅ ዘመድ የመጨረሻ ሕልምም ልጄ ተቀጥሮ ደመወዝ ይበላል ወይስ አይበላም የሚል ነበር።

ከ1992 ዓ.ም. ወዲህ ግን እነ ናፖሊዮን ሒል ብቅ አሉ። እሳቸውም “Think and Grow Rich”ን ነበር መጀመሪያ ያነበቡት።

ከፍተኛ መነቃቃት ፈጠረላቸው። ከዚያ ወዲያ የሞቲቬሽን መጽሐፍት አደን ውስጥ ገቡ።

ዘመኑን መለስ ብለው ሲያስታውሱ “ከዚያች ሥልጠና ወዲህ በነበሩ ስድስት ዓመታት ነበር ራሴን አፍርሼ እንደ አዲስ የሠራሁት” ይላሉ።

ሞቲቬሽን የሚሠራው እንዴት ነው?

አእምሯችን ከልጅነታችን ጀምሮ የሐሳብ ድር ሲያደራ ነው የኖረው።

በቀን በአማካይ ከ60 ሺህ በላይ የሐሳብ ዘለላዎችን ይመዛል፤ ይፈትላል። እያነሳ ይጥላል።

ከዚህ ሁሉ ሺህ የሐሳብ ደውር አብዛኛው ፀፀት እና ተስፋ ነው። ትናንት እና ነገ።

በሌላ አነጋገር አእምሯችን ወይ ወደ ትናንት ይንሸራተትብናል፤ አሊያ ደግሞ ወደ ነገ ይስፈነጠራል።

ዛሬ ላይ፣ አሁን ላይ ሁን ስንለው እሺ አይልም።

ለዚህም ነው “ከቀልቡ የሆነ ሰው ማግኘት አስቸጋሪ የሚሆነው” ይላል ናትናኤል።

ከቀልብ መሆን ምን ማለት ነው?

ክፍል ውስጥ አስተማሪ ስም ሲጠራ በአካል የተገኘውን ተማሪ ለመቁጠር ነው። ከቀልቡ የሆነ ሰውን ‘አቴንዳንስ’ ቢይዝ ግን አስተማሪው ራሱ ‘አብሰንት’ ሊባል ይችላል።

ከቀልብ መሆን ቀላል ነገር አይደለም። ሐሳብን ማቆም የዋዛ አይደለም።

ሌላ አብነት፤ ሰዎች መለኪያ ውስኪ የሚጎነጩት ኋላ እና ፊት የሚፈነጭን ሐሳብ ለማስቆም ነው። የሆነ መለኪያ ቁጥር ላይ ስንደርስ ይህ ይሳካል።

ፊልም የምናየውም ለተመሳሳይ ግብ ነው። ሐሳብን ለማስቆም። በምንወደው ፊልም ውስጥ እጅግ ፍሰሐ የምናደርገው ያ ቀዥቃዣው ሐሳብ ቢያንስ ለአንድ ሰዓት ስለሚቆም ነው።

አለበለዚያ በ5 ደቂቃ የ15 ዓመት ፀፀት እያሰብን ሕመም ውስጥ እንገባለን፤ እናረጃለን።

ወደ ዋናው ነጥባችን እንምጣ።

አነቃቂ (ሞቲቬሽን) ንግር ስንሰማ ወይም ጽሑፍ ስናነብ ከፍታ ላይ እንወጣለን፤ የስሜት ማማ ላይ።

ብዙዎቹ በቁማችን ቂቤ ያጠጡናል። ምኞታችንን እንድናመነዥግ ያግዙናል፤ በዲስኩር፣ በመጽሐፍ የሕልም ዓለም ውስጥ ያንሳፍፉናል።

ስለዚህ ከፍተኛ የስሜት መነቃቃት ይፈጠርብናል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ታዲያ ከሰዎች መማር፣ ጥልቅ የንባብ ፍቅር ውስጥ መግባት፣ በራስ ማመን ሊፈጠሩ ይችላሉ።

“ሞቲቬሽን ወደ ጠንካራ ዲሲፕሊን የመራቸው ሰዎች አሉ፤ ይህ በጎ ገጽታው ነው” ይላል ናትናኤል።

ክፋቱ ግን ሞቲቬሽን በራሱ ሱስ ሊሆን ይችላል።

ወደ እውነታው ስንመለስ ስለሚያመን እዚው መቅረት እንመርጣለን። ከሞቲቬሽን ወደ ሞቲቬሽን።

በማነቃቂያ መድኃኒት የምንሠራ ከሆነ የዚያ መድኃኒት ጥገኛ መሆናችን አይቀርም። ሞቲቬሽን ሱስ ነው። ሁሉም ሱስ ሃንጎአር አለው፤ ሞቲቬሽንም ቢሆን፣ ይላል።

ናትናኤል በሞቲቬሽን አብዮት ጊዜ ብዙ በጎ ነገሮች እንደተፈጠሩ አይክድም።

ሰዎች ንባብን ለምደዋል። ከአዲስ ሐሳብ ጋር ተዋውቀዋል። የጊዜ አጠቃቀማቸው ተሸሽሏል።

የሞቲቬሽን መሠረታዊ ችግሩ ግን አንድ ነው ይላል፤ “የብድር ደስታን መፍጠሩ።”

ሞቲቬሽን የደስታ ወረፋ ውስጥ ያሰልፈናል ይላል።

“ወደፊት ይህ ዓይነት መኪና፣ እንዲህ ዓይነት ቤት፣ እንዲያ ዓይነት ትዳር ሲኖረኝ ደስተኛ እሆናለሁ…” ካልን የደስታ ወረፋ ውስጥ ነን ማለት ነው።

ከአነቃቂ ንባብ/ዲስኩር በኋላ ሰዎች መጠነኛ ድብርት ውስጥ ይገባሉ የሚለው ናትናኤል ምክንያቱ “የብድር ደስታ ውስጥ ስለነበሩ ነው” ይላል።

“እኔም በሞቲቬሽን ሙሉ ጉባኤ ሙሉ ቁጭ ብድግ የማደርግበት ጊዜ ነበረ። ይሄ እኔ ሳልሆን ተማሪዎቼ የሚመሰክሩት ነገር ነው። ስህተት እንደሆነ ለመረዳት ግን ጊዜ ወስዶብኛል።”

ታዲያ መፍትሄው ምንድነው?

ሃብታም ሳይሆኑ ሃብታም የመሆን ምሥጢርን ማስተማር አይከብድም?

በአሜሪካ ብዙዎቹ የብልጽግና ሰባኪዎች፣ የይቻላል አቀንቃኞች ቢያንስ የሃብት ጥያቄያቸውን መልሰዋል።

ሚሊዮን ቅጂዎችን ሽጠዋል። ሕዝብ አነቃንቀዋል።

በእኛ አገር ይህ ብዙም አይታይም።

የሃብትን ምሥጢር፣ የብልጽግናን ቁልፍ እንካችሁ የሚሉን ሰባኪዎች ለራሳቸውም ያወቁ የማይመስሉበት አጋጣሚ አለ።

ይህን ጥያቄ ለዶ/ር ወሮታው አንስተንላቸው ነበር።

ሁሉንም በአንድ ቅርጫት ማስቀመጥ አግባብ እንዳልሆነ ጠቀሱ።

በልምድ እና በሕይወት ተሞክሮ አልፈው የሚያሠለጥኑ አሉ። አዳራሽ ሕዝብ ሰብስበው ያለ ምንም የሕይወት ልምድ፣ ሕዝብ ላይ ቴአትር የሚሠሩም አሉ።

“ለምሳሌ ናፖሊዮን ሒል ‘ቲንክ ኤንድ ግሮው ሪች’ን ሲጽፍ 25 ዓመት ነው የወሰደበት።”

ስለዚህ እያሉን ያሉት ዶ/ር፣ ችግሩ ከሥልጠናው ሳይሆን ከአሠልጣኞቹ ነው?

“አዎ! ለምሳሌ የእኔ አሠልጣኞች ያሰብከውን ስላለምክ ብቻ ትደርስበታለህ አላሉኝም። ለስኬት የምከፍለው ከፍተኛ ዋጋ እንዳለ ነው ያስተማሩኝ።”

ባልተፈተነ ሕይወት፣ በጣፈጠ ቋንቋ ብቻ በሰው አእምሮ መጫወት ትክክል አይደለም የሚሉት ዶ/ር ወሮታው “ሙሉ አዳራሽ አስፈንጥዞ ማስወጣት ይቻላል። እኔ ያንን አልከተልም።”

ዶ/ር ግን የማነቃቂያ ሥልጠና በመስጠት ሰውን ከድህንት ማውጣት ይቻላል? የምር ይህ ዘዴ ይሠራል ብለው ያምናሉ?

“እንዴታ! ሰው ከዋሻ የወጣው ከችግር ለመውጣት ነው። ቁርጠኝነት እና ዓላማ ካለ ምን የማይሠራ ነገር አለ። ደግሞም በኢትዮጵያ። አንድ ሰው 8 ሰዓት ቢሮ ከሠራ ሌላውን 8 ሰዓት ባጃጅ ቢነዳ ምንድነው ችግሩ። የመለወጥ ቁርጠኝነት ካለ ማለቴ ነው።”

ዶ/ር ሌላው ጥያቄ ሰዎችን አትቀጠሩ እያላችሁ ለምን በተሳሳተ መንገድ ታበረታታላችሁ?

“ተቀጥረህ አትቅር እናለለን እንጂ አትቀጠር አንልም። ሰው ልምድ ማግኘት አለበት እኮ።”

የመጨረሻ ጥያቄ ዶ/ር፣ ሃብት እና ብልጽግናን የምትሰብኩ ሰዎች ለራሳችሁም ሃብት አልፈጠራችሁም ይሏችኋል?

“ይህ የተሳሳተ ነው። የእነ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ አሰልጣኝ ሯጭ ሳይሆን ለምን ያሰለጥናል ይባላል እንዴ? አዋቂ ያወቀውን ቢያስተምር በቂ ነው።”

ዶ/ር ወሮታው ይህን ካሉ በኋላ ግን በልምድ እና በዕውቀት ያልዳበረ ሕይወት ሌላውን ለማብቃት ባይደፍር መልካም እንደሆነ አልሸሸጉም።

እርሳቸውም ከእነዚህ አንዱ እንዳልሆኑ እንዲህ መልሰዋል።

“እኔ ሚሊዮነር ሆኛለሁ፤ 20 ጊዜ የታተመ መጽሐፍ አለኝ። ሌላ 12 ጊዜ የታተመ መጽሐፍ አለኝ። 6.6 ሚሊዮን ሕብረት ባንክ አክሲዮን አለኝ፤ የማከራየው ቤት አለኝ፤ ገንዘብ መሥራት የጀመረ ዩቲዩብ አለኝ። ምን ትፈልጋለህ?”

ስለዚህ ሞቲቬሽን ይሠራል ነው የሚሉኝ?

“አዎ! የሰው ልጅ ዋናው ሃብቱ አስተሳሰቡ ነው። የሰው ልጅ ሃብቱ የመሬት ስፋት ቢሆን ሲንጋፖር አትኖርም ነበር። ምቹ መሬት ቢሆን ጃፓን አትኖርም ነበር። ዋናው ነገር ከአንገት በላይ ያለን አካል በአግባቡ መጠቀም ነው።

“እኔ ያን ሥልጠና ባልሳተፍ አሁን ጡረታ ወጥቼ ዳማ ስጫወት ነበር የምታገኘኝ። መሠልጠን በመቻሌ ግን ገና የ30 ዓመት ሕልም አለኝ።”

የናትናኤል አማራጭ መንገድ

ዶ/ር ወሮታው ከሚሉት በተቃራኒው የሚቆመው ናትናኤል እንደ ግለሰብም እንደ አገርም ለገባንበት ቀውስ መፍትሄው የሞቅታ ሞቲቬሽን አይደለም ይላል።

ታዲያ መፍትሄው ምንድነው ሲባል “ኮንሽየስ መሆን” ብሎ በድፍኑ ይመልሳል።

ከቀልብ መሆን፣ መንቃት፣ ያለንበትን ማወቅ ማለቱ ነው።

ሞቲቬሽን ያልነቃ ሕዝብ ኪስ ውስጥ ገብቶ ገንዘብ ለማውጣት ይሰራል። ለፖለቲከኞችም ሕዝብን ለመንዳት ይጠቅማል።

ምንጊዜም ያልነቃ ሕዝብ አእምሮ ውስጥ የሞቲቬሽን ጠብታ በመጨመር ማስከር ይቻላል። ለውጥን በሞቲቬሽን ማምጣት ግን ፍጹም አይቻልም ይላል።

“ጃፓን ድምጽ የለም፤ ሥራ ግን ይሠራል። እኛ ጋር ግን አገሩ ሁሉ በሞቲቬሽን ቀረርቶ ተሞልቷል። ለምን ይመስልሃል?”

ሞቲቬሽን መር ፍልስፍና እንደ አገር አይበጀንም የሚለው ናትናኤል፣ ይህ ያልተጨበጠ ባለጸጋ የመሆን ዲስኩር ከአስተዳደር አልፎ ወደ እምነት ቤቶች መግባቱን ይተቻል።

“ብዙ ቸርቾች ውስጥ አሁን አሁን ወንጌል ሳይሆን ሞቲቬሽን ነው የሚሰበከው። ኢየሱስ ምን ሊያመጣልኝ ይችላል እንጂ መቼ ይመጣል የሚል ሰው ከምዕመኑ ዘንድ የለም።”

“አገራችን ካለችበት ቀውስ ለመውጣት ሞቲቬሽን አይሠራም። እንችላለን፣ ታላቅ ነበርን፣ ታላቅ ነን በሚል ፉከራ አገር አይለወጥም። ከባድ ቀውስ ውስጥ ነን። ሞቲቬሽን ለዚህ መፍትሄ አያመጣም።”

ናትናኤል በተደጋጋሚ አሁን አማራጩ ‘ኮንሺየስነስ’ን መሞከር ነው ሲል አበክሮ ይሞገታል።

ምንድነው ኮንሺየስነስ ሲባል ግን የተፍታታ መልስ መስጠትን ገሸሽ ያደርጋል።

“መንቃት። በአእምሮ ሰላም ውስጥ መሆን። ከቀልብ መሆን። አሁን ላይ መሆን።”

ይህ ማለት ምን ማለት ነው?

“አጠገብህ የሚሻክር ነገር አለ?”

“አዎ!”

“ካለ ስሜቱን በቃላት ግለጽልኝ?”

ገለጽኩለት።

“አሳምረህ በቃላት ስሜቱን ገልጸኸዋል፤ እኔን ግን አልሻከረኝም።”

ለማለት የፈለከው አልገባኝም።

“ኮንሺየስነስ እንደዚያ ነው። ትኖረዋለህ እንጂ ቃላት በመደርደር አትገልጸውም። ወሬ ሳይሆን ተግባር ነው።”

***

*ይህ ጽሑፍ ባለፈው ዓመት “ሚሊየነር የመሆን ጥበብን የሚሰብኩን ሰዎች ለምን ‘ድሆች’ ሆኑ?” በሚል ርዕስ በቢቢሲ አማርኛ ላይ ወጥቶ የነበረ ሲሆን፣ ከጥቂት ማሻሻያ ጋር በድጋሚ የቀረበ ነው።