August 12, 2023

በአማኑኤል ይልቃል

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተፈጻሚነት ጊዜ “ከአንድ ወር ወይም የተወሰኑ ሳምንታት ላልበለጠ ጊዜ ብቻ” እንዲሆን እንዲያደርግ እና የተፈጻሚነት ወሰኑንም በአማራ ክልል ብቻ እንዲገድብ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጠየቀ። በአዋጁ ለአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ “የተለያዩ የአስተዳደር እርከኖችን እና መዋቅሮችን መልሶ ለማቋቋም” የተሰጠውን ስልጣን ፓርላማው እንዲሰርዝም ጥያቄ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እነዚህን ጥያቄዎች ያቀረበው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ባለ 22 ገጽ የምክረ ሃሳብ ሰነድ ላይ ነው። ኢሰመኮ ይህንን ምክረ ሃሳብ  ዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 6፤ 2015 ይፋ ያደረገው፤ የተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን መርምሮ ውሳኔ ለማሳለፍ ከነገ በስቲያ አስቸኳይ ስብሰባ እንደሚያካሄድ መገለጹን ተከትሎ ነው።

ብሔራዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም፤ የሰብአዊ መብቶች ስጋቶች እና የማሻሻያ ምክረ ሃሳቦች ባካተተበት ሰነድ ላይ በቅድሚያ ያነሳው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለተወካዮች ምክር ቤት ያለመቅረቡን ጉዳይ ነው። የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገው ባለፈው ሳምንት ሐምሌ 28፤ 2015 ቢሆንም፤ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለእረፍት በመበተናቸው አዋጁ እስካሁን  ለፓርላማ አልቀረበም። 

አዋጁ በፓርላማ ሳይጸድቅ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ተፈጻሚ መሆኑ፤ “የመንግስት የአስቸኳይ ጊዜ ስልጣን ለበርካታ ቀናት ያለ ምክር ቤቱ እይታ እና ቁጥጥር” እንዲቆይ ምክንያት እንደሆነ ኢሰመኮ በምክረ ሃሳቡ ላይ አመልክቷል። የተወካዮች ምክር ቤት በመጪው ሰኞ በሚያካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው አዋጁን የሚያጸድቀው ከሆነ፤ ድንጋጌው ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የነበረውን አፈጻጸም የተመለከተ ሪፖርት መንግስት ለፓርላማ እንዲያቀርብ እንዲደረግ ኮሚሽኑ ጠይቋል። 

በኢሰመኮ የምክረ ሃሳብ ሰነድ ላይ የተጠቀሰው ሌላኛው ጉዳይ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተፈጻሚነት ወሰን ነው። የአማራ ክልል ለፌደራል መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት እንደወጣ በተገለጸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ፤ ድንጋጌው ከአማራ ክልል በተጨማሪ “እንደ አስፈላጊነቱ በየትኛዉም የሃገሪቱ አካባቢ ተፈጻሚነት” እንደሚኖረው ሰፍሯል። የአዋጁ “አካባቢያዊ ተፈጻሚነት ወሰን በግልጽ ተለይቶ ባልተመለከተ መንገድ እና መስፈርት” መቀመጡ፤ ድንጋጌው “ከልክ በላይ እንዲለጠጥ በር የሚከፍት ነው” ሲል ኢሰመኮ ተችቷል። 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሌሎች ክልሎች ተፈጻሚ እንዲሆን መሟላት ያለበት መስፈርት አስቀድሞ በህግ ሳይቀመጥ “መስፈርቶች መሟላታቸውን የሚያረጋግጠው እና የሚወስነው አካል ራሱ በአዋጁ የተቋቋመው ዕዝ ብቻ ነው” መባሉንም ኮሚሽኑ በስጋት ተመልክቶታል። ይህ አይነት አካሄድ “ከሕጋዊነት፣ ከአስፈላጊነት እና ከተመጣጣኝነት መርህ አንጻር” “ክፍተት የሚፈጥር ነው” ሲል ኢሰመኮ በሰነዱ ላይ ስጋቱን አስቀምጧል።  

Post

Ethiopia Insider

@ethiopiainsider

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ “ስምሪት የሚሰጡ” ያላቸውን እና ሌሎችንም ግለሰቦች በቁጥጥር ስር

ማዋል መጀመሩን መንግስት አስታወቀ። ዕዙ እርምጃውን መውሰድ የጀመረው ከትላንት ምሽት ጀምሮ

መሆኑ ተነግሯል።

* ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2023/11661/

Translate Tweet

Image

· 5,295 Views

6 Reposts 33 Likes

“ከአንድ ክልል ብቻ በቀረበ የጸጥታና ደህንነት አደጋ ምክንያት ጠቅላላ ሀገሪቱን የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ማስገባት እና አጠቃላይ የሀገሪቱን የሕግ አስከባሪ አካሎች በአስቸኳይ ጊዜ መምሪያው ዕዝ ስር ማድረግ” በመደበኛው የፍትህ አስተዳደር ስራ ላይ “እጅግ አሉታዊ አንድምታ የሚፈጥር” እንደሆነም ኮሚሽኑ በሰነዱ አጽንኦት ሰጥቷል። 

የተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን በሚመለከትበት ወቅት፤ የተፈጻሚነት ወሰኑን “ጥያቄው በቀረበበትና አደጋው ተከስቷል በተባለበት ክልል ብቻ የተገደበ እንዲሆን” እና በሌሎች አካባቢዎች መደበኛው የህግ ስርዓት እንዲቀጥል እንዲያደርግ ኢሰመኮ በሰነዱ ምክረ ሀሳቡን አቅርቧል። ከአማራ ክልል ውጪ ባሉ አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አስፈላጊነት ከተከሰተ፤ “መንግስት ከክልሎች በሚቀርብለት ጥያቄ ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወደፊት እራሱን ችሎ በሚያቀርበው አዋጅ ብቻ እየታየ እንዲወሰን” እንዲደረግም ኮሚሽኑ ጠይቋል።

ኢሰመኮ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተፈጻሚነት ወሰን በተጨማሪ የቆይታ ጊዜው ላይም ማሻሻያ እንዲደረግበት ይሻል። ኢሰመኮ የአዋጁ ተፈጻሚነት የጊዜ ወሰን “ከስድስት ወር እጅግ ዝቅ ተደርጎ በተቻለ መጠን ከአንድ ወር ወይም የተወሰኑ ሳምንታት ላልበለጠ ጊዜ ብቻ ተፈጻሚ እንዲደረግ” ለተወካዮች ምክር ቤት ምክረ ሀሳብ አቅርቧል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ለስድስት ወራት እንደሚጸና ቢደነገግም፤ ቀነ ገደቡ ከመድረሱ በፊት ግን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዋጁን ተፈጻሚነት ቀሪ የሚሆንበትን ጊዜ ሊወስን እንደሚችል በአዋጁ ላይ ሰፍሯል። 

Ethiopia Insider

@ethiopiainsider

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ ከአማራ ክልል በተጨማሪ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም “እንዳስፈላጊነቱ” ተፈጻሚ እንደሚሆን ተገለጸ። አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ለ6 ወር ጸንቶ ይቆያል ተብሏል። * ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2023/11636/

Translate Tweet

Image

· 7,268 Views

ኢሰመኮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተፈጻሚነት ጊዜን ፓርላማው እንዲያሳጥር ምክረ ሀሳብ ያቀረበው፤ “በአሁኑ ወቅት የጸጥታና ደህንነት አደጋው ተወግዶ መደበኛ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው በይፋ እየተገለጸ መሆኑን” በምክንያትነት በመጥቀስ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ትላንት አርብ ነሐሴ 5፤ 2015 በሰጠው መግለጫ፤ በአማራ ክልል በታጣቂዎች ተይዘው የነበሩ ከተሞችን “ነጻ የማድረግ እና ክልሉን ወደ ሰላማዊ ሁኔታ የመመለስ” ስራ “በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቁን” አስታውቆ ነበር።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያስፈጽም የተቋቋመው ይህ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ፤ በአዋጅ የተሰጡት አንዳንድ ስልጣኖች እንዲሰረዙ ኢሰመኮ በምክረ ሃሳብ ሰነዱ ላይ ጠይቋል። ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል “የህዝብን ሰላም፣ የሀገር ደህንነትን ለማስፈን አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን የመውሰድ እና ውሳኔዎችን የማሳለፍ፣ ትዕዛዞችን የመስጠት ስልጣን አለው” የሚለው ይገኝበታል። ዕዙ “ኃላፊነቱን ለመወጣት ሌሎች አስፈላጊ እና አግባብ የሆኑ ስልጣኖች” እንደሚኖሩትም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተደንግጓል። 

እነዚህ የአዋጁ አንቀጾች በሕገ መንግስቱም ሆነ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መርሆች የተከለከለውን፤ “ስልጣንን ያለአግባብ የመጠቀም ስጋት የሚፈጥሩ” እንደሆኑ ኢሰመኮ በምክረ ሃሳቡ ላይ አስፍሯል። አንቀጾቹ በህገ መንግስቱ ለተለያዩ የመንግስት አካላት የተሰጡ “ስልጣናትን ጭምር ሊያካትቱ ወይም ሊሻሙ የሚችሉ” እንደሆኑ የጠቀሰው ኮሚሽኑ፤ በእነዚህ ምክንያቶች ድንጋጌዎቹ እንዲሰረዙ በምክረ ሃሳቡ ጠይቋል። 

Post

Ethiopia Insider

@ethiopiainsider

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች “አንዳንድ የዞንና የወረዳ ከተሞችን መቆጣጠራቸውን” እንዲሁም

በተወሰኑ ቦታዎች “ወንጀለኞችን ከማረሚያ ቤት ማስለቀቃቸውን” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ

ዕዝ ዋና ሰብሳቢ አስታወቁ

https://ethiopiainsider.com/2023/11682/

Translate Tweet

Image

· 14K Views

5 Reposts 7 Quotes 48 Likes

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ “የተለያዩ የአስተዳደር እርከኖችን እና መዋቅሮችን መልሶ የማቋቋም፣ የማደራጀት እና የአስተዳደርና የጸጥታ ጉዳዮችን በተመለከተ ውሳኔዎችን የማስተላለፍ እና ሌሎች እርምጃዎችን የመውሰድ” ስልጣን እንዳለው በአዋጁ የተቀመጠው ድንጋጌም ከኢሰመኮ ተቃውሞ ገጥሞታል። ይህ ድንጋጌ “ለተለጠጠ ትርጓሜ ወይም ተገቢ ላልሆነ አፈጻጸም ክፍት” እንደሆነ የጠቀሰው ኮሚሽኑ፤ “በክልሎች የዞን፣ የወረዳ እና ተያያዥ የአስተዳደር እርከኖች እና መዋቅር ላይ ከህገ መንግስታዊ ስርዓት ውጪ ለውጥ የማድረግና ውሳኔ የማሳለፍ እንድምታ የሚሰጥ” እንደሆነ አብራርቷል።

ይህ አይነቱ ድርጊት “የጥብቅ አስፈላጊነት፣ ተመጣጣኝነት እና ሕጋዊነት መርሆዎች ጋር ሊቃረን የሚችል” መሆኑን በምክረ ሃሳቡ ላይ ያነሳው ኢሰመኮ፤ ከዚህም ባሻገር ለሌላ “የፖለቲካ ውጥረት እና ለግጭት ተጨማሪ ስጋት” የመሆን እድል እንዳለውም አስገንዝቧል። በዚህም ምክንያት የተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን በሚመለከትበት ወቅት፤ ይህንን ድንጋጌ ሊሰርዘው እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አሳስቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)