August 6, 2023 – EthiopianReporter.com 


የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያደረገው ውይይት

ዜና የምዕራብ ወለጋ ዞን የሰላም ሁኔታ እንዲስተካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ግፊት እንዲያደርጉ ተጠየቀ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: August 6, 2023

በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ወለጋ ዞን የሰላም ሁኔታ ‹‹ለሥራዬ አመቺ አልሆነልኝም›› ያለው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች መንግሥትና በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ኃይሎች ችግሩን እንዲፈታ ግፊት እንዲያደርጉ ጥያቄ አቀረበ፡፡

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከተውጣጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር አድርጓል፡፡

‹‹ለዚህች አገር ከመሣሪያ ይልቅ መፍትሔ የሚያመጣው ውይይት በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናችሁን ተወጡ፤›› ሲሉ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) አሳስበዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የወለጋ ዞኖች በታጣቂዎች ሥር በመሆናቸው ኮሚሽኑ ተንቀሳቅሶ መሥራት አለመቻሉ ተገልጿል፡፡

‹‹በምዕራብ ኦሮሚያ ያለው ሁኔታ አሁንም ተንጠልጥሎ የቀረ በመሆኑ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በተቻለ መጠን መንግሥትና ታጣቂዎች ላይ ግፊት እንድታደርጉ ጥያቄ እናቀርባለን፤›› ሲሉ መስፍን (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡

‹‹የምክክር ኮሚሽኑ ለምን በፍጥነት ሰላም አያመጣም እየተባለ ይነሳል፣ ነገር ግን የኮሚሽኑ ኃላፊነቶች የተወሰኑ ናቸው፤›› ያሉት መስፍን (ፕሮፌሰር)፣ ኮሚሽኑ ዕርቀ ሰላም ማከናወን ሳይሆን ኃላፊነቱ የምክክር ሒደቱን የተመቻቸ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

‹የአገራችን ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት ከመሻሻል ይልቅ የመባባስ ሁኔታ ይታይበታል፡፡ በተለይ የትጥቅ እንቅስቃሴ በየቦታው እየታየ በመሆኑ፣ ችግሩን በውይይት ለመፍታት ሁሉም ታጣቂ ኃይል ትጥቁን ፈትቶ ወደ ጠረጴዛ ውይይት እንዲመጣ ማድረግ ያስፈልጋል፤›› ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የምክክር ኮሚሽኑ እያከናወነ ባለው የተሳታፊዎች ልየታና ምልመላ ሥራ በተለይም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በድሬዳዋና በሐረር ክልሎች የተሳታፊዎች ልየታና ውይይት መከናወኑን ዋና ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

ተሳታፊዎችን የመለየትና የውይይት ሒደት በአማካይ በ1,300 ወረዳዎች በአጠቃላይ ከ600 ሺሕ በላይ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡ ኮሚሽኑ በጀመረው ሒደት የተሳታፊዎች ቁጥር መብዛትና የምግብ አቅርቦት አለመመጣጠን እንደ ማነቆ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ተባባሪ አካላት ኃላፊነታቸውን በበቂ ሁኔታ አለመረዳት፣ በቂ የሎጂስቲክስ አቅርቦት አለመኖር፣ በተለይም ከረዥም ርቀት ለሚመጡ ተሳታፊዎች የውሎ አበል ገንዘብ እጥረት የተጠቀሱ ችግሮች ናቸው፡፡

በተሳታፊዎች ምርጫ ወቅት ብዙ ጊዜ ወደ አንድ ያዘመሙ ግለሰቦች በተለይም ወደ ብልፅግና ፓርቲ ያደሉ ዓይነት ሰዎች መሆን፣ የአዳረሽ መጥበብ፣ ያልተደራጁ መዋቅሮችና የመሳሰሉ ተግዳሮቶችም በኮሚሽኑ የተጠቀሱ ናቸው፡፡

በውይይቱ ከተገኙት ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራር አባል መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር)፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል አካባቢ ከተለዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተመረጡ 400 አወያይ ግለሰቦች መካከል 446 ያህሉ የብልፅግና ፓርቲ አባላት መሆናቸው ታውቋል ብለዋል፡፡ ‹‹ይህ ለምን ተብሎ ጥያቄ ሲቀርብ ከክልል የመጣ ትዕዛዝ ስለመሆኑ ተነግሮናል፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡