August 20, 2023 – EthiopianReporter.com 


ዜና
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምሥረታ ተቃውሞ ገጠመው

ሔለን ተስፋዬ

ቀን: August 20, 2023

የቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በአራት ክልሎች ሲከፈል ጉራጌ፣ ስልጤ፣ ከንባታ ጠንባሮ፣ ሃላባ፣ ሐድያ ዞኖችንና የም ልዩ ወረዳን በማካተት ነሐሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. የተመሠረተው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምሥረታ ተቃውሞ ገጠመው፡፡

የአዲሱ ክልል የምሥረታ ጉባዔ ዓርብ ነሐሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ተካሂዶ የክልሉ ሕገ መንግሥት ግን በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡

ተቃውሞ ካቀረቡት መካከል የጉራጌ ዞን ያለበትን ቅሬታ ጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት አቶ ጀሚል ሳኒ እንደተናገሩት፣ ነሐሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በክልሉ በተጠራው አስቸኳይ ጉባዔ ይከናወናሉ ከተባሉ ጉዳዮች ውስጥ የሕገ መንግሥት ማፅደቅ አንዱ ነው፡፡

ረቂቅ ሕገ መንግሥቱን በማፅደቅ የክልል፣ የዞን ምክር ቤቶችና ልዩ ወረዳዎች ተሰብስበው እንዲሻሻል መጠየቅ እንደነበረባቸው ገልጸው፣ እነዚህ አካላት ውይይት ካደረጉ በኋላ ወደ ውሳኔ መግባት እንደነበረባቸው ሕጋዊ መሠረት ነው ያሉትን ሐሳብ አቶ ጀማል ጠቅሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከሕግ አሠራር በተቃራኒ የተጠቀሱት አካላት ሳይወያዩና ሳይወስኑ በክልል ምሥረታ ወቅት መቅረቡ በሕዝቡ ዘንድ ትልቅ ውዥንብር የሚፈጥር ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ የጉራጌ ሕዝብ ከክልል መቀመጫ ጋር በተያያዘ ጥያቄ እንደሌለው የገለጹት አቶ ጀሚል፣ ዞኑ ራሱን የቻለ ክልል እንዲሆን በተደጋጋሚ ጥያቄ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

ጥያቄው የሕገ መንግሥት መሠረት ያለውና የጉራጌ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ መሆኑን አስረድተው፣ አሁንም የሕዝብ ጥያቄ በአግባቡ ካልተፈታ ውሎ ሲያድርም ውጥረቶች ያሉበት አካባቢ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

በክልል ምሥረታ የሚደረገው አካሄድና ውሳኔ ሕገ መንግሥቱን የመጨፍለቅና የዜጎችን ሐሳብ የሚያፍን ሁኔታ እንደሚያሳይ ገልጸው፣ በጉባዔው የሚተላለፉት ውሳኔዎችም አካባቢውን ወደ አለመረጋጋት የሚወስዱ አዝማሚያ ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ሰባት ማዕከል ያለው የክልል አደረጃጀት በዓለም ታይቶ አይታወቅም፡፡ ለክልሉ ዘለቄታዊ መፍትሔ ከማምጣት ይልቅ፣ ከሕዝብ የሚነሳውን ጥያቄ ዝም ለማስባል እንደ መለጎሚያ (አፍ ማዘጊያ) የሆነ አሠራር ነው፤›› ተብሎ መፍትሔዎች መቅረባቸውን አቶ ጀሚል ገልጸዋል፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን ለማዋቀር ምንም ዓይነት የሕዝብ ውሳኔ ያልተደረገበት መሆኑን፣ በተለይ የጉራጌ ዞን ጥያቄ አሁንም ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ‹‹በሕዝበ ውሳኔ›› መፈታት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ከዚህ ቀደም ለሕዝበ ውሳኔ በአዲስ የተዋቀሩ ክልሎቹን በምሳሌነት ያወሱት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፣ ይህንን መብት ለጉራጌ ሕዝብ መነፈጉ ተገቢነት የሌለው ብለውታል፡፡

የጉራጌ ዞንን ከሌሎች ጋር መጨፍለቅ ሕጋዊነት እንደሌለውና ገዥው ፓርቲ ያመጣው በክላስተር የማደራጀት ውሳኔ ተገቢ ባይሆንም እንኳን፣ ሐሳቡ  በምክር ቤት ቀርቦ ውድቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሕዝቡ ከፈለገው ወይም መብቱን በጠየቀው መሠረት ችግሩን ከመፍታት ይልቅ፣ ‹‹እኔ አውቅልሃለሁ›› ተብሎ ጥያቄውን ለማደባበስ መሞከሩን ገልጸው፣ ይህ አካሄድ ለየትኛውም ለፍትሕ ሥርዓት አመቺ አለመሆኑን፣ ለአገር ግንባታ የማያዋጣና የዜጎችን መብት የሚጥስ ነው ብለዋል፡፡

የአደረጃጀትና የመዋቅር ተቃውሞ ሲያቀርቡ የነበሩት የከንባታ ጠንባሮ ዞን የምክር ቤት አባላት፣ በሕዝብ ሲነሱ የነበሩ መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ ወደ ክልል ምሥረታ መገባቱ አግባብነት የለውም በማለት ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡

የከንባታ ጠንባሮ ዞን ጥያቄ ፍትሐዊ የመዋቅር ችግር መሆኑን፣ የዞኑ ምክር ቤት አባል ወ/ሪት ሰናይት ለገሰ ተናግረዋል፡፡ የክልል ምሥረታ ከመካሄዱ በፊት በየደረጃ ካሉ ምክር ቤቶች ጀምሮ፣ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ድረስ የሕዝቡ ጥያቄ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ በክልሉ በሚወሰኑ ውሳኔዎች ቡራቡሬ አፈጻጸሞች መኖራቸውን ገልጸው፣ ቀድሞም በአደረጃጀቱ ላይ ቅሬታ መቅረቡንና በየደረጃው ውይይት ያልተደረገ  ስለሆነ፣ በገለልተኛ አካላት እንዲታዩ ምክር ቤት መጠየቁን አስታውሰዋል፡፡

ምክር ቤቱና ሕዝብ ከተወያየበት በኋላ ጉባዔው መካሄድ የነበረበት ቢሆንም፣ ከሕግ አግባብና ሥርዓት ውጪ ጉባዔው ተጠርቶ ውሳኔዎች ሲወሰኑ ችግሩን ውስብስብ ያደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ለዞኑ የተሰጠው መዋቅር ግብርና፣ ቴክኒክና ሙያ፣ ወጣቶችና ስፖርት መሆኑንና የሕዝብ ጥያቄ ለማደባበስ የአካባቢ፣ ደንና ግብርና ውስጥ አንድ ዳይሬክቶሬት የነበረውን እንደ ቢሮ አድርገው አፍ ለማስያዝ መጠቀማቸውን አስረድተው፣ ይህም የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄ ለመመለስ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተቋማቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳቸው ተንትኖ በአግባቡ ለሁሉም ዞኖች እኩል መልማት ፍትሐዊ ክፍፍል ሊኖር ይገባል በማለት ሕዝቡ ጥያቄውን ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡  

ይሁንና የእኩልነትና የፍትሐዊነት ጥያቄ የጠየቀው የዞኑ ነዋሪ ጆሮ ዳባ መባሉን ጠቁመው፣ በሕግ አግባብ መሠረት የዜጎች ጥያቄዎች እስኪስተካከሉ ድረስ ትግሉ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡

የደቡብ ክልል መፍረስ ዋነኛ ምክንያት የፍትሐዊነት ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፣ አሁን አብሮ ለመቀጠል የሚያስችል ፍትሐዊነትና የእኩልነት ሥርዓት መዘርጋት አለበት ብለዋል፡፡

አብሮ ለመኖር በክልሉ የሚገኙት ሁሉም መዋቅሮች በፍትሐዊነት መደልደልና መሻሻል እንደሚገባ ገልጸው፣ ይሁን እንጂ በጉባዔው የሚተላለፉ ውሳኔዎች የሕዝብ ድምፅ ተገፍቶ የሚያልፉ በመሆናቸው ተቀባይነት የሌላቸው፣ አሁንም ለዞኑ የተሰጡ መዋቅሮች ለመደለያ እንደሆነ ሕዝቡ ስለሚያውቅ ፍትሐዊነት እስኪረጋገጥ ድረስ ሰላማዊ ትግል እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል፡፡