
30 ሀምሌ 2023, 07:36 EAT
ዛሬ ማንበብ እና መጻፍ የሚችል ሰው እጅ ላይ ሁሉ የሚገኘው እስክሪብቶ የ85 ዓመት ታሪክ አለው።
ይህንን የ85 ዓመት አዛውንት ውልደትህ የት ነው ቢሉት ሃንጋሪ ቡዳፔስት ይላል።
እድገቱ ግን ላቲን አሜሪካ ነው፤ አርጀንቲና።
ጫፎቹ ሾል ብለው ለረዥም ጊዜ ሊቆይ በሚችል ፕላስቲክ ውስጥ በተቀመጠ ቀለም እንዲያገለግል ሆኖ ነው የተሠራው፤ የእስክሪብቶ ፈጣሪ አባቱ ጋዜጠኛ ነው።
ለመጀመሪያ ጊዜ እስክሪብቶ ለዓለም ከተዋወቀ ወዲህ መሠረታዊ ለውጥ አልተደረገበትም።
በትንሽ ማሻሻያ ብቻ እስከ ዛሬ ድረስ አብሮን አለ።
ከተደረጉለት ማሻሻያዎች መካከል አንዱ የእስክሪብቶው ክዳን ነው።
ከጤና ጋር በተያያዘ የተነሳበትን ስጋት ለመቅረፍ ሲባል ክዳኑ ቀዳዳ እንዲኖረው የተደረገው በምክንያት ነው።
በስህተት አንድ ሰው ቢውጠው የሕክምና እርዳታ እስኪያገኝ መተንፈስ እንዳይቸገር ታስቦ ነው ቀዳዳ የተበጀለት።
እስክሪብቶ በመላው ዓለም አገልግሎት ላይ ይውላል።
ከዚህም ተነስተን በቀን ምን ያህል ተጠቃሚ ሊኖረው ይችላል ብንል 50 ሚሊዮን እስክቢርቶዎች በየዕለቱ እንደሚሸጡ ይገመታል።
በአውሮፓውያኑ 2006 መስከረም ወር ላይ ትልቁ የእስክሪብቶ አምራች የፈረንሳዩ ቢክ ኩባንያ ብቻ 100 ቢሊዮንኛውን እስኪብርቶ ለገበያ አቅርቦ መሸጡ በታሪክ ድርሳናት ተመዝግቧል።
ግን ይህ እስክሪብቶ እንዴት ለዓለም ሊተዋወቅ ቻለ?
- ልዩ ፍላጎት ላላት ልጃቸው ሲሉ ለዓመታት ዩኒቨርስቲ የቆዩት እናት እና በማዕረግ የተመረቀችው ልጃቸው25 ሀምሌ 2023
- በመጀመሪያው የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ከፍተኛ ነጥብ ካስመዘገቡ ተማሪዎች አንዷ19 ሀምሌ 2023
- 51 ኮርሶችን A+ ያመጣው ተማሪ21 ሀምሌ 2023
ታሪኩ የሚጀምረው በአውሮፓውያኑ 1930ዎቹ ሀንጋሪ ቡዳፔስት ውስጥ ነው።
ላስዝሎ ጋዜጠኛ ነው። ለአንድ ጋዜጣ በሪፖርተርነት ተቀጥሮ ሲሠራ በየዕለቱ ዜናዎችን ይጽፋል።
የሚጽፈው ደግሞ ቀለም በሚጠጣው ብዕር ነው።
በየዕለቱ የሚሰራቸውን ዘገባዎች ቀለም እየተነከረ በሚጻፍበት ብዕር ወረቀት ላይ ሲያሰፍር ቀለም እጁን ያበላሸዋል።
ቀለም የሚጠጣው ብዕር እጅን ማበላሸቱ ብቻ ሳይሆን፣ የጎንዮሽ ጉዳቱ ወረቀቱ ላይ ካረፈ በኋላም ቶሎ አለመድረቁ ሌላው ችግር ነበር።
ወረቀቱ ላይም ቢሆን ተዝረክርኮ ሥራን ጎዶሎ ያደርጋል።
እና ላስዝሎ ለብዕር የሚገለገልበትን ቀለም በሚገባ ሲያጠናው ቶሎ አለመድረቁ መሠረታዊ ችግር መሆኑን ተረዳ።
የሚሠራበትን ጋዜጣ ማተሚያ ሲያየው ደግሞ ማሽኑ ቀለሞቹን እየተሽከረከረ ወረቀቱ ላይ ሲያሳርፍ፣ ወረቀቱ በፍጥነት ቀለሙን መጥጦ እንደሚደርቅ ተመለከተ።
ስለዚህ ይህንን በአነስተኛ መጠን መሥራት ቢቻል፣ ቀለም እየተፋ እጅን ከሚያጨማልቀው ብዕር መገላገል እንደሚቻል አሰበ።
እስክሪብቶን ለማዘመን ግን እንደ ማተሚያ ማሽኑ ቀለምን የሚተፋ ሳይሆን፣ ዶልዶም ያለ ጫፍ እንዲሁም የሚጠቀመውን ቀለም ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ተገነዘበ።

ጋዜጠኛው ላስዝሎ ይህንን የፈጠራ ሐሳቡን ይዙ በቅርቡ ያገኘው ሰው የጥርስ ሐኪም የሆነው ወንድሙን ነው።
ጆርጅ የጥርስ ሐኪም ብቻ ሳይሆን የተዋጣለት ኬሚስት ጭምር ነው።
የእስክሪብቶን ቀለም ለማሻሻል ለጋዜጣ ሕትመት እንደሚጠቀሙበት ያለ ቶሎ ወረቀት ላይ ካረፈ በኋላ የሚደርቅ ቀለም አንደሚያስፈልግ ተረዳ።
ይህንን ማድረግ በኬሚስትሪ እውቀት ለተካነው የጥርስ ሐኪም ከባድ አልነበረም።
ወረቀት ላይ ሲያርፍ ቶሎ የሚደርቅ፣ ነገር ግን በእስክሪብቶው ውስጥ እያለ ምንም የማይሆን፣ በትንሽ ቀለም በርካታ ጽሑፎችን መጻፍ የሚያስችል ቀለም መሥራት ቻለ።
ይህ ሐሳብ ግን በምርምር እና በሙከራ ሂደት ውስጥ ስድስት ዓመታት ያህል አስፈልጎት ነበር።
ጋዜጠኛው ላስዝሎ ከወንድሙ ጆርጅ ጋር በመሆን ብዙዎች አስበው ማሳካት ያልቻሉትን ነገር ማድረግ ቻለ።
የጋዜጠኛው እስክሪብቶ ምትሃት የሚጀምረው እስክሪብቶው ከወረቀት ጋር ሲገናኝ ነው።
ወረቀቱ እና እስክሪብቶው ሲገናኙ ቀለሙ እየፈሰሰ በአግባቡ ይጽፋል። ሥራን ጨርሰው ሲያስቀምጡት ደግሞ ቀለሙ አይፈስም፤ አይንጠባጠብም።
ይህንን ሐሳብ የወሰደው የሕትመት ማሽን የሚሰራውን በመቅዳት ነው።
ላስዝሎ ለዚህ የፈጠራ ሥራው በ1938 ከብሪታኒያ የፈጠራ ባለመብት መሆኑን የሚገልጽ ምስክር ወረቀት አግኝቶበታል።
አንድ ቀን በሚኖርባት ሃንጋሪ የባሕር ዳርቻ ተቀምጦ የራሱ ፈጠራ በሆነው እስክሪብቶ እየጻፈ እያለ አንድ ግለሰብ ጠጋ ብሎ ምን እየሠራ እንደሆነ ጠየቀው።
ያ ሰው የአርጀንቲና ፕሬዝዳንት አውገስቲን ሁስቶ ነበር።
ላስዝሎ ለአንጀንቲናዊው ግለሰብ የራሱ ፈጠራ በሆነው እስክሪብቶ እየጻፈ መሆኑን ሲነግረው በሐሳቡ በመመሰጡ በስፋት ለገበያ ማቅረብ የሚፈልግ ከሆነ በጋራ መሥራት እንደሚችሉ ገልጾ አድራሻውን ሰጠው።
ላስዝሎ አድራሻውን ገረፍ አድርጎ ሲመለከት ፕሬዝዳንት የሚለውን ማየቱ የአንድ ኩባንያ ፕሬዝዳንት የሆነ ግለሰብ ያወራው መስሎት ነበር።
የሁለተኛው ዓለም ጦርነት መቀስቀስ ላስዝሎ ወደ ፕሬዝዳንት አውገስቲን አገር እንዲያመራ አደረገው።
በእርግጥ የጦርነቱ መቀስቀስ እስክሪብቶውን ለዓለም ገበያ በስፋት ለማስተዋወቅም እንቅፋት ሆኖ ነበር።

ላስዝሎ እና ወንድሙ የአይሁድ ዝርያ ስላለባቸው በ1941 ከአውሮፓ ወደ አርጀንቲና ተሰደዱ።
ሁለተኛው ዓለም ጦርነት አውሮፓን እና ፓስፊክን ሲያምስ ላስዝሎ እስክሪብቶውን በአርጀንቲና እያመረተ ለገበያ ማቅረብ ጀመረ።
እስክሪብቶዎቹ እንደ ዛሬው በየመደብሩ በቅናሽ ዋጋ የሚሸመቱ አልነበሩም።
በውድ ዋጋ እየተቸበቸቡ፣ ለሚወዱት እና ለሚያከብሩት ሰው በስጦታ መልክ የሚሰጧቸው ውድ ንብረቶች ነበሩ።
በወቅቱ 12 ዶላር ከ50 ሳንቲም ያወጡ የነበሩት እስክሪብቶዎች በዛሬ ዋጋ ቢተመኑ ከ210 ዶላር በላይ ይከፈልባቸዋል።
በ1945 (እኤአ) ደግሞ ሁለት የአሜሪካ ኩባንያዎች ግማሽ ሚሊዮን ዶላር በማውጣት ለሰሜን እና መካከለኛው አሜሪካ እስክሪብቶዎቹን አምርቶ የመሸጥ ፈቃዱን ለመግዛት ተጣመሩ።
ነገር ግን የመጨረሻ ስምምነቱን አድርጎ ፊርማቸውን ለማኖር ዘገዩ።
በዚህ መካከል ነው የፈረንሳዩ ኩባንያ ቢክ የእስክሪብቶውን የፈጠራ መብት የገዛው።
ለቢክ የላስዝሎ እስክሪብቶ የኩባንያው ዋና ምርት ሆነ።
ቢክ እስክሪብቶ ለገበያ በሚገባ እንዲዳረስ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል።
በዋጋ ረገድም ለብዙኃኑ እንዲዳረስ ማድረግ ችሏል።
በዚያው ዓመት ላስዝሎ የፈጠራ መብቱን ማይልስ ማርቲን ኤርክራፍት ካምፓኒ ለሚባል ለእንግሊዝ ኩባንያ ሸጠ።
በአርጀንቲና ገበያ የደራለት እስክሪብቶ የሮያል ኤር ፎርስን ቀልብ ገዛ።
ሮያል ኤር ፎርስ 30 ሺህ እስክሪብቶዎችን ለማዘዝ ሁለቴ ማሰብ አላስፈለገውም።
እስክሪብቶዎቹ የአውሮፕላን ሠራተኞች በአየር ላይ ከፍ ብለው ሲበሩ እንዲጠቀሙበት የታሰበ ነው።
ቀለም የሚጠጡት ብዕሮች አውሮፕላኖች ከፍታቸውን ጨምረው በበረሩ ቁጥር በሚኖር ግፊት የተነሳ ቀለማቸውን ያንጠባጥቡ እና የሚጻፍባቸውን ወረቀት ያበላሹ ነበር።
ስለዚህ የላስዝሎ እስክሪብቶ ውጤታማነቱ ቀለም ከሚጠጣው ብዕር የተሻለ ሆኖ ተገኘ።
ከዚህ በኋላም ቢሆን የላስዝሎ እስክሪብቶ የበርካታ ባለሀብቶችን ቀልብ መሳቡን አላቋረጠም።
አሜሪካዊው የቢዝነስ ሰው ሚልተን ሬይኖልድ፣ የአርጀንቲና ዋና ከተማ ቦነስ አይረስን ሲጎበኝ ባየው እስክሪብቶ ተመሰጠ።
በርካታ እስክሪብቶዎችንም ገዝቶ ወደ አሜሪካ ተመለሰ።
ከዚያም ሬይኖልስ ኢንተርናሽናል ፔን ካምፓኒን በመመሥረት እስክሪብቶዎቹን በአዲስ ዲዛይን ለአሜሪካ ገበያ አስተዋወቀ።
ላስዝሎ የጋዜጠኝነት ደመ ነፍሱ ነገሮችን በሚገባ እንዲመለከት፣ እንዲመረምር እና እንዲጠይቅ ረድቶታል።
ላስዝሎ ዓለምን ካጥለቀለቀው እስክሪብቶ በተጨማሪ በስሙ የተመዘገቡ 300 የፈጠራ ሥራዎች አሉት።
በ1985 (እአአ) ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ላስዝሎ የልብስ ማጠቢያ ማሽንን ጨምሮ በርካታ የፈጠራ ሥራዎችን ለዓለም አበርክቷል።
ዛሬ በሁሉም ሰው እጅ በመላው ዓለም የሚገኘው እስክሪብቶ በሃንጋሪ ምድር የመጀመሪያው ፈጠራ ተሠርቶ፣ በአርጀንቲና በሚገባ ተሞክሮ እና ተፈትሾ በገበያ ውስጥ በስፋት ተሰራጭቶ የሚጽፉ እጆችን ያለ ችግር ያገለግላል።