የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

16 ነሐሴ 2023, 15:39 EAT

በአማራ ክልል በመከላከያ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ በንግግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ከፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ጌዴዮን ጢሞቲዮስ ጋር በመሆን መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ትናንት ማክሰኞ ነሐሴ 09/2015 ዓ.ም ባደረጉት ገለጻ ነው።

በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎችን አስመልክቶ ከፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ጌዴዮን ጢሞቲዮስ ጋር በመሆን ማብራሪያ የሰጡት አቶ ደመቀ፣ ለግጭቱ ሰላማዊ እልባት ለማግኘት ተጀምሯል ስለተባለው ጥረት ዝርዝር መረጃ ስለመስጠታቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያለው ነገር የለም።

የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን በበኩላቸው ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሄ በንግግር ለማምጣት እንዲሁም ሁኔታዎችን ወደ ቀደመው መልካቸው ለመመለስ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት በሰላም መቋጨት ይቻል ዘንድ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ፣ የአገሪቱ የተለያዩ የእምነት ተቋማት እና ግለሰቦች ጥሪ እያደረጉ ይገኛሉ።

አቶ ደመቀ መኮንን የሽግግር ፍትህ እና ብሔራዊ የምክክር ሂደቶችን ጨምሮ በአገሪቱ ሰላምን የማጠናከር ሥራ እየተሠራም እንደሆነም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአማራ ክልል ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም በጠየቀበት መግለጫው በክልሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም የተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መንግሥታዊ መዋቅሮች መፍረሳቸውን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በአማራ ክልል ከተሞች እና በከተሞች ዙሪያ ግጭቶች መከናወናቸውን አረጋግጫለሁ ያለ ሲሆን፣ በእነዚህ ግጭቶች ከባድ የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን፣ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት የንጹሃን ሕይወት መጥፋቱን፣ ንብረት መውደሙን እና ዘረፋ መፈጸሙን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ እንዲሁ ባለፈው ሳምንት አስታውቋል።

በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ለቀናት በዘለቀው ግጭት በአማራ ክልል ከተሞች እና የተለያዩ አካባቢዎች እስካሁን በውል ያልታወቁ ሰዎች መሞታቸውን ቢቢሲ የሆስፒታል ምንጮችን በመጥቀስ መዘገቡ ይታወሳል።

በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት መባባስ ተከትሎ በክልሉ በዋነኝነት እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች እንደ አስፈላጊነቱ ተፈጻሚ እየሆነ ስላለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም አስፈላጊነትን በተመለከተ አቶ ደመቀ ለውጭ ዲፕሎማቶቸ አስረድተዋል።

አቶ ደመቀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስፈለገው ችግር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ሕግ እና ሥርዓትን ወደነበረበት መመለስ በማስፈለጉ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዶ/ር ጌዲዮን በበኩላቸው የአማራ ክልልን ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ በጥልቀት እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስፈላጊነት በተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል።

በተጨማሪም መንግሥት ሕግ እና ሥርዓትን ወደቀደመ ሁኔታ ለመመለስ እንዲሁም ሰላማዊ ዜጎችን ለመጠበቅ እያደረገ ስላለው ጥረትም ማስረዳታቸው ሰፍሯል።

“የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” አርብ ሐምሌ 28/ 2015 ዓ.ም. የተደነገገ ሲሆን የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ሕግ እና ሥርዓት ለማስከበር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ከተማ እና በዙሪያዋ በሚገኙ አካባቢዎች የጅምላ እስሮች እየተፈጸሙ እንደሆነ እና እነዚህም እስሮች አብዛኛዎቹ የሕግ ሥርዓትን ያልተከተሉ ተጠርጣሪዎችም ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ነሐሴ 08/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

በአማራ ክልል የተፈጠረውን “ግጭት ለማባባስ የከተማ ውስጥ ግዳጅ በመውሰድ የሎጅስቲክስ እና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ የተለያዩ ሕገወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙ ነበር” ያላቸውን 23 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መምሪያ ዕዙ ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ ይታወሳል።

ባለፈው ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎች ፈርሰው ወደ ተለያዩ የፀጥታ እና የመከላከያ መዋቅሮች እንዲገቡ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በአማራ ክልል የተከሰተው ተቃውሞ እየተጠናከረ ሄዶ፣ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭቶች እና የተኩስ ልውውጦች ሲካሄዱ ቆይተዋል።

በአማራ ክልል ያሉ ከተሞችን ከፋኖ ታጣቂዎች ነጻ ማድረጉን መንግሥት ከሰሞኑ ማስታወቁንም ተከተሎ በአንዳንድ አካባቢዎች አንጻራዊ መረጋጋት መታየቱም ተዘግቧል።

በበርካታ የአማራ ክልል ውስጥ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ግጭት ከዋና ዋና ከተሞች በመውጣት በሌሎች አካባቢዎች እየተካሄደ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ፍኖተ ሰላም ከተማ ላይ ነሐሴ 07/2015 ዓ.ም. በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 26 ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ50 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች እና የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥቃቶቹን በተመለከተ አንዳንዶች የደረሰው በከባድ መሳሪያ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) የተፈጸመ መሆኑንም ነው ለቢበሲ የገለጹት።

ኢሰመጉ በበኩሉ በፍኖተ ሰላም እና በቡሬ ከተሞች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ እና በግጭቱ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ሳይለዩ ጥቃት መፈጸማቸውንና በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እንደሞቱ፣ የአካል ጉዳት እና ንብረት ውድመት መድረሱን ትናንት ማክሰኞ ባወጣው መግለጫው አስፍሯል።

ዶክተር ጌዲዮን ለዲፕሎማቶች በሰጡት ገለጻቸው ከአማራ ክልል በተጨማሪ ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት የቋጨውን የፕሪቶሪያውን ግጭት በዘላቂነት የመፍታት ስምምነትን አፈጻጸምን በተመለከተ ለተሳታፊዎቹ ማብራሪያ ሰጥተዋል።