የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት ሕገወጡን የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንደማይቀበል ገለጸ !
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት በትግራይ ክልል የተፈጸመውን ሕገወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንደማይቀበል የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ መምህር ዜናዊ ሀሸተ ለተ.ሚ.ማ ገለጹ።
መጋቤ ሐዲስ መምህር ዜናዊ ሀሸተ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ከተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል ጋር ባደረጉት የስልክ ቆይታ ለሀገረ ስብከታችሁ ኤጲስ ቆጶስ ሾመንላችኋል መባላቸው እንዳሳዘናቸው ገልጸው ሀገረ ስብከቱን ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲመሩት ከመደበልን ሊቀ ጳጳስ ውጪ የምንቀበለው አካል አይኖርም ነው ያሉት።
ሾምን ያሉት እና ተሿሚ ነን የሚሉት ግለሰቦች በአንድ ወንበር ሁለት አገልጋይ ስለማይኖር ተሾምን ያሉት አካላት በሀገረ ስብከታችን ቦታ እንደሌላቸው ሊያውቁ ይገባል ሲሉም አክለዋል።
በተመሳሳይም ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መጋቤ ሰላም ሀይሌ አምዴ ጋር ባደረግነው የስልክ ቆይታ በትግራይ ክልል የተፈጸመው ሕገወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት በጣም እንዳሳዘናቸው፤ የሀገረ ስብከቱ አመራርም ሆነ ምዕመናን ሊቀበሉት እንደማይችሉም ገልጸዋል።
የሰሜኑ ክፍል የክርስትናው ምንጭ ሆኖ ሳለ የፖለቲከኞች ተላላኪ ሆነው ማየታችን በጣም የሚያሳዝነን ጉዳይ ነው ፤ ሀገረ ስብከቱም ከምዕመኑ ጋር ስብሰባን አካሂዶ ይሔን ጉዳይ ሊቀበሉ እንደማይችሉ በመወሰን መግለጫ ለማውጣት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ነው ዋና ጸሐፊው የገለጹት።
በመጨረሻም ቅድስት ቤተክርስቲያንን ከልብ አገልግለን እና ጠብቀን ወደ ቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ የምንሰራበት ሰዓት አሁን በመሆኑ ሁሉም የተሰጠውን ሥልጣን ለግል እና ለፖለቲካ አላማ ማዋል አግባብ አይደለም፤ የቤተክርስቲያን ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ ስለሆነ ሁሉም ከቤተክርስቲያን ጎን ሊቆም ይገባል ብለዋል።