
July 30, 2023
ተሟገት አገርን ሰላም የነሳት ሰላማዊ ያልሆነ ትግል ነው
ቀን: July 30, 2023
በገነት ዓለሙ
የአገራችን የሰላምና የዴሞክራሲ ጉዳይ ዛሬም የሕዝብን ሆድ እየቆረጠ ያለ ዋነኛው ብሔራዊ አጀንዳ ነው፡፡ ዴሞክራሲን ለማቋቋም የሚያስችሉ ለውጦች ውስጥ ብንገባም የጉዞ ዓይነትም (የትግሉ ሥልትም) የጉዞው መስመር፣ ፌርማታና መዳረሻ ላይ ሁላችንም የገጠመ አመለካከት ስለመያዛችን ዛሬም እያጠራጠረ ነው፡፡ ዴሞክራሲን አልወድም፣ አልፈልግም፣ እንዲያውም እታገለዋለሁ፣ ፀረ ዴሞክራሲ ነኝ የሚል ባይኖርም፣ የለም እንጂ፣ ዴሞክራሲን ማቋቋም ማለት ገለልተኛና ነፃ ተቋማትን ማቋቋም፣ የኢትዮጵያን የመንግሥት አውታሮች ፓርቲያዊነት በማፅዳትና ነፃና ገለልተኛ አድርጎ በመቅረፅ ነው እስከ ማለት ድረስ የሚስማሙ የሉም፡፡ አገራችን ውስጥ ዴሞክራሲ! ዴሞክራሲ! እያለ የሚፎክረው፣ የሚከራከረው፣ የሚወራረደው ሁሉ ዴሞክራሲ ማለት ከየትኛውም ፓርቲ ወገናዊነት ነፃ የሆነ የተቋም ግንባታ የግድ ያስፈልጋል የሚል አቋም ድረስ ሲሄድና ሲስማማ አናይም፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ሰላምን እንዲያስከትል የፖለቲካው መድረክ ለሁሉም በእኩልነት መከፈት ያለበት ስለመሆኑ ሁሉም እኩል ያምናል? ይህንን ዕውን ለማድረግስ ልዩ ልዩ ሐሳቦችን፣ የተለያዩ ፍላጎቶችን፣ የሚጣሉ አቋሞችን የማስተናገድ ልምምድ ብቻ ሳይሆን፣ ማስተናገድና ማስተናበር ምን ማለት እንደሆነ ጨርሶ ሰምቶም የማያውቀው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ዝም ብሎ ይፈቅዳል ወይ? እዚያ ውስጥስ ዝም ብሎ ሰተት ብሎ ይገባል ወይ? የኢትዮጵያ የፖለቲካ አየር እየጠራ፣ እየሰከነና ወደ ሠለጠነ የፖለቲካ ኃይሎች ሰላማዊና ሕጋዊ ግብግብ ተለውጧል? ለውጠነዋል ወይ? ፖለቲካው ውስጥ፣ የፖለቲካው ሒደት ውስጥ ማን ትክክለኛ ማን ስህተተኛ ለመሆኑ መለያው መንገድ ጦርነት ነው ወይ? ጦርነትስ ውስጥ የማን ዓላማ ያሸንፋል? ወይስ የሕዝብን ፈቃድ ረትቶና አግኝቶ፣ የድምፅ ብልጫ አስመዝግቦ ፍላጎትንና ዓላማን ውሳኔና ሕግ ማድረግ የሚያስችል የጋራ የጨዋታ ሕግ፣ የመጫወቻ መድረክና የፖለቲካ አየር መመሥረት ነው?
ይህንን ጥያቄ ለማንሳት የተገደድኩት ከብዙ መከራና ምክር፣ ከእጅግ ብዙ የመከራ ምክር በኋላ የሰላም ስምምነት ላይ ደረስን፡፡ ፕሪቶሪያ ላይ የተፈረመው ስምምነት በዚያ ሁሉ መስዋዕትነት ዋጋና ኪሳራ፣ ለዓለምም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ያሳወቀውና ያወጀው፣
- ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ትግራይ ክልል ውስጥ የተነሳውና እስከ ስምምነቱ ድረስ የቀጠለው ነውጠኛና ደም ያፈሰሰ ግጭት ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ጋር በተጣጣመና በተስማማ፣ እንዲሁም ለእሱ በተገዛ አሠራርና ሥልት በሰላም ይፈታ ዘንድ መስማማታችንን፣
- ፖለቲካዊ ችግሮች በዘላቂነት የሚፈቱትና ሊፈቱም የሚችሉት በፖለቲካዊ መንገድ ብቻ መሆኑን፣ ይልቁንም ፖለቲካዊ ልዩነቶችን ለመፍታት ደመ ነውጠኛነት (ቫዮለንስ) የትግል መሣሪያ በጭራሽ አለመሆኑን መገንዘባቸውን፣ እንዲሁም ግጭትን፣ ጦርነቱን በቋሚነትና በዘላቂነት የማቆም የመርህ መሠረታቸው የኢፌዴሪን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነትና አንድ አገርነት እንደሚያከብሩ ማረጋገጣቸውን፣
- የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመከላከያ ኃይል አንድና አንድ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ስምምነቱም ተስማሚዎቹም ለዓለም ያወጁትና ያሳወቁት ይህንን ነው፡፡ በዚህ መሠረት ነው ትጥቅ የማስፈታት፣ በጦርነቱ ከዚያም ቀደም ሲል ባለመግባባቱና በግጭቱ ምክንያት ‹‹ትግራይ ክልል የተሰናከለውን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መልሶ ማቋቋም›› (የስምምነቱ መግቢያና አንቀጽ 1) ተግባር ከሌሎች መካከል የስምምነቱ የአፈጻጸም ዋና ዋና ጉዳዮች የሆኑት፡፡
አገራችንና ሕዝቧ የሆነ ቡድን ተነስቶ በየትኛውም መንግሥት ላይ (በፌዴራልም ሆነ በክልል መንግሥት ላይ) እንዳይተኩስና የአገሪቱን ብቸኛ የመከላከያ ሠራዊት ከጀርባው የሚያርድ፣ በጎረቤት አገር ላይም የሚተኩስ እንዳይሆን ለማድረግ የፕሪቶሪያውን ስምምነት እስከ መፈረምና እዚያ ላይ እስከ መድረስ ድረስ ያን ሁሉ ጊዜና መስዋዕትነት መክፈል አልነበረብንም፡፡ ይህ ሁሉ ዋጋ የተከፈለው ሕገ መንግሥቱን ራሱን መሬትና መሠረት የያዘና የጨበጠ ባለማድረጋችን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ገና ተወራርዶ ያላለቀ ብዙ ዋጋ ከፍለናል፡፡ ያንን የመሰለ ኪሳራ አስመዝግበናል፡፡ የአንድ ወይም የሌላ የክልል መንግሥት ገዥ ቡድን የአገር ሥልጣን የያዘበትን ልምድ፣ ገጠመኝና ጎዳና ተጠቅሞ ሕግን ተገን አድርጎ እንደምን ሆኖና ምን ምን ሠርቶ የጥቅምት 24ን (2013 ዓ.ም.) ‹‹ጀብድና ገድል›› ኢትዮጵያ ላይ እንደፈጸመ ገና አሁንም ዝርዝሩና ሙሉ ታሪኩ አልተነገረም፡፡ ይህ ታሪክ፣ ቀውስና አደጋ እንዳይደገም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ኃይልና ትጥቅ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ብቻ ነው፣ በዚህም መሠረት የታጠቀ ኃይል አደረጃጀት ሕጋዊ ፈር ውስጥ መግባት፣ እዚያ ግቢ ውስጥ መዋል ማደር አለበት እያልን ደፋ ቀና ማለታችን ገና አልቀረም፡፡ አማራ ክልል ውስጥ እያሞቀሞቀና እያስፈራራ ያለው ችግር መነሻ ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ይህንን መነሻና አጋጣሚ በማድረግ የእኛ ዴሞክራቶች የእኛ ‹‹አዋጊ›› ሚዲያዎች ስለ‹‹ፋኖ›› ዓላማ ሕዝባዊነት ሲያወሩ፣ ሲያወያዩ እንሰማለን፡፡ ውይይታቸውንና ወሬያቸውን አስደንጋጭ የሚያደርገው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ኃይሎች ትግል ከሰላማዊና ከሕጋዊ ትግል/ግብግብ ግቢ ውጪ ስለሚያደርግ ነው፡፡ ደጋግመን እንደምንነጋገረውም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሰላም የሚያምሰውና የሚያናውጠው በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች፣ በተቃዋሚዎች በራሳቸው ውስጥና መካከል የሚደረገው ትግል ከሕጋዊና ከሰላማዊ መንገድ ውጪ መሆኑ ነው፡፡
ከፍ ሲል ላነሳናቸው ‹‹አዋጊ ሚዲያዎች›› ምሳሌ ያደረግነው አንዱ ለምሳሌ ፋኖ ጦርነቱን ያሸንፋል አያሸንፍም ብሎ እርስ በርስም፣ አድማጮችን ጋበዞ ተወያዩበት ባለበት መድረክ፣ አንድን ተዋጊ ኃይል (የተጠቃ ተዋጊ ኃይል) አሸናፊ የሚያደርገው አንደኛውና ዋናው ዓላማው ነው፡፡ ዓላማው ሕዝባዊ ነው አይደለም የሚለው ነው፡፡ ሁለተኛው አደረጃጀቱ ነው፡፡ ጠንካራ ድርጅት መመሥረት የቻለ አሸናፊ ይሆናል፡፡ ፋኖንም አሸናፊ የሚያደርገው ዓላማው ሕዝባዊ ነው ወይ? አደረጃጀቱስ ለድል የሚያበቃው ነው ወይ? የሚለው ነው›› ሲሉና ለእነዚህ መሟላት ሲለማመኑ፣ ሲፀልዩ፣ ምናልባትም ‹ግፋ በለው በርታ ገና ነው› ሲሉ ሰምተናል፡፡
እና የትጥቅ ትግል ተመራጭ የትግል ሥልት ሆኖ በይፋ ሲመረቅ፣ ሲወደስና ሲሰበክ አጋጥሞናል፡፡ ደጋግመን እንደገለጽነው ዋነኛው የአገራችን የፖለቲካ ሰላም ፈተና የገዥው ፓርቲና የተቃዋሚዎች ትንቅንቅ፣ ግብግብ (በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ ገዥዎችና ተቃዋሚዎች ሁሉ) ከሰላማዊና ከሕጋዊ መድረክ ውጪ መሆኑ ነው፡፡ የሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ልብ አንድ የሰላማዊ መንገድና ግቢ ውስጥ አለመገኘቱ ነው፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳ አንድ ጥያቄ ወይም አቋም አለ፡፡ የአገራችን ፖለቲካ ራሱ ሕጋዊና ሰላማዊ ትግል ይፈቅዳል ወይ? አለዚያም ይከለክላል የሚል፡፡ ወይም ከእነ ጭራሹ ‹‹ሳትዋጋ ንገሥ ቢሉት ግድ ተዋግቼ›› ብሎ የሚከራከር፡፡ ዋናው ጉዳይና መጀመሪያ ግን ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ራሱ ትግል ይጠይቃል፡፡ ሕጋዊነትን በሚመለከት ረገድ የትኛውምን ጥቅም የመግለጽ ወይም የማስተጋባት ጉዳይ ሕጋዊነት ወይም ሕገወጥነት ጥቅሙን የሚጠይቀው/የሚያስተጋባው ሰው/ቡድን በመረጠው መንገድ፣ ወይም ድርጊት ዓይነትና ድርጊቱን በሚገዛው የአገሪቱ ሕግ ይወሰናል፡፡ ሰላማዊነቱና ነውጠኛ አለመሆኑን የሚወስነው ደግሞ ከዚህ ሕጋዊነት በተጨማሪ የኃይልና የጉልበት ሥራ ወይም ተግባር መጠቀሙ ነው፡፡ የፖለቲካኞቻችን የጥበብ መጀመሪያ መነሻው ማድረግና መነሳት ያለበት፣ በጉልበትና በሸፍጥ መንገድ ሁሉ መዋደቅን ትግል ነው ማለትን እርግፍ አድጎ ከመተው ነው፡፡ ሲጀመር ፖለቲካ ሕይወታቸው ውስጥም ሆነ በግል ኑሯቸውም ልዩነትን በውይይት በመነጋገር የመፍታት ጨዋነትንና ዴሞክራትነትን የአደባባይም የግልም ባህርያቸው ሊያደርጉት ይገባል፡፡ ከመነሻው ፉርሽ የሚሆነው ለዴሞክራሲ እታገላለሁ እያሉ ዴሞክራት ነኝ፣ ዴሞክራሲያዊ ነኝ እያሉ በመረጃና በዕውቀት መከራከርን አለመግባባትን በውይይት መፍታትን አለመለማመድና ባህርይ አለማድረግ ነው፡፡
በዛሬዋ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ይበልጥ ሰፊና ጥልቅ ለሆነ ሰላማዊ ትግል ብቻ ሳይሆን የዴሞክራሲ፣ አምጪ ለመሆን ያለ ጥርጥር ተመራጩ መንገድ ነው፡፡ ዛሬ ቀርቶ ትናንትም በኢሕአዴግ አድራጊ ፈጣሪነት ወቅት ሰላማዊ ትግል የ1997 ምርጫና ትግል፣ ሁለት፣ ሦስት ዓይነት ምስክርነት ይሰጣል፡፡ የምርጫ 97 ያ ሁሉ የሰላማዊ ትግል ድንቅ፣ ምርትና ውጤት ውኃ የበላው (ለዚያውም ያን በመሰለ ጭቆናና አፈና ውስጥ) ተቃዋሚዎች አሸናፊነታቸው ላይ መገንባት፣ ድላቸውን ለሌላ ድል መረማመጃ ማድረግ ባለመቻላቸው ነው፡፡ አዲስ አበባ ፒያሳ ላይ (የከተማ አስተዳደሩን) አራት ኪሎ ከሚቋቋመው መንግሥት የተለየ ሌላ ገዥ ፓርቲ የሚመራው መንግሥት የማቋቋም ድላቸውንና ዕድላቸውን፣ ወዘተ አምክነው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ ያለውን ጉዞና አበሳ ያበዙት በገዛ ጥፋታቸው ነው፡፡ ሰላማዊ ትግል በኢሕአዴግ ዘመንም ይቻላል የምለው (አሁን ዛሬ ለውጡ በሚገኝበት የዕድገት ደረጃ ላይ ያለንን ልዩነት እንተወውና) አገር ሳይቃወስ መንግሥት ሳይደረመስ የተጓዝንበት ከ2006 ዓ.ም. የጀመረው የሰላማዊ ትግል ጉዞ ኢሕአዴግን አስገድዶ ለውጥ ያመጣ በመሆኑ ነው፡፡
አሁን ዛሬ ላይ ሆነን አይደለም፣ ትናንትም ሕወሓት/ኢሕአዴግ ገና 27 ዓመት አፍላ የሥልጣን ዘመኑ ውስጥ እያለ እሱ ሥልጣን በያዘበትና በሚኮራበት፣ ለትክክለኛነቱ፣ ለአሸናፊነቱና ሥልጣንም የእሱ ብቻ ስለመሆኑ ማስረጃ አድርጎ በሚያቀርብበት መንገድና ሥልት (በትጥቅ ትግል) ሥልጣን መያዝ አግባብ እንዳልሆነ፣ ትክክለኛው የትግል ሥልት አይደለም ሲባል/ስንል እናውቃለን፡፡ የዚህ ምክንያት የትጥቅ ትግል በገዛ ራሱ ምክንያት ሰላማዊና ሕጋዊ ስላልሆነ ነው፡፡ በሌላም የታወቀ ምክንያት የትጥቅ ትግል ወይም ጦርነት ረዥም ጊዜ ይወስዳል፣ ከሚወጉት/የምወጋው እሱን ነው ከሚሉት መንግሥት ጋር አገርን ሕዝብን አብሮ ያደቃል፡፡ ለረዥም ጊዜ (ለዓመታት) ሲተኩሱ፣ ፈንጂ ሲዘሩና መሠረተ ልማት ሲያወድሙ ኖረው ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ (ሥልጣን መያዙ ቀጥተኛው መዳረሻ እንኳን ቢሆን)፣ እንደገና መልሶ ግንባታ ማለት ለዛሬው ዘመን በኢትዮጵያም በዓለምም ዕብደት ነው፡፡ ጦርነቱን አሸንፎ፣ ፈንጂ ሲዘራና መሠረተ ልማት ሲያወድም ኖሮ፣ አሁን ደግሞ ወደ ‹‹ልማቱ ግንባር›› ወደሚለው ገዥ የሥልጣን ዘመን ከመግባታችን በፊት የአገርን የፖለቲካ ሰላም ዋና ሕመም የሆነውን ጉዳይ መርሳት የለብንም፡፡ ሕመማችን የፖለቲካ ኃይሎች ትግል ከሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ መውጣቱ ነው፡፡ ሰላማዊና ሕጋዊ ግቢ ውስጥ መገናኘት እምቢ ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች የእርስ በርስ ግንኙነት በሰላም ሊፈታ ያልቻለ የውስጥ ተቃውሞ ለውጭ ጠላት ይመቻል፡፡ ከጎረቤት ባላንጣነትና ባላጋራነት ጋር ይሸራረባል፡፡ በዚህ ላይ የምንኖርበት አካባቢ በርካታ ጣጣዎች ያለበት ቦታ ነው፡፡
ከሁሉም በላይ የሚገርመው፣ የሚያስደንቀውና የሚያስደንግጠው ደግሞ የተቀደሰ ዓላማ ያለው ተዋጊ ኃይል ወይም በሌላ አነጋገር፣ ያ የተቀደሰ ዓላማ ጦርነትን ተገቢ ያደርጋል፣ ጦርነት ውስጥ መግባትን የግድ ያደርጋል፣ በዚያውም ያንኑ ጦርነት ‹‹የተቀደሰ›› ያደርጋል የሚለው ዓይነት መከራከሪያና የትግል ሥልት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ስለተቀደሰ ጦርነት በመተረክ፣ በመናገር፣ በመደንፋትና በመታበይ እንደ አሜሪካኖች አስተምራለሁ፣ እሰብካለሁ የሚል የለም፡፡ ስለሦስት የተቀደሱ ማንም ‹‹የማይናገራቸው›› እና የልቡን ‹የማይናገርባቸው› ጦርነቶች ይነግሩናል፡፡ ፍትሐዊ ዓላማ አምጦ የወለዳቸው ናቸው ይሉናል፡፡ ፍትሐዊ ዓላማቸውን ላንጠይቅ፣ ላንጠረጥር እንችላለን፡፡ የግድ ጦርነት ውስጥ መግባትን ያንን ሁሉ ዕልቂት በውጤትነት ማስከተልን ግን በጭራሽ ግድ ማድረግ የለባቸውም፡፡ የአሜሪካ አብዮታዊ ጦርነት የሚባለው ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጡበት ነው፡፡ የእርስ በርስ ጦርነት የሚባለው ሁለተኛው ‹‹የተቀደሰ›› ጦርነት ደግሞ ‹‹ባርነት››ን አስወገድን የሚሉበት ነው፡፡ ሦስተኛው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ነው፡፡ ይህንን ለጊዜው ወደ ጎን ልተወውና የመጀመርያ ሁለቱ ጦርነቶች ራሳቸው ሳይሆኑ፣ ጦርነቱን የግድ አደረጉት የተባሉት ዓላማዎች እውነትም ፍትሐዊ ናቸው፡፡ ከቅኝ ገዥ መላቀቅ ከባርነት ነፃ መውጣት ፍትሐዊ ዓላማ ነው፡፡
ጥያቄው ግን የእንግሊዝን የቅኝ አገዛዝ ለመገላገልም ሆነ ባርነትን ለማስወገድ የግድ ጦርነት ውስጥ መግባት ያስፈልጋል ወይ? አሜሪካኖች ሁለቱም ዓላማዎች ጦርነትን የግድ ያደርጋል ብለው ጦርነት ውስጥ ገብተው የከፈሉት ዋጋ ብቻ ሳይሆን፣ ያገኙት ውጤት ጭምር ሲታይ ጦርነት የግድ ብቸኛው መንገድ አይደለም፡፡ ካናዳ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነበረች፡፡፡ የእንግሊዝ ቅኝ ገዥነት ያስወገዱት ግን ጦርነት ውስጥ ገብተው አይደለም፡፡ በ‹‹ሰላማዊ›› መንገድ ነው፡፡ ባርነትንም ለማስወገድ የግድ ጦርነት ውስጥ መግባት እንደሚያስፈልግ በዚህ ታሪክ ውስጥ ያለፉ አገሮች ምስክሮች ናቸው፡፡ በዚያ ላይ እንዲህ ዓይነት ‹‹የተቀደሰ›› ጦርነት የግድ አላስፈላጊ ነው ተብሎ በዚህ ጦርነት አማካይነት የተገኘው ድል አሜሪካን ‹‹ነፃ አገር›› አላደረጋትም፡፡ ዋናው ቁምነገሬ አሜሪካ ከቅኝ ግዛትና ወይም ከባርነት በኋላ ነፃ አገር ሆነች? የነፃ ሰው አገር ሆነች ስላይደለ ወደ እሱ አልገባም፡፡ መሠረታዊው ጥያቄ ግን ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል አለመሥራቱን ፉርሽ መሆኑን ሳያረጋግጡ፣ ስለፍትሐዊ ዓላማ የፍትሐዊ ዓላማም ልጅ ስለሆነው ስለፍትሐዊ ጦርነትና የትጥቅ ትግል ስለማይቀረው ‹‹ፍትሐዊ ድልም›› ማውራት ፖለቲካ ገደል ግቢ ከማለት ቁጥር ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን አቋቁማለሁ፣ ዴሞክራሲን እገነባለሁ ብሎ የመፈጠምና የመታገል ዋናው መለኪያና ማረጋገጫው በፈለገው ዘዴ ‹‹አሸንፎ›› የሌሎችን ሐሳብና ፍላጎት ከቁጥር ሳያስገቡ ሥልጣንን በብቸኝነት መያዝ፣ ከዚያም ዴሞክራሲ ‹‹እነሆ›› ማለት አይደለም፡፡ በአንድ አገር ውስጥ የተባለው ዓይነት ሥርዓት ስለመተከሉ፣ ሥር ስለመያዙ መለኪያውና ሐውልቱ ለቅሬታ ምንጭ የሆኑ ጉዳዮች ደም መቀባት በሌለበት መንገድ ይፈታል ወይ? የሕዝብ አቤቱታዎች፣ ቅሬታዎች፣ የፖለቲካ አለመግባባቶችና ፀቦች ወደ ጠመንጃ የሚሄዱበት ዕድል እያጠበብን፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መስተንግዶ እያሰፋን እየሄድን ነው ወይ ብለን እጠየቅንና እየመለስን ነው፣ ለዚህም እየጣርን ነው፡፡
ሰላማዊ ያልሆነ ትግል እተካዋለሁ የሚሉትን መንግሥት ብቻ ለይቶ አያጠቃም፣ አያደቅም፡፡ እንደምናየውና እንደምንሰማው ደግሞ የአንዳንዶቹ ‹‹ሰላማዊና ሕጋዊ ያልሆነ የትግል ሥልት አፍኖ ገንዘብ ከመሰብሰብ፣ ከአሸባሪነትና ከጅምላ ጭፍጨፋ መፅዳት ያቃታው ብቻ ሳይሆን እንዲያውም እዚያው ውስጥ እየተዘፈቀ ነው፡፡ ሰዎችን በነሲብ የሚያጠቃ ሽብር በ‹ትግል› ባህርይው የሰዎችን መከበር ይድጣል፣ በዚህም ምክንያት ቀደም ሲል እንደተባለው የዴሞክራሲ አማጭ አዋላጅ ሊሆን አይችልም፡፡ የጠላት ‹ወገን› የሆኑ ሰዎችን ለይቼ እቀጣለሁ ማለት ከጅምላ ጭፍጨፋ በላይ ምን ዓይነት የተለየ ስምና ስያሜ እንዳለው፣ ስያሜ ብቻ ሳይሆን ልዩ ዓይነት ወንጀል እንደሆነ አላውቅም የሚል ካለ ቢቀር ይሻለዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የጠላት ወገን የሆኑትን ለይቶ ማጥቃት በበቀል ዕርምጃ የገዛ ራስን ወገን ያስጨፈጭፋል፡፡
ሕጉ ‹‹በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጪ በማናቸውም አኳኋን የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው፤›› ይላል፡፡ ይህን የሚለውና የሚከለክለው አሁን ሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ብቻ አይደለም፡፡ የበፊት ሕገ መንግሥቶቻችን የወንጀል ሕጎች ሁሉ ይህንን ሲከለክሉ፣ ሲቀጡም ኖረዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት መመሥረቻ ሰነድም ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ የመንግሥት ለውጥን/የሥልጣን አያያዝን ያወግዛል፣ ይከለክላል፡፡ ይህንን የሚለው ሕጉ ነው፡፡ የአገርም የአኅጉር ሕግ በአገር ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጪ የመንግሥት ሥልጣንን መያዝ (በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥትም፣ በታጠቁ አማፅያን አማካይነትም ወይም የመንግሥት ሥልጣን እንቢ አልለቅም በማለት) የተከለከለ ነው ይላል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካውም የሚለው ይህንኑ ነው፡፡ የፖለቲካ ቡድኖች መንግሥታዊ ገዥነት መፍለቅና መውጣት ያለበት ከጠመንጃ አፈሙዝ አይደለም፡፡ ከነፃና ከትክክለኛ ምርጫ የሚመጭበት አዲስ ምዕራፍ ይከፈት ይላል፡፡ ለዚህም ጥርጊያ መንገዱ ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችን በየሥፍራውና በየቦታው ማደላደል ነው፡፡ እዚህም ላይ የሚካሄደው ሰላማዊ ያልሆነ ትግል ወይም የትጥቅ ትግል ወይም አመፅም ዓላማም እኮ ይኼው ነው፣ ሥልጣን ለመያዝ አይደለም፡፡ መሣሪያነቱ የተወሰነ ሕዝባዊ ዓላማን ለማሳካት፣ ዴሞክራሲን ለማስፈን ነው ይባልም ይሆናል፡፡ ‹‹ሳትዋጋ›› [አደላድል] እየተባሉ ‹ግድ ተዋግቼን› ምን አመጣው? ብቻ አይደለም ጥያቄያችንና የሚያሳስበን ጉዳይ፡፡ እንዲህ ያለውን ‹‹የተቀደሰ›› ዓላማ (ወይም ፊልም፣ ሕልም፣ ቃል ኪዳን) ከዚህ በፊትም በአገራችንም በሌላው አገርም ኖረነዋል፡፡
ሰላማዊ ያልሆነው ትግል መሣሪያነቱ ዴሞክራሲን ለማደላደል ነው ማለት ያው ዓላማ ራሱ ሥልጣን ከተጨበጠ በኋላ ‹‹በተግበር የሚገለጽ›› በመሆኑ፣ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ነግሮን ውጤቱን ያየነው ከሽግግሩ ዘመን በፊት ወዲያውኑ ነው፡፡ ሥጋታችንና መከራችን ግን ይኼ ብቻ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ቡድኖች መንግሥታዊ ገዥነት ከነፃና ከትክክለኛ ምርጫ እንዲመነጭ አዲስ ምዕራፍ የመክፈት ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ብቻ ማድረግ የምንገደድበት ከፍ ያለ ዕዳና ግዳጅ አለብን የምንልበት ወቅት፣ አብሮና እኩል የሚያመን ይበልጥ ሕመም የሆነብን ‹‹ጥራኝ ጫካው ጥራኝ ዱሩ›› (ከሰላማዊ መንገድ መውጣቱ፣ ሰላማዊ ያልሆነ ትግል መመረጡ) መባሉ ብቻ አይደለም፡፡ የትግሉ ዓይነት ሰላማዊ አለመሆኑ፣ አውዳሚነቱ፣ መብትና ነፃነት ረጋጭነቱ ሳያንስ፣ ወደ እዚህ ዓይነት ደመ ነውጠኛ ትግል የተገባበት የአደረጃጀት ዘይቤ ሰላማዊ ሕይወት ውስጥ እንኳን መጨራረስን የሚደግስ፣ አብሮ መኖርን የሚያፈርስ፣ ሌላም ጣጣና መከራ ያለበት ነው፡፡ ይህም ችግራችን ክፍልፋይነትና ጎጆኝነት ነው፡፡ የምናቋቁመው ዴሞክራሲ የትኛውንም የብሔር የበላይነት የሻረና እኩልነትን ያረጋገጠ ሥርዓት እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ይህንን ፍላጎታችንን ግን ዕውን የሚያደርገው በየብሔረሰብ ውስጥ የታጠረ ወይም የተወሸቀ ትግል አይደለም፡፡ ትግሉ ደግሞ ከሰላማዊ መድረክ ሲወጣ ምን ሊሆን እንደሚችል እስኪበቃን ድረስ ዓይተን፣ ለይተን አውቀነዋል፡፡
የብሔርን መብት ጉዳይ አንዳንዶች እንደሚሉት፣ ወይም ለብዙ ጊዜ ከዚህ ቀደም ሲባል እንደኖረው ‹‹የዜግነት›› መበት ከተከበረ… የምንለው ጉዳይ አይደለም፡፡ ሰላማዊ ትግል ውስጥ፣ ዴሞክራሲን ማቋቋም ትግላችን ውስጥ ዘላቂ መፍትሔ የሚገባው ግዙፍ የአገር አደራ ነው፡፡ መፍትሔውና ትግሉ ግን ራሱ ሰላም ይፈልጋል፡፡ በብሔርተኛ ታጣቂ አማካይነት ጦር ሜዳ ላይ የሚገኝ መላና መድን አይኖርም፡፡ በብሔረሰብ መደራጀት እንደ ብዙኃን ማኅበር፣ እንደ ሃይማኖታዊ ስብስብ መብት ነው፡፡ በፓርቲነት በብሔር ተደራጅቶ ብሔረ ብዙነት ባለበት አካባቢያዊም ሆነ አገራዊ የሕዝብ ጥንቅር ላይ በገዥነት መውጣት ግን መብት ሊሆን የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ ግን አሁንም እንደግመዋለሁ ሰላምን ይፈልጋል፡፡ በሰላምም ውስጥ ሕግ ከማውጣት፣ በሕግ ከመከልከል በፊት በንግግር ሊወቀጥ ይገባል፡፡
እስከ ዛሬ ከደርግ ውድቀት በኋላ ባለው ጉዞ ውስጥ ብሔርተኛ ፖለቲካ አደረጃጀትና አገዛዝ ያደረሰው ችግር ከታትፎናል፣ ለያይቶናል፣ አናቁሮናል፡፡ ጭፍን ብሔረሰባዊ ጥቃትና መበቃቀል ውስጥ ዘፍቆናል፡፡ አካባቢዎችን በየ‹ድርሻ› ከፋፍሎና አከፋፍሎ በአገር ውስጥ በአጠቃላይ ብቻ ሳይሆን በአንድ የአካባቢ አስተዳደር በራሱ ውስጥም እኛና እነሱ፣ ባላገርና ባላገር ያልሆነ አድርጎ ከታትፎናል፡፡ ሕዝቡን ቤተኛና ባይተዋር፣ ባላገርና መጤ አድርጎ የከፋፈለ በአንድ አገር ውስጥ የብዙ ሉዓላዊ አገሮች ‹‹የግዛት አንድነት›› የሚባል መዘዝና ጠንቅ አምጥቷል፡፡
ይህ ሁሉ ችግር ደግሞ ከሰላማዊ ትግል ውጪ የሆነ ሌላ ጣጣና ቀውስ አይፈልግም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡