
July 30, 2023
እኔ የምለዉ እያደር መበርታት ሲቻል መንገዳገድና መውደቅን ምን አመጣው?
ቀን: July 30, 2023
በያሲን ባህሩ
ፖለቲካ ተለዋዋጭና የማይጨበጥ ዕሳቤ ነው፡፡ ያውም በመረጃና በሚዲያ ቴክኖሎጂ ብዛት በሚታመሰው የአሁኑ ዓለም፣ እንኳንስ ነገን ለመተንበይ ዛሬንም ለመጨበጥ የሚያስቸግር ነው፡፡ እንደ ታዳጊ አገርና ደሃ ኢኮኖሚ ደግሞ በሌላው ዓለም ሰላም ውሎ ማዳር ላይ የተመሠረተ የልብ ምት በአገረ መንግሥት ውስጥ መፈጠሩ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ የአንዱ ተፅዕኖ ለሌላው የህልውና ሥጋትም ሆነ ድጋፍ ሚናው ከፍተኛ ነውና፡፡
ያም ሆኖ አገራችን ካላት ታሪክና ሰፊ ሕዝብ ብሎም አኅጉራዊ ሚና አንፃር፣ ብሎም ካለፈችባቸው ፈተናዎችና የፖለቲካ ኢኮኖሚ ውጣ ውረዶች አኳያ መበርታት፣ ጫናን መቋቋምና ወደፊት መራመድ እንጂ መዳከምና መንሸራተት ፈጽሞ ሊመጥናት አይችልም፣ አይገባምም፡፡ ይህን እውነት በመረዳትና በማስተዋል መራመድና በመተሳሰብ መንቀሳቀስ የሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች፣ የመንግሥትና የሕዝቡ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡
እውነት ለመናገር በፖለቲካው ሥነ ምኅዳር ረገድ ከ1983 ዓ.ም. በፊት በአገራችን ፓርቲ ማቋቋም በራሱ ከባድ ወንጀል እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህ የተነሳ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ጽንሰ ሐሳብ ከ1983 ዓ.ም. በፊት ለነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባዳ ነበር ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ ዕሳቤውን ዕውን ለማድረግ በተደረጉ ሙከራዎች ስንቶች መስዋዕት እንደሆኑ ታሪክ አይዘነጋውም፡፡ የተደራጀና ተቋማዊ ተቃውሞን ማስተናገድ ለቅድመ ኢሕአዴግ የፖለቲካ ልሂቃን የማይታሰብ እንደነበር አይረሳም፡፡
ከዚያ ወዲህ ቢያንስ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት፣ ከሥርዓቱ መገለጫዎች አንዱ ሆኗል፡፡ ስለሆነም ይህንኑ ሥርዓት ከእነ ጉድለቱ ለመጀመርያ ጊዜ በአገሪቱ በማስተዋወቅና ተግባራዊ በማድረግ ረገድ፣ የቀድሞው ኢሕአዴግና በወቅቱ የነበሩ ተቃዋሚዎች የነበራቸው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ አያከራክርም፡፡ ይህን ሥርዓት በመዘርጋት ሒደት የመጀመርያዎቹ ዓመታት በአገራችን የፖለቲካዊ መልከዓ ምድር ላይ ከባድ ልዩነትና ተጠራጣሪነት ሰፍኖ የነበረ መሆኑም ሌላኛው የማያከራክር ገጽታ ነው፡፡
ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ብዙኃነትን ከቀደምት አስተዳደሮች በተለየ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ ለመያዝና ለማስተዳደር እንደሚፈልግ ባሳወቀ ጊዜ ሰፋ ያለው የከተማ ማኅበረሰብ፣ በተለይም የአገሪቱ ልሂቃን አቅጣጫውን በከፍተኛ ጥርጣሬ ይመለከቱት ነበር። ኢትዮጵያ አንድ ሆና እንድትቀጥል የነበራቸው ፍላጎት አደጋ የሚጋረጥበት የሚመስላቸውም ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ከአሀዳዊና ከወታደራዊ አምባገነን ሥርዓት ወደ ፌዴራላዊ (ብሔር ተኮር መሆኑ የራሱ ችግር ቢሆንም) እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መንገድ ሲጀመር ያልተቀሰቀሰ ፕሮፓጋንዳም አልነበረም፡፡
ያም ሆኖ ግን ወደ 27 ዓመታት ገደማ ኢትዮጵያ ብዙኃነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማስተናገድና ለማስተዳደር እየሞከረች፣ አሁን ሲታይ ቀላል ግምት የማይሰጠው ልማትና ዕድገት እያሳየች፣ ከሁሉ በላይ አንፃራዊ ሰላምና ደኅንነትን አረጋግጣ ለመቀጠል ችላ ነበር፡፡ ይህም በብዙኃኑ ሕዝቦቿ ላይ የፈጠረው የእርስ በርስ መተማመን በመጀመርያዎቹ ዓመታት ተፈጥሮ የነበረውን ጥርጣሬና ሥጋት ቀስ በቀስ እያረገበው ሊሄድ ችሎም ነበር።
የያን ጊዜው ሥርዓት ድክመት ሆኖ እየጎላ የመጣው በአውራ ፓርቲ ስም ፀረ ዴሞክራሲያዊነት እየተጠናወተው መምጣቱ፣ የከፋ የመልካም አስተዳደር ችግርና ሙስና ሥር እየሰደደ መታየቱ፣ ኢፍትሐዊነትና መድልኦ እየተንሰራፋ መሄዱ፣ እንዲሁም ፌዴራሊዝሙ ለማንነት ፖለቲካ ቢያግዝም አገራዊ አንድነትን እያላላው መሄዱ ነበር፡፡ እነዚህና መሰል ችግሮችን ለማስተካከል ደግሞ የተጀመረው ለውጥ ሥርዓቱን ቢቀይረውም አንድ ዕርምጃ ወደፊት የሚወስድ አገራዊ ሁኔታ ለመፈጠሩ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ አሁንም በእነዚያው ችግሮች የተተበተበ መሆኑም እየታየ ነው፡፡
እስካሁን መብታቸው የተከበረ ማኅበረሰቦች በአንድነት ከመኖር የተሻለ አማራጭ ሊኖር እንደማይችል በተግባር እያዩ ቢመጡም፣ አሁንም ከአንድነትና መተባባር ይልቅ መገፋፋትንና የራሴ የራሴ ማለትና መታየቱ አልቀረም፡፡ በዚህ ላይ ያልተማከለው ፌዴራላዊ አስተዳደር ሁሉም ሕዝቦች ያላቸውን ፀጋ በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑና በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ላይ በጎ አመለካከት እንዲያዳብሩ መንገድ እየከፈተ መሄድ ሲገባው፣ ወጥ አገራዊ ሥርዓትና ተመጋጋቢ የፖለቲካ ኢኮኖሚ መስተጋብር እንዳይፈጠር እያወከ ነው የሚሉ በዝተዋል፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች በሕዝብ መካከል የመጠራጠር በር ከፍቷል ባይ ናቸው፡፡
በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት የዴሞክራሲና የሰላም፣ የፍትሕና የእኩልነት ዋስትና እንደሆነ ነው ሲነገር የቆየው፡፡ አሁንም ይህንኑ የሚናገሩ አሉ፡፡ በተመሳሳይ ሕገ መንግሥቱ በዋና ዋና የዜግነት መብቶችና በአገራዊ አንድነት፣ ብሎም የአገረ መንግሥት ጥንካሬ በማስፈን ረገድ ማካተትና ማስተካከል ያለባቸው አናቅጽትን በመጥቀስ ጭምር የሚሞግቱ አሉ፡፡ እነዚህ ዕሳቤዎች ሁሉ ትክክል ናቸው የሚባሉት መሠረቱ ሳይናድ በመነጋገርና በድርድር ጅምሩን ለማቀላጠፍ የሚረዱ በመሆናቸው ነው፡፡
የሚገነባው ሥርዓት ነፃ ገበያ መሆን እንዳለበትና ሰዎች ሠርተው የመጠቀም ሕጋዊ ዋስትና ሊያገኙ እንደሚገባቸው ተመሳሳይ መግባባት መፈጠሩ ብቻ ሳይሆን፣ ከሁለት አሥርት በላይ ዓመታት ከእነ ጉድለቱም ቢሆን ተሠርቶበታል፡፡ በተለይ ድህነትና ኋላቀርነት ዋነኞቹ ጠላቶቻችን እንደሆኑ፣ ለዚህ ደግሞ በፍጥነት መልማትና የሕዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ወሳኝ እንደሆነ ተደጋግሞ ይነገርም ነበር፡፡ ከለውጡ ወዲህ ግን ጭራሽ ነገሮች ወደኋላ ተመልሰው እርስ በርሳችን ጠላት፣ ሰላምና ደኅንነት ጠፍተው የመንቀሳቀስ መብቶችም አደጋ ላይ ወድቀው እየታዩ ነው፡፡ ለምን ወደኋላ የሚያስብለው አንዱ ጭብጥ ይህ ነው፡፡
የሕግ የበላይነት መከበር እንዳለበትና ዜጎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል እንደሆኑ ቢያንስ ቢያንስ በመርህ ደረጃ መተማመን ነበር፡፡ ያም ቢሆን አተገባበር ላይ የነበረው ችግር ቀላል አልነበረም፣ የአሁኑም ግን የባሰ እየሆነ ነው፡፡ ዜጎች በሰላም ወጥተው መግባት ሲቸገሩ፣ ሁሉም ብረት በመነቅነቅ መብቴ የሚለውን በኃይል ለማስከበር መሞከሩ፣ ዕገታ፣ ግድያና ዘረፋ በባሰ ሁኔታ መመልከት፣ እንደ ሙስናና ሌብነትን የመሰሉ የቀደሙ ችግሮች አለመወገዳቸው ሲታዩ ወደፊት ሳይሆን ወደኋላ የመመለስ ነገር እንዳለ መረዳት አይከብድም፡፡ ግን ለምን?
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች የተጀመሩት ዕሳቤዎች በፅኑ የፖለቲካ ኢኮኖሚ መሠረት ላይ የተገነቡ ባለመሆናቸው፣ ብሎም እንደ ሕዝብ አካታች መሆን ባለመቻላቸው የመዋለልና ወደፊትና ወደ ኋላ የመመለስ አዝማሚያዎች ይታያባቸዋል ይላሉ፡፡ ሙስናና ግለኝነት መጥፎ እንደሆነ የሚቀበለው ደግሞ ትንሽ በማይባል ደረጃ በዚሁ ዝንባሌ ሲለከፍና በአቋራጭ ለመበልፀግ ሲሯሯጥ ይታያል፡፡ የሕግ የበላይነትና ሰላማዊ የትግል አግባብን የተቀበለው ኅብረተሰብ፣ አልፎ አልፎ ፍላጎቱን በኃይልና በግጭት ለማሳካት ሲንቀሳቀስ ይታያል፡፡ ይህ ካልታረመ ደግሞ ከውድቀት መውጣት አይቻልም፡፡
በፖለቲካው ንፍቀ ክበብም ረገድ ነገሩ መታየት ያለበት እንዲሁ ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ የአንድ ፓርቲ ሥርዓትን እንደማይፈቅድ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ፣ ፓርቲዎች እንዲጠናከሩና ለመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ብቻ ሳይሆን፣ ያለ እነሱ ተሳትፎ የትም መድረስ የማይቻል መሆኑን ካለፈውም በበለጠ በአሁኑ ወቅት ብዙ ተነግሯል፡፡ በተግባርም የተሞካከሩ (በአመራር ውስጥ ተቃዋሚዎችን መካተትን ልብ ይሏል) ሥራዎች አሉ፡፡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል ተደካመ እንጂ አላደገም ወይም አልተነቃቃም፡፡
እንደ አገር በኃይል፣ በግጭትና ጦርነት የሚፈታ ችግር እንደሌለ የሚታወቅ ነው፡፡ በእርስ በርስ ጦርነትም በጋራ ከመዳከም ውጪ አሸናፊና ተሸናፊ እንደሌለ ያለፉት ዓመታት አሳይተውናል፡፡ አሁንም ግን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የትግል ሥልትን ብቸኛ ተመራጭ ማድረግ አልተቻለም፡፡ በመሠረቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም ሲደረግላቸው በነበሩ ድጋፎች ታግዘው መንቀሳቀስና መነቃነቅ ያቃታቸው በምን ምክንያት ነው? ሕዝቡስ አማራጭ ዕሳቤዎችን ስለምን ሲፈልግና ሲንቀሳቀስ አይታይም ብሎ መፈተሽ ግድ የሚለውም እዚህ ላይ ነው፡፡
መንግሥትም ሆነ ገዥው ፓርቲ በመደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆኑ መድረኮች የአገሪቱን ብዝኃነት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገንቢ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉበትን ዕድል ለማመቻቸት አለመትጋቱ ትዝብት ላይ የሚጥለው ነው፡፡ በእርግጥ አገራዊው ሁኔታ ከቀውስ ያልወጣና ቅድሚያ ለሰላም ሲባልበት የከረመ ነው ቢባል እንኳን፣ ለፖለቲካ ተዋንያን ይቅርና ለተርታው የሚሆን የመኖርና የመንቀሳቀስ ዋስትና አለመረጋገጡ የውድቀታችን መጀመርያ ሆኖ መታየት አለበት፡፡ እናም ቅድሚያ ከዚህ መውጣት ግድ ይላል፡፡
እዚህ ላይ ምናልባትም በብሔራዊ የምክክር መድረኩም ቀድሞ የፖለቲካ ውይይት ሊጀመር ይገባል፡፡ በምክክሩም ሰላማዊ፣ የታጠቀ፣ ኅብረ ብሔራዊ፣ ብሔራዊ፣ ጠንካራ፣ ደካማ፣ ወዘተ ሳይባል ሁሉንም የተደራጀ የፖለቲካ ተዋናይ ማሳተፍ ይኖርበታል፡፡ ገዥው ፓርቲም ራሱን ችሎ እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ስለአገሪቱ ሰላምና ደኅንነት፣ ብሎም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
በቀዳሚነትም ውይይቶቹና ድርድሮቹ የሚካሄዱባቸውን ዝርዝር ሥነ ሥርዓቶች መወሰን፣ ለመተማማን የሚያስችሉ አወያዮች፣ ሎጂስቲኮችና አጀንዳዎችን በመግባባት አሰናድቶ፣ መግባቢያ ተፈራርሞ ሥራውን መጀመርም ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ በተለይ የድርድሩ ዓላማዎች፣ የድርድርና ውይይት ተሳታፊ ፓርቲዎች፣ የፓርቲ ተወካዮች ብዛት፣ ምልዓተ ጉባዔና ውሳኔ አሰጣጥ፣ የድርድር አጀንዳ ስለማቅረብና የማቅረቢያ ጊዜ ገደብ፣ እንዲሁም የድርድር አጀንዳ አወሳሰንና አጀማመር የመሳሰሉትን አካሄዶች ከእኛ አገር ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም ልምድ ወስዶ መቀመር ይገባል፡፡
እንዲሁም የሚዲያ አጠቃቀም፣ የንግግርና የተናጋሪዎች አሰያየም፣ የድርድርና የክርክር አመራር፣ ታዛቢዎችና የሚኖራቸው ሚና፣ ሥነ ምግባርና ዲሲፕሊን፣ ውስጣዊ አደረጃጀት፣ አስተዳደርና የሎጂስቲክስ ድጋፍና የስብሰባ ቦታ ሳይቀሩ እንደ ቀላል የማይታዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ካለፉት ችግሮቻችን በመማርም ለድርድር፣ ለውይይትና ለክርክር ዝግጁ ከሆነ የትኛውም ፓርቲ የኋላን አንስቶ ከማብጠልጠል ይልቅ ነገ አገር እንዴት ትራመድ ብሎ ማብሰልሰል እንዲበረታታም መደረግ አለበት፡፡
እንዲህ ያሉ አገራዊ ምክክሮች በተለይም የተለያዩ ፍላጎቶች ባላቸው ፓርቲዎችና የፖለቲካ ተዋንያን መካከል ሲደረግ፣ ሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ወይም ከሕግና ሥርዓት ውጪ የሥልጣን መጋራት ለመፍጠር እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡ ይልቁንም በርከት ባሉ አገሮች እንደሚደረገው ወደፊት ከመራመድ ይልቅ፣ አገርን ወደ ኋላ እየመለሱ ያሉ የውስጥና የውጭ ችግሮችን በተለይም የሰላምና ደኅንነት ተግዳሮቶች በጋራ ቀርፎ የጋራ አገርና ሥርዓት ለመገንባት ነው፡፡ በአጠቃላይ ሕዝቡ ለሚሳተፍበት አገራዊ ምክክር መደላድል ለመፍጠርም ይረዳል፡፡
በውይይትና በድርድር መጨረሻም በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ብሎም ተንቀሳቅሶ የመኖርና መሥራት እንዲከበር ለማድረግ፣ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሥልጣን በምርጫ ሥርዓት ብቻ ለአሸናፊ የፖለቲካ ፓርቲ የሚተላለፍበትን ሥርዓት ይበልጥ ለማስፋት፣ በድርድር ወቅት የሚነሱ የተለያዩ ሐሳቦችን እንደ ግብዓት በመጠቀም መሠረታዊ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ሕጎችን ለማሻሻልና የአፈጻጸም ጉድለቶችን ለማስተካከል የሚረዱ መተማመኖችን ለመፍጠር ግብ መቀመጥ አለበት፡፡ የሁሉም ቁርጠኝነትም መታየት አለበት፡፡
የአመፃና የግጭትን በሮችን በጋራ እየደፈኑ፣ የፓርቲዎችን የዴሞክራሲያዊ የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከርና ለአገሪቱ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ለማጎልበት የሚረዳ ምክክርም ነው መደረግ ያለበት፡፡ ሕዝቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን አማራጭ ሐሳብ፣ ያላቸውን አማራጭ ሐሳብ ተገንዝቦ በዕውቀትና በመረጃ ላይ ተመሥርቶ እንዲንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣ ለብሔራዊ መግባባት አስተዋጽኦ ለማድረግ፣ እንዲሁም የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት፣ ድርድሩን እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀም የሁሉም ታሪካዊ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡
በመሠረቱ ዴሞክራሲው ላለመጎልበቱም ሆነ ለሚታየው የአገረ መንግሥት መዳከም ገዥው ፓርቲ ብልፅግና ብቻ ሳይሆን መጠየቅ ያለበት፣ በፖለቲካ ተንታኞችም በተደጋጋሚ እንደሚገለጸው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውም ተወቃሽ ናቸው፡፡ በከፊል ሕዝቡና በዋናነት ልሂቃኑ በአገሪቱ የፖለቲካ ሕይወት ብዙም ትርጉም ያለው ለውጥ እንዳያመጣ በመገደባቸው ተጠያቂ ናቸው፡፡ እናም እንዲህ ያሉ አገራዊ ሕመሞችን አንዱ ወደ ሌላው ሳይወራወር፣ ሁሉም ራሱን በመፈተሽ ለጋራ መፍትሔ ቢተጋ ነው የሚመረጠው፡፡
በእርግጥ የአገራችን ብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሚከሰሱባቸው ጉዳዮች መካከል እጅግ ደካማ መሆናቸው (በመበታተን የሚታወቁ)፣ ብሔርን መሠረት ያደረጉና የተከፋፈሉ መሆናቸው ከሁሉም በላይ ለራሳቸው ክብር ይበልጥ ትኩረት በሚሰጡ ግለሰቦች የሚመሩ መሆናቸው፣ ትኩረታቸው ሥልጣን እንጂ የአገርና የሕዝብ ጥቅም እንዳልሆነ ድርጊታቸው የሚያሳብቅባቸው፣ ጠንካራ የድጋፍ መሠረትና አማራጭ ፖሊሲ የሌላቸው መሆናቸው፣ እንዲሁም እርስ በርስ በጥርጣሬ የሚተያዩና የሚገዳደሩ መሆናቸው በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ ትብትቦችን ከምክክሮቹ በኋላ ለማስቀረት ቁርጠኝነት ከሌለም ትርፉ ድካም እንዳይሆን ሊታሰብበት ይገባል፡፡
በአጠቃላይ የምንገኝበት አገራዊ ሁኔታ ሁላችንንም ሊያስቆጭ ይገባል፡፡ ከጦርነት፣ ከቀውስና ከግጭት አለመውጣት ማንንም ሊያሳምም ግድ ይላል፡፡ ተስፋ ያለው ለውጥ ተጀምሮ ሲያበቃ እያደር መበርታት እንጂ መንገዳገድና መውደቅንስ ምን አመጣው? ብሎ ለሌላ ለውጥና መሻሻል መነሳትም ያስፈልጋል፡፡ ቅድሚያ ግን ፖለቲካውና ፖለቲከኞች ከሕመማቸውና ከዕብደታቸው ወጥተው ኳስ በመሬት ያድርጉልን፡፡ ያኔ ቀሪው ጉዳይ መፍትሔ መገኘቱ አይቀርም፡፡