
August 9, 2023 – EthiopianReporter.com

ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያና ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ሒሩት ገብረ ሥላሴ
ዜና ችግሮች በመባባሳቸው ቀጣይ ሥራዎችን በአግባቡ ለማከናወን እንደሚቸገር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ
ቀን: August 9, 2023
- በመላ አገሪቱ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል
በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮች እየተባባሱ በመምጣታቸው፣ ቀጣይ ሥራዎችን በአግባቡ ለማከናወን እንደሚቸገር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ይህንን ያስታወቀው ወቅታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት ማክሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ባቀረበው አስቸኳይ አገራዊ ጥሪ ነው፡፡
ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ሒሩት ገብረ ሥላሴ፣ ‹‹እስከ ዛሬ ችግሮች አልነበሩም ማለት አይደለም፣ ትግራይ ክልል ችግር ነበር፣ ኦሮሚያ ክልል ችግር ነበረ፣ አሁን ደግሞ አማራ ክልል ችግር ተፈጥሯል፡፡ እንዲሁም ደቡብ ክልል ውስጥ ችግሮች አሉ፡፡ ግን ተባብሰው መጥተው ሥራችንን ለመሥራት የማይመች ዓውድ ስለተፈጠረ አስቸኳይ ጥሪ ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው ሁኔታ በብዙ ቦታዎች ችግሮች አሉ፡፡ ለትግራይ ክልል ጥሪያችንን አስተላልፈን እየጠበቅን ነው፣ ትንሽ ጊዜ ወስዷል፡፡ ጊዜ መውሰዱም አንድ ችግር ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል እየሠራን ቆይተን አንዳንድ ዞኖች ውስጥ ሙሉ በሙሉ መግባት አልቻልንም፣ ግን ሥራችንን ሠርተናል፣›› ያሉት ምክትል ኮሚሽነሯ፣ ‹‹አሁን ደግሞ በቀጣይ ልንሠራ ባሰብናቸው ጉዳዮች አገራዊ ምክክሩ ሊከናወን የሚችለው፣ የተለያዩ ወገኖች ያላቸውን ችግር ይዘው መጥተው በመመካከር ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
‹‹ይሁን እንጂ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የምንጠራው መሪ ብቻ አይደለም፡፡ ሕዝቡም የሚሳተፍበት ሒደት መሆን አለበት፡፡ ያንን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ደግሞ በሚገባ መንቀሳቀስ መቻል አለብን፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ ‹‹ኮሚሽኑ የተቋቋመበትን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ባለበት በተለይም በሐረሪና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተሳታፊዎች ልየታ እየተከናወነ ባለበት፣ በሌሎችም ክልሎች ተመሳሳይ ተግባራት ለማከናወንና አጀንዳዎች ለመሰብሰብ ኮሚሽኑ በተዘጋጀበት በዚህ ወቅት፣ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች እየታዩ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች የኮሚሽኑን ሥራ አዳጋች እያደረጉት ነው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በቀጣይ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ አዲስ የተቋቋመውን ክልል አፋር፣ ትግራይን ጨምሮ ሁሉንም ክልሎች ለመሄድ መንደርደሪያ ሰዓታችን ላይ ነው፤›› ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ‹‹ስለዚህ የተሳታፊ ልየታው በትክክል መሄድ አለበት፣ አጀንዳ በትክክል መሰብስብ አለበት፡፡ የተሰበሰቡ አጀንዳዎች በተለይ እጅግ መሠረታዊ የሆኑና በኢትዮጵያ ላለመግባባት ያደረሱትን ችግሮች በሙሉ ተመርጠውና ተነቅሰው ወደ ምክክር የሚወስዱን ነው የሚሆነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
‹‹ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሙሉ ምክንያቶች ይኖሯቸዋል ብለን እናምናለን፤›› ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ‹‹ስለዚህ ወደ ትጥቅ ትግል የሚያስገቡ አጀንዳዎች ተለይተው ለውይይትና ለምክክር መብቃት አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ቦታ ብቻ አይደለም ችግር ያለው፡፡ በምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በሰሜን ምዕራብ በተለያዩ ጊዜዎች ችግሮች ሲከሰቱ ከርመዋል፤›› ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ይህንን ድርጊት በማስቆም ወደ ውይይት እንዲመጣ ጥሪ ሲያደርጉ እንደነበርም አስረድተዋል፡፡
‹‹የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ቅድመ ሁኔታዎች በማስኬድ አምስት ክልሎች ደርሰናል፡፡ የቀሩን ሰባት ክልሎችና አንድ የከተማ መስተዳደር ናቸው፡፡ ሥራዎቻችንን ለመሥራት ከተፈለገ ዋናው ቅድመ ሁኔታችን ወደ ሰላም መምጣት ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
ምክትል ኮሚሽነሯ ወ/ሮ ሒሩት በበኩላቸው፣ ‹‹ትልቁን አገራዊ ምክክር ለማስጀመር ተሳታፊዎችን መረጣ እያካሄድን ባለንብት ወቅት ባሰብነው ልክ ይህንን ሥራ መቀጠል አልቻልንም፡፡ ሥራችንን የሚያስተጓጉሉ ነገሮች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ችግሮች ነበሩ ግን እየበረከቱ መጥተው በሚገባው መጠን ሥራችንን ለመሥራት የማንችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ነው በሚለው ግምገማ ላይ ተመሥርተን ነው ይህንን ጥሪ ያቀረብነው፤›› ብለዋል፡፡
አሁን ይህን ጥሪ ማቅረብ ያስፈለገው እስከ ዛሬ ችግር ሳይኖር ቀርቶ ሳይሆን አሁን እየተባባሰ ስለመጣ መሆኑን አክለዋል፡፡ በመሆኑም በመላ አገሪቱ ግጭቶች በአስቸኳይ ቆመው ጥያቄ ያላቸው አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ ምክክር እንዲያደርጉ ኮሚሽኑ ጥሪ አቀርቧል፡፡
ኮሚሽኑ ማክሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የኮሚሽኑ ምክር ቤት ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ባደረገው ልዩ ስብሰባ በመላ አገራችን የሚታዩ ግጭቶች በአስቸኳይ ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ ቆመው፣ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ አሉን የሚሏቸውን ልዩነቶች ወይም ጥያቄዎች በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በምክክር እንዲፈቱ አስቸኳይ አገራዊ ጥሪ ቀርቧል፤›› ብሏል፡፡
‹‹ለዚህም ተግባራዊነት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለድርሻ አካላትን በማቀራረብ፣ የልዩነት አጀንዳዎችን ሰብስቦ ለማወያየትና ለማመካከር አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ዝግጁ መሆኑን ያሳውቃል፤›› ሲል አክሏል፡፡
‹‹በአገራችን ኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካና የሐሳብ መሪዎች፣ እንዲሁም የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሐሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ያሉ መሆናቸው በግልጽ ይታወቃል፤›› በማለት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡
ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ አለመግባባቶች በሠለጠነ መንገድ በምክክር የሚፈቱበትን ዓውድ ለመፍጠር ኮሚሽኑ ቢቋቋምም፣ እነዚህ ልዩነቶችና አለመግባባቶች በንግግርና በምክክር መፍታት ሲገባ በተለያዩ አካባቢዎች፣ በተለያዩ ወገኖች እየተወሰዱ ያሉ የኃይል ዕርምጃዎች የኢትዮጵያን ደኅንነትና ህልውና በመፈታተን ላይ ናቸው ብለዋል፡፡