ኒጀር

ከ 8 ሰአት በፊት

በኒጀር የአገሪቱ ጦር መፈንቅለ መንግሥት በመፈጸም ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ የአውሮፓ ሕብረት ከአገሪቱ ጋር የነበረውን ሁሉንም አይነት የደኅንነት ትብብር ማቋረጡን አስታወቀ።

ይህ የአውሮፓ ሕብረት የእግድ ውሳኔ የተሰማው ዩናይትድ ስቴትስ መፈንቅለ መንግሥት ለተፈጸመባቸው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ባዙም “የማይናወጥ ድጋፍ አለኝ” ካለች በኋለ ኣነው።

የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ሕብረቱ መፈንቅለ መንግሥት ፈጻሚዎቹን እንደ አገር አስተዳደሪ አይመለከትም በማለት የደኅንነት ትብብር እና የበጀት ድጋፍ ላልተወሰ ጊዜ እንዲቆም መደረጉን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ለኒጀር አደርግ የነበረውን እርዳታ እና የበጀት ድጋፍ አቁሜያለሁ ብላለች።

አሜሪካ ደግሞ መፈንቅለ መንግሥት ለመፈጸሙት እውቅና አልሰጥም ብላለች።

የአፍሪካ ሕብረት ደግሞ የኒጀር ጦር ወደ ጦር ሰፈሩ በ15 ቀናት ውስጥ እንዲመለስ ጥሪውን አቅርቧል።

ጸንፈኛ እስላማዊ ቡድኖችን በመዋጋት ረገድ የምዕራባውያን ቁልፍ አጋር ናቸው የሚባሉት ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ባዙም ከቀናት በፊት በራሳቸው የክብር ዘብ መሪ ጄኔራል አብዱራህማኔ ቺያኒ ከስልጣን ተወግደዋል።

ጄኔራል አብዱራህማኔ ቺያኒ በአገሪቱ የደኅንነት እጦት እና ሙስና ተንሰራፍቷል እንዲሁም የምጣኔ ሃብት ችግሩ ሕዝቡን አማሯል በማለት ነው ፕሬዝዳንቱን ገልብጠው እራሳቸውን የሾሙት።

አሁን ላይ ምዕራባውያን አገራት በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙት የጦር ጄኔራል ከየትኞቹ አገራት ጋር ወዳጅነት ይመሰርታሉ የሚለውን በትኩረት እየተመለከቱ ነው።

መፈንቅለ መንግሥት ተፈጽሞባቸው በወታደራዊ አገዛዝ ሥር የሚገኙ የኒጀር ጎረቤት አገራት ቡርኪና ፋሶ እና ማሊ ፊታቸውን ወደ ሩሲያ አዙረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነር በኒጀር የተፈጸመውን መፈንቅለ መንግሥት ትልቅ ድል ነው ሲል ገልጾታል።

የቫግነር መሪ ዬቭጌኒ ፕሪጎዢ “በኒጀር የሆነው ነገር የኒጀር ሕዝብ በቅኝ ገዚዎቻቸው ላይ ያደረጉት ትግል ነው። . . . ዛሬ ነጻነታቸውን እያገኙ ነው” ስለማለታቸው ከቡድኑ ጋር ቅርበት ያለው የቴሌግራም ቻናል ገልጿል።

ቫግነር በመካከለኛው አፍሪካ ሪፓብሊክ እና ማሊ ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች በአፍሪካ አሰማርቶ የሚገኝ ሲሆን አብዛኛውን ግዜ በየአገራቱ የሚገኙ የማዕድን ማውጫ ስፍራዎችን በመቆጣጠር በንግድ ሥራ ላይ ይሰማራል።

የቡድኑ አባላት በተሰማሩባቸው አገራት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸም ይከሰሳሉ።