
ከ 9 ሰአት በፊት
የሩሲያው ቅጠረኛ ቡድን ቫግነር ተዋጊዎች ስደተኛ መስለው ወደ አውሮፓ ኅብረት አገራት ዘልቀው ሊገቡ እንደሚችሉ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ።
የፖላንድ ጠቅላይ ሚንስትር ማቲዩዝ ሞራዌይችኪ የተዋጊ ቡድኑ አባላት የሕገ-ወጥ የስደተኞች ዝውውርንም ሊያቀላጥፉ ይችላሉ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደሚሉት በቅርብ ቀናት ወደ 100 የሚጠጉ የቫግነር ተዋጊዎች ከፖላንድ እና ሊቱዌኒያ ድንበር አቅራቢያ ወደምትገኘው የቤላሩስ ከተማ ተጠግተዋል።
ቫግነር በቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ላይ ያነሳው አመጽ ከከሸፈ በኋላ ከክሬምሊን ጋር በደረሰው ስምምነት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የተዋጊ ቡድኑ አባላት ወደ ቤላሩስ መሻገራቸው ይታወሳል።
የቫግነር ቡድን በቤላሩስ መገኘት እረፍት የነሳት ፖላንድ ከቤላሩስ በምትዋሰንበት የምስራቅ ድንበሯን ማጠናከርን መርጣለች።
የፖላንድ ጠቅላይ ሚንስትር ማቲዩዝ ሞራዌይችኪ ወደ 100 የሚጠጉ ተዋጊዎች ወደ ድንበር መቅረባቸውን ገልጸው እነዚህ የቅጠረኛ ቡድኑ አባላት ስደተኛ መስለው ወይም ከስደተኛ ጋር ተመሳስለው ወደ አውሮፓ ሊገቡ ይችላሉ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ጨምረውም የቡድኑ አባላት የቤላሩስ ድንበር ጠባቂ ዘብ መስለው ስደተኞች የአውሮፓ ድንበርን እንዲያቋርጡ ሊረዱ ይችላሉ ብለዋል።
- ከአስራ አንዱ መነኮሳት ግድያ ጀርባ ያለው ምስጢር30 ሀምሌ 2023
- ጽሕፈትን እስከ መጨረሻው የቀየረው ርካሹ እስክሪብቶ እንዴት እውን ሆነ?30 ሀምሌ 2023
- “የአቶሚክ ቦምብ አባት” የሚባለው ኦፕንሃይመር እና የሒንዱ እምነት29 ሀምሌ 2023
ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ አገራቸው በአውሮፓ የስደተኞች መጥለቅለቅልን በመፍጠር የአውሮፓ ኅብረት አገራትን ማስቆጣት እንደማትፈልግ ገልጸው ነበር።
ቫግነር በፑቲን አስተዳደር ላይ የቀሰቀሰው አመጽ ከከሸፈ በኋላ ቡድኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቹን ወደ ቤላሩስ አዟዙሯል።
ወታደሮቹ በቤላሩስ ስለሚኖራቸው ቆይታ ቡድኑ ያለው ነገር ባይኖርም ለቤላሩስ ሠራዊት አባላት ግን ወታደራዊ ስልጠና እንደሚሰጡ የቤላሩስ መሪዎች ተናግረው ነበር።
የቫግነር ወታደሮች ቤላሩስ መግባታቸውን ተከትሎ ፖላንድ፣ ሊቱዌኒያ እና ላትቪያ ከቤላሩስ የሚያዋስናቸውን ድንበር ለመዝጋት በጋራ ሊወስኑ እንደሚችሉ የፖላንድ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ከጥቂት ቀናት በፊት ተናግረው ነበር።
የቤላሩሱ ሉካሼንኮ ግን የቫግነር ተዋጊዎች በመካከለኛው ቤላሩስ ይቆያሉ ሲሉ ተናግረው ተናግረዋል። ሉካሼንኮ ከፑቲን ጋር በነበራቸው ንግግር “ወደ ምዕራብ ለመሄድ እየጠየቁ ነው . . . ወደ ዋርሶው ጉዞ ለማድረግ . . .” ብለው ከቀለዱ በኋላ፤ “ግን እንደተስማማነው በመካከለኛው ቤላሩስ እንዲቆዩ እያደረኩ ነው” ብለዋል።
የፖላንዱ ጠቅላይ ሚንስትር በዚህ ዓመት ብቻ ከቤላሩስ ወደ ፖላንድ ድንበር ለመሻገር 16ሺህ ሙከራዎች ተደርገዋል ብለዋል።
ፖላንድ እና ሊትዌኒያን ከቤላሩስ በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበራቸውን የሚሻገሩ ሰዎች ቁጥርን ለመቀነስ አጥር አጥረዋል።