ጠመንጃ የያዘ ሰው

ከ 6 ሰአት በፊት

በአማራ ክልል ለወራት የቆየው እና ባለፈው ሳምንት ተባብሶ የቀጠለው ግጭት በበርካታ የክልሉ ከተሞች በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ባለፉት ዓመታት መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ግጭቶች ውስጥ የቆየ ሲሆን፣ ከትግራይ ጦርነት ማብቃት በኋላ በአማራ ክልልም ተመሳሳይ ግጭቶች እያጋጠሙ መሆናቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

ይህ ግጭት በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ የተለያዩ አካላት ጥሪ እያቀረቡ ነው። ካለፈው ጦርነት በመመራር የተፈጠረውን ችግር በጥበብ እና በማስተዋል በውይይት እንዲፈታ የሃይማኖት ተቋማት፣ ፖለቲከኞች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥሪ አቅርበዋል።

ማን ከማን ጋር እየተዋጋ ነው?

በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭቶች እና የተኩስ ልውውጦች ሲካሄዱ ቆይተዋል።

ግጭቱ ባለፈው ሳምንት ተባብሶ ከክልሉ አቅም ውጪ በመውጣቱ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ተጠይቆ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አርብ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታውጆ እርምጃ መወሰድ መጀመሩ ተገልጿል።

ባለፈው ሳምንት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማጽደቅ በእረፍት ላይ የሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀጣይ ቀናት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት ሠራዊቱ “በፋኖ ስም እየተንቀሳቀሱ ሠላም በሚያውኩ ላይ እርምጃ ይወሰዳል” ካሉ በኋላ ችግሩ በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የጣለውን እገዳ ተከትሎ ስሜ መጠቀሱ ይቅር ያሉና የክልሉን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ምሁር ግጭቱ በአንድ በኩል የአገሪቱ መከላከያ እና የክልሉ የፀጥታ ኃይል ተሰልፈው እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

“በሌላ በኩል ደግሞ የታጠቀው ፋኖ አለ። ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ ይዞ የሚንቀሳቀስ የፋኖ ኃይል አለ። ነገር ግን የሚያወግዘውም ስላለ፣ ድጋፉ የሁሉም ሕዝብ ነው ማለት አይቻልም። …ከሕዝቡም በተለይ ከወጣቱ ክፍል ሰፊ ድጋፍ አለው” ብለዋል።

ከዚህ አንጻር ፋኖን በተለያዩ ስሞች መጥራት ጥንቃቄ የሚያሻው መሆኑን ይመክራሉ፤ “ፋኖ ጽንፈኛ መባሉ ሕዝቡንም ፋኖንም ምን ያህል እንዳስቆጣው መንግሥትም የገባው ይመስለኛል። ዘራፊ ማለቱም አይጠቅምም። ከእንዲህ ዓይነት አጠራር መጠንቀቅ ያስፈልጋል” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ፋኖ ስሙ ይነሳ የነበረው በህቡዕ ትግል ነበር።

በወቅቱ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የነበሩ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን ተከትሎ ፋኖም በአማራ በተለይ ደግሞ በጎንደር አካባቢ የወጣቶች የህቡዕ አደረጃጀት እንደነበር ይነገራል።

ከዚያ በኋላ ግን በአገሪቱ የተከሰቱ አለመረጋጋቶችን ተከትሎ ስሙ በተደጋጋሚ የሚነሳው “የታጣቂዎች ኢ-መደበኛ አደረጃጀት” በሚል ሆኗል።

ፋኖ የፌደራል መንግሥቱ ከትግራይ ኃይሎች ጋር ባደረገው ጦርነት፣ በተለይ ደግሞ የህወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል የተወሰኑ ስፍራዎችን ተቆጣጥረው በነበረበት ወቅት ከመንግሥት ኃይሎች ጎን በመሆን በቀጥታ ተሳትፏል።

ቡድኑ በአማራ ክልል መንግሥት የሕዝብ ደጀን ተደርጎ ሲቀርብ፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ደግሞ “አንዳንድ የአማራ ጽንፈኛ ታጣቂዎች” በሚል ይወገዛል።

ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ደግሞ ቡድኑን በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመፈፀም ይከሱታል።

ዋና ዋና ጥያቄዎቹ ምንድን ናቸው?

ቢቢሲ ያናገራቸው ግለሰብ በክልሉ የሚነሱ ጥያቄዎች ለረዥም ጊዜ ሲንከባለሉ የቆዩ በፌደራል መንግሥቱም ሆነ በክልሉ መንግሥት የታወቁ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ደመቀ መኮንን በክልሉ የተከሰተውን ግጭት አስመልክተው በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ላይ በክልሉ የተቀሰቀሰውን ግጭት “የጥያቄዎችን መፍቻ መንገድ የሚያደናቅፍ” መሆኑን ገልጸው ነበር።

ምንም እንኳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎቹ ምን አንደሆኑ በይፋ ባይገልጹም ግጭቱን “በዘላቂነት ሊታዩ ይገባቸዋል የምንላቸውን ጉዳዮች እንዳይፈቱ የሚያወሳስብ አካሄድ” መሆኑን አስፍረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “ከለውጡ ብዙ የጠበቅናቸው ግን ደግሞ ምላሽ ያላገኘንባቸው ያላረኩን እና ሌሎች ችግሮች እና ስሜቶች ይኖራሉ” ሲሉ በመልዕክታቸው ላይ ገልፀዋል።

ክልልሉን በቅርበት የሚከታተሉት ምሁር ከወሰን እና ከማንነት ጋር የሚያያዘው ቀዳሚው ጥያቄ መሆኑን በመጠቆም “የወልቃይት፣ ራያ እና ጠለምት” ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

ከክልሉ ውጭ የሚኖረው የአማራ ሕዝብ በሠላም የመኖር፤ ተገቢውን ውክልና የማግኘትም ሌላኛው ጥያቄ መሆኑንም ያነሳሉ።

“ሦስተኛው የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ነው” ያሉት ምሁሩ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ዘርፍ ተገፍቻለሁ ብሎ የሚያምንባቸው ጉዳዮች ስላሉ ይህ እንዲስተካከል ጥያቄ አለው” ብለዋል።

አዲስ አበባ አካባቢ ያለው የአማራ ሕዝብ መብቱ እና ጥቅሙ በሚገባ አልተከበረም በማለት “አዲስ አበባ የሁላችንም እንጂ አንድ ብሔር ናት የሚለው እንቅስቃሴ መቆም አለበት የሚሉት ዋና ዋና ጥያቄዎች ነበሩ” ይላሉ።

“ግድያ እና መፈናቀሉ” ካለመቆሙም በላይ “የህልውና ስጋት ገጥሞናል የሚል ደረጃ ላይ ተደርሷል።” ይህ ጥያቄም ገዢ ሆኖ መምጣቱን አንስተዋል።

ጥያቄዎቹ ከብልጽግና በፊት የተፈጠሩ መሆናቸውን አንስተው፣ ይህንን ለመቀየርም ሕዝቡ ሰፊ ትግል ማካሄዱን ጠቁመዋል።

ህወሓት ከሥልጣን ተነስቶ ብልጽግና ሲተካ “የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎቹ ይመለሱልኛል የሚል ተስፋ ቢኖርም እየባሰ መሄዱ አሁን ለተደረሰበት ሁኔታ አባባሽ ሆኖ ቀጥሏል” ብለዋል።

“በችኮላና በጥድፊያ የህልውና ስጋቶች የሚባሉት ሳይስተካከሉ” በኋላም “ጥያቄዬን ያስመልስልኛል ወይንም መከታ ይሆነኛል ያለው ልዩ ኃይል መፍረሱም የአማራን ሕዝብ አበሳጭቶታል” ብለዋል።

ፋኖን ለመያዝ እና ለማስተዳደር የሄደበት አካሄድ ተደማምረው “ለምናየው የአማራ ሕዝብ ቁጣ መንስኤ እንደሆኑ ይሰማኛል” ብለዋል።

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ለተፈጠረው ችግር የአማራ ክልልን እና የፌደራሉ መንግሥትን የወቀሰ ሲሆን፣ ለዚህም የሕዝቡ ጥያቄ እና ስጋት ተገቢው ምላሽ አለማግኘቱ መሆኑን ጠቅሷል።

ከክልሉ ውጪ ነዋሪ በሆኑ አማሮች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እና መፈናቀል፣ መሳደድ እና አስር፣ ከህወሓት ጋር በተካሄደው ጦርነት በክልሉ ውስጥ ያደረሰው ውድመት ትኩረት መነፈግ፣ የይገባናል ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎች ጉዳይ መቋጫ አለማግኘት ቅሬታ መፍጠሬን አብን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

አሁን ለተፈጠረው ግጭት እና ቀውስ ደግሞ የክልሉን ልዩ ኃይል ያለ ዝግጅት እንዲፈርስ መደረጉ እና በጦርነቱ ውስጥ መስዋዕትነት ለመክፈል የተሰለፉ የፋኖ አባላትን ማሳደድ ችግሩን እንዳባባሰው ገልጿል።

የመጨረሻ ግቡ ምንድን ነው?

አሁን በአማራ ክልል ውስጥ የተፈጠረው ቀውስ የመጨረሻ ግቡን በተመለከተ መመለስ የሚችሉት እንቅስቃሴውን የሚመሩ ሰዎች ቢሆኑ እንደሚመረጥ ምሁሩ ተናግረዋል።

አክለውም እንቅስቃሴውን የሚመሩት ሰዎች እነማን አንደሆኑ በግልጽ መናገር አዳጋች መሆኑን በማንሳት፣ ነገር ግን አመራር እንደሚኖረው ያምናሉ።

“መሪ እንዳለው የሚገመት ነገር ነው። በእነማን እየተመራ ነው የሚለውን በግልጽ ለማወቅ እና ለመናገር ግን ትንሽ አስቸጋሪ ነው። ሰዎቹ ወጥተው በምን መንፈስ፣ በምን አካሄድ እየመሩት እንደሆነ ግልጽ ስላለሆነ የብስለት ጥያቄ ሊነሳበት ይችላል።”

ይህ ሁኔታም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄደው እንቅስቃሴ አንድ የተማከለ አመራር አለ ወይ የሚል ጥያቄ እንዲነሳ እንደሚያደርግ የሚናገሩት ምሁሩ፣ “ይህ ደግሞ የሚፈልግው ግብ ላይ ከመድረሱ አንጻር ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጋል” ይላሉ።

ምሁሩ የእንቅስቃሴውን ውጤታማነት ቢጠራጠሩም እየተባለ ካለው እና ከሚታየው በመነሳት ውጤት ላይ ቢደርስ “መነሻችን አማራ መዳረሻችን ኢትዮጵያ የሚለውን መርኅ ያነገበ በመሆኑ” ከኢትዮጵያዊነት ስሜት የሚወርድ እንደማይሆን ይገምታሉ።

“ውጤታማ ከሆነ ኢትዮጵያን እንደገና የማጽናት ወይም ከአንድነት ኃይሎች ጋር ተባብሮ የኢትዮጵያን ሠላምና አንድነትን የሚመልስ ይመስለኛል። ኢትዮጵያን እንደገና የማጽናት ችግሮቿን የመፍታት ሙከራ የሚያደርግ ኃይል ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

ነገር ግን እንቅስቃሴው ውጤታማ መሆኑን ከሚጠራጠሩት አንዱ መሆናቸውን የሚናገሩት ምሁሩ፣ መንግሥት በተነጻጻሪነት ጉልበት ስላለው ነገሮችን መቆጣጠር ዕድል እንደሚኖረውም ይገምታሉ።

“ከፍተኛ ሕዝብ ቁጣ አለ፤ ሕዝብ እንዲመለሱ የሚፈልጋቸው ጥያቄዎች አሉ። ጥያቄዎቹ እስካልተመለሱ ድረስ አማራ ሕዝብ ላይ የተረጋጋ አመራር ለመፍጠር ከባድ ይመስለኛል” ይላሉ።

ስለዚህም ሲነሱ የቆዩ ጥያቄዎች ሳይመለሱ በአማራ ክልል ምን አይነት የወረዳ፣ የዞን እና የክልል አመራር ነው የሚኖረው? የሚል ተጨማሪ ጥያቄ የሚያነሱት ምሁሩ፣ “እጅግ የሚያሳስብኝ እንዲያውም የሕዝቡ መጻኢ ዕጣው ነው” በማለት የወደፊቱ አሳሳቢ መሆኑን ይገልጻሉ።

አክለውም ለወራት ሲካሄድ የነበረው ግጭት ተባብሶ ወደ ለየለት ቀውስ የገባው አሁን ያለው ሁኔታ ቶሎ በሠላማዊ መንገድ መፍትሄ ካልተፈለገለት በክልሉ እና በአገሪቱ ላይ ውድመት ማስከተሉ እንደማይቀርም ጠቁመዋል።

መንግሥት እየተነሱ ያሉት ጥያቄዎች የፋኖ እና የታጣቂዎች ጥያቄ ብቻ አድርጎ ከወሰደው ስህተት ይፈጽማል ያሉት የሚሉት ምሁሩ፣ “በሕዝቡ ዘንድ የመከፋት ስሜት አለ። ይህንን ከግምት አስገብቶ ረጋ እያለ፣ አንዳንዴም መንግሥት ተሸንፎም ቢሆን ማሸነፍ ይቻላል” ይላሉ።

አክለውም መንግሥት የሚነሱ ጥያቄዎችን ሳይመልስ በአማራ ክልል ውስጥ የተረጋጋ አስተዳደር ለመፍጠር ማሰብ “በጣም አስቸጋሪ ነው” ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናቅቃሉ።

በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት በተባባሰበት ጊዜ የዞን እና የወረዳ ከተሞች ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ መውጣታቸው የተዘገበ ሲሆን፣ በትልልቅ ከተሞች ውስጥም እንቅስቃሴው እንደነበረ ይታወቃል።

በዚህም ሳቢያ በየአካባቢዎቹ ያሉ አመራሮች ኢላማ በመሆናቸው የመንግሥት የአስተዳደር መዋቅር ተገቢውን ተግባሩን ማከናወን ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽመው አካልም በክልሉ ውስጥ ከሚወስዳቸው እርምጃዎች መካከል ቀዳሚው በየቦታው የመንግሥት እና የፓርቲ መዋቅርን የማጠናከር መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።

አብን በበኩሉ “ማኅበረሰቡን የሚመጥን እና በማኅበረሰቡ የሚታመንበት አደረጃጀት በየደረጃው ተመስርቶ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ተቋማዊ በሆነ አግባብ ምላሽ እንዲያገኙ እንዲደረግ” መንግሥት ጠይቋል።