
5 ነሐሴ 2023
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በመከላከያ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ሲደረጉ የነበሩ ግጭቶች ተባብሰው መቀጠላቸውን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል።
አርብ ሐምሌ 28/ 2015 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ሕግ እና ሥርዓት ለማስከበር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በክልሉ በትጥቅ የተደገፈ ሕገወጥ እንቅስቃሴ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር ወደማይቻልበት ደረጃ የተሸጋገረ በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ ማወጅ አስፈላጊ መሆኑም ነው የተገለጸው።
በክልሉ የታዩት ግጭቶች የክልሉን ነዋሪ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ ያወኩ እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣሉ እንደሆኑ አዋጁ በመግቢያው ላይ አትቷል።
የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማዋቀር ከተያዘው ዕቅድ ጋር ተያይዞ የተነሳው ግጭት ከሰሞኑ ተባብሶ በክልሉ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል፣ ትራንስፖርት ተስተጓጉሏል እንዲሁም እንቅስቃሴዎች ተገድበዋል።
ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ በርካታ የክልሉ አካባቢዎች በግጭት ላይ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የጠቀሰ ሲሆን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በሲቪል ነዋሪዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን እና የሰላማዊ ሰዎች እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱንም አመልክቷል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅትም ሰብዓዊ መብቶች መከበር ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ኢሰመኮ አስታውሷል።
“የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” ተብሎ አርብ ዕለት የወጣው ድንጋጌ ዝርዝር አምስት ገጾችን ይዟል።
- የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደነገገ4 ነሐሴ 2023
- መንግሥት በአማራ ክልል በሚወስዳቸው እርምጃዎች ለነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲደረግ ኢሰመኮ ጠየቀ5 ነሐሴ 2023
ለመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምን አካቷል?
አዋጁ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስተዳደር እንዲሁም በክልሉ አስተዳደር የሕዝብን ሰላም እና ፀጥታ ለማስከበር እንደወጣ ያትታል።
ሆኖም በክልሉ ወይም በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የፀጥታ ችግር የሚያባብስ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ወይም ሁኔታን በሚመለከት እንደ አስፈላጊነቱ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ ተፈጸሚነት እንደሚኖረውም አካቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽም በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል የሚመራ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ተቋቁሟል።
የጠቅላይ መምሪያ ዕዙ አባላት፣ መዋቅር እና አደረጃጀት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚወሰን ሲሆን፣ ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን ተጠቅሷል።
በአስቸኳይ አዋጁ የተከለከሉ ተግባራት እና ግዴታዎች
- ማንኛውም ሰው ይህንን አዋጅ፣ አዋጁን መሠረት አድርገው የሚወጡ መመሪያዎችንም ሆነ ትዕዛዞች ማክበር እና መተግበር ግዴታ እንዳለበት ተቀምጧል።
- የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙን እንቅስቃሴ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አላማ የሚቃረን፣ የሚቃወም እና በክልሉ የአመጽ እንቅስቃሴን የሚያበረታታ፣ ሰላማዊ ዜጎችን የሚያሸብር፣ እንዲሁም የፀጥታ መደፍረሱን የሚያባብስ ንግግር፣ የቀጥታም ሆነ የተዘዋዋሪ ቅስቀሳ በማንኛውም መንገድ ማድረግ ወይም ማሰራጨትን ከልክሏል።
- በየትኛውም መንገድ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለታጣቂ ቡድኖች የገንዝብ፣ የመረጃ፣ የቁስም ሆነ የሞራል ድጋፍ ማድረግም የተከለከለ ነው።
- ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ፈቃድ ውጪ ማንኛውንም የአደባባይ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግንም አይፈቅድም።
- ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ፈቃድ ውጭ ማናቸውንም የጦር መሳርያ ይዞ መንቀሳቀስ ተከልክሏል።
- ማንኛውንም ወሳኝ በሆነ የአገልግሎት ዘርፍም ሆነ በምርት ሂደት ላይ የሥራ ማስተጓጎል ወይም የኢኮኖሚ አሻጥር መፈፀም የተከለከለ ስለመሆኑም አስፍሯል።
- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም ሰበብ በማድረግ የግል ጥቅም ለማግኘት ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም፣ ምክንያታዊ የሆነ ጥርጣሬ ሳይኖር ሆን ብሎ ዜጎችን ማሰር ወይም መሰል እርምጃ መውሰድ በጥብቅ የተከለከለ ነው።
በአስቸኳይ ጊዜ የሚወሰዱ እርምጃዎች
የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ይህን አዋጅ ለማሳካት አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን የሚያከናውናቸው እርምጃዎች ተዘርዝረዋል።
- የአደባባይ ስብሰባ እና ሰልፍ ማድረግ፣ መደራጀት፣ በቡድን ሆኖ መንቀሳቀስን መከልከል፣
- የሰዓት እላፊ የማወጅ፣ ለተወሰነ ጊዜ አንድ መንገድ፣ አገልግሎት መስጫ ተቋም መጓጓዣ ዘዴ እንዲዘጋ እና እንዲቋረጥ ማድረግ፣
- ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ፣ ወደ ተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዲለቁ ማዘዝ፣
- የጦር መሳሪያ፣ ስለት ወይም አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉ ነገሮችን ይዞ መንቀሳቀስን መከልከል፣
- በአገረ መንግሥቱ እና በሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱ ላይ የሚቃጡ ወንጀሎችን እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመጣስ እና አፈፃፀሙን የማደናቀፍ ወንጀልን በፈጸሙ፣ በሞከረ ወይም ለመፈፀም በዝግጅት ላይ መሆኑ የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር በማድረግ ለማቆየት፣
- ወንጀል እንደተፈፀመባቸውን ወይም ሊፈፀምባቸው እንደሚችል የተጠረጠሩ እቃዎችን ለመያዝ ሲባል ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በየትኛዉም ጊዜ ማንኛውንም ስፍራ እና መጓጓዣ መበርበር፣
- መንግሥታዊ እና ሕዝባዊ ተቋማት እና የመሠረተ ልማቶች የጥበቃ ሁኔታን ለመወሰን፣
- ማናቸውም ከዚህ አዋጅ አላማ በተፃረረ መልኩ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ የተጠረጠሩ የመገናኛ ብዙኃንም ሆነ ሌሎች አካላት እንዲዘጉ፣ እንዲቋረጡ፣ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ወይም እንቅስቃሴያቸው እንዲገደብ ማድረግ፣
- ማንኛዉንም አገልግሎት መስጫ ተቋም እንዳይዘጋ እና ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ ማዘዝ፣
- ማንኛውንም የሕዝብ ትራንስፖርት መስጫ ተሽከርካሪ እና ማጓጓዣ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ፣
- የተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች እና መዋቅሮችን መልሶ ማቋቋም፣ ማደራጀት ወይም የአስተዳደር እና የፀጥታ ጉዳዮችን በተመለከተ ውሳኔዎችን የማስተላለፍ እና ሌሎች እርምጃዎችን የመውሰድ፣
- የሕዝብን ሰላም፣ የአገር ደኅንነትን ለማስጠበቅ አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን የመውሰድ፣ ውሳኔዎችን የማስተላለፍ እና ትእዛዝ የመስጠት ሥልጣን አለው፡፡
ተመጣጣኝ ኃይል ስለመጠቀም እና የማይታገዱ መብቶች
- መምሪያ ዕዙ በዚህ አዋጅ የተመለከቱ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን ለማስፈጸም በሚያስፈልግበት ወቅት ሕግ አስከባሪ አካላት ተመጣጣኝ ኃይል እንዲጠቀሙ መመሪያ ለመስጠት እንደሚችልም ተቀምጧል።
- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ በሚያወጣቸው መመሪያዎች፣ በሚወስናቸው ውሳኔዎች እና በሚወስዳቸው እርምጃዎች በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሊታገዱ የማይችሉ የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎችን እና መብቶችን፣ እንዲሁም የተመጣጣኝነትን እና የአስፈላጊነት መርሆዎችን ማክበር አለበት።
የወንጀል ተጠያቂነት
በአማራ ክልል በታወጀው በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ወቅት የሚፈጸሙ የአዋጁ ጥሰቶች አስከ አስር ዓመታት የሚደርስ እስርን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ተደንግጓል።
- የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች እና በአዋጁ መሠረት የወጡ መመሪያዎችን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም እንደጥፋቱ ክብደት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል።
- የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች እና በአዋጁ መሠረት የወጡ መመሪያዎችን በመተላለፍ የተፈፀመ ወንጀል በሌሎች ሕጎች ከዚህ ከፍ ያለ ቅጣት የሚያስከትል ከሆነ የከበደው ቅጣት ተፈጻሚ ይሆናል።
- በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የተፈፀሙ የአዋጁ እና በአዋጁ ማዕቀፍ የሚወጡ የደንብ እና የመመሪያ ጥሰቶች የሚያስከትሉት የወንጀል ተጠያቂነትን በተመለከተ የአዋጁ ተፈጻሚነት ጊዜ ቢያበቃም በኢፌድሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 9(2) መሠረት የወንጀል ክስ ሊቀርብ ይችላል።
- የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች እና በአዋጁ መሠረት የወጡ መመሪያዎችን በመተላለፍ የሚመጣ የወንጀል ተጠያቂነትን አስመልክቶ ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረኑ መደበኛ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎችም ተፈፃሚነት አይኖራቸውም።
- የፀጥታ ሁኔታው የመደበኛ የዳኝነት እና የፍትህ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በማያስችልበት ሁኔታ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች ከዚህ አዋጅ ጥሰት ጋር ተያያዥ የሆኑ የወንጀል ጉዳዮችን አስመልክቶ የወታደራዊ ፍርድ ቤቶች እና የፍትህ አካላት መደበኛ የዳኝነት እና የፍትህ አካላትን ተክተው እንዲሰሩ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ሊወስን ይችላል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ለስድስት ወራት የሚጸና ሲሆን፣ የስድስት ወር ጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዋጁ ተፈፀሚነት ቀሪ የሚሆንበትን ጊዜ ሊወስን እንደሚችልም ተቀምጧል።