የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመላው ሀገሪቱ የሚታዩ ግጭቶች “ያላንዳች ቅደመ ሁኔታ ቆመው” “በአስቸኳይ” በምክክር እንዲፈቱ ጥሪ አቀረበ። ኮሚሽኑ ባለድርሻ አካላትን “በማቀራረብ፣ የልዩነት አጀንዳዎችን ሰብስቦ ለማወያየት እና ለማመካከር አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ዝግጁ መሆኑን” አስታውቋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የሚመለከታቸው አካላት ልዩነቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በምክክር እንዲፈቱ የጠየቀው፤ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 2፤ 2015 በጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕ/ር መስፍን አርዓያ በንባብ ባሰሙት መግለጫ፤ ለሀገራዊ ምክክሩ የተሳታፊዎች የተሳታፊዎች ልየታ እየተከናወነ ባለበት ሁኔታ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አየታዩ ያሉ “ደም አፋሳሽ ግጭቶች” የኮሚሽኑን ስራ “አዳጋች እያደረጉበት ይገኛሉ” ብለዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመላው ኢትዮጵያ የሚታዩ ግጭቶች በአስቸኳይ ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲቆሙ አስቸኳይ አገራዊ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በግጭቶቹ የሚሳተፉ አካላት በሙሉም “አሉን” የሚሏቸውን ልዩነቶች ወይም ጥያቄዎች በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በምክክር እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡
ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ እና የሀሳብ መሪዎች እንዲሁም የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች ያሉ መሆናቸው በግልፅ እንደሚታይ ገልጿል፡፡
ይህንንኑም ታሳቢ በማድረግ አለመግባባቶች በሰለጠነ መንገድ በምክክር የሚፈቱበትን አውድ ለመፍጠር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ አስታውሷል፡፡
ነገር ግን “እነዚህን ልዩነቶችና አለመግባባቶች በንግግርና በምክክር መፍታት ሲገባ፤ በተለያዩ አካባቢዎች እና በተለያዩ ወገኖች እየተወሰዱ ያሉ የኃይል እርምጃዎች የአገራችን ኢትዮጵያን ደህንነትና ህልውና በመፈታተን ላይ መጥተዋል፡፡” ሲል ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ የተቋቋመበትን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገና በተለያዩ አካባቢዎች የተሳታፊዎች ልየታ እየተከናወነ እንዲሁም በሌሎችም ክልሎች ተመሳሳይ ተግባራት ለማከናወንና አጀንዳዎች ለመሰብሰብ በተዘጋጀበት በዚህ ወቅት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየታዩ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች የኮሚሽኑን ሥራ አዳጋች እያደረጉት እንደሚገኙም አስታውቋል፡፡
በመሆኑም የኮሚሽኑ ምክር ቤት ነሐሴ 1 ቀን 2015 ባደረገው ልዩ ስብሰባ “በመላው ኢትዮጵያ የሚታዩ ግጭቶች በአስቸኳይ ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ ቆመው፤ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ አሉን የሚሏቸውን ልዩነቶች ወይም ጥያቄዎች በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በምክክር እንዲፈቱ አስቸኳይ ሀገራዊ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ለዚህም ተግባራዊነት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለድርሻ አካላትን በማቀራረብ፣ የልዩነት አጀንዳዎችን ሰብስቦ ለማወያየትና ለማመካከር አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ዝግጁ መሆኑንም አስታውቋል፡፡