የአሜሪካ የድሮን ጥቃትና የአልሸባብ ህልውና
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ፔንታጎን በአልሸባብ ላይ ባለፈው ሰኞ የፈጸመው ጥቃት የአሸባሪ ቡድኑን መሪ አህመድ አብዲ ጎዳኔን ሳይገድል እንዳልቀረ ሪፖርቶች እያመለከቱ ነው፡፡
አልሸባብ የእኔ ነው በሚለው ትዊተር ገጽ መሪው መሞቱን አስታውቋል፡፡ ነሐሴ 27 ቀን 2006 ዓ.ም. በጉዳዩ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው ፔንታጎን የአየር ጥቃት የፈጸመው፣ የደኅንነት መረጃዎች የአልሸባብ መሪዎች ስብሰባ የሚያደርጉበትን ቦታ ከጠቆሙ በኋላ እንደነበርም አስታውቋል፡፡
ጥቃቱ የተፈጸመው በታችኛው የሸበሌ ክልል ሲሆን፣ በአካባቢው የሚገኘው ባራዌ ከተማ ባለፈው ጥቅምት ወር አልሸባብን ለማጥፋት የተደረገው ‘ናቪ ሲል’ የተሰኘውና የከሸፈው ዘመቻ የተካሄደበት ሥፍራ ነው፡፡ የታችኛው ሸበሌ አስተዳዳሪ አብዱቃድር መሐመድ ኑርሲዲ፣ በጥቃቱ ጎዳኔን ጨምሮ የአልሸባብ አመራሮች እንደተገደሉ የሚያሳዩ ሪፖርቶች እንደደረሷቸው አስታውቀዋል፡፡
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ግን የጎዳኔን መሞት ባለፈው ዓርብ ምሽት አረጋግጧል፡፡ የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ጆን ኪርቢ አሜሪካ በሰው አልባ እንዲሁም ሰው የያዙ አውሮፕላኖች በመታገዝ ‘ሄል ፋየር’ የተሰኙ ሚሳይሎችና በጨረር የሚመራ ቦምብ በመጣል የአልቃይዳ መሪዎች የነበሩበትን መኪና ማውደሟን አረጋግጠዋል፡፡ ጥቃቱ በደኅንነት መረጃው መሠረት ያነጣጠረበት ቦታ ላይ በማረፍ በአካባቢውና በተሽከርካሪው ላይ ጉዳት ቢያደርስም፣ ቃል አቀባዩ የአልሸባብ መሪ ስለመገደሉ ግን እርግጠኛ ሆነው ከመናገር ተቆጥበው ነበር፡፡ ዘመቻው ሲፈጸም አንድም አሜሪካዊ በአካባቢው በመሬት ላይ እንዳልነበርም አመልክተዋል፡፡
ጎዳኔ የአልሸባብ መሪነትን በ1999 ዓ.ም. ከተረከበ በኋላ በሌሎች የአልሸባብ አባላትና በውጭ ኃይሎች ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ ተደርጎበት ማምለጡን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የሶማሊያ የደኅንነት ባለሥልጣን የሆኑት ሞሐመድ ፋራህ፣ ጎዳኔ በወቅቱ በአካባቢው እንደነበረ ማረጋገጫ ማግኘታቸውን ተናግረው፣ በጥቃቱ በወደመው ተሽከርካሪ ውስጥ ስለመኖሩ ግን አጠራጣሪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የአልሸባብ ቃል አቀባይ ሞሐመድ አቡ የሱፍ በበኩሉ፣ ጎዳኔ በወቅቱ በአካባቢው እንደነበረ ገልጾ፣ በጥቃቱ ሕይወቱ ስለማለፉ ግን ከመናገር ተቆጥቧል፡፡
አሜሪካ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ በየመንና በፓኪስታን የአልቃይዳ መሪዎችን ለመግደል ድሮኖች (ሰው አልባ አውሮፕላኖች) ተጠቅማ መሞታቸው ሪፖርት ከተደረገ በኋላ፣ መሪዎቹ በሕይወት መኖራቸው በኋላ መረጋገጡን ተከትሎ፣ ተመሳሳይ ሪፖርቶችን ላለማቅረብ እየተጠነቀቀች መሆኗን የደኅንነት ኤክስፐርቶች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ አሜሪካ በጥቃቱ ጎዳኔ መሞታቸውን ብታምንም ማረጋገጫ መስጠት ያልፈለገችው ያለፉትን ስህተቶች ላለመድገም እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ነገር ግን ዘግይቶ መገደላቸውን ማረጋገጫ ሰጥታለች፡፡
ጥቃቱን አስመልክተው እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች ግን የጎዳኔን መሞት አመላካች ናቸው ያሏቸውን ዝርዝር ሁኔታዎች አካተዋል፡፡ የዓይን እማኞች ከጥቃቱ በኋላ የአልሸባብ ወታደሮች በአካባቢው ሰዎች ላይ አሰቃቂ ግድያዎችን መፈጸማቸውን በተለይም ተንቀሳቃሽ ስልክ የነበራቸው ሰዎች በሰላይነት ተፈርጀው አንገታቸው መቀላቱ የአልሸባብ መሪ ለመገደሉ አመላካች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ንቁ ተሳታፊ የነበረው አልሸባብ ከጥቃቱ በኋላ የራሴ ነው በሚለው በትዊተር መሪው መሞቱን ከመግለጽ ባለፈ ዝምታን መምረጡም፣ ሌላ መሪ እስኪመርጥ ድረስ ፋታ እየወሰደ መሆኑን አመላካች ነው በማለት የጎዳኔን መሞት ጠቋሚ መሆኑን ተንታኞች አስረድተዋል፡፡
የጎዳኔ መገደል ቢረጋገጥ ከአልቃይዳ ጋር በትብብር የሚሠራው አልሸባብ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል? በቀላሉ ተሰባሪ የሆነው የሶማሊያ መንግሥትስ አገሪቱን ከጦርነት አውጥቶ የተረጋጋች ለማድረግ የአልሸባብ አመራር ለውጥ ምን ያህል ይረዳዋል? ኢትዮጵያን ጨምሮ የጎረቤት አገሮችና የአፍሪካ ኅብረትስ ሚና ምን ሊሆን ይችላል? የአሜሪካ ጣልቃ ገብነትስ በአፍሪካ ኅብረት ኃይሎች ተስፋ በመቁረጥ የመጣ ወይስ በትብብር የተፈጸመ? የሚሉት ጥያቄዎች ግን ጥቃቱን ተከትሎ እየተብላሉ ይገኛሉ፡፡
መሪውን ያጣው አልሸባብ ይለወጣል?
በበርካታ መሥፈርቶች ጎዳኔ ለየት ያለና በቀላሉ የሚተካ መሪ እንዳልሆነ የሚገልጹ የደኅንነት ተንታኞች፣ መሞቱ እርግጥ ከሆነ መልካም ዕድል የማምጣቱን ያህል ያልተጠበቁ አዳዲስ አደጋዎች ሊጋርጥ ስለመቻሉም ያመለክታሉ፡፡ በተለይ የሥልጣን ሽኩቻን መሠረት አድርጎ ጎዳኔ የፈጸማቸው ግድያዎች አልሸባብን ከፋፍለውት እንደነበር የጠቆሙ ሪፖርቶች፣ የሰውየው ሞት ዳግም የተባበረና ጠንካራ ቡድን ሊፈጥር የመቻሉን አደጋ አጉልተው ያሳያሉ፡፡
በሌላ በኩል ተፃራሪ አመለካከት ያላቸውን ሁሉ ወይ በመግደል አልያም ከቡድኑ እንዲርቁ በማድረግ ጎዳኔ ከነበረው ቁልፍ ሚና አንፃር መሞቱ ቡድኑን በማዳከም በአፍሪካ ኅብረትና በአሜሪካ እየደረሰበት ካለው ጥቃት ጋር ተዳምሮ መልካም አጋጣሚን ለአካባቢውና ለሶማሊያ ሊያበረክት እንደሚችልም ተስፋቸውን እየገለጹ ያሉ ኤክስፐርቶች አሉ፡፡
የጎዳኔ ጽንፍ የያዘ አክራሪነትን ከግምት ውስጥ በማስገባት ደጋፊዎቹ መረጃ ሰጥተዋል በማለት የጀመሩት የበቀል ዕርምጃ ደግሞ፣ የሰውየው መገደል የተሻለ ጊዜን ሳይሆን የሚፈራ ጊዜ ሊያመጣ እንደሚችል በማመልከት ሥጋታቸውን የሚገልጹም አልታጡም፡፡
የሶማሊያ መንግሥት ከፍተኛ የፀረ ሽብር አማካሪ የሆኑት ሁሴን መሐሙድ ሼክ አሊ፣ ጎዳኔ ትልቅ ዕቅድ የነበረውና ከአልቃይዳ ቁልፍ መሪዎች መካከል አንዱ አድርጎ ራሱን የሚያስቀምጥ መሪ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ ባለፉት ሰባት ዓመታት ጎዳኔ የሽብር ቡድኑ ቀጣይ መሪዎች ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችን በመግደል ቡድኑን የአንድ ሰው ቡድን በማድረጉ እሱን ለመተካት አዳጋች እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
የጎዳኔ ሞት ለአልሸባብ ህልውና መጠናከርም ሆነ መዳከም የሚኖረው ተፅዕኖ ወደፊት የሚታይ ቢሆንም፣ የሽብር ቡድኑን አካሄድ የሚቀይር መሆኑ ግን የሚያጠራጥር አይመስልም፡፡ የአልሸባብን ዓላማ ከሃይማኖታዊ ርዕዮተ ዓለም ጋር አቀናጅተው የሚደግፉ አካላት ጎዳኔን ማጣታቸው ትልቅ ጉዳት ቢሆንባቸውም፣ አልሸባብ ለሶማሊያውያን መብትና ነፃነት ብቻ መታገል ካለበት ከሶማሊያ ግዛት መውጣት እንደሌለበትና ሶማሊያዊ ያልሆኑ ታጣቂዎችን ሊያስወግድ ይገባል ብለው ለሚያስቡ ግን፣ የጎዳኔ መሞት ትልቅ እፎይታ የሚሰጣቸውና አንፃራዊ መረጋጋትን በአካባቢው የሚያመጣ ስለመሆኑም ትንተናዎች እየቀረቡ ናቸው፡፡
ከሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ በስተደቡብ በኩል የሚገኘው የታችኛው ሸበሌ ክልል ነዋሪ የሆኑት አዛውንቱ ሁሴን ቢሂ ግን አልሸባብ መሪውን ቢያጣ ለጊዜው የአመራር ቀውስ ቢገጥመው እንጂ፣ መልሶ ማንሰራራቱ እንደማይቀር ይናገራሉ፡፡ የሽብር ቡድኑ የያዘው የርዕዮተ ዓለም መሠረት የአንድ ግለሰብ ሞት የድርጅቱን ህልውና እንዳይገዳደር ማድረጉንም ይጠቅሳሉ፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ኃይሎችና የሶማሊያ መንግሥት ተደጋጋሚ ወታደራዊ ጥቃቶች አልሸባብን አጠፉት ሲባል መልሶ የሚያንሰራራውም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ጎዳኔ ተቀናቃኞቹን ከመግደልም ባሻገር እሱን ራሱን ወደ ሥልጣን እንዲመጣ የመረጠውን የአገር ሽማግሌዎች ምክር ቤትን (ሹራ ካውንስል) እንዲፈርስ በማድረጉ፣ አሁን ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር አዳጋች እንዲሆን በማድረጉም ይተቻል፡፡ በአሜሪካ ጥቃት ሕይወታቸው ያለፉት ስድስት የአመራር አባላትም እንደ ጎዳኔ ባይሆንም ትልቅ ክፍተት እንደሚፈጥሩ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ ቀጣዩ መሪ ማንም ሆነ ማን የአልሸባብን የሽብር እንቅስቃሴ ወሰን በሶማሊያ መገደብ ወይም ዓለም አቀፋዊነቱን ማጠናከር የመጀመሪያ ምርጫው እንደሚሆንም ተንታኞች ገምተዋል፡፡
የሶማሊያ መንግሥት የምሕረት ጥሪ
ባለፈው ረቡዕ አስቸኳይ ስብሰባ ያደረገው የሶማሊያ መንግሥት ካቢኔ የአሜሪካ ጥቃትን ተከትሎ ግራ ተጋብቶ ያለውን አልሸባብን ይበልጥ ለማዳከም፣ የአልሸባብ ታጣቂዎች በ45 ቀናት ውስጥ በበጎ ፈቃዳቸው እጃቸውን ከሰጡ ምሕረት እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ የሶማሊያ የደኅንነት ሚኒስቴር ካሊፍ አህመድ ኢሬግ ራሳቸውን አሳልፈው ለሚሰጡ የአልሸባብ ታጣቂዎች የተሻለ ኑሮ እንደሚመቻች ገልጸዋል፡፡
መሪያቸውን እንዳጡ ከሚነገርላቸው ታጣቂዎች መካከል የምሕረት ጥሪውን የሚቀበሉት ቁጥር ቀላል እንደማይሆን የደኅንነት ተንታኞች ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን የምሕረት ጥሪው ዝርዝር ጉዳዮችን ያልያዘና ግልጽነት የሚጎድለው እንደሆነ በማንሳት ኤክስፐርቶቹ ተችተዋል፡፡ የምሕረት ጥሪው የተሟላ ዝርዝር ጉዳይ ያቀፈና ለአፈጻጸም የተመቸ በማድረግ፣ ታጣቂዎቹን ለማማለል የሶማሊያ መንግሥት የተገኘውን መልካም አጋጣሚ ይጠቀምበት ዘንድም ጥሪ አድርገዋል፡፡
ዓለም አቀፋዊ ሥጋት
ሶማሊያ ውስጥ ተፈጥሮ አነሳሱ ሶማሊያን መሠረት ያደረገው አልሸባብ ከሶማሊያ ድንበር ተሻግሮ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን ለማሸበር የቻለ ዓለም አቀፍ ሥጋት የፈጠረ የሽብር ቡድን ነው፡፡ በኬንያና በኡጋንዳ ከፈጸመው አሰቃቂ ጥቃት ባሻገር የመን ውስጥም ከአልቃይዳ ጋር በመተባበር ይንቀሳቀሳል፡፡ አልሸባብ በየካቲት 2004 ዓ.ም. ከአልቃይዳ ጋር በትብብር እንደሚሠራ ያስተዋወቀው መሪው ጎዳኔ ከአልቃይዳው አቻው አይማን አልዛዋህሪ ጋር በመሆን በለቀቁት የቪዲዮ መልዕክት ነበር፡፡
የሽብር ቡድኑ ከአልቃይዳ ጋር እንደሚሠራ ካስታወቀ በኋላ የሚፈጽማቸው ጥቃቶች ዓለም አቀፋዊ ትኩረት አግኝተዋል፡፡ በሶማሊያ የዕርዳታ ሠራተኞችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ሲቪል ነዋሪዎችንና የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይሎችን መግደል የሽብር ቡድኑ የሚታወቅበት ተግባር ሲሆን፣ በሌሎች ጎረቤት አገሮች የሚፈጽመው ጥቃት ግን የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት እንዲስብ አስገድዷል፡፡ በሐምሌ 2002 ዓ.ም. የአልሸባብ አጥፍቶ ጠፊዎች በፈጸሙት የፈንጂ ጥቃት ካምፓላ ኡጋንዳ ውስጥ አንድ አሜሪካዊን ጨምሮ የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታን እየተከታተሉ የነበሩ የ70 ሰዎችን ሕይወት አጥፍቷል፡፡ እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት ደግሞ በኬንያ የዌስትጌት የገበያ ማዕከል አልሸባብ ያደረሰው ጥቃት የ67 ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ይታወሳል፡፡ የአልሸባብ ሶማሊያን አክራሪ እስላማዊ አገር የማድረግ ዕቅድ እዚያ የሚቆም አለመሆኑም ሌላ ዓለም አቀፋዊ ሥጋት ፈጥሯል፡፡
የአሜሪካ ልዩ ፍላጎት
አሜሪካ የዓለምን ሰላም የሚያደፈርስን የሽብር ኃይል የመታገል ፍላጎቷ ከተቀረው የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በምን ይለያል ሲሉ የሚጠይቁ በርካቶች ናቸው፡፡ ባለፈው ሰኞ የወሰደችው የድሮን ጥቃትም ከምን ልዩ ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ ጥያቄ አጭሯል፡፡
የፔንታጎን ቃል አቀባይ አድሚራል ኪርቢ አሜሪካ የአፍሪካ ቀንድን የሚያሸብሩ ቡድኖችን ለመለየት፣ ለመቅጣት፣ ለመረበሽና ለማጥፋት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ጥቃት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ቃል አቀባዩ አልሸባብንና ሌሎች አሸባሪ ቡድኖችን ለማፈራረስ አሜሪካ በእጇ ላይ የሚገኙ የገንዘብ፣ የዲፕሎማሲ፣ የመረጃና ወታደራዊ ኃይሏን እንደምትጠቀም ገልጸዋል፡፡
አልሸባብ ለአሜሪካ ቀጥተኛ ሥጋት አይፈጥርም ሲሉ የሚከራከሩ አሜሪካዊ የደኅንነት ኤክስፐርቶች በርካቶች ናቸው፡፡ የፔንታጎኑ ቃል አቀባይ ግን የሽብር ቡድኑ ከሶማሊያ የዘለለ ሰፊ አካባቢያዊ ሥጋት መፍጠሩና በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ የአሜሪካ ዜጎችን ዒላማ ማድረጉም፣ አልሸባብ ለአሜሪካ ቀጥተኛ ሥጋት እንዲሆን ማድረጉን አስረድተዋል፡፡
አሜሪካ የአልሸባብ አመራርን ለማጥፋት ያለሙ በርካታ የሚሳይል ጥቃቶችን ከዚህ ቀደምም ፈጽማለች፡፡ ባለፈው ጥር ወር አህመድ አብዱቃድር የተባለ የሶማሊያ ዜጋና የውጭ ዜግነት ያላቸው ታጋዮችን የሚመለምል የአልሸባብ አባልን በሚሳይል ጥቃት መግደሏም ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይ በጥቅምት ወር የአልሸባብ አመራር አባል የሆነውን አብዱቃድር ሞሐመድ ላይ ያነጣጠረ የሚሳይል ጥቃት ሰንዝራ ነበር፡፡
በሶማሊያ የአሜሪካ ሰው አልባ የስለላ አውሮፕላኖች መሰማራታቸው የተለመደ ሲሆን፣ የአየር ጥቃት መሰንዘር ግን ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡ እ.ኤ.አ. በ1993 18 የአሜሪካ ወታደሮች ‹‹ብላክ ሀውክ ዳውን›› በተሰኘው ዘመቻ ሕይወታቸው ከጠፋ በኋላ፣ የአሜሪካ ወታደሮችን በቀጥታ በሶማሊያ ጉዳይ ማሳተፍ የሚበረታታ ባይሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አልሸባብን ለማጥፋት የአፍሪካ ኅብረት እያደረገ ያለው ጥረት በአሜሪካ ወታደሮች እየታገዘ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
አሜሪካ በሶማሊያ ያላት ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ነው፡፡ ወታደሮቿ በይፋም ሆነ በሚስጥር በተለያዩ ዘመቻዎች እንደሚሳተፉም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የሶማሊያ የደኅንነት መሥሪያ ቤትም በአሜሪካ የስለላ ድርጅት ሲአይኤ የሚታገዝ እንደሆነ ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ በሶማሊያ የሚገኙ የአፍሪካ ኅብረት ኃይሎችም በገንዘብ የሚታገዙትና ሥልጠና የሚያገኙት በአሜሪካ እንደሆነ ዘገባዎች አትተዋል፡፡
አልሸባብ በአሜሪካ በሽብርተኝነት የተፈረጀው በመጋቢት ወር 2000 ዓ.ም. ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ደግሞ ለሶማሊያ መንግሥት አሜሪካ ዕውቅና ሰጥታለች፡፡ አሜሪካ ከጎዳኔ በፊት የነበረውን የአልሸባብ መሪ አደን ሃሺ አይሬን በ2000 ዓ.ም. በተመሳሳይ ሁኔታ ገድላዋለች፡፡ የአሁኑ ለየት የሚያደርገው የሶማሊያ መንግሥት የተሻለ ጥንካሬ በያዘበት ወቅት የተደረገ መሆኑ ነው፡፡
‹‹ኦፕሬሽን ኢንዲያን ኦሽን››
ከ22 ሺሕ በሚበልጡ ወታደሮች የተዋቀረው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል በመካከለኛውና በደቡብ ሶማሊያ ከሶማሊያ ብሔራዊ ጦር ጋር በመተባበር አልሸባብን ለማጥፋት ያለመ ‹‹ኦፕሬሽን ኢንዲያን ኦሽን›› የተሰኘ ዘመቻ ከከፈተ ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡
ዘመቻው ከሌሎች መሰል ዘመቻዎች የሚለየው በአሜሪካ ልዩ ኃይሎች የሚታገዝና የአየር ቅኝትና የሚስጥራዊ መረጃ እንዲሁም ወሳኝ የሆኑ የሰውና የቁስ ኃይሎች የተሟሉለት በመሆኑ ነው፡፡ የአልሸባብ መቀመጫዎች ናቸው የተባሉ ትናንሽ መንደሮች ሳይቀሩ በተቀናጀው ጦር ከአልሸባብ ይዞታነት እየተነጠቁ ለመሆናቸው ሪፖርቶች እየወጡ ነው፡፡ የአልሸባብ የመጨረሻ ወሳኝ ይዞታ ባራዌን ለመቆጣጠርም ያለመ ዘመቻ ነው፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ዒላማና ዓላሚ
አልሸባብ ከአፈጣጠሩ መነሻ ከኢትዮጵያ ጋር ልዩ ግንኙነት አለው፡፡ እስካሁን ባይሳካለትም ኢትዮጵያን ለማጥቃት ያለውን ዕቅድ በተደጋጋሚ በመግለጽ ከቀደምት ዒላማዎቹ አንዱ አድርጎ ያስቀምጣታል፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ በሶማሊያ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ ስትሆን፣ በ1998 ዓ.ም. ያጠፋችውን የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትን ተክቶ በሶማሊያና በአካባቢው ሽብር እየነዛ የሚገኘውን ቡድን ለማጥፋት የተደረጉ ዘመቻዎችን ሁሉ በመሪነትና በተሳታፊነት ተቀላቅላለች፡፡
ከአሜሪካ ጋርም በትብብር ሽብርን ለመዋጋት ትሠራለች፡፡ ዘግይታም ቢሆን የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይሉን የተቀላቀለች በመሆኑ፣ የአሁኑ የአሜሪካ የአየር ጥቃት አፈጻጸም ላይ አብራ መሥራቷን የሚጠቅሱ ሪፖርቶችም አሉ፡፡ በተለይ አሜሪካ የሰው አልባ አውሮፕላኖች መጠቀሚያ የገነባች መሆኗን በመጥቀስ የአሜሪካ አጋር መሆኗን የሚያመለክቱ ተንታኞች፣ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ፖሊሲ በኢትዮጵያ አማካይነት የሚፈጸም መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
አልሸባብ ባለፈው ሳምንት በሞቃዲሾ በሚገኝ እስር ቤት ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ በተጠናከረ ሁኔታ የሽብር ቡድኑን ለማጥፋት የአፍሪካ ኅብረት፣ የሶማሊያ ጦርና አሜሪካ የተቀናጀ ጥቃት በመፈጸም መጠመዳቸው ተገልጿል፡፡ የቡድኑ መሪዎች ላይ ከተከሰተው የሞት አደጋ ጋር ተዳምሮ የአልሸባብ ህልውና መጨረሻ ሊሆን ይችላል በሚል ብዙዎች ተስፋ አድርገዋል፡፡ ነገር ግን በ2003 ዓ.ም. በአሜሪካ ዕርዳታ ከወሳኝ ግዛቱ ኪስማዩ በተወገደ ጊዜ አልሸባብ አበቃለት ቢባልም አንሰራርቶ በመመለስ በአካባቢው ሽብር መልቀቁን ቀጥሎበታል፡፡
አልሸባብ ከኢትዮጵያ፣ አሜሪካና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ኃይሎች ጋር በሚያደርገው ትንቅንቅ የሶማሊያ ዜጎች በገዛ አገራቸው ለአሰቃቂ አደጋ መጋለጣቸው አለመለወጡ እየተገለጸ ይገኛል፡፡ ባለፈው ሳምንት የወጣው የተመድ ግምገማ በሶማሊያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለረሃብ መጋለጣቸውን ይጠቁማል፡፡ አልሸባብን ማጥፋት ለሶማሊያውያንና ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን የኑሮ ሁኔታን የመለወጥ አቅም ካለው፣ በዚህ መሰል ዘመቻ ሌሎች ኃይሎችም አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ እየቀረበ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ግን ከወታደራዊ ጥቃት ባሻገር የአልሸባብን ርዕዮተ ዓለማዊ መሠረት ለማጥፋት ዜጎችን በማሳመን ለአልሸባብ የድጋፍ መሠረቱን ማጥፋት ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ውጤት እያስመዘገበ ከመጣ አልሸባብ ለጊዜውም ቢሆን በዜጎች ላይ አሰቃቂ ጥቃት መፈጸሙ የማይቀር ቢሆንም፣ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠቱ ግን ብዙዎች አይጠራጠሩም፡፡
