August 1, 2023

በሃሚድ አወል

የደቡብ ክልል ምክር ቤት ከመጪው አርብ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በሚያደርገው መደበኛ ጉባኤ፤ በህዝበ ውሳኔ ለተመሰረተው 12ኛው አዲስ ክልል ስልጣን እንደሚያስረክብ የምክር ቤቱ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ አልማዝ ዘውዱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ከስልጣን ርክክቡ በኋላ የመዋቅር፣ የህገ መንግስት እና የስያሜ ለውጦችን እንደሚያደርግ የሚጠበቀው የነባሩ የደቡብ ክልል የወደፊት አደረጃጀት ሁኔታ በዚህ ጉባኤ ላይ እንደማይነሳ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል። 

አዲሱ የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልል የኢፌዴሪ 12ኛ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ የወሰነው፤ ከአንድ ወር በፊት ሰኔ መጨረሻ ላይ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ ላይ ነበር። ይህ ውሳኔ በተላለፈበት ወቅት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር “ነባሩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል አዲስ ለተመሰረተው ክልል በአፋጣኝ የስልጣን ርክክብ እንዲያደርግ አቅጣጫ ተቀምጧል” ማለታቸው ይታወሳል።

Tweet

Ethiopia Insider

@ethiopiainsider

የፌዴሬሽን ምክር ቤት “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” የኢፌዲሪ 12ኛ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ በሙሉ ድምጽ

ወሰነ። በነባሩ ክልል የቀሩ መዋቅሮች፤ ራሳቸውን መልሰው በማደራጀት ባሉበት እንዲቀጥሉም ውሳኔ

ተላልፏል። #Ethiopia

ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2023/11371/

Translate Tweet

Image

· 5,830 Views

10 Retweets 2 Quotes 32 Likes

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ይህን ቢሉም የደቡብ ክልል የስልጣን ርክክቡን ለማድረግ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉባኤ በኋላ አንድ ወር ፈጅቶበታል። በኢትዮጵያ ካሉ ክልሎች የዚህን ዓመት ማጠቃለያ መደበኛ ጉባኤ ለማካሄድ የመጨረሻ የሆነው የደቡብ ክልል፤ እስከ መጪው እሁድ ሐምሌ 30 በሚቆየው ስብሰባው ከስልጣን ርክክብ በተጨማሪ የክልሉን አስፈጻሚ አካላት የ2015 ሪፖርት ይገመግማል ተብሏል። የክልሉ ፍርድ ቤቶች እና የኦዲተር መስሪያ ቤት ሪፖርትም በምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ እንደሚቀርብ ተገልጿል።

በዚህ ሳምንት መጨረሻ ከነባሩ የደቡብ ክልል በይፋ የሚለያዩት ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች፤ የራሳቸውን የጋራ ክልል ለመመስረት የሚያስችላቸውን ህዝበ ውሳኔ ያካሄዱት ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ እና ሰኔ 12፤ 2015 ነበር። አዲሱን ክልል የመሰረቱት የጌዲኦ፣ የወላይታ፣ የጋሞ፣ ጎፋ፣ የኮንሶ፣ የደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶ እና የአሌ ልዩ ወረዳዎች ናቸው። 

https://youtube.com/watch?v=Z1biIVcAru0%3Ffeature%3Doembed%26enablejsapi%3D1

አዲሱ የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልል ከነባሩ ደቡብ ክልል በህዝበ ውሳኔ ተነጥሎ ፌደሬሽኑን በመቀላቀል ሶስተኛው ነው። ከደቡብ ክልል በመለየት የራሱን ክልል በመመስረት የመጀመሪያ የሆነው የቀድሞው ሲዳማ ዞን ነው። የሲዳማ ዞን ከሶስት ዓመታት በፊት በ2012 መጨረሻ ላይ ከደቡብ ክልል ስልጣን መረከቡ ይታወሳል። ከሲዳማ ክልል በመቀጠል አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ በጋራ የመሰረቱት “የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል”፤ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ከነባሩ የደቡብ ክልል በተመሳሳይ ስልጣን ተረክቧል።

በሳምንቱ መጨረሻ የሚደረገው የስልጣን ርክክብ “የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል” ተብሎ በሚጠራው ክልል ላይ መሰረታዊ ለውጥ ያስከትላል። ነባሩ የደቡብ ክልል ለሶስተኛ ጊዜ የሚደረገውን የአደረጃጀት ለውጥ ተከትሎ፤ የመዋቅር፣ የህገ መንግስት እና የስያሜ ለውጦችን እንደሚያደርግ ከዚህ ቀደም መገለጹ አይዘነጋም። ነባሩ ክልልን የተመለከቱ መሰረታዊ ለውጦች የሚደረጉት፤ “አሁን የስልጣን ርክክብ ተደርጎ ቀጣይ በሚኖሩ ሂደቶች” መሆኑን የደቡብ ክልል ምክር ቤት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ አልማዝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። (

ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)