August 14, 2023 – EthiopianReporter.com 

“በኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ከወንድ እኩዮቻቸው ሲነፃፀሩ በሦስት እጥፍ ሥራ፣ ትምህርትና ሥልጠና አላገኙም፡፡” ጥናት

አፍሪካ ውስጥ ከ72 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ወጣቶች የመማር፣ ሥልጠና የማግኘትና የመቀጠር ዕድል እንዳላገኙ ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት አስታውቋል፡፡ ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ ወጣት ሴቶች መሆናቸውን ነው ያመለከተው።

የዓለም ሥራ ድርጅት (አይኤልኦ) ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች በሚገኙት ሰባት አገሮች ማለትም ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ሴኔጋልና ዑጋንዳ ውስጥ ባካሄደው ጥናት አካሂዷል።

በዚህም ጥናት ላይ እንደተመላከተው በአፍሪካ ከአራት ሰዎች መካከል አንዱ የመማር፣ የመሠልጠንና የመሥራት ዕድል ተነፍጓል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሁለት ሦስተኛው ወጣት ሴቶች ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2005 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን የቅጥር፣ የመማር ወይም ሥልጠና የማግኘት ዕድል አሽቆልቁሏል፡፡ ይህ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች በ2.8 በመቶ የጨመረ ሲሆን፣ በቀጣናው አንድ አራተኛ ወጣቶች አልተቀጠሩም ወይም ትምህርትም ሆነ ሥልጠና አላገኙም፡፡

በጥናቱ በተካተቱ ሰባት አገሮች ከ15 እስከ 29 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣት ሴቶች፣ በተመሳሳይ ዕድሜ ከሚገኙ ወንዶች ጋር ሲነፃፀሩ ከፍተኛ ያለመቀጠር፣ ያለመማርና ሥልጠና ያለማግኘት ሁኔታን አስመዝግበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ከወንድ እኩዮቻቸው ሲነፃፀሩ በሦስት እጥፍ ሥራ፣ ትምህርትና ሥልጠና አላገኙም፡፡ በናይጄሪያ፣ ሴኔጋልና ኡጋንዳ በሁለት እጥፍ ልዩነት ሲኖር፣ ባልተመጣጠነ መልኩ ሴቶች የቤት ውስጥ ሥራን ተሸክመው ይኖራሉ፡፡

ጥናቱ በተካሄደባቸው በሰባቱም አገሮች ከ25 እስከ 29 ዕድሜ ክልል በሚገኙ ወጣቶች፣ መሠረታዊ ትምህርት የተማሩት በከፍተኛ ደረጃ ከተማሩት ልቀው ተገኝተዋል፡፡ በአገሮቹ ወጣት ሴቶች ከወንዶች በትምህርት፣ በሥልጠናና በሥራ ዘርፍ ዝቅ ብለው ይገኛሉ፡፡

አገሮች በዘላቂ የልማት ግብ በተራ ቁጥር ስምንት ላይ ሥራን ለሁሉም ወጣቶች ተደራሽ ለማድረግ የተቀመጠውን አጀንዳ ለማሳካት፣ ፆታዊ አድልኦና መገለልን ከወዲሁ መዋጋትና ማስቀረት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁሟል፡፡

ምንጭ: ሪፖርተር