አቶ ክርስቲያን ታደለ እና ዶ/ር ካሳ ተሻገር
የምስሉ መግለጫ,የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ዶ/ር ካሳ ተሻገር

ከ 5 ሰአት በፊት

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉን ተከትሎ የታሰሩትን የፌደራል እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት እንዳያገኙ መከልከላቸውን ከጠበቆቻቸው አንዱ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ጠበቃ ሰለሞን ገዛኽኝ እንዳሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ እንዲሁም የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ዶ/ር ካሳ ተሻገርን በፖሊስ ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም እስካሁን ፈቃድ አላገኙም።

ፖሊስ ያለ መከሰስ መብት ያላቸው ደንበኞቻቸውን በሕገ ወጥ መንገድ እንዳሰራቸው በመጥቀስም ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ነሐሴ 02/ 2015 ዓ.ም. ጠበቆቻቸው ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት አካልን ነጻ የማውጣት ክስ መስርተው ጉዳዩን እየተከታተሉ ይገኛሉ።

ከፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሙሊሳ አብዲሳ ጋር መወያያታቸውን እና አቶ ክርስቲያንን ማግኘት እንዲችሉ መጠየቃቸውን የሚናገሩት ጠበቃ ሰለሞን፣ “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታሰሩ ስለሆነ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጠበቃም እንዳያገኙ የሚከለክል ስለሆነ ማግኘት አትችሉም፤ ነገር ግን ደኅንነቱን በተመለከተ አረጋግጥላችኋለሁ” የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

“ቤተሰቦቹን ስንጠይቅም ‘በሩቁ እናየዋለን። ምን እንደሆነ አላወቅንም’ ነው የሚሉን፤ እንደ ጠበቃ ግን ሁለቱም የምክር ቤት አባላት በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አናውቅም። አላየናቸውም፤ አላገኘናቸውም” ብለዋል።

ጠበቃ ሰለሞን ጨምረውም ደንበኞቻቸው እስካሁን ቃል ስለመስጠት አለመስጠታቸውም ሆነ በምን ተጠርጠረው እንደተያዙ እንደማያውቁ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአቶ ክርስቲያን ታደለ ቤተሰብ ወ/ሮ በዛብሽወርቅ ካሳ፣ አቶ ክርስቲያንን በቀን አንድ ጊዜ እንዲያዩት እንደተፈቀደላቸው እና ምግብ አቀብለው እንደሚመለሱ ገልጸው፣ ነገር ግን ቀርበን መነጋገር ስላልተፈቀደልን ስለሚገኝበት የጤና ሁኔታ ማወቅ አልቻልንም” ብለዋል።

“በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተደበደበ፣ ታመመ የሚሉ ብዙ መረጃዎችን የሚሰሙ ሰዎች ይደውሉልናል። እኛም አይተነው ከመጣን በኋላ መልሰን እስከምናገኘው ድረስ ‘ምን ሆኖ ይሆን?’ እያልን ጊዜውን በጭንቀት ነው የምናሳልፈው። የደረሰበት የጤና እክል ካለም ቀርበን ለመጠየቅ አልቻልንም። አልተፈቀደልንም” ሲሉም ቤተሰቡ ስጋት ላይ እንደሆነ ገልጸዋል።

አቶ ክርስቲያን ታደለ አርብ፣ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ በፀጥታ ኃይሎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተይዘው መወሰዳቸውን ቤተሰቦቻቸው መግለጻቸው ይታወሳል።

በወቅቱ “ሕጋዊ ሰው ነኝ፣ ለምንድን ነው የምትፈልጉኝ?” ብሎ ሲጠይቁ ከፖሊሶቹ መካከል አንደኛው “በቦክስ ደበደበው” ብለዋል በወቅቱ እዚያው የነበሩት የምክር ቤት አባሉ የቤተሰብ አባል።

አቶ ክርስቲያን ታደለ በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በተለይም በኦሮሚያ ክልል በአማራ ተወላጆች ላይ ይደርሳል የሚሉትን የዘር ጭፍጨፋ እና ሌሎች በደሎችን ያነሱ ሲሆን፣ በቅርቡ ምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል።

የአዲስ አባባ ከተማ የምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ካሳም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተደነገገበት ዕለት እኩለ ሌሊት ላይ በፌስቡክ ገጻቸው “ፖሊሶች ነን የሚሉ ሰዎች በሌሊት መጥተው ክፈት እየተባልኩ ነው” የሚል መልዕክት ካሳፈሩ በኋላ ነበር በፖሊስ መወሰዳቸው የተሰማው።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል የተፈጠረውን “ግጭት ለማባባስ የከተማ ውስጥ ግዳጅ በመውሰድ የሎጅስቲክስ እና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ የተለያዩ ሕገወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙ ነበር” ያላቸውን 23 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጿል።

ከእነዚህም መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአዲስ አበባ ከተማ የምክር ቤት አባሉ ዶክተር ካሳ ተሻገር ይገኙበታል።

የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እና ቤተሰቦች ግን በፀጥታ ኃይሎች በጅምላ እስር እየተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ቁጥር ከተጠቀሱት በላይ ነው ብለዋል።

በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አርብ፣ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንን አዋጅ ሰኞ ነሐሴ 08/ 2015 ዓ.ም. በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁ ይታወቃል።

የተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን በመመርመር ለማጽደቅ አስቸኳይ ስብሰባ ባደረገበት ጊዜ በእስር ላይ ያሉት አባሉ የአቶ ክርስቲያን ታደለን ያለመከሰስ መብት ጉዳይን ያነሳል ተብሎ ቢጠበቅም፣ አንድ አባል ጉዳዩን ከማንሳታቸው ውጪ የተባለ ነገር የለም።

የኢትጵያ ሠንደቅ ዓላማ እና የሕግ ምልክት

ስለ “ያለመከሰስ መብት” ሕጉ ምን ይላል?

ጠበቃ ሰለሞን እንደሚሉት የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት አላቸው። እጅ ከፍንጅ ካልተያዙ በስተቀር ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ሊከሰሱ፣ ምርመራ ሊደረግባቸው ወይም ሊታሰሩ አይችሉም።

ለአቶ ክርስቲያን እና ለዶ/ር ካሳ “አካልን ነጻ የማውጣት” ክስ የመሠረቱትም ይህንን ሕግ መሠረት አድርገው እንደሆነም ተናግረዋል።

የምክር ቤት አባላቱ የታሰሩት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣውን ደንብ መሠረት ነው የሚል መልስ እንደሰጣቸው የሚናገሩት ጠበቃ ሰለሞን፤ “ሕጉ ግን ይህን አይፈቅድም፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣው ደንብ እንጂ አዋጅ አይደለም። ደንብ ደግሞ ሕገ መንግሥትን ሊሽር አይችልም” ብለዋል።

ጠበቃው እንደሚሉት አሁን ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣው ደንብ በተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀ ቢሆንም “ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ቀሪ አያደርገውም። ቀሪ የሚሆነው ያለመከሰስ መብታቸው በምክር ቤቱ ሲነሳ ብቻ ነው።”

“ያለ መከሰስ መብት”

“ያለመከሰስ መብት” በበርካታ የሕግ መዝገበ ቃላት ላይ የሚደጋገመው ትርጓሜው “አንድ ግለሰብ ወይንም አካል የሕግ ጥሰት የፈፀመ መሆኑ እየታወቀ ለወንጀሉ ተጠያቂ እንዳይሆን የሚደረግለት ሕጋዊ ከለላ” ከሚለው ጋር የሚስተካከል ነው።

የዚህ “ልዩ ከለላ” ተጠቃሚዎች ከሆኑት መካከል የሕዝብ እንደራሴዎች፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት እና የዳኝነት አካላት ይገኙበታል።

የመብቱ የጀርባ አመክንዮ ግለሰቦቹን እና አካላቱን በመክሰስ ወይንም ለፍርድ በማቅረብ ከሚገኘው ጠቀሜታ ይልቅ፣ ካለ ክስ እና ተጠያቂነት በማለፍ የሚሳካው ማኅበረሰባዊ ግብ የላቀ ነው ከሚል እምነት ጋር ይያዛል።

ሆኖም ይሄ የከለላ መብት ተነስቶ ግለሰቡ ወይንም አካሉ ላይ ክስ የሚከፈትባቸው አግባቦች ፈፅሞ የሉም ማለት አይደለም።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲዊ ሪፐብሊክ ሕገ- መንግሥት እና የክልል ሕገ-መንግሥታት ይሄን መብት ከሰጧቸው አካላት መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና የክልል ምክር ቤት አባላት ተጠቃሽ ናቸው።

ለአብነት የሕዝብ ተወካዮችን በሚመለከተው የአፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 55 (6) ላይ ያለመከሰስ መብትን እና መብቱ የሚነሳበትን አግባብ እንደሚከተለው ደንግጓል።

“ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል ከባድ ወንጀል ሲፈፅም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም፣ በወንጀልም አይከሰስም” ይላል።