August 2, 2023

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች ጋር በሴንት ፒተርስበርግ ጉባዔ ውይይት ባደረጉበት ወቅት

ፖለቲካ

ዮናስ አማረ

August 2, 2023

JANUARY 1, 2023አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉFEBRUARY 5, 2023

እ.ኤ.አ. በ1987 የተጻፈው ‹‹አፍሪካና አምባገነን መሪዎቿ›› በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ በተተረጎመው የአሜሪካዊው ጋዜጠኛ ዴቪድ ላምብ “The Africans” መጽሐፍ፣ ስለአፍሪካ የባከነ እምቅ አቅም ጠቃሚ ቁም ነገሮችን ያስነብባል፡፡

‹‹የአፍሪካን ታይቶ የማያልቅ ለጥ ያለ ባዶ መሬት ያየ ሁሉ እዚህ ለም መሬት ላይ በአሥር ሺሕ የሚቆጠሩ የአሜሪካ አርሶ አደሮችን በማስፈር ብቻ መላው አፍሪካን የዳቦ ቅርጫት ማድረግ እንደሚቻል ቀድሞ በሐሳቡ ይመጣበታል፤›› በማለት ነበር ዴቪድ ላምብ የከተበው፡፡ ከዓለማችን የሚታረስ መሬት  61 በመቶውን የያዘችው አፍሪካ የሚበላ አጥታ በችጋር ለምን እንደምትቀጣ ጸሐፊው በአስደናቂ አተራረክ አስቀምጦታል፡፡

አፍሪካ በተለያዩ አጋጣሚዎች በተለያዩ ጸሐፍት ከችግርና ከችጋር እንድትወጣ ብዙ ምክረ ሐሳቦችና ውትወታዎች ቀርበውላታል፡፡ ይሁን እንጂ አኅጉሪቱ በዳቦ ዛሬም ድረስ ራሷን መቻል አቅቷት የሌሎችን እጅ ጠባቂ ስትሆን ትታያለች፡፡

ከሰሞኑ በአፍሪካ-ሩሲያ የምክክር መድረክ ላይ የአፍሪካ የስንዴ ዋስትና ጉዳይ የገዘፈ ቦታ ይዞ ነበር፡፡ ሩሲያ በነፃ ለአፍሪካ አገሮች ስንዴ አቀርባለሁ ማለቷ ትልቅ ከበሬታና አድናቆት ያስገኘላት ጉዳይ ነበር፡፡

አፍሪካ በምግብ ራሷን መቀለብ አለመቻሏ ሁሌም አኅጉሪቱን ተጋላጭ ሲያደርጋት ቆይቷል፡፡ አኅጉሪቱ የሩሲያና ዩክሬን ግጭት ሰለባ የሆነችው በስንዴ አቅርቦት የሁለቱ አገሮች ጥገኛ በመሆኗ እንደሆነ ይነገራል፡፡

የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት የአፍሪካዊያንን የምግብ ዋስትና ከባድ አደጋ ላይ እንደጣለው ይነገራል፡፡ ሁለቱ አገሮች የስንዴ አቅርቦት መቋረጥን ጉዳይ አንዱ ለሌላው በመስጠት አፍሪካን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ሲጣጣሩ ቆይተዋል፡፡ ምዕራባዊያኑ ይህን ተገን በማድረግ ዩክሬን በሩሲያ በመወረሯ አፍሪካዊያን የሚገዙት ስንዴ አጡ የሚለውን ጉዳይ ከፍ አድርገው ሲያጮኹት ሰንብተዋል፡፡ ዩክሬን የዓለም ስንዴ አቅርቦትን ከዘጠኝ በመቶ በላይ እንደማትሸፍን እየታወቀ፣ ሩሲያ ዩክሬንን በመውረሯ አፍሪካዊያን በስንዴ አቅርቦት ተቸገሩ ብለው ምዕራባዊያኑ የሄዱበት ርቀት አስገራሚ ነበር፡፡

በስተመጨረሻ ግን የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን እንዳስታወቁት አገራቸው ለተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በነፃ የተፈለገው ቦታ ድረስ እህል እንደምታቀርብ አረጋግጠዋል፡፡ ለብሩንዲ፣ ለማሊ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ለሶማሊያና ለኤርትራ በሦስት/በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ከ25 እስከ 50 ሺሕ ቶን ስንዴ ሩሲያ እንደምታቀርብ ማረጋገጫ በመስጠት ችግሯን አርግበውታል፡፡

የጥቁር ባህር ስንዴ ጉዳይ ለረዥም ጊዜ አፍሪካዊያንን ወደ ዩክሬን ወይም ሩሲያ ለመጎተት መጠቀሚያ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከሰሞኑ የአፍሪካ-ሩሲያ ጉባዔ ላይ ፕሬዚዳንት ፑቲን ቁርጥ ያለ ምላሽ የሰጡበት ቢመስልም፣ ጉዳዩ መልኩን ቀይሮ ላለመከሰቱ ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡

የአፍሪካ ተጋላጭነት የሚመነጨው ግን ከምግብ ዋስትና ጥያቄ ጋር በተያያዘ ብቻ አለመሆኑ ይነገራል፡፡ አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ውክልና አኅጉሪቱን ተጋላጭ አድርጓት ቆይቷል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ የቋሚ መቀመጫ አልባ መሆኗ ሲጎዳት ኖሯል፡፡ የዓለም አቀፍ ንግድ ፍትሕ ጥያቄ፣ በእስራኤል-ፍልስጤም ግጭት አፍሪካ ያላት አቋም፣ ውድ የማዕድናት ሀብቶቿ ተፈላጊነት፣ ድህነትና ዕርዳታ ተቀባይነት፣ እንዲሁም የዓለም ኃያላን አገሮች የእርስ ብርስ ሽኩቻና ፍጥጫ ሁሉ አፍሪካ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ጉዳዮች ናቸው፡፡

በሰሞነኛው የሴንት ፒተርስበርግ ከተማ የአፍሪካ-ሩሲያ ስብሰባ ላይ፣ እነዚህ አፍሪካን ለዓለም አቀፍ ጫና የዳረጉ ጉዳዮች በተለያዩ መሪዎች በስፋት ተነስተዋል፡፡

የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተለየ ሁኔታ ያነሱት የምዕራባዊያኑን የዓለም ፍፁማዊ የበላይነት ፍላጎት ያሳደረውን ዓለም አቀፍ ጫና ነበር፡፡ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በበኩላቸው፣ ፍትሕ በጎደለው ዓለም አቀፍ የቡና ግብይት አፍሪካ እየደረሰባት ያለውን ጫና በሰፊው አንስተዋል፡፡ የቡርኪናፋሶ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ትራኦሬ፣ የምዕራባዊያኑን ቅኝ ገዥነት አመለካከት አለመላቀቅ እንደ ትልቅ ችግር አውስተዋል፡፡

የመጀመሪያው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ እ.ኤ.አ. በ2019 ሲካሄድ 43 የአፍሪካ መሪዎች በሶቺ ከተማ ተገኝተው ነበር፡፡ ዘንድሮ ለሁለተኛው ጉባዔ ግን 49 መሪዎች ተጋብዘው የነበረ ቢሆንም፣ በሴንት ፒተርስበርግ ተገኝተው ጉባዔውን የተካፈሉት ግን 17 መሪዎች መሆናቸው ተነግሯል፡፡ ሩሲያ ስንዴ በነፃ እሰፍርላችኋለሁ ብላ የአፍሪካን ወቅታዊ  የምግብ ዋስትና ችግር ለመፍታት ትልቅ ተነሳሽነት አሳይታለች፡፡

ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር ያላት የንግድ ልውውጥ ከ18 ቢሊዮን ዶላር እንደማይበልጥ የሚናገሩ አንዳንድ ወገኖች፣ ሩሲያ ለአፍሪካ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም ሆነ የሰብዓዊና የልማት ዕርዳታ ምንጭ ሆና እንደማታውቅ በሰፊው ዘርዝረዋል፡፡ ጉባዔው ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ይልቅ ሩሲያ በተቻለ መጠን የአፍሪካዊያንን ድጋፍ ለማሰባሰብ የምታደርገው መጣጣር ስለመሆኑ፣ በርካታ የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ዘዴዎች በመዘገብ ላይ ይገኛሉ፡፡

አንዳንዶች የአፍሪካ የሩሲያ ጉባዔ ድግስ ሩሲያ የአፍሪካ አገሮችን በተፅዕኖ ክበቧ ውስጥ ለማስገባት አለፍ ሲልም ቅኝ መግዣ መንገድ ስለመሆኑ በሰፊው እየተናገሩ ይገኛል፡፡ የሩሲያ ባለሥልጣናት ግን ይህን አስተባብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ‹‹ሩሲያ አፍሪካዊያን ከቅኝ ተገዥነት ራሳቸውን ለማላቀቅ ባደረጉት ትግል አጋራቸው ነበረች፤›› ብለዋል፡፡

ሩሲያ ለአፍሪካዊያን በክፉ ቀን የምትደርስ ወዳጅ እንጂ ጠላት ሆና እንደማታውቅ ፕሬዚዳንት ፑቲን ተከራክረዋል፡፡ ‹‹ባለሙያዎችን በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በመላክ ድህነት ጠፍቶ ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲረጋገጥ አግዛለች፡፡ የሩሲያ ባለሙያዎች የኢንዱስትሪ፣ የግብርናና የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ገንብተዋል፤›› በማለት ነበር ፕሬዚዳንት ፑቲን የተናገሩት፡፡ ፑቲን አገራቸው ከአፍሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ‹‹በእኩልነት፣ በወዳጅነትና በመከባበር ላይ የተመሠረተ›› መሆኑን ነው አጠንክረው የገለጹት፡፡

ምዕራባዊያኑ ሩሲያ የአፍሪካን ድጋፍ በስንዴ ፖለቲካ ለማግኘት እየጣረች ነው እንደሚሉት ሁሉ፣ ሩሲያም ምዕራባዊያኑ አፍሪካን በዕርዳታና ብድር ቅኝ ተገዥያቸው አድርገው ለመቀጠል ይፈልጋሉ የሚል ክስ በተደጋጋሚ ታሰማለች፡፡

በሌላ በኩል ቻይና በዕዳ ጫና አፍሪካን ለመያዝ ትሞክራለች እየተባለች ትወቀሳለች፡፡ አፍሪካ ከምዕራባዊያኑ፣ ከሩሲያ ወይም ከቻይና ጋር ባላት ግንኙነት ብቻ ሳይሆን የገልፍ አገሮች፣ ኢራን፣ ቱርክ፣ ብራዚል፣ ጃፓንና ሌሎችም የየራሳቸውን ፍላጎት ጭነው ወደ አፍሪካ ስለሚመጡ አኅጉሪቱ በውጭ ኃይሎች ጫናና ጣልቃ ገብነት እየተፈተነች ስለመሆኑ ይነገራል፡፡

የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ከጥቂት ወራት በፊት ደቡብ አፍሪካ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹የአፍሪካ መሪዎች የማንጠራበት የትብብር ፎረምና ጉባዔ ዓይነት የለም›› ሲሉ እንደተናገሩት ሁሉ፣ በርካታ የዓለም ኃያላን አኅጉሩን ወደ ራሳቸው ለመውሰድ በራሳቸው መንገድ መጣጣራቸው ጎልቶ እየታየ ነው፡፡ ዊልያም ሩቶ የአፍሪካ መሪዎች በየተጠሩበት መድረክ ተሰብስበው ከመገኘትና ፎቶ ከመነሳት በዘለለ፣ የአኅጉሩን ተጨባጭ ችግሮች አድምጦ መፍትሔ የሚሰጥ ወገን አለመኖሩ በጉልህ ይነሳል፡፡

የሰሞኑ የአፍሪካ ሩሲያ መድረክም ከዚህ የተለየ እንደማይሆን የገመቱ በርካታ ናቸው፡፡ የአፍሪካ-አሜሪካ፣ የአፍሪካ-ቻይና፣ የአፍሪካ-ህንድ፣ የአፍሪካ-ብራዚል፣ ወዘተ እንደሚሏቸው የምክክር መድረኮች ሁሉ የአፍሪካ ሩሲያ ጉባዔም ከመርሐ ግብርነት የዘለለ እንደማይሆን በርካቶች ሲናገሩ ሰንብተዋል፡፡

ያም ቢሆን ግን አፍሪካዊያን መሪዎች የአፍሪካን ችግሮች በተመለከተ በመድረኩ በጉልህ አንስተዋል፡፡ እነዚህን የአፍሪካ ችግሮች ኃያላኑ አድምጠው መልስ ይሰጣሉ ተብሎ ባይጠበቅ እንኳን፣ በመድረኩ የተስተጋባው የአፍሪካ መሪዎች መልዕክት ትኩረት ሊነፈገው የማይችል እንደሆነ ነው የተገመተው፡፡

የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ አፍሪካ በኢፍትሐዊ የዓለም ንግድ በአስከፊ ሁኔታ ስለመጎዳቷ ዘርዝረዋል፡፡

‹‹የአፍሪካ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) 2.7 ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን ይህም ከጀርመን፣ ከጃፓን፣ ከአሜሪካም ሆነ ከቻይና ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) ያነሰ ነው፡፡ ቡና በዓለማችን የ460 ቢሊዮን ዶላር ኢኮኖሚ ነው፡፡ እንደ ኡጋንዳ ያሉ የዓለም ቡና ላኪ አገሮች ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 25 ቢሊዮን ብቻ ነው የሚደርሳቸው፡፡ የአፍሪካ ቡና ላኪ አገሮች ድርሻ ደግሞ እጅግ ያነሰና ከ2.4 ቢሊዮን ዶላር ያልተሻገረ ነው፡፡ ኡጋንዳ ከዚህ ውስጥ 800 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው የምታገኘው፡፡ ጀርመን አንድም ፍሬ ቡና ሳትልክ 6.85 ቢሊዮን ዶላር ለብቻዋ የምታገኝ ሲሆን፣ ይህም የመላው አፍሪካ ቡና ላኪዎችን ድርሻ ይበልጣል፡፡ ይህ ዘመናዊ ባርነት ነው፡፡ ጥሬ ቡና በዓለም ገበያ 2.5 ዶላር በኪሎ ይሸጣል፡፡ የተቆላ ቡና ግን በኪሎ 40 ዶላር ነው የሚሸጠው፡፡ ኃያላን አገሮች አፍሪካን አጋራችን የምትሉ ከሆነ የተቀነባበረና እሴት የተጨመረበት ቡና ከእኛ ግዙን፤›› በማለት ነበር ኃያላን አገሮች ለአፍሪካ አጋርነታቸውን በንግድ ፍትሕ እንዲያረጋግጡ የነገሯቸው፡፡

የቡርኪናፋሶው የ35 ዓመት ወጣት ፕሬዚዳንት የጦር መኰንኑ ኢብራሂም ትራኦሬም ዓለም ሊያደምጠው የሚገባ የአፍሪካን የዘመናት ቁስል የጠቀሰ ንግግር ነበር በሴንት ፒተርስበርግ  ጉባዔ ያደረጉት፡፡

‹‹የእኔ ትውልድ የሆነው አፍሪካዊ አኅጉሪቱ ይህን ሁሉ ሀብት ታቅፋ እንዴት እንደደኸየች ሁሌም ይጠይቃል፡፡ አፍሪካ ዓመቱን ሁሉ ፀሐይ፣ ውኃ፣ ለም መሬትና የተትረፈረፈ ተፈጥሮ እያላት ደሃዋ አኅጉር እንዴት እንደሆነች እንቆቅልሽ ነው፡፡ አፍሪካ ረሃብተኛ አኅጉር ነች፡፡ መሪዎቻችን ለልመና ዓለምን ይዞራሉ፡፡ ይህ ለምን ሆነ የሚለውን እኛ ብንጠይቅም እስካሁን ግን አጥጋቢ ምላሽ አላገኘንም፡፡ ከዓለም ኃያላን ጋር አዲስ ዓይነት ግንኙነት እንዲፈጠር እንፈልጋለን፡፡ ይህ ግንኙነት ደግሞ ለአገሬ ቡርኪናፋሶም ሆነ ለአፍሪካ መፃዒ ተስፋ በጎ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ላለፉት ስምንት ዓመታት ኢምፔሪያሊዝምና ኒዮኮሎኒያሊዝም በፈጠረው ጨካኝ ጦርነት ስንማቅቅ ቆይተናል፡፡ ዛሬም ድረስ ባርነት ሊጫንብን ጥረት ይደረጋል፤›› በማለት የተናገሩት ፕሬዚዳንት ኢብራሂም፣ የአፍሪካ አገሮች ከኃያላን አገሮች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት መቀየር እንደሚያስፈልገው ጠቃሚ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ለወትሮም ከምዕራባዊያኑ ጋር ዓይንና ናጫ ሆነው የኖሩት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ‹‹የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም›› በሚል ይመስላል ከምዕራባዊያኑ ጋር ለሚካሄደው የጂኦ ፖለቲካ ጦርነት አፍሪካዊያንና ሩሲያ እንዲዘጋጁ ጥሪ ሲያቀርቡ ተደምጠዋል፡፡ ምዕራባዊያኑ የፈጠሩት እንደሆነ ስለሩሲያ ዩክሬን ጦርነት የተናገሩት አቶ ኢሳያስ፣ ‹‹ኔቶ በሩሲያ ላይ ያወጀው ጦርነት›› በማለት ጠርተውታል፡፡

ሩሲያ ከምዕራባዊያኑ ጋር የሚደረገውን የጂኦፖለቲካ ጦርነት የመምራት ታሪካዊ አደራ እንዳለባት የጠቀሱት ኢሳያስ፣ የምዕራባዊያኑን ዓለምን የማስገበርና የመጠቅለል ሩጫ ለመመከት የሚያስችል ስትራቴጂ እንዲዘጋጅና አፍሪካዊያን ከሩሲያና ቻይና ጋር በጋራ እንዲቆሙ ጭምር ጥሪ እስከ ማቅረብ ደርሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጨምሮ በሩሲያ አፍሪካ ስብሰባ ላይ የተካፈሉ የአፍሪካ መሪዎች ከሩሲያ ለየአገሮቻቸወ ሊያገኙ ስለሚችሉት የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲና የንግድ ጥቅም አስልተው በሴንት በፒተርስበርጉ ስብሰባ እንደተገኙ ይገመታል፡፡ መሪዎቹ ወደ ሩሲያ በመቅረባቸው ከአንድ ወገን ሊያገኙት የሚችሉት ጥቅም ከሌለ እንዳለ ሁሉ ወገን ሊያጡት የሚችሉት ጥቅም መኖሩም ይገመታል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፍትጊያው፣ ፉክክሩና ውጥረቱ እየጨመረ በመጣበት የዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የአፍሪካ አገሮች የሚጠብቃቸው ፈተና ከእስካሁኑ እንደሚብስ ነው የሚጠበቀው፡፡