
JULY 30, 2023

ለአንድ አገር ኢኮኖሚና ዕድገት የግል ዘርፉ ሚና የማይተካ መሆኑ ይታመናል፡፡ የአገሮች ዕድገት የሚመሠረተውና የሚለካው የግል ዘርፉ በሚኖረው ተሳትፎ ነው፡፡ የአገሮች የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በቀዳሚነት የሚያመለክቱትም ይህንኑ ነው፡፡ ያለ ግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የማይታሰብ መሆኑን በማመን የግል ዘርፉን በመደገፍ አገራዊ ኢኮኖሚያቸውን እያሳደጉ ስለመሆኑ ከማንም የተወሰረ አይደለም፡፡
ነገሩን ከኢትዮጵያ አንፃር ስናየው መንግሥት አገራዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ሲቀርፅ ይህንን ዓለም የሚሰማማበትን ሐሳብ አካትቷል፡፡ ስለ ግሉ ዘርፍ በተደጋጋሚ የሚጠቅሰውም የመንግሥት ዕቅዶች የግሉ ዘርፍ ካልተሳተፉበት የማይሳካ መሆኑ ነው፡፡ ኢኮኖሚው መመራት ያለበት በግሉ ዘርፍ መሆኑንም በየመድረኩ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ስለ ግሉ ዘርፍ የመናገር ዕድል ሲያገኙ የሚያወሱት ነው፡፡ ያለ ግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የአገራዊ የዕድገት ግቦችን ማሳካት የማይቻል መሆኑን ደጋግመው የመናገራቸውን ያህል ከግሉ ዘርፍ ጋር ተቀራርበው ሲሠሩ አይታይም፡፡
ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ቁጥር አንድ ተሳታፊ የግሉ ዘርፍ ከሆነ ተገቢው ድጋፍ ሊደረግበት ሲገባ ለምን አልተደረገለትም ተብሎ ቢጠየቅ ትክክለኛ ምላሽ የሚሰጥ የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ የግሉ ዘርፍ ሞተር ነው እየተባለ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች ሲቀረፁ፣ የግሉ ዘርፍ በበቂ ደረጃ እንዲሳተፍ አይደረግም፡፡ እነሱን የሚመለከቱ ፖሊሲዎችም ሆነ ሕግጋቶች ከመውጣታቸው በፊት ቀድሞ ሐሳብ እንዲሰጥበት ዕድል ሲሰጠውም አይታይም፡፡ መንግሥት በራሱ መንገድ የሚቀርፃቸው ፖሊሲዎች ብቻቸውን ውጤት ሊያመጡ አለመቻላቸውም ታስቦ ኢኮኖሚያዊ የሆኑ ድንጋጌዎችና ማሻሻያዎች ላይ የግሉ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖረው ያለመደረጉ ደግሞ ብዙ ነገሮችን አሳጥቷል፡፡
የግል ዘርፉን የሚመለከቱ ብዙ መመርያዎች በወረዱ ቁጥር በኋላም ችግር ሲፈጥሩ የምናየው በአግባቡ ያልተመከረባቸው በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ችግር ዛሬ የተፈጠረ ሳይሆን ትናንት የነበረ አሁንም እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ መታወቅ ያለበት ግን የግሉ ዘርፍ በሚባለው ልክ ሲደገፍ የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆነው መንግሥት ስለመሆኑ አይጠረጠርም፡፡ የተሻለ ገቢ ማግኘት የቻለ የግል ዘርፍ የተሻለ ግብር ይከፍላል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ዛሬ የአገሪቱ ከፍተኛ ራስ ምታት እየሆነ የመጣውን የዋጋ ንረት ለመቀነስም ቢሆንም በምክክርና በመግባባት መሥራት ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡
አገሪቱ በዋጋ ንረትና ባልተገባ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ሆና በምትተዳደርበት በዚህ ወቅት፣ የሸማቹን ኅብረተሰብ እሮሮ ለመቀነስ ነጋዴውና የመንግሥት አካላት ተመካክረው እንዲህ ያለ መፍትሔ አመጡ የሚል ዜና ለመስማት ያልታደልነው በትብብር የመሥራት ባህላችን ደካማ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡
ዛሬ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የሚታየውን ለከት ያጣ ችግር ለማምከንም መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ሲነጋገሩ ያልሰማነው ተመካክሮ መፍትሔ ከማምጣት ይልቅ፣ ማዶ ለማዶ ሆኖ አንደኛው ሌላኛውን ተጠያቂ በማድረግ መጠመዳቸውን ያሳየናል፡፡ ቢሆን ሰዶ ማሳደድ ሳይሆን ለችግሩ መፍትሔ ለማበጀት መነጋገርና መተራረም ያስፈልጋል፡፡
ቋሚ የሆነ የመወያያ መድረክ እንኳን የላቸውም፡፡ ከዓመታት በፊት በቋሚነት ይደረግ የነበረው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ ሳይስተጓጎል እንዲካሄድ ያለመቻሉ በራሱ የሚነግረን ተቀራርቦ የመሥራት ችግር ያለ መሆኑ ነው፡፡
የንግድ ኅብረተሰብ ተወካዮች የሚባሉት፣ ንግድ ምክር ቤቶችም ለዚህ የራሳቸው አስተዋጽኦ ያላቸው ሲሆን ጠንካራ ሆነው ያለመውጣታቸውም የችግሩ አካል ያደርጋቸዋል፡፡
የንግድ ምክር ቤቶች አንዱ ተግባራቸው መንግሥትና የግል ዘርፉን ድልድይ ሆነው ማገናኘት፣ በወቅታዊ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በጥናት ላይ የተመሠረተ ሐሳብ ይዞ በመቅረብ መፍትሔ ማፈላለግ ቢሆንም ይህንን ሲያደርጉ አይታዩም፡፡ ለዋጋ ንረት መባባስ ሕገወጥ ነጋዴዎች የሚፈጥሩት ያልተገባ ተግባር ሆኖ ሳለ ይህንን ሲገስጹና መልካሙ ደግሞ ሲያበረታቱ አለመታየታቸው ራሱ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ ስለዚህ ለአገር ተባብሮ ላለመሥራት እንዲሁም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቶሎ ለመፍታት ጠንካራ የንግድ ኅብረተሰብ ወኪሎች ያለመኖራቸው ነው ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡
በአጠቃላይ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ተቀራርበው እስካልሠሩና ተለዋዋጭ የሆነውን ኢኮኖሚ ሁኔታ በመመልከት ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እስካልተቻለ ድረስ ኢኮኖሚን ማሳደግ አይቻልም፡፡
ዓለም አቀፋዊ ውድድር በበዛበትና አገራዊ የዋጋ ንረት ጎልቶ በወጣበት በዚህ ወቅት ተጋግዞ መሥራት የግድ መሆን አለበት፡፡ ተጋግዞና ተባብሮ እንዲሁም ተነጋግሮ ለችግሮች መፍትሔ መስጠት ባለመቻሉ፣ ዛሬም የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ተመሳሳይ የሆኑ ችግሮች አሉብኝ ብሎ በአደባባይ እየተናገረ ነው፡፡ ከሰሞኑ ከዓመታት በኋላ ተቋርጦ እንደገና ተጀመረ በተባለው የግሉ ዘርፍና የመንግሥት የምክክር መድረክ ላይ መታዘብ የቻልነውም ይህንኑ ነው፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብ ዛሬም የማልሚያ መሬት ዕጦት ችግር አለብኝ እያለ ነው፡፡ በፋይናንስ አቅርቦት ችግርና በውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚገባኝን ሥራ ለመሥራት አልቻልኩም ብሎ እያማረረ ነው፡፡ አላሠራ ያሉ መመርያዎች እንዲሻሻሉ ጥያቄ እየቀረበ ነው፡፡
መረን የለቀቀው ሙስናና የአገልግሎት አሰጣጥ አለመቀላጠፍ፣ ዛሬም ከነጋዴዎች የመፍትሔ ያለህ የሚባልበት ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ከታክስ ጋር በተያያዘም ተመሳሳይ ጥያቄዎች ይቀርባሉ፡፡ ስለዚህ አገርን ለማሳደግ የግሉ ዘርፍ ያስፈልገናል ከተባለ ያሉ ችግሮችን ነቅሶ በአግባቡ ምላሽ የሚሰጥ የመንግሥት አካል ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ጠንካራ የንግድ ማኅበረሰብ ወኪሎችንም ማፍራት ግድ ይላል፡፡