የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዛሬ የአማራ ክልል ግጭትን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ተፋላሚ ወገኖች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ፣ ለውይይት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር እና ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንዲስማሙ ጥሪ አቅርቧል።
በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች እና የከተሞች ዙሪያ ከባድ ውጊያ እንደነበረ አረጋግጫለሁ ያለው ኢሰመኮ፤ በከባድ መሳሪያዎች ሰላማዊ ሰዎች ላይ ሞትና የአካል ጉዳት እንዲሁም የንብረት ውድመት ደርሷል ብሏል።
በግጭቱ ሳቢያ በክልሉ የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች ተሰባብረዋል፣ መሳሪያ እና ጥይቶች ተዘርፈዋል፣ ያለፍርድ የታሰሩ እና ፍርደኛ እስረኞችም ያመለጡ ሲሆን የተለያዩ የአማራ ክልል ባለስልጣናት የጥቃት ኢላማ ሆነዋል ሲልም አስታውቋል። በዚህም ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ጊዜያዊ የመንግሥታዊ መዋቅር መፍረስ እና የመንግስት ባለስልጣናት ግድያ መከሰቱን ኮሚሽኑ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከደብረ ብርሃን፣ ፍኖተ ሰላም እና ቡሬ ጨምሮ በርካታ ንፁሀን ዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱን እንዲሁም በመኖሪያ አካባቢዎች እና በህዝባዊ ቦታዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የሚገልጹ ተዓማኒነት ያላቸው ሪፖርቶችም ደርሰውኛል ብሏል።
የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ተፋላሚ ወገኖች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ህግ ጥሰቶችን እንዲሁም ግጭቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ፣ የፌደራል መንግስት በስፋት የሚስተዋለውን እስር በማቆም ኢሰመኮ እና ሌሎች የቁጥጥር አካላትን ማረሚያና ማቆያ ተቋማትን መደበኛ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲመለከቱ እንዲፈቅድ እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ)፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አለም አቀፍ ማህበረሰብ እና ተልእኮዎች በተፋላሚዎች መካከል የሚደረጉ ውይይቶችን እንዲደግፉ እና እንዲያመቻቹ ጠይቋል።