
30 ሀምሌ 2023, 07:35 EAT
“የሞቱበት መንገድ የዚህ ታሪክ አስኳል እንደሆነ ግልጽ ነው። ለእኔ ግን ዋነኛው ጉዳይ እነዚህ ሴቶች መነኮሳት ያደረጉት አስደናቂ ተግባር ነው። ታሪኩን ልዩ የሚያደርገውም ይህ ነው።”
ወቅቱ ከሰማንያ ዓመታት በፊት ነበር፤ በጎርጎሪዮሳውያኑ ነሐሴ 01/1943 ዓ.ም።
የጀርመን ናዚ ጦር 11 የሮማ ካቶሊክ መነኮሳትን ገደለ።
እማሆይ ክላራ ቮልቼክ በናዚ ጦር የተሰዉትን የእነዚህን መነኮሳት መቃብር በተደጋጋሚ ይጎበኛሉ።
መነኮሳቱ “የኖዎግሮዴክ ሰማዕታት” ወይም “የተባረኩት ሜሪ ስቴላ እና አስሩ መነኮሳት” በመባልም ይታወቃሉ።
“መነኮሳቱ ከሞት ተርፈው ለአስገዳጅ የጉልበት ሥራ ለግዞት የተዳረጉ 120 ሰዎችን ሕይወት ታድገዋል” በማለት እማሆይ ክላራ ከሚገኙበት ምሥራቅ አውሮፓ፣ ቤላሩስ ለቢቢሲ በስልክ ተናግረዋል።
መነኮሳቱ ለፈጸሙት መስዋዕትነትም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ሰጥታቸዋለች።
በጎርጎሪዮሳውያኑ 2000 ዓመት የሮማው ሊቀ ጳጳስ ጆን ፖል በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከቅድስና በፊት የሚሰጠውን ማዕረግ በመስጠት ስለመስዋዕትነቸው ተናግረዋል።
ጳጳሱ “እነዚህ ሴቶች በእስር ለነበሩ የኖዎግሮዴክ ነዋሪዎች ሕይወት ምትክ ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት የሚያስችል ጥንካሬ ከየት አገኙት?” ሲሉም ጠይቀዋል።
ነገር ግን መነኮሳቱ የተገደሉት እስረኞቹ እንዲፈቱ በሚል ምትክ ስለመሆኑ ግልጽ ማስረጃ የለም።
- ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ‘ጃ’ በዓለም አቀፉ ምናብ23 ሀምሌ 2023
- ጃፓን ላይ የወረደው አቶሚክ ቦምብ ፈጣሪ፤ ሮበርት ኦፕንሃይመር ማን ነው?21 ሀምሌ 2023
- አነቃቂ ንግግሮች ወዴት ያደርሱናል? ወደ የማይጨበጥ ተስፋ ወይስ ወደ ስኬት?29 ሀምሌ 2023
መነኮሳቱ ለምን ተገደሉ?
ታሪኩ የሚጀምረው በአውሮያውያኑ 1929 ነው።
የሆሊ ፋሚሊ ኦፍ ናዝሬት አባላት የሆኑ ሁለት መነኮሳት አነስተኛ ወደሆነችው ኖዎግሮዴክ ከተማ የመጡበት ወቅት ነው።
የኖዎግሮዴክ ከተማ ነዋሪ ባለፉት መቶ ዓመታት ቢቀያየሩም ሁለተኛው ዓለም ጦርነት በተቀሰቀሰበት እና በፖላንድ ቁጥጥር ስር በነበረችበት ወቅት 20 ሺህ ያህል ነዋሪዎች ነበሯት።
በ1939 የሶቪየየት ኅብረት ኃይሎች ከተማዋን ተቆጣጠሯት።
በዚያ ወቅት መነኮሳቱ ከገዳማቸው ወጥተው በምዕመናን ቤቶች ለመጠለል ተገደዱ።
በ1941 የጀርመን ናዚ ጦር የሶቪዬት ኃይሎችን ወራሪዎች ናቸው ሲል ከከተማዋ ማስወጣት ቻለ።
ከተማዋን የተቆጣጠረው የናዚ ጦር መነኮሳቱ ወደ ገዳማቸው እንዲመለሱ አበረታታቸው። የከተማዋ ነዋሪዎች ግማሽ ያህሉ አይሁዳውያን ነበሩ።
ወዲያውኑ ነበር የናዚ ጦር አይሁዳውያኑን ለማጥፋት ወደ ጭፍጨፋ የገባው።
በመጀመሪያው የ1941 ጭፍጨፋ 5100 አይሁዶች ተገደሉ። በዓመቱ 4500 አይሁዶች ተጨፈጨፉ።
በ1943 የተለያዩ ቡድኖች በአካባቢው መንቀሳቀስ ጀመሩ።
የናዚ ምስጢራዊ ፖሊስ የሆነው ጌስታፖ ማንኛውንም ተቃውሞ ለመደምሰስ በሚል 180 ሰዎችን አሰረ።
ብዙም ሳይቆይ እነዚህ የታሰሩ ሰዎች ሁሉ እንደሚገደሉ ተነገረ።

የካህኑ የዐይን እማኝነት
አባ አሌክሳንደር ዚየንኪዊስዝ በኖዎግሮዴክ ከጭፍጨፋው የተረፉ ብቸኛው ካህን ነበሩ።
በገዳሙ አስራ ሁለት መነኮሳት ነበሩ።
የ55 ዓመቷ እማሆይ ሜሪ ስቴላ በዕድሜ ትልቋ ሲሆኑ፣ ትንሿ ደግሞ የ27 ዓመቷ እማሆይ ሜሪ ቦሮሜያ ናቸው።
በከተማዋ ውስጥ የነበረውን እስር አስመልክቶ የእማሆይ ሜሪ ምላሽ ምን እንደነበር አባ አሌክሳንደር አስፍረዋል።
“አምላኬ ሆይ የሕይወት መስዋዕትነት ካስፈለገ የቤተሰብ ግዴታ የሌለብንን እኛን ተቀበል። ቤተሰብ፣ ባለቤት እና ልጆች ያላቸውን አትርፋቸው። አምላክ ሆይ ይህንን እንድታደርግ እንጸልያለን” ሲሉም እማሆይ ሜሪ መናገራቸውን አባ አሌክሳንደር የሰጡት እማኝነት እና በኋላ የታተመ ሃይማኖታዊ ጽሁፍ ላይ ሰፍሯል።
አክለውም እስረኞቹ የሚገደሉበትን ሁኔታ ለማስቀረት የተጠቀሙባቸው ዘዴዎችም ሆነ ይገደላሉ ስለተባሉ እስረኞች ማንነት ለማወቅ ስለመሞከራቸው የሚጠቁሙ ምንም መዛግብት የሉም” ብለዋል።
ከአንድ ሳምንት በኋላም መነኮሳቱ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተጠሩ።
አባ አሌክሳንደር እማሆይ ሜሪ ስቴላ ለመጨረሻ ጊዜ ያገኟቸው ከመገደላቸው አንድ ቀን በፊት ነበር።
አባ አሌክሳንደር የሚገናኙበት የመጨረሻ ጊዜ እንደሆነም አልተረዱም።
ሆኖም እማሆይ ሜሪ ተጨንቀው፣ ግራ መጋባታቸውም ፊታቸው ላይ ይታይ ነበር።
እማሆይ ሜሪ ለአስገዳጅ የጉልበት ሥራ ወደ ጀርመን በግዞት ለመሄድ እየጠበቁ እንደሆነ ለአባ አሌክሳንደር ነገሯቸው።
እማሆይ ሜሪ ከ12ቱ መነኮሳት መካከል እማሆይ ማልጎርዛታን አስቀርተው ከአስር መነኮሳት ጋር ሆነው ወደ ፖሊስ ጣቢያው አመሩ።
በማግስቱም አባ አሌክሳንደር በቅዳሴ ወቅት የመነኮሳቱ ቦታ ባዶ መሆኑን ተመለከቱ። ጥልቅ የሆነ ሐዘን ተሰማቸው።
በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንደሚደረገው የምዕመናኑን ኑዛዜ ለመስማት በዝግጅት ላይ እያሉም መነኮሳቱ በዚያች ቀን ነሐሴ 01/1943 እንደተገደሉ ተረዱ።
የተገደሉበት ምክንያት ለአባ አሌክሳንደር ግልጽ አልነበረም። በኋላም የናዚው ምስጢራዊ ፖሊስ ጌስታፖ በስህተት እንደገደላቸው ሲወራ ሰምተዋል። ጌስታፖ የሶቪዬት ሽምቅ ተዋጊዎችን በመርዳት የተጠረጠሩ ሌሎች አባላትን ሊገድል እንደሆነ ተነገረ። ሆኖም አባ አሌክሳንደር ራሳቸው ተደበቁ።
በ1945 የናዚ ጦር ተሸንፎ ከከተማዋ ሲወጣ አባ አሌክሳንደር መነኮሳቱን ከተቀበሩበት አውጥተው እንደገና ከቤተ ክርስቲያኑ አጠገብ አጽማቸው በክብር እንዲያርፍ አድርገዋል።

የሚቃረኑ ማስረጃዎች
የአባ አሌክሳንደር የእማኝነት ምስክር ታማራ ቬርሺትስካያ ካደረጉት ጥናት ጋር ይቀራረባል።
ታማራ በኖዎግሮዴክ በናዚ ጭፍጨፋ ለተቀጠፉ አይሁዳውያን መታሰቢያ ሙዚየም በአውሮፓውያኑ 1992 አቋቁመዋል።
“እኔ እንደምረዳው በዚያን ወቅት የተፈጸሙ ሁለተ ክስተቶች ተቀራራቢነት ቢኖራቸውም ተዛማጅነት ያላቸው አይመስለኝም” በማለት ታማራ ከኖዎግሮዴክ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአውሮፓውያኑ 2011 ከአሜሪካው የሆሎኮስት መታሰቢያ ሙዚየም ጋር በመጣመር የዐይን ምስክሮችን እንዲሁም ከናዚ ጭፍጨፋ የተረፉ በርካታ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ አድርገዋል።
ማሪያ ካራቫስካ የተባሉ ግለሰብም ወደ ጀርመን በግዞት ከተላኩት መካከል ሁለት ወንድሞቻቸው እንደነበሩበት ለታማራ ነግረዋቸዋል።
በዚህም ወቅት 112 ፖላንዳውያን ወደ ጀርመን ለጉልበት ሥራ ተግዘው ነበር።
ታማራ በጀርመንኛ ቋንቋ የተጻፈ የስም ዝርዝር መዛግብትን ሲያገላብጡ አግኝተዋል። ይህም ዝርዝር ምናልባትም ወደ ጀርመን የተላኩ 95 ፖላንዳውያን ስምን ሳይዝ አይቀርም።
ማሪያ ወንድሞቿ እንዴት እንደታሰሩም ይናገራሉ።
“ሦስቱ ወንድሞቼ ተይዘው አንዱ ሊያመልጥ ቻለ። በድብቅ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ቡድኖችን እያንቀሳቀሱ ነው በሚልም ተከሰሱ። ጀርመኖቹ ሊገድሏቸው አስበው ነበር። መቃብሮቻቸውን ጭምር ቆፍረዋል” ይላሉ።
መጀመሪያ ላይ በጌስታፖ የታሰሩት 180 ሰዎች ነበሩ።
እነዚህ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉት የጌስታፖ ኃላፊ ዊልሄልም ትራብ ባልነበረበት ወቅት ነበር። ዊልሄልም ቤተሰቦቹ በጀርመን ትልቅ እርሻ ነበራቸው።
ኃላፊው የግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር መዋል እንደሰማ ወደ መዲናዋ ሚኒስክ አቅንቶ እስረኞቹ በቤተሰቦቹ እርሻ ቦታ እንዲሰማሩ አለቆቹን መማጸኑን ታማራ ይናገራሉ።
“ዊልሄልም ለማሪያ ወንድሞች ለጉዞው አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ይዘው እንዲመጡ በሚል ለአንድ ምሽት ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ እንደፈቀደላቸው ማሪያ ነገረችኝ” ይላሉ ታማራ።
ሁሉም እስረኞች በማግስቱ ወደ ባቡር ጣቢያው እንዲመጡ ቀጭን ትዕዛዝ ተላልፎላቸው እንደነበርም ማሪያ ለታማራ ነግረዋቸዋል።
“እውነት ነው ግለሰቦቹ ከታሰሩ በኋላ፣ የታሰሩባቸው ፖላንዳዊ ቤተሰቦች ወደ ቤተ ክርስቲያኗ አምርተው እርዳታ ጠይቀው ነበር” ይላሉ ታማራ።
“መነኮሳቱም ጸለዩ። እማሆይ ሜሪ ስቴላ በዚህ ጸሎት ወቅት በእነሱ ፈንታ የእኛ ሕይወት ይሰዋ በማለት የተናገሩት እውነት ሊሆን እንደሚችል አምናለሁ” ይላሉ ታማራ።
ሆኖም ታስረው የነበሩ ግለሰቦችን ዕጣ ፈንታ በተመለከተ በመነኮሳቱ እና በናዚዎች መካከል ድርድር ስለመደረጉን የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም ሲሉም ታማራ ይናገራሉ።
“መነኮሳቱ የታሰሩት እነዚህን ፖላንዳውያን እስረኞች ከማስለቀቅ ጋር የተገናኘ አይመስልም” ሲሉ ታማራ የደረሱበትን ያስረዳሉ።

ለሌሎች የመኖር ጥሪ
ለግዳጅ የጉልበት ሥራ ወደ ጀርመን በግዞት የተወሰዱት ፖላንዳውያን በሙሉ ከጦርነቱ በሕይወት እንደተረፉ ታማራ ይናገራሉ።
የሆሊ ፋሚሊ ኦፍ ናዝሬት ገዳም ኃላፊ እማሆይ አማቢሊስ በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ የሚገልጹ የቤተ ክርስቲያን ሰነዶችን አዘጋጅተዋል።
በእነዚህ ሰነዶች ላይ እንደሰፈረው “መነኮሳቱ በእምነት፣ በአምላክ ፍቅር፣ የሰው ልጆችን እና ጎረቤታቸውን በማፍቀር ሕይወታቸውን መስዋዕት እንዳደረጉ እኛ መነኮሳቱ በሙሉ እርግጠኞች ነን” ይላል።
መነኮሳቱ በሕይወታቸው መስዋዕትነት ስለመክፈላቸው ገለልተኛ መረጃ አለመኖሩን በተመለከተ ቢቢሲ እማሆይ አማቢሊስን ሲጠይቃቸውም “መነኮሳቱ እንደሚሰው ተናግረው ነበር። አምላክም መስዋዕትነታቸውን እንደተቀበለ እናምናለን” የሚል ምላሽም ሰጥተዋል።
በኖዎግሮዴክ ያለው የአማኞች ቁጥር እየተሸረሸረ ባለበት ወቅት እማሆይ ክላራ በሃይማኖታቸው እንደጸኑ ናቸው።
“የእህቶቻችን መስዋዕትነት እስረኞቹን እንዳዳነ አምናለሁ” ይላሉ።
“የሰው ልጅ አመክንዮን በመጠቀም እውነታዎችን በተለያየ መንገድ ሊተረጉም እንደሚችል አውቃለሁ፤ ነገር ግን ጌታ መስዋዕትነታቸውን ሰምቶ ተቀብሏል” ብለዋል።