August 13, 2023 – EthiopianReporter.com 

አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በቅርቡ ባወጣው መግለጫ በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ተልዕኮውን ለማከናወን መሰናክል እንደሆኑበት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ለአገር ዘለቄታዊ ሰላም ተስፋ ይፈነጥቃል ተብሎ የሚጠበቀው ብሔራዊ የምክክር ሒደት ሲደናቀፍ፣ መጪው ጊዜ ብሩህ ይሆናል ብሎ መጠበቅ በፍፁም አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሐሳብ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በንግግርና በምክክር መፍታት ሲገባ፣ በተለያዩ አካባቢዎችና በተለያዩ ወገኖች እየተወሰዱ ያሉ የኃይል ዕርምጃዎች የአገርን ህልውና እየተፈታተኑ መሆናቸውን ኮሚሽኑ በከፍተኛ ሥጋት ሲገልጽ ያሳስባል፡፡ ኮሚሽኑ የተቋቋመበትን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚካሄዱ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ሥራውን አዳጋች እንዳደረጉበት ማስታወቁ የችግሩን ግዝፈት ያሳያል፡፡ ይህ እንግዲህ ከዘርፈ ብዙ ችግሮች መካከል ሊጠቀስ የሚችል ማመሳከሪያ ሲሆን፣ በዚህ ከባድ ሁኔታ ውስጥ የኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ጉዳይ እንቅልፍ የሚነሳ ነው፡፡ ስለዚህም ልዩነት ያላቸው ወገኖች በሙሉ ቀልባቸውን ሰብሰብ አድርገው፣ ለሕጋዊና ለሰላማዊ ንግግርና ድርድር እንዲዘጋጁ ማሳሰብ የግድ ይሆናል፡፡

ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚያስተዳድረው መንግሥትም ሆነ ገዥው ፓርቲ ከአገራዊ የምክክር መድረኩ በተጨማሪ፣ ጥያቄ አለን ከሚሉ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ሕጋዊና ሰላማዊ ንግግር እንዲጀመር ተነሳሽነቱን ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ ተገፍተናልና ተበድለናል ከሚሉ ወገኖች ጋር ተነጋግሮ ሰላማዊ መፍትሔ መፈለግ አለበት፡፡ መንግሥት ሕግ ሲያስከብር መጀመሪያ ራሱ ማክበሩን ማሳየት ይኖርበታል፡፡ ለአድሎአዊና ለብልሹ አሠራር የሚያጋልጡ ድርጊቶችን በማስወገድ ለንግግርና ለድርድር መደላድል ይፍጠር፡፡ በሰላማዊው የፖለቲካ ምኅዳርም ሆነ ከዚያ ውጪ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ግፊት ያድርጉ፡፡ የጠብና የግጭት መንገድ ያተረፈው ነገር ቢኖር ዕልቂትና ውድመት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአስከፊ የኑሮ ውድነት እየተጠበሰ ሰላሙ ተናግቶ ዕድገት ይኖራል ብሎ መጠበቅ አያዋጣም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ትጥቅ ያነገቡም ሆኑ ያላነገቡ ወገኖች ወደ ውይይትና ድርድር ጠረጴዘው እንዲመጡ የመጋበዝ ኃላፊነት የመንግሥት ስለሆነ፣ አገር የለየለት ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ ሲባል አስቸኳይ ውሳኔ ላይ መደረስ አለበት፡፡ ዋስትና ያለው ሰላም የሚሰፍነው መነጋገርና መደራደር ሲቻል እንጂ፣ አሁን እንደሚስተዋለው በመሣሪያ የበላይነት በሚገኝ ድል አይደለም፡፡

እንደ መንደርደሪያ የተነሳው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ወቅታዊ ማሳሰቢያ ይሁን እንጂ፣ በአሁኑ ጊዜ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖረው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የናፈቀው ሰላም ነው፡፡ መንግሥትም ሆነ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እንዲሁም ትጥቅ አንግበው የሚፋለሙ ኃይሎች ሰላም የሚሰፍንበትን የጋራ ፍኖታ ካርታ የሚያዘጋጁበት ዓውድ መፈጠር አለበት፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና የአገር ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ፣ ከኢትዮጵያ ምድር የጉልበት ፖለቲካ ተወግዶ ሁሉንም በእኩልነት የሚያሳትፍ ምኅዳር እንዲፈጠር ይነጋገሩ፣ ይደራደሩ፡፡ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች ሆኖ የሚደረግ ግንኙነትም ሆነ ንግግር ፋይዳ ስለሌለው፣ ለዘላቂ ሰላም መፈጠር የሚያግዙ አማራጮች ላይ ይተኮር፡፡ እውነተኛ ሰላም ሲኖር የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያ መብቶች ይከበራሉ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ ሰፍኖ አድሎአዊነት ይወገዳል፣ ብልሹ አሠራሮች ከሥራቸው ተነቅለው ይጣላሉ፣ ሌብነትና ዝርፊያ ቦታ አይኖራቸውም፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ስለሚኖር በሥልጣን መባለግ አይቻልም፣ ልዩነት ሲኖር ወደ መነጋገሪያ ጠረጴዛ እንጂ ጠመንጃ መነቅነቅ ይቀራል፣ እንዲሁም በእኩልነትና በነፃነት መኖር ይለመዳል፡፡

በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብና በሌሎች አካባቢዎች ሰላም በመጥፋቱ ምክንያት የተጎዳው ሕዝብ ነው፡፡ አርሶ አደሩ ተረጋግቶ እርሻውን እንዳያከናውን፣ አርብቶ አደሩ በሰላም ከብቶቹን እንዳያረባ፣ ነጋዴው ከሥፍራ ወደ ሥፍራ ተንቀሳቅሶ እንዳይነግድ፣ ተማሪዎች በተረጋጋ መንፈስ እንዳይማሩ፣ የመንግሥትና የግል ሠራተኞች ሥራቸውን እንዳያከናውኑ፣ ሕፃናት በሰላም እየቦረቁ እንዳያድጉ፣ አገራቸውን አገልግለው በጡረታ የተሸኙ አዛውንቶች የማምሻ ዕድሜያቸውን ተረጋግተው እንዳያጣጥሙ፣ ወዘተ የሚያደርግ የሰላም መቃወስ በተደጋጋሚ ሲያጋጥም የበርካታ ሚሊዮኖች ተስፋ ይጨፈግጋል፡፡ በተደጋጋሚ ለማስታወስ እንደተሞከረው ኢትዮጵያ አብዛኛው የታሪኳ ክፍል የጦርነት በመሆኑ ያተረፈችው መራር ድህነት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በተፈጥሮ ፀጋዎች የታደለች አገር ምንም ሳይጎድልባት የድህነት መፈንጫ የሆነችው ሰላም በመጥፋቱ ነው፡፡ የቅርቡ የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት ካደረሰው መጠነ ሰፊ ጥፋት ያላገገመች አገር፣ እንደገና ተመልሳ እዚያው የቀውስ አዙሪት ውስጥ ስትገባ ካላስደነገጠ ምን ሊያስደነግጥ ነው? ችግሮች ሲያጋጥሙ በሰከነ መንገድ የሚያነጋግር መድረክ ማመቻቸት እየተቻለ፣ እርስ በርስ የሚያፋጅ ጦርነት ውስጥ ገብቶ አገር ማውደም ያሳቅቃል፡፡

ስለሰላም ጥያቄ ሲነሳ የመገፋትና የመብት ጉዳይ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ይህ ጉዳይ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገውም ነው፡፡ ለዚህም ሲባል ከማንም በላይ አገር የሚያስተዳድረው ገዥ ፓርቲም ሆነ መንግሥት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያ መብቶች እንዲከበሩ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍንና ከሕግ ተቃራኒ የሆኑ ማናቸውም ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ዜጎች ቅሬታ ተሰምቷቸው አቤቱታ ሲያቀርቡ በሕጉ መሠረት መደመጥ አለባቸው፡፡ ከዚያ አልፈው በመንግሥት ላይም ሆነ በሌላ አካል ላይ ክስ ሲመሠርቱ ፍትሕ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ሕጋዊና ሰላማዊ ጥያቄ የሚያቀርቡ ዜጎችን በሥርዓት ማስተናገድ የግድ መሆን አለበት፡፡ ጥያቄም ሆነ አቤቱታ ያላቸው ወገኖች ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ መከተል ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ሥልጡን አሠራር መመራት ባለመቻሉ ነው አገርም ሆነች ሕዝብ አሳራቸውን የሚያዩት፡፡ አንድ ችግር ሲያጋጥም ሰላማዊ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ የኃይል አማራጭ ውስጥ ሲገባ፣ የአገር ሰላም ተናግቶ ዕልቂትና ውድመት የዘወትር ተግባር ይሆናል፡፡ ዘለቄታዊ ሰላም እንዲሰፍን ለሕግ የበላይነት ቅድሚያ መስጠት ይገባል፡፡

ሰኞ ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ ሲሰበሰቡ፣ አገር እየገባችበት ያለውን መከራና ሥቃይ ከግምት ውስጥ በማስገባት ኃላፊነታቸውን ይወጡ፡፡ አገር ከፓርቲ ወይም ከስብስብ በላይ መሆኗን በመገንዘብ ዘለቄታዊ ሰላም የሚያመጡ አማራጮች ላይ ይነጋገሩ፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የጠመንጃ ልሳን የሚዘጋባቸው የመፍትሔ ሐሳቦች የሚፈልቅባቸው የምክክር መድረኮ በስፋት እንዲኖሩ ዕገዛ ያድርጉ፡፡ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ኃላፊነት በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ እንዲያከናውን፣ ሕግ አውጭው ምክር ቤት የተቆጣጣሪነት ሚናውን እንዲወጣ፣ እንዲሁም ሕግ ተርጓሚው አካል በነፃነት እንዲሠራ የቁጥጥርና የሚዛናዊነት አሠራር ይከበር፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረታዊ መብቶች ቢገደቡም አፈጻጸሙ በጠንካራ ቁጥጥር መመራት ይኖርበታል፡፡ በዚህ መሠረት ኃላፊነትን መወጣት ሲቻልና የጉልበት አማራጭ ሲቀንስ ለሰላም ጥርጊያው ይመቻቻል፣ መተማማን ይፈጠራል፡፡ ዘለቄታዊ ሰላም የሚሰፍነውም በንግግርና በድርድር ብቻ ነው!