እኔ የምለዉ የአዲስ አበባ ከተማ የመጠጥ ውኃ መገኛዎችና ተያያዥ ታሳቢዎች

አንባቢ

ቀን: July 30, 2023

በአሰፋ ኢያሱ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ ከ1879 ዓ.ም. ጀምሮ የአገሪቱ ዋና ከተማ፣ እንዲሁም ከ1955 ዓ.ም. ጀምሮ የአኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መናኸሪያ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ከከተማዋ መመሥረት በኋላ ከሕዝብ ዕድገት ጋር ተያይዞ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት አፄ ምንሊክን ዕረፍት ስለነሳቸው፣ በስዊሱ ተወላጅ አልፍሬድ ኢልግ አማካይነት የእንጦጦ አካባቢ የምንጭ ውኃ በኖራ በተገነባ ቦይ ተስቦ ምንሊክ ቤተ መንግሥት አካባቢ በተሠራ ማጠራቀሚያ እንደ ደረሰና የውኃ መዘውር በ1887 ዓ.ም. እንደ ተገጠመለት ይነገራል፡፡

ይህ በከተማው የተገነባው የመጀመርያው ዘመናዊ የውኃ ተቋም ሲሆን፣ በቀጣይም የቀበናንና የቀጨኔ ወንዞችን በዘመኑ ሥልጣኔ በማጣራት ወደ ሕዝቡ በመሳብ፣ እንዲሁም በየአካባቢው ያሉ ምንጮችን በመገንባትና የእጅ ጉድጓዶችን በመጠቀም በየጊዜው ከሕዝብ ዕድገት ጋር እየጨመረ የመጣውን የመጠጥ ውኃ ፍላጎት ለማስተንፈስ ተሞክሯል፡፡

በ1916 ዓ.ም. አልጋ ወራሽ የነበሩት አፄ ኃይለ ሥላሴ ከአውሮፓ ጉብኝት መልስ ቧንቧ ይዘው በመምጣት ስድስት ኪሎ ጊቢ ውስጥ ለነበረው ቤተ መንግሥት፣ ለቀዳማዊ ኃይለ ሥስላሴ (የካቲት 12) እና ለዘውዲቱ ሆስፒታሎች ውኃ ከእንጦጦ ተስቦ እንዲገባ አደረጉ፡፡ እስከ 1928 ዓ.ም. ድረስ የውኃ አቅርቦት ሥራ ይከናወን የነበረው በሥራ ሚኒስቴር ነበር፡፡ በ1934 ዓ.ም. (ከንጉሡ የስደት መልስ በኋላ) የተሻለ ትኩረት ለመስጠት የውኃ አገልግሎት በማዘጋጃ ቤት ሥር ተደራጀ፡፡

በ1942 ዓ.ም. የኅብረተሰቡ የውኃ ፍላጎት በመጨመሩ በጣሊያን ወረራ ወቅት ታቅዶ የነበረውን የገፈርሳ ግድብ በመሥራት በመጀመርያ 3,000 ሜትር ኩብ ጥሬ ውኃ እስከ ጊዮርጊስ አካባቢ ድረስ ማሠራጨት ተችሏል፡፡ ቀጥሎም የግድቡን ውኃ የመያዝ አቅም በማሻሻልና ዘመናዊ ማጣሪያና ማከፋፈያ በመጠቀም በ1948 ዓ.ም. ከግድቡ እስከ 15,000 ሜትር ኩብ በቀን ማቅረብ ተጀመረ፡፡ በ1950ዎቹ መጨረሻ ከገፈርሳ በላይኛው በኩል አነስተኛ ግድብ ከመሥራት በተጨማሪ የለገዳዲ ግድብና የፍሳሽ መስመር ጥናት ተከናወነ፡፡ ጎን ለጎንም ጉድጓዶች እየተቆፉሩ ውኃው ወደ አገልግሎት ይገባ ነበር፡፡፡

የውኃ እጥረቱ ሲባባስ 40 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ የሚይዘው የለገዳዲ ግድብ በቀን 50,000 ሜትር ኩብ የማጣራት አቅም ካለው፣ ከእነ ማጠራቀሚያውና ማሠራጫው በ1963 ዓ.ም. ተገባደደ፡፡ ከግድቡ ሥራ መጀመር ጋር ተያይዞ የውኃ አገልግሎትን ሥራ በተለየ የሚሠራ ድርጅት በማስፈለጉ፣ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በማዘጋጃ ቤቱ ሥር በ1963 ዓ.ም. በአዋጅ ተቋቋመ፡፡ በዚህ ወቅት የከተማዋ የቀን የውኃ አቅርቦት 80,000 ሜትር ኩብ ነበር፡፡ እስከ 1970ዎች ዓ.ም. አጋማሽ ባለሥልጣኑ ተጨማሪ የማከፋፈያና የማስፋፊያ ሥራዎች እየሠራ ቢቆይም፣ የውኃ እጥረቱ እንደገና እየባሰ ስለመጣ የለገዳዲን ግድብ የማጣራት አቅም በቀን ከ50,000 ወደ 150,000 ሜትር ኩብ የማሳደግ ሥራ በ1978 ዓ.ም. ተጠናቀቀ፡፡

ሆኖም የገፈርሳ ግድብ በእርጅና ምክንያት የማጣራት አቅሙ በ7,000 ሜትር ኩብ በመቀነሱ፣ የለገዳዲ ግድብ በጥሬ ውኃ ዕጥረት ምክንያት የማጣራት አቅሙ ወደ 110,000 ሜትር ኩብ በቀን በመወረዱ፣ እንዲሁም የምንጮችና ጉደጓዶች አቅም በመቀነሱ በደርግ መንግሥት መጨረሻ የከተማዋ የውኃ አቅርቦት 140,000 ሜትር ኩብ የማይሞላ ነበር፡፡ በ1986 ዓ.ም. አካባቢ የውኃ እጥረቱ በመባባሱ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው በ1991 ዓ.ም. 40,000 ሜትር ኩብ ጥሬ ውኃ የሚይዘው የድሬ ግድብ በመጠናቀቁ የለገዳዲ ማጣሪያ አቅም ወደ ነበረው ከመመለስ በተጨማሪ የአቃቂ ጉድጓዶች በመጠናቀቃቸው በቀን እስከ 42,000 ሜትር ኩብ ውኃ ማግኘት ተችሏል፡፡ ቢሆንም ቀድሞ ከነበረው የፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም በተጨማሪ የኢንቨስትመንት መስፋፋት፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የሕዝቡ አኗኗር መለወጥና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ዕድገት ጋር ተያይዞ የውኃ ፍላጎቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል፡፡

ይህን ተከትሎ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ችግሮችን ሊፈቱ የሚችሉ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ፕሮጀክቶች በመንደፍ የውኃ ብክነትን መቀነስ፣ የገፈርሳን ግድብ አቅም በ7,000 ሜትር ኩብ በቀን ማሳደግ፣ የለገዳዲን ግድብ በ30,000 ሜትር ኩብ በቀን ማሳደግ፣ የተለያዩ ጉድጓዶችን በከተማው ውስጥ መቆፈርና የሲቪሉና ገርቢን ግድቦች ለመገንባት አቀደ፡፡ በ1997 ዓ.ም. በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ግንባታው በ2008 ዓ.ም. መጨረሻ ሁለቱም ደረጃዎች (Phases) ቢተገበሩ 685,000 ሜትር ኩብ ውኃ  በቀን ሊያመርት የሚችለው የሲቪሉና ገርቢ ግድብ ጥናት ቢጠናቅቅም፣ የፕሮጀክቱ ግምት ከፍተኛ መሆን (በጊዜው 474 ሚሊዮን ዶላር) ከዓባይ ተፋሰስና ከፕሮጀከት ግንባታ ቦታ ማስከበር ጋር በተያያዘ ከግድብ ይልቅ፣ ሌሎች ጊዜ የሚሰጡና አነስተኛ ወጪ ያላቸውን አማራጮች ላይ መግፋትን ተመርጧል፡፡ በዚህም ምክንያት ከላይ የተጠቀሱት ሌሎች አማራጮች ተተግብረው ወደ አገልግሎት ቢገቡም እንደተለመደው እየጨመረ ከመጣው ፍላጎት ጋር ሊጣጣሙ አልቻሉም፡፡

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሚሆነው ባለሥልጣኑ ከ1940ዎቹ ጀምሮ ከነበረው ግድብ መርሕ ውኃ አቅርቦት ከ1997 ዓ.ም. በኋላ ወደ ጥልቅ ጉድጓድ ተኮር አቅርቦት ማተኮሩና የሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ ነው፡፡ በመጀመርያ እንደ ጊዜያዊ (Emergency) አማራጭና አጣማሪ (Conjunctive Use) ተይዞ የነበረው የጉድጓድ ውኃ ቀስ በቀስ እንደ ዋና መፍትሔ ተወስዷል፡፡

በዚህም መሠረት በ2000 ዓ.ም. ባለሥልጣኑ በተሰጠው አቅጣጫ በአዲስ አባባ ዙሪያ በሚገኙ የጉድጓድ ውኃ መገኛዎች ከፍተኛ ግንባታ (እስከ 500 ሜትር ጥልቀት ያላቸው ጉድጓዶች፣ አሌክትሮ ሜካኒካልና ማከፋፈያ መስመር ዝርጋታ) በማካሄዱ በ2007 ዓ.ም. አካባቢ ምርቱን በ2000 ዓ.ም. ከነበረው 256,000 ሜትር ኩብ በቀን በእጥፍ ከማሳደጉም በላይ. የጉድጓድ ውኃ ድርሻ ከ2000 ዓ.ም. በፊት ከነበረው ከ20 በመቶ በታች በ2008 ዓ.ም. ወደ 65 በመቶ አደገ፡፡

ይህም የከተማውን የመጠጥ ውኃ ሽፋን በ2000 ዓ.ም. ከነበረው 50 በመቶ አካባቢ ትርጉም ባለው ደረጃ ቢያሻሽለውም፣ ከ2001 ዓ.ም. በኋላ የተቆፈሩት 80 በላይ ጥልቅ ጉድጓዶች የሚሰጡት መጠን ከ2009 ዓ.ም. በኋላ እየቀነሰ በመምጣቱና ፍላጎቱ በከተማው ዕድገት ፍጥነት ምክንያት በመጨመሩ ሽፋኑን ለማስጠበቅ፣ ባለሥልጣኑ ጉድጓድ ቁፋሮውን በከተማው ውስጥና ከከተማው ዳርቻዎች አጠናክሮ በመቀጠሉ በ2015 ዓ.ም. መጨረሻ ከጉድጓደች 512,000 ሜ.ኩ (70 በመቶ) ከግድቦች 210,000 ሜትር ኩብ (30 በመቶ) በአጠቃላይ የውኃ ምርቱ 722,000 ሜትር ኩብ በቀን ሊያደርስ ችሏል፡፡ በነባር ጉድጓዶች መዳከም፣ በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ በውኃ ብክነትና በሌሎች የአሠራር እክሎች የተጠቀሰው መጠን በሙሉ ወደ አገልግሎት ላይገባ ይችላል፡፡

በሌላ በኩል በሲቪሉና ገርቢ ጥናት መሠረት በአሁኑ ወቅት የከተማው የመጠጥ ውኃ ፍላጎት ወደ 1,300,000 ሜትር ኩብ በቀን የሚጠጋ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ጊዜ የሕዝብ ብዛት ትንበያውም ወደ 5.5 ሚሊዮን ይሆናል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት የትንበያ ጊዜ እስከ 2018 ዓ.ም. ስለነበር ከሞላ ጎደል የትንበያ ጊዜው እየተገባደደ ስለሆነ ክለሳ ያስፈልገዋል፡፡ ፍላጎቱ አቅርቦቱን እየቀደመ በመገኘቱ እንዲሁም ፕሮጀክቶች ለመጠናቀቅ ጊዜ በመውሰዳቸው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የአጭርና መካከለኛ ጊዜ መፍትሔ ከመተግበር አልቦዘነም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጉድጓዶችን ከመቆፈር በተጨማሪ፣ ከገርቢ ግድብ እስከ 70,000 ሜትር ኩብ በቀን ለማምረት ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በከተማው ውስጥና ውጪ የተቆፈሩት ጉድጓዶች መጠናቸው እየቀነሰ ከመምጣቱ በላይ ጥልቀታቸው እየጨመረ ሲሄድ፣ የውኃው ሙቀትና የኬሚካል ይዘቱ በመጨመሩ በጉድጓዶች ላይ ወደፊት መተማመኑ አዋጪ ላይሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ የአቃቂ ከርሰ ምድር ውኃ ፕሮጅክት በ1993 ዓ.ም. ወደ ምርት ሲገባ በቀን እስከ 42,000 ሜትር ኩብ የሚሰጥ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ወደ 6,000 ሜትር ኩብ በቀን ወርዷል፣  በቅርብ ጊዜም ሙሉ ለሙሉ ሊቆም ይችላል፡፡ አሮጌ ጉድጓዶች እሰከ 500 ሜትር ድረስ ጥልቅ በሆኑ አዳዲስ ጉድጓዶች ቢተኩም እነዚህም ከጊዜ በኋላ መድከማቸው አይቀርም፡፡ በአንዳንድ አዲስ ጉድጓዶች የውኃው ሙቀትና ኬሚካል ይዘቱ ከፍተኛ ሆኖ በመገኘቱ ምርቱ ሲስተጓጎል ይታያል፡፡

ከእነዚህም ሌላ ዋና ዋና የከርሰ ምድር ውኃ መገኛ ቦታዎች በከተማው በታች (ዝቅተኛ ቦታ) በኩል ስለሚገኙ በሒደት ከከተማው በሚወጣው የፋብሪካና ሌሎች ፍሳሽ ለብክለት ስለሚጋለጡ፣ በዚህም ምክንያት ምናልባትም በሒደት ጠቀሜታቸው ሊጤን ይችላል፡፡ ከሁሉም በላይ ባለፉት 80 ዓመታት በከተማው እንደታየው የመሬት ውስጥ ውኃ ይዘት ቀስ በቀስ እየወረደ በመሄዱ የተቆፈሩ ጉድጓዶች በጊዜ ሒደት ሲጠፉ ጥልቀት መጨመሩም፣ ከውኃ ሙቀትና ኬሚካል ይዘት መጨመር ጋር ተያይዞ ጥንቃቄ የሚያሻው ነው፡፡ በሌላ በኩል የመነሻ ወጪያቸው ከፍተኛ ከመሆኑና ከሚወስዱት ቦታ ማስከበር አንፃር ለግንባታ አስቸጋሪ ቢሆኑም፣ ግድቦች የሚገመት ውኃና በንፅፅር የተሻለ የአገልግሎት ዘመን አላቸው፡፡ የአቃቂ 25 ጉድጓዶች የአገልገሎት ዘመናቸው (Design Period) 20 ዓመት ቢሆንም ቀድመው ነው መድከም የጀመሩት፡፡ በ1942 እና በ1963 ዓ.ም. የተሠሩት የለገዳዲና የገፈርሳ ግድቦች ከማሻሻያ ጋር እስካሁን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ይህም የሆነው በአመዛኙ የዝናብ ውኃ ከጉድጓድ ውኃ በተሻለ ታዳሽ ሀብት በመሆኑ ነው፡፡ የጉድጓድ ውኃ ከሚተካው ውኃ መጠን በላይ ከተጠቀምነው ጉድጓዱ ከታሰበው ጊዜ በፊት ሊደርቅ ይችላል፡፡

በባለሥልጣኑ ለከተማ መጠጥ ውኃ የተቆፈሩ ጉድጓዶችን ታሪክ ብንመለከት እስከ 1950ዎቹ የነበሩት በአመዛኙ ከ100 ሜትር በታች፣ እስከ 1980ዎች መጨረሻ የነበሩት በአማዛኙ ከ200 ሜትር በታች፣ እሰከ 1990ዎች መጨረሻ የነበሩት ከ300 ሜትር በታች ጥልቀት ያላቸው ሲሆን፣ የመጀመርያዎች ሁለቱ በአሁኑ ወቅት በአመዛኙ ከአገልግሎት ውጨ ሆነዋል፡፡ የሦስተኛው ዓይነቶችም ቢሆን በውኃ ማነስና በኬሚካል (TDS and Fluoride) መጨመር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከአገልግሎት ውጪ እየሆኑ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተቆፈሩ ያሉት እስከ 600 ሜትር ጥልቀት ያላቸው ጉድጓዶችም ከጥቂት አሥርት ዓመታት በኋላ ዕጣ ፈንታቸው ካለፉት የተለየ ላይሆን ይችላል፡፡ በተለይም የውኃ እጥረት በሚባባስበት በከታማው የላይኛው አካባቢ (ካራ፣ ኮተቤ፣ አንቆርጫ፣ ፈረንሣይ፣ ሽሮሜዳ፣ ቀጨኔ፣ ጎጃም በር፣ ሸጎሌ፣ አስኮ፣ ቀራንዮና ዓለም ባንክ) የተቆፈሩትም ሆኑ እየተቆፈሩ ያሉት ጉድጓዶች ለአጭር ጊዜ መፍትሔ ቢያመጡም፣ በተወሰኑ ዓመታት ውስጥ የሚቀንሱ ወይም የሚደርቁ ናችው፡፡

በአጠቃላይ ጉደጓዶችን እንደ ጊዜያዊ (Emergency) አማራጭና አጣማሪ (Conjuctive Use) ከመጠቀም ውጪ አንደ ዋና የከተማው የውኃ አማራጭ መውሰዱ፣ የከተማው ሕዝብ ቁጥርና የአጠቃቀም ዘይቤው እየጨመረ ሲሄድ የተጨማሪ ግድቦች ግንባታ ካሁኑ ካልታሰበበት ወደፊት ከአሁኑ የባሱ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ አገልግሎት ላይ ያሉ ጉድጓዶችም ለውሳኔ እንዲያመች ዘመናዊ የሆነ የክትትል ሥርዓት (Temporal Well Water Level Mentoring System) ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በየጊዜው በከፍተኛ ወጪ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የከተማውን የመጠጥ ውኃ ሥርጭት ሥርዓት እንደሚያዘምን ተገምቶና እንደ መጠጥ ውኃ ማስተር ፕላን ማሻሻያ ታስቦ ከነበረው የገርቢና የሲቪሉ ግድብ ፕሮጀክት ጋር እያገናዘቡ መገንባቱ መልካም ይሆናል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከ800 ኪሎ ሜትር በላይ አዳዲስ መስመሮች፣ እንዲሁም ከ41 በላይ ከፍታ መቆጣጠሪያና ማጠራቀሚ ጋኖች (Pressure Zone Reservoirs) ነበሩት፡፡ አዳዲስ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ሲጠኑም እግረ መንገዱን መጠጥ ውኃ ማስተር ፕላኑን ከከተማዋ ማስተር ፕላን ጋር ማገናዘቡ ይጠቅማል፡፡

በተለይ ከ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የተከናወኑትን የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውኃ ጥናቶች ተመጋጋቢ ለማድረግና ተቋማዊ መረጃን (Institutional Memory) ለማስቀጠል የሚያስችል አሠራር ቢጠናከር ለፖሊሲ አውጪዎች የተሻለ አማራጭና መረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አሁን ካሉት ጉድጓዶችና ግድቦች በተጨማሪ ሌሎች የግድብ አማራጮችን በማስተር ፕላን ደረጃ ቢያስቀምጥ ይመረጣል፡፡ ከሲቪሉና ገርቢ ግድብ ጥናቶች በተጨማሪ ለግድብ ከሚሆኑ ቦታዎች ማለትም የትልቁና ትንሹ አለልቱ፣ የሮቢ ጂዳ፣ የመልካ ቁንጡሬ ወይም ሌሎች ቦታዎች ከአሁኑ መርጦ ማዘጋጀቱ መልካም ይሆናል፡፡

በራስ አቅም ወይም በብድር የግድብ ፕሮጀክቶችን መሥራት የማይቻል ከሆነ፣ ከዚህ በፊት በተለያዩ የውጪ አገር ድርጅቶች ተጠይቆ ያልተፈቀደውን የግሉን ዘርፍ እንደ አዲስ ለሚገነቡ ግድቦች ብቻ በግንባታ ማስተዳደርና ማስተላለፍ (Built Operate Transfer) ስምምነት (Concession) ማስገባት እንደ መጨረሻ አማራጭ ሊታይ ይችላል፡፡ እስከ 2001 ዓ.ም. ድረስ የእንግሊዝ፣ የጣሊያንና የፈረንሣይ ድርጅቶች በዚህ ዘርፍ ለመሰማራት ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ሆኖም ከግንባታ ዋጋ ውድነትና ከዶላር ምንዛሪ ትይዩ በየጊዜው ሊኖሩ የሚችሉ የውኃ ሽያጭ ማስተካከያዎች ማኅበራዊ ችግር ይፈጥራሉ በሚል መቅረታቸው ይታወሳል፡፡ መንግሥት አሁንም ቢሆን ከፍተኛ በጅት ለግንባታና ለማስተዳደር እየደጎመ ይገኛል፡፡ ምናልባት ውኃው በበቂ ሁኔታ ቀርቦ የመንግሥት ድጎማ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ማጥናት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡

የመረጃ ምንጭ፡- ‹‹Water III Executive Summary, 2005 (1997 EC)››, የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ  ባለሥልጣን መጽሔት (2000 ዓ.ም.)፣ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን መጽሔት (2001 ዓ.ም.)፣ ከ2001 ዓ.ም. በኋላ ያለው መረጃ በሥራና ጥናት ምክንያት ከባለሥልጣኑና ከተለያዩ ምንጮች የተገኙ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው  aseyasu@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡