
August 6, 2023 – EthiopianReporter.com

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ባወጀበት ወቅት
ዜና ለአማራ ክልል በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ…
ቀን: August 6, 2023
ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ለአማራ ክልል በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በ15 ቀናት ጊዜ ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የሕዝብ ተወካዮች በሚሰጡት ድምፅ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኛል ተባለ
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅ በሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን እንዳለው የገለጹ አንድ የሕግ ባለሙያ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ዓርብ በአማራ ክልል ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀውም የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ አንድ መሠረት አድርጎ መሆኑን እንዳሳወቀ አስረድተዋል።
ክልሎችም ተመሳሳይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በክልላቸው የአስተዳደር ወሰን ውስጥ ማወጅ እንደሚችሉ የተናገሩት ባለሙያው፣ ክልሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ የሚችሉት የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል የበሽታ ወረርሽኝ ሲከሰት ነው፡፡ ለፌዴራል መንግሥት የተሰጠው ሥልጣን በባህሪው እንደሚለይና አዋጁን የሚያወጣበት ዓላማም ጠበብ ተደርጎ የተወሰነ መሆኑን አስረድተዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ያጋጠመው የፀጥታ መደፍረስ በክልሉ ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያስከተለ የሚገኝና ሁኔታውን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች እንደሆነ በመግለጽ፣ የፌደራል መንግሥት አስፈላጊውን የሕግ ማዕቀፍ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት እንዲደነግግና ተገቢውን ዕርምጃ እንዲወስድ ጥያቄ እንዳቀረበለት አስታውቋል።
ሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ የተቃጣ አደጋን በመደበኛ የሕግ ሥርዓት ለመቆጣጠር ባልተቻለ ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ከአደጋ የመከላከል ሥልጣን እንዳለው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 (1) መደንገጉን መሠረት በማድረግ አዋጁን እንዳወጀም የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስታውቋል።
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያ የፌዴራል የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህንን አዋጅ የማወጅ ሥልጣን እንዳለው አከራካሪ እንዳልሆነው ሁሉ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ሊሻር የሚችልበት ሕገ መንግሥታዊ አሠራር በግልጽ መቀመጡን አስረድተዋል። መሻር የሚችለውም የአገሪቱ ሕግ አውጪና የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ለመቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሆነ አስረድተዋል። ነገር ግን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በእረፍት ላይ በሚሆንበት ወቅት የታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለምክር ቤቱ እንዲቀርብ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ የተራዘመ በመሆኑ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ቁጥጥር የማይደረግበት ወይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊሻር የማይችልበትን ጊዜ እንደሚያራዝመው በዚህም ሳቢያ የመብት ጥሰት ሊከሰት፣ ወይም ነገሮች ባልተገባ መንገድ የሚፈጸሙበት ሁኔታ ሊፈጥር ይቻላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 93 1 (ሀ)፣ ‹‹የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፣ የፌዴራሉ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን አለው፤›› በማለት ደንግጋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባለ ጊዜ የታወጀ ከሆነ በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ካላገኘ ወዲያውኑ እንደሚሻር የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ ሁለት (ሀ) ይደነግጋል።
ከላይ የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባልሆነበት ወቅት የታወጀ እንደሆነ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ እንዳለበት፣ የምክር ቤቱን ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ካላገኘም ወዲያውኑ እንደሚሻር የሕገ መንግሥቱ ቀጣይ አንቀጽ ይደነግጋል።
ስድስተኛው ዙር ምርጫ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረ ግጭትና አለመረጋጋት ሳቢያ በተሟላ ሁኔታ ባለመከናወኑ፣ በሥራ ላይ የሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 547 ወንበሮች መካከል የተወሰኑት የተጓደሉ መሆናቸው ይታወቃል። በአጠቃላይ አሁን በሥራ ላይ በሚገኘው ምክር ቤት መቀመጫ የያዙ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ብዛት 427 መሆኑን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ መረዳት ይቻላል።
በመሆኑም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክር ቤቱ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ማፅደቅ ይኖርበታል በሚለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ መሠረት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊፀና የሚችለው ከአጠቃላይ የምክር ቤቱ አባላት ማለትም በስድስተኛው ዙር ተመርጠው በምክር ቤቱ መቀመጫ ከያዙት 427 ተወካዮች መካከል 285 የሚሆኑት የድጋፍ ድምፅ ከሰጡ ነው። ከተጠቀሱት 427 ተመራጮች ውስጥ 142 የምክር ቤት አባላት የተቃውሞ ድምፅ ከሰጡ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀሪ ሊሆን ይችላል።
በምክር ቤቱ ወንበር ካገኙ አጠቃላይ 427 አባላት ወስጥ 410 የሚሆኑት በብልፅግና ፓርቲ አቅራቢነት ተወዳድረው የተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 125 ያህሉ በአማራ ብልፅግና ፓርቲ አቅራቢነት የተወዳደሩና የክልሉን ሕዝብ የሚወክሉ ናቸው። ከብልፅግና ፓርቲ ውጪ በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አቅራቢነት ተወዳድረው የተመረጡ አምስት የሕዝብ ተወካዮች ሲኖሩ፣ በኢዜማ አቅራቢነት ተወዳድረው የተመረጡ ሌሎች አራት የሕዝብ ተወካዮች እንደሚገኙም ይታወቃል።
ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም ለምክር ቤቱ በቀረቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ላይ ለተሰጠው ድምፅ ሥሌት የተደረገው በዕለቱ የነበረውን የምክር ቤቱ ምልዓተ ጉባዔ መሠረት አድርጎ በመሆኑ፣ ባለፈው ዓርብ የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ15 ቀናት ጊዜ ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚቀርብበት ወቅት የሚኖረው የድምፅ አሰጣጥ ሥሌት በዕለቱ የሚኖረውን ምልዓተ ጉባዔ ታሳቢ የሚያደርግ ይሆናል። በመሆኑም የሁለት ሦስተኛ ድምፅ ሥሌቱ ከላይ የምክር ቤቱን ጠቅላላ አባላት መሠረት በማድረግ ከተገለጸው ውጤት ያነሰ የድጋፍና ተቃውሞ ድምፅ የመከሰት ዕድሉ ሰፊ ነው።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣቸው ደንቦች መሠረት የአገርን ሰላምና ህልውና የሕዝብን ደኅንነት፣ ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሥልጣን እንደሚኖረው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 ሥር ተደንግጓል።
በዚህም መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማስወገድ ተፈላጊ ሆኖ በተገኘው ደረጃ፣ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን መሠረታዊ የፖለቲካና የዴሞክራሲ መብቶችን እስከ ማገድ የሚደርስ ሥልጣን እንደሚኖረው ይደነግጋል።
ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 (1 እና 2) ሥር ለብሔር ብሔረሰቦች የተሰጠው፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠልና ቋንቋን ባህልና ታሪክን የማሳደግና የማጎልበት መብቶች፣ እንዲሁም ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል መሆኑን የሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25፣ ኢሰብዓዊ አያያዝ መከልከሉን የሚደነግገው አንቀጽ 18 እና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ አንድ ላይ የተቀመጠው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሚለው የመንግሥት ስያሜ በማናቸውም ሁኔታ ሊገደቡ እንደማይችሉ ይደነግጋል።