August 13, 2023 – EthiopianReporter.com 


የዱራሜ ከተማ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ባደረገበት ወቅት

ዜና የከምባታ ጠምባሮ ምክር ቤት የክልል መዋቅሮች ድልድልን ተቃወመ

ዮናስ አማረ

ቀን: August 13, 2023

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሥር እንዲደራጅ የተወሰነው የከምባታ ጠምባሮ ዞን ምክር ቤት አዲሱን የመዋቅር ድልድል ተቃወመ፡፡ በመዋቅር ድልድሉ መሠረት የተለያዩ ቢሮዎች መቀመጫ በሰባት የክላስተር ከተማ ማዕከላት እንዲሆን ሲወስን፣ የዞኑ ዋና መዲና ዱራሜ ከተማ ፍትሐዊ ድልድል አለማግኘቷ ቅሬታን ፈጥሯል ተብሏል፡፡

በዚህ ጉዳይ ዓርብ ነሐሴ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ስብሰባ የጠራው የዱራሜ ከተማ ምክር ቤት ውሳኔውን የሚቃወም አቋም ይዞ መበተኑ ታውቋል፡፡ የከተማው ምክር ቤት ውሳኔ በዞን ምክር ቤት በኩል ፀድቆ ለክልልና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሚላክ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት ተናግረዋል፡፡

የዱራሜ ከተማ እንዲሁም የዞን ምክር ቤት አባሏ ወ/ሮ ሰናይት ለገሰ በአዲሱ የመዋቅር ድልድል ከግብርና ነክ ቢሮዎች ውጪ ዞኑ አለማግኘቱ፣ የቅሬታ ምንጭ መሆኑን ተናግረዋ፡፡ ዱራሜ ከተማ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር በሚል ግብርና ነክ ቢሮዎች ብቻ መቀመጫ መሆኗ፣ ክልሉ ሲደራጅ ቃል ከተገባው ውጪ የሆነ፣ ሕጋዊም ሆነ ፍትሐዊነትን ያልተከተለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከምባታ ጠምባሮ ዞን በመንግሥት ጥናት ተብሎ ክላስተር ክልል የሚባል ነገር ከመምጣቱ በፊት የክልልነት ጥያቄ ማቅረቡን አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ከሌሎች ዞኖች ጋር በክላስተር ክልል ሥር ሲደራጅ ከሁሉም ዞን ሁለት ሰዎች እየተወከሉ በሀብት ክፍፍልና በመዋቅር ድልድል ላይ ኮሚቴ ተዋቅሮ እንዲሠራ ተወስኖ ነበር፤›› ይላሉ፡፡

የማዕከል ከተሞች ውሳኔ እንዲሁም የመዋቅር ድልድል ጉዳይ፣ ከሲዳማና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ መመሥረት ጀምሮ ሲያጨቃጭቅ የመጣ ጉዳይ መሆኑን የምክር ቤት አባሏ አስታውሰዋል፡፡ ይህ እንዳይደገም ሥጋት እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ሆኖም ባልታወቀ ሁኔታ ለከምባታ ጠምባሮ ዞን አንድ ቢሮ በመስጠት፣ ለጉራጌ ዞን 12 ቢሮ፣ ለሐዲያ ዞን ስምንት፣ አላባ ዞን ሦስት ቢሮ በማድረግ መዋቅሮች በተለያዩ ክላስተር ማዕከላት ተበትነዋል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ስድስት ክላስተር ማዕከላት ብቻ እንደሚደራጁ ቃል ተገብቶ እንደነበር ያስታወሱት ወ/ሮ ሰናይት፣ ይሁን እንጂ ቡታጅራን በመጨመር ወደ ሰባት ማደጉን ተናግረዋል፡፡

በአዲሱ የማዕካላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሥር ሆሳዕና ከተማ ክላስተር፣ ቡታጅራ ከተማ ክላስተር፣ ወልቂጤ ከተማ ክላስተር፣ ወራቤ ከተማ ክላስተር፣ ዱራሜ ከተማ ክላስተር፣ ሃላባ ከተማ ክላስተር እንዲሁም የም ልዩ ወረዳ ሳጃ ከተማ ክላስተር የተባሉ የከተማ ማዕከላት መፈጠራቸው ታውቋል፡፡ የዞን ሕዝብ ብዛትን፣ ማዕከላዊነትን (ቅርበትን) እንዲሁ ተወዳዳሪነትን ታሳቢ ያደረገ የክላስተር ማዕከላት ድልድል ስለመደረሱ ተነግሯል፡፡

ይሁን እንጂ አንዳንድ ከተሞችና ዞኖች ከሌላው በቁጥርም ሆነ በጠቃሚነት የተሻለ ቢሮ አግኝተዋል የሚል ቅሬታ በተለያዩ አካባቢዎች መፈጠሩ ተሰምቷል፡፡ ከሰሞኑ በከምባታ ጠምባሮ ዞን የቢሮ ድልድሉን የሚቃወም ሰላማዊ ሠልፍ መደረጉ ተሰምቷል፡፡

የዞኑ ምክር ቤት አንዳንድ አባላት ይህንኑ የሚደግፍ አቋም አንፀባርቀዋል፡፡ ጠምባሮን በመወከል የዞን ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ለገሰ ሎምቤቦ ዞናቸው መሠረታዊ ጥያቄዎቹ እንዳልተመለሱለት ተናግረዋል፡፡ ‹‹የክልልነት ጥያቄያችን አልተመለሰም፡፡ ጠምባሮ ልዩ ወረዳ ይሰጠው የሚለው ጥያቄያችንም አልተመለሰም፡፡ በክላስተር ክልል ተደራጁ የሚለውን አሜን ብለን ብንቀበልም ነገር ግን ከሌሎች ዞኖች በእጅጉ ባነሰ ሁኔታ አንድ ቢሮ ብቻ ነው ለዞኑ የተሰጠው፤›› በማለት የተፈጠረውን ቅሬታ ተናግረዋል፡፡

ዞኑ በምክር ቤት አፀድቆ ጥያቄውን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሚወስደው አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት የምክር ቤት አባላት አረጋግጠዋል፡፡