ቭላድሚር ፑቲን

ከ 9 ሰአት በፊት

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን ጋር ለሰላም መደራደር የሚለውን ሐሳብ እንደማይቃወሙት ገለጡ።

በሴይንት ፒተርስበርግ ከአፍሪካ ሃገራት መሪዎች ጋር ስብሰባ የነበራቸው ፑቲን፤ የአፍሪካና የቻይና አሸማጋዮች ሰላም ለማምጣት መላ ሊፈጥሩ ይችላሉ ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን አክለው እንደሚሉት የዩክሬን ጦር ጥቃት እየፈፀመ ሳለ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ እጅግ ከባድ ነው።

ዩክሬን እና ሩሲያ ከዚህ ቀደም ለንግግር እንዲቀመጡ ተጠይቀው ያለቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር መድረክ እንደማይመጡ ገልጸው ነበር።

ዩክሬን ደንበሮቿ ልክ በፈረንጆቹ 1991 እንደነበረው እንዲከለል ትፈልጋለች። ሩሲያን ይህ አጥብቃ ትቃወማለች።

ሞስኮው እንደምትለው የሰላም ስምምነቱ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ ኪየቭ “አዲሱን የግዛት ሁኔታ” መቀበል አለባት።

ቅዳሜ ምሽት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ በአሁኑ ወቅት በዩክሬን ጦርነት ጥቃት የማጠናከር ዕቅድ እንደሌላቸው ፑቲን ተናግረዋል።

አንዳንድ ሰዎች ሩሲያን ከውስጥ ሆነው እየጎዷት ነው የሚሉት ፑቲን ተቃውሞ ያሰሙ ሰዎች መታሠራቸውን ተከላክለዋል።

ብዙ ሐሳቦችን በዳሰሱበት መግለጫቸው የሩሲያው ፕሬዝዳንት በያዝነው የፈረንጆቹ ወር መባቻ የክሪሚያ ድልድይ ላይ ፍንዳታ ከደረሰ በኋላ ሃገራቸው “የመከላከል እርምጃ” መውሰዷን አሳውቀዋል።

ሁለት ሰዎች ከሞቱበት የክሪሚያ ፍንዳታ በኋላ ፕሬዝዳንት ፑቲን ለዚህ የዩክሬን “የሽብር ድርጊት” ምላሽ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

ዩክሬን፤ በቁጥጥር ሥር ያለውን ሠርጥ ከሩሲያ ስለሚያገናኘው ድልድይ ፍንዳታ ኃላፊነት አልወሰደችም።

ሰባት የአፍሪካ ሃገራት መሪዎችና ተወካዮች ባለፈው ወር የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪን እና የሩሲያው አቻቸውን አግኘተው ማናገራቸው ይታወሳል።

መሪዎቹ ዓላማቸው ሰላም ማምጣት ቢሆንም አሁንም የዩክሬን ጦርነት እንደቀጠለ ነው።

በሰሜን-ምስራቅ የዩክሬን ክፍል ሱሚ በምትባለው ሥፍራ አንድ ሰው በሮኬት ጥቃት ሲሞት አምስት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ሲል የዩክሬን ሃገር ውስጥ ጉዳይ መግለጫ አውጥቷል።

ሚኒስቴሩ በቴሌግራም ገፁ እንዳለው የሩሲያ ሚሳዔል ቅዳሜ አመሻሹን አንድ የትምህርት ተቋም መቷል።

ቢቢሲ ይህን መረጃ በራሱ ማጣራት አልቻለም።

በሌላ በኩል በደቡባዊ ዩክሬን ዛፖርዥዢያ ከተማ በሚሳዔል ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን የከተማዋ ባለሥልጣን ገልጠዋል።

ባለሥልጣኑ እንደሚሉት “የጠላት ሚሳዔል” የመኖሪያ ቤት መስኮቶችን አርግፏል፤ የትምህርት ተቋማትና መገበያያ ሥፍራዎች ላይ ጉዳት አድርሷል።

ሩሲያ በበኩሏ እሑድ ንጋት ሞስኮው ላይ በደረሰ የድሮን ጥቃት ሕንፃዎች መጎዳታቸውን አሳውቃለች።

የከተማዋ ከንቲባ ሰርጌይ ሶባያኒን ዩክሬንን በወቀሱበት ጥቃት ማንም ሰው እንዳልተጎዳ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ እጅግ ከባድ የውጊያ ቀጣና የሆነችው ባኽመት አቅራቢያ ያሉ የዩክሬን ልዩ ኃይሎችን ጎብኝተዋል።

የዩክሬን ባለሥልጣናት እንሚሉት ወታደሮቻቸው ቀስ በቀስ ባለፈው ግንቦት በሩሲያ ወታደሮች ወደተያዘችው ምስራቃቂት ከተማ እየተጠጉ ነው።