August 16, 2023


ዜና
‹‹የታሰሩ ሰዎችን ሁኔታ ለመከታተል ፈቃድ አልተሰጠኝም››  ኢሰመኮ

አሸናፊ እንዳለ

ቀን: August 16, 2023

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተገናኘ፣ የታሰሩ ሰዎችን ለመጎብኘትና ያሉበትን ሁኔታ ለመከታተል ከመንግሥት ፈቃድ አላገኘሁም አለ፡፡ ኮሚሽኑ ፈቃድ ከጠየቀ ሳምንት ቢሆነውም እስከ ትናንት ማክሰኞ ነሐሴ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ ማክሰኞ ባወጣው ሪፖርት ላይ ‹‹በተለይ በአዲስ አበባ መስተዳደር በአማራ ተወላጆች ላይ እንዲሁም በኤርትራ ስደተኞች ላይ ሰፋ ያለ አፈሳና እስር እየተደረገ ነው፡፡ ኮሚሽኑ ብዛት ያላቸው ቅሬታዎችንና ማመልከቻዎችን ከታሰሩት ሰዎች ቤተሰቦች የተቀበለ ቢሆንም፣ ታሳሪዎች የት እንዳሉና ሁኔታቸውን ለመከታተል ፈቃድ አልተሰጠውም፤›› ሲል አትቷል፡፡

ኮሚሽኑ በመደበኛ ሁኔታ ውስጥ እስር ቤቶችን የመጎብኘት ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ነገር ግን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት የፀጥታ አካላት ሥልጣን ለኮማንድ ፖስቱ ስለተሰጠ የሚፈቅድለት አካል አለማግኘቱንና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ የሚቋቋም ቦርድ ስለሚኖር ከእነሱ ጋር በመናበብ ለመሥራት እየጠበቀ መሆኑን ገልጿል፡፡ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ጋርም እየተነጋገረ መሆኑን በኢሰመኮ የሰብዓዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ የሪጅን ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ አስረድተዋል፡፡

ከጠቅላይ መምሪያው ምላሽ መዘግየቱን ዳይሬክተሯ ጠቁመው፣ ኮሚሽኑ እስር ቤቶችን እንዳይጎበኝና የታፈሱ ሰዎችን ሁኔታ እንዳይከታተል በግልጽ ክልከላ ባይደረግበትም፣ በአሁኑ ሰዓት እስር ቤቶቹን በሚያስተዳድረው ኮማንድ ፖስት በአፋጣኝ ምላሽ ባለመገኘቱ መጎብኘት እንዳልቻለ አስረድተዋል፡፡

‹‹ኢሰመኮ ፈቃድ ሳይጠይቅ በድንገትም እስር ቤቶችን የመጎብኘት ሥልጣን በአዋጁ ተሰጥቶታል፡፡ ግን አሁን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይኼን ስላስተጓጎለው፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያው ፈቃድ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ከመምሪያው ፈቃድ ጠይቀን ምላሽ እየተጠባበቅን ነው፤›› ሲሉ ዓለሙ ምሕረቱ (ዶ/ር) በኢሰመኮ የሰብዓዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ከፍተኛ ዳይሬክተር ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልልም ኮሚሽኑ ክትትሉን እንዳልጀመረ ዓለሙ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ‹‹በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ሁሉም ነገር ስለተዘጋጋ መንቀሳቀስም አልተቻለም፡፡ ወቅታዊ ሁኔታ ሲባልና መንግሥት የእንቅስቃሴ ገደቦችን ሲጥል ሁልጊዜ እንቸገራለን፡፡ ከዚህ ቀደምም በዓደዋ በዓል አከባበር ጊዜ እንዲሁም በሙስሊሞች ጥያቄ ጊዜ በመንግሥት በኩል ኮሚሽኑን ፈቃድ የመከልከል ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ስለዚህ በየእስር ቤቱ ገብተን የሰብዓዊ መብቶችን አያያዝ ለመከታተል አንችልም፡፡ በመደበኛ ጊዜ የፈቃድ (Access) ችግር የለም፤›› ብለዋል፡፡ ኮሚሽኑ ትናንትና (ማክሰኞ) ባወጣው መግለጫ  ‹‹የፓርላማው የአስቸኳይ ጊዜ ወቅት ክትትልና የኢሰመኮ የሰብዓዊ መብቶች  ክትትል የማድረግ ኃላፊነት ሊረጋገጥ ይገባል›› ሲል መንግሥትን ጠይቋል፡፡

ኮሚሽኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አተገባበር፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ የትንታኔ ሰነድና ምክረ ሐሳቦችን ለፓርላማው ማቅረቡንም ገልጿል፡፡

በሰነዱ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለመንግሥት የሰጠው ሥልጣን፣ የአዋጁ የከባቢያዊና የጊዜ ተፈጻሚነት ወሰን፣ የፓርላማ አባላትና የዳኞች ያለመያዝ ልዩ መብት (Immunity)፣ በአዋጁ የተመለከተ ክልከላዎችና ግዴታዎች፣ በማንኛውም ሁኔታ ሊገደቡ ስለሚገባቸው መብቶችና ሌሎችም ጉዳዮች ከተመጣጣኝነት (Proportionality)፣ አስፈላጊነት (Necessity) እና ሕጋዊነት (Legality) አንፃር እንዲመረመሩ ይጠይቃል፡፡