ያልተናገርንለት ያልመሰከርንለት ታሪክ እንደሌለ ይቆጠራል
‹‹ባሕረ ጻና ብሩር
ባሕረ አፍሪቃ ምሉእ ዕጣቃ ደረታ››፡
ትርጉሙም ብርሃን የለበሰ ንጹሕ የጣና ባሕር ለብሔረ አግዓዚ (ለኢትዮጵያ) ዕንቋ ሽልማቷ ነው ።”
በኢትዮጵያ ከሚገኙ ሐይቆች በስፋትም በታሪካዊነትም በቀዳሚነትም የሚጠቀሰው ለአፍሪካ መከበቢያ እንደሆነ የተረገረለት በልብ አምሳያ የተሠራ፣ ከልብ የመነጨ ሃይማኖት፣ እምነት፣ ታሪክ፣ ትውፊት፣ አርቆ አሳቢነትና ደግነትን አቅፎ የያዘዉ ከኤዶም ገነት የተጨለፈ፣ የቃል ኪዳኗን መርከብ ያንሳፈፈ፣ ፍጥረቱንም ሁሉ ያተረፈዉ
የዓባይ መኖር ህልውና፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ማስቀመጫ ሳንዱቅ፣ የቅዱሳት መጻሕፍት፣ የቅዱሳን ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት መገኛ መሸሸጊያ በመሆን ክፉውን ዘመን ያሳለፈው ፣ ፍጥረታትን ያተረፈው ፣ ዓባይን ያንሳፈፈ ሚስጥራዊ ሐይቅ ፡፡
ይህ ምንጩ ከኤዶም ገነት ሚወርደው ግዮን በላዩ ላይ አልፎ የሚሄድበት በኢትዮጵያ ትልቁ የሆነዉና
አጠቃላይ ስፋቱ 695,885 ሔክታር ላይ የተንጣለለው
ይህ ሀይቅ ከሰሜን እስከ ደቡብ ያለው የሐይቁ ርዝመት 85 ኪሎ ሜትር ሲቃረብ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ያለው ስፋቱም 66 ኪሎ ሜትር የሚገመተው ሀይቅ
በልብ አምሳያ እንደሚቀመጡ ሁሉ ከልብ የመነጨ ሃይማኖት፣ እምነት፣ ታሪክ፣ ትውፊት፣ አርቆ አሳቢነትና ደግነትን መገለጫው የሆነ እልፍ ሚስጥራትን በጉያው የያዘ የኢትዮጵያ የታሪክና የጥበብ መናገሻ ነው
በሃይቁ የተከማቸው ውኃ ብቻ አይደለም፤ ዓሳና አዕዋፋት ብቻም አይደለም፡፡ የቀደመውን ዘመን ማውጫ የሚመጣው ዘመን አቅጣጫ መትለሚያ፣ ታሪክ፣ ቅርስና ጥበብን ሁሉ አቅፏል፡፡
የጣና ሐይቅና አካባቢው ዉበትም ከወንዙ፣ ከመንደሩ ፤ከቀየዉ ፣ ከአገሩ ከአህጉሩ አልፎ የዓለም ቅርስ የብዝኃ ሕይወት መለያ ሆኖ
በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ከሰኔ 1 ቀን እስከ ሰኔ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ጉባኤውን ያካሄደውና የብዝኃ ሕይወት ጉዳይን የሚመረምረው ዓለም አቀፉ ምክር ቤት ጣና ሐይቅን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኒስኮ በያዘው ብዝኃ ህይወት ክምችት በቅርስነት መዝግቦታል።
ጣና በጥንታዊ ቋንቋ (ግእዝ) አገላለጽ ‹‹ጻና ሐይቅ›› ይባላል፡፡ድንግል ማርያም በገዳሙ የነበራትን ቆይታ አጠናቃ ስትመለስ “ፀአና በደመና” በደመና ጫናት የተባለው በጊዜ ብዛት ለአሁኑ የሐይቁ መጠሪያ ስም “ጣና” መሠረት እንደሆነዉም በሃይቁ የሚገኙ የብራና መፅሐፍት ያስረዳሉ ።
የአቴናው ድራማ ጸሐፊ አስክለስ ‹‹መዳብ የተቀባው ሐይቅ የኢትዮጵያ ጌጥ›› ብሎ የተቀኘለት፡፡
ባለቅኔው ሆሜርም ‹‹ከሌሎች የተለየና ጥርት ያለ የውኃ ባለቤት ነው፤›› ብሎ ያሞካሸዉ ግልገል ዓባይ፣ ርብ፣ ጉማራ፣ እንፍራንዝና መገጭ ጨምሮ
ከ40 በላይ ወንዞችና ጅረቶች የሚፈሱለትና
የዓለማችን በርዝመቱ ትልቁ ወንዝ ዓባይ መንሳፈፍያ የሆነዉ ጣና ሐይቅ
ከ31 በላይ ደሴቶች እነዚህ ደሴቶች ላይ ደግሞ ከ21 የሚበልጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ገዳማት በርካታ እድሜ ጠገብ ጽላቶች፣ ንዋየ ቅዱሳት፣ ብርቅዬ የብራና መጻህፍት፣ የታላላቅ መሪዎችና ቅዱሳን አጽም፣ ከኦሪት እስከ አዲስ ኪዳን የተንጣለለ ታሪክ፣ ብዙ ብዙ ገና ያልደረስንባቸው ምስጢራዊ ታሪኮች ያሉበት የኢትዮጵያዊያን ሁሉ መስታወት ነዉ
በ14ኛ ምዕት ዓመት አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ባመነኮሷቸው ‹‹ሰባቱ ከዋክብት›› ተብለው በሚጠሩት ቅዱሳን አባቶች የተመሠረቱት በሐይቁ ገዳማትና አድባራት በታሪክ ተሞልተዋል፣ በሃይማኖት ከብረዋል፣ በቅዱስ መንፈስ ጸንተዋል።
በገዳማቱና በአድባራቱ ስለአለም የሚማለዱ ቅዱሳን ይኖራሉ፣ ያለ ማቋረጥ ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም ይጸልያሉ፣ የፈጣሪን ስም እየጠሩ ምስጋና ያቀርባሉ፣ አምላክ ምድርን በበረከት ይዋጃት ዘንድ ይማጸናሉ፡፡
ጣና ምድር ጥፋት ውኃ በጠፋች ጊዜ ዘር እንዲያተርፍ ቃል ኪዳን የተሰጠው የኖኅ መርከብ ማየ አይኅ መጉደል ሲጀምር በ7ኛ ወር ከወሩም በ27ኛው ቀን በአናቱ ላይ ያረፈበት ታላቅ ሐይቅ ሲሆን የኖኅ መርከብ ያረፈበትም አራራት ተራራ በጣና ራስጌ (ዘጌ) የይጋንዳ ተክለሃይማኖት ቤተ ከርስቲያን ላይ ይገኛል።
ከ3000 ዓመት በፊት የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ የኾነችው ታቦተ ጽዮን ቀዳማዊ ምኒሊክ ከ318 ሌዋውያን እና ከ12 ነገደ እስራኤል ጋር ይዞ ወደ ኢትዮጵያ በመጣ ጊዜ ያረፈችው ጣና ቂርቆስ ገዳም ላይ ዛሬም ጣና ቂርቆስ 4 ሺህ 518 ዓ.ዓ ጀምሮ መሰዋዕተ ኦሪት ይቀርብበት የነበረ፣አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ከአናቱ ላይ እንደ ሙቀጫ የተቦረቦረው ድንጋይና የኦሪት የብረት መስዋዕት ማቃጠያ በሥፍራው ይገኛሉ።
ከታቦተ ጽዮን ጋር የመጣው ሊቀ ካህናቱ አዛርያስ ጣና ቂርቆስ ገዳም ላይ ነው የተቀበረው።
ከ3000 ዓመት በፊት የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ የኾነችው ታቦተ ጽዮን ባረፈችበት ጣና ቂርቆስ ገዳም በአንደኛው መክዘ ሄሮድስ ጌታን ሊገድል በፈለገ ጊዜ
ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር 3 ወር ከ10 ቀናት የተቀመጠችበት ቦታ በዚሁ ሃይቅ ነዉ ።
ስለዚህ የተለያዩ የአለም ሀያላን ሀገራት ምስጥሩን ለማወቅ ብዙ የደከሙለት ግን መርምረው ያልደረሰበት
ጀምስ ብሩስ ፖርቱጋላዊው ሚሲዮናዊ ማኖኤሊ ደ አልሜዳ ጨምሮ በርካታ አሳሾች ሊያዉቁት ሊፈትሹት ባህር አቆራርጠዉ የተመሙለት ቅዱስ ሃይቅና ከክርስቶስ ልደት በፊትና በኋላ ያለዉ ታሩኩ ቢፃፍ ድርሳኑን ገልፀን አንጨርሰዉምና ለዛሬው በሀይቁ የሚገኙ ደሴቶችና ገዳማትን ዝርዝር ተመልክተን ፅሁፉን እናጠናቅ።
የጣና ሀይቅ ደሴቶች
ደቅ ደሴት -ከባህርዳር ከተማ በ 37 ኪሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡በውስጡ 7 አድባራት ስላሉ የሰባት ደብር አገር ይባላል፡፡
ዳጋ እስጢፋኖስ፣ናርጋ ስላሴ፣ቅድስት አርሴማ፣ኮታ ማርያም፣ዝባድ ኢየሱስ፣ጆጋ ዮሀንስ እና ጋደና ጊዮርጊስ በደሴቱ ውስጥ የሚገኙ ገዳማት ናቸው፡፡
ክብራን ገብርኤል እና እንጦስ ደሴቶች ከባህርዳር በጀልባ 45 ደቂቃ ያስጉዛሉ፡፡
ክብራን ገብርኤል በአፄ አምደፅዮን ዘመን ገዳም ተመስርቶበታል፡፡
በአረንጓዴ ተፈጥሮ የተከበቡት ክብራን የወንዶች ሲሆን፣እንጦስ ደግሞ የሴቶች ገዳም ናቸው፡፡
ዘጌ ባህረገብ ደሴት ከባህርዳር 15 ኪሜ ርቆ ይገኛል፡፡ሰባት አብያተ ክርስቲያናት በውስጡ አሉ፡፡
መሃል ዘጌ ጊዮርጊስ፣ኡራ ኪዳነ ምህረት፣አቡነ በትረ ማርያም፣አዝዋ ማርያም፣ደብረ ስላሴ. . . ወዘተ በዘጌ ባህረገብ ደሴት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ደብረማርያም ደሴት ከባህርዳር በእግር የአንድ ሰዓት በጀልባ ደግሞ 20 ደቂቃ የሚወስድ ሲሆን ከከተማው በሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ ይገኛል፡፡
ደብረማርያም ገዳም የተመሠረተችው እዚህ ደሴት ላይ ነው፡፡ገዳሟ በአፄ አምደ ፅዮን ዘመነ መንግስት ከ (1307-1337) መመስረቷ ተነግሯል ፡፡
ደብረማርያም ደሴት አባይ እና ጣና የሚተላለፉበት በር በመሆኑም “የአባይ ራስ ” ይባላል
< አባይ በጣና ላይ እንዴት ቀለደበት
ለአንድ ቀን ነው ብሎ ዘላለም ሄደበት >
የሚለው ቃላዊ ግጥም አባይና ጣና ደብረማርያም ላይ ለሚያሳዩት ትርኢት የተገጠመ ይመስላል፡፡
በደብረማርያም አካባቢ ጣና ብዙ ጉማሬዎችን ስለያዘ ጉማሬ ባህርም ይባላል፡፡
በአጠቃላይ በጣና ሀይቅ ከ 7 መቶ ዓመት በላይ የሆናቸው 37 የሚደርሱ ገዳማት አሉ፡፡
ጣና በውሀነቱ የኢትዮጵያን ጨው አልባ ውሃ 50 በመቶ እንደሚሸፍን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡28 የዓሳ ዝርያዎች ያሉት ሲሆን 21ዱ በጣና ብቻ ይገኛሉ፡፡
የጣና ገዳማት የመካከለኛው ዘመን የሸዋና የጎንደር ነገስታት መካነ መቃብር መገኛም ናቸው፡፡የአፄ ዳዊት ፣የአጼ ፋሲለደስ. . . ወዘተ አጽም መገኛም በነዚሁ በጣና ደሴቶች ላይ ነው ፡፡
ኦሪታዊው የጣና ቂርቆስ ቤተክርስቲያን እስከ አሻራዎቹ ከጣና ሀይቅ ገዳማት በአንዱ ይገኛል፡፡
ምንጭ፦ ታዴ የማመይ ልጅ ገጽ
