
August 13, 2023
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ ብዙ ዞኖችንና ልዩ ወረዳዎችን በአንድ አሰባስቦ በኢትዮጵያ ሦስተኛው ትልቁ ክልል ሆኖ ሲመሠረት ጀምሮ የነበረውን ሒደት በቅርበት ከሚያውቁ ሰዎች አንዱ ናቸው፡፡ ክልሉ ያለፈበትን ውጣ ውረድና በስተኋላም ወደ ተለያዩ ክልሎች ለመከፋፈል የበቃበትን ሒደት የታዘቡት የሕግ ባለሙያው አቶ ታረቀኝ አበራ፣ ያኔ መዋቅሩ የፈጠራቸውን ስህተቶች ያብራራሉ፡፡ መዋቅር ሲደራጅ ወይም አዲስ ክልል ሲፈጠር ሊታሰብባቸው የሚገቡ ቁልፍ ጉዳዮችን ያነሱበት ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ሪፖርተር፡– የቀድሞው ደቡብ ክልል ሲዳማ ክልል፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ እንዲሁም ገና ቁርጡ ያልለየለት አንድ የክላስተር ክልል ሆኖ እንዲደራጅ ብዙ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ከሰሞኑ ከቀድሞው ክልል የወጣው ደቡብ ኢትዮጵያ የሚል ስም የተሰጠው ክልል እየተደራጀ ሲሆን፣ በዚህ ሒደትም በተለያዩ አካባቢዎች አለመግባባትና ተቃውሞ እየተፈጠረ ነው፡፡ ያለመግባባቱ መነሻ ምንድነው?
አቶ ታረቀኝ፡- ደቡብ ክልል ኢሕአዴግ በግብታዊነት የመሠረተው ክልል ነው፡፡ በግብታዊነት ስል ደግሞ በአንድ ጀንበር በዘፈቀደ የተመሠረተ ክልል ነው፡፡ እንዲያው ለአንዳንድ የፖለቲካ ፍላጎቶች ለማስፈጸም ሲባል የተመሠረተ ነበር፡፡ የሕዝቡን ስሜት በማየት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የክልሉን አደረጃጀት ሒደት ካየህ በቅሬታ የተመሠረተ ክልል ነበር፡፡ የደቡብ ክልል ታሪክ በቅሬታ ተደራጀ በስተመጨረሻም በቅሬታ ፈረሰ የሚል ነው፡፡ ደቡብ ክልል ሲመሠረት አንቀላቀልም ያሉ ብዙ ሰዎች ታስረዋል፡፡ ብዙ ሰዎች ተሰደዋል፣ ብዙ ሥቃይ ዓይተዋል፡፡ በጊዜው የነበረው ፖለቲካ ለራሱ ጥቅምና ለራሱ ሥልጣን ማቆያ የሚያደርጋቸው ብዙ ነገሮች ስለነበሩ፣ በክልል ምሥረታው ሒደት የተጠና ነገር አልነበረም፡፡ በጊዜው ጀማሪ ኤክስፐርት ሆኜ በቅጥር የማገለግልበት ጊዜ ነበርና ነገርዬውን አልተቀበልኩትም፡፡ ምናልባትም ከሚቃወሙት አንዱ ነበርኩ፡፡ እነ ናይጄሪያ ሲጀምሩ አራትም ዘጠኝም ሆነው ጀምረው አሁን ከ30 በላይ ደርሰዋል በሚል፣ የሰው አገርን የክልል አደረጃጀት የመኮረጅና እኛም ወደ እነሱ እንደርሳለን የሚል ዝንባሌ እንጂ የተጠና ነገር አልነበረም፡፡ በዚያም የተነሳ ሲመሠረት ጀምሮ የተረጋጋ ሁኔታ አልነበረም፡፡ በየተወሰነ ዓመቱ ብቅ ጥልቅ እያለ ግርግርና ግጭት ይነሳ ነበር፡፡ የተወሰነ ዓመት እያለፈ ማለትም በየሦስት አራት ዓመቱ ግጭት ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- እነዚህን ውጥረቶችና ውዝግቦች ይፈጥር የነበረው ችግር ምን ነበር?
አቶ ታረቀኝ፡- የዞን፣ የልዩ ወረዳና የወረዳ ጥያቄ እየተባለ የሚፈጠር ግጭትና ውዝግብ ነበር፡፡ ይህ በሲዳማ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አካባቢዎችም በየጊዜው ሲያመረቅዝ የሚታይ ችግር ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- አስተዳደሩን ወይም መዋቅሩን ለማሻሻል ጥረት አልተደረገም?
አቶ ታረቀኝ፡- የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሳለሁ አሁን ለአራት ክልሎች የተከፈለውን የክልል መዋቅር በሚመስል መንገድ አንድ ያልተማከለ አሠራር ጀምረን ነበር፡፡ የፍትሕ ተደራሽነትን ለማስፋትና ኅብረተሰቡን በተቻለ መጠን ለማገልገል ያስችላል በሚል በአራት ቦታዎች አደረጃጀት ፈጠርን፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምድብ ችሎቶች በሚል ቦንጋ ማዕከል፣ ወላይታ ማዕከል፣ ሲዳማና ሐዋሳ ማዕከል ብለን በአራት ቦታዎች ፍርድ ቤቶች መሠረትን፡፡ የራሳቸው በጀት፣ የሰው ኃይልና ሙሉ ሥልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶች ነበር የመሠረትነው፡፡ የፍትሕ ተደራሽነት ለማምጣት አደረጃጀቱ ትልቅ ጥቅም ነበረው፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ፍትሕ ሥርዓቱን ችግር ላይ እንደጣልን ተደርጎ ከባድ ተቃውሞና እንቅፋት ሲገጥመን ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ደቡብ ክልል ከሞላ ጎደል ወደ አራት ክልሎች ተከፍሏል፡፡ የክላስተር ክልል አደረጃጀት በደቡብ ክልል ተፈጥሯል፡፡ አደረጃጀቱ ከቀደመው በተሻለ ሊሰጠው የሚችል ጠቀሜታ አለ?
አቶ ታረቀኝ፡- አሁን ያለውን የክልል መዋቅር አደረጃጀትም በአራት ለመክፈል እየሠሩ ነው፡፡ ይህ በመርህ ደረጃ ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ደቡብ ክልል ሲመሠረት በታሪክ፣ በባህል፣ በቋንቋና በሌላም አንግባባም የሚሉ ማኅበረሰቦችን በአንድ በመጨፍለቅ ነበር አደረጃጀት ለመፍጠር የተሞከረው፡፡ የኢትዮጵያ ዘመናዊ አስተዳደር ከተመሠረተ ጀምሮ እንዲህ ዓይነት አደረጃጀት ታይቶ አይታወቅም፡፡ እንዲህ ዓይነት ግብታዊ ሥራ ሲጀመርም መሠራት አልነበረበትም፡፡ አሁን እየተፈጠረ ባለው አደረጃጀት ግን በግሌ የሕዝቡን ጥያቄ በተወሰነ ደረጃ የሚመልስ መዋቅር ለማበጀት እየተሞከረ ያለ ይመስለኛል፡፡ በተወሰነ መልኩ መረጋጋት ሊፈጥር ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡
ነገር ግን በአሁኑ አደረጃጀትም ቢሆን መዋቅር በመፍጠር ሒደት የተጠና ነገር አላይም፡፡ ቢሮዎችን ዝም ብሎ የመከፋፈል ነገር አያለሁ፡፡ ይህ ኅብረተሰቡን አይጠቅምም፡፡ ወደ ድሮው ችግር ውስጥ መልሶ የሚከት ስህተት ነው፡፡ አደረጃጀቶች የጎሳን ወይ የብሔር ፍላጎት አይደለም ማዕከል ማድረግ ያለባቸው፡፡ አደረጃጀቶች በጥናት በተደገፈ መንገድ የሕዝቡን አገልግሎት ፍላጎትና ተደራሽነት ባገናዘበ መንገድ ነው መፈጠር ያለባቸው፡፡ እንደምሰማው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አደረጃጀት ለአስተዳደር አልተመቸም ነው የሚባለው፡፡ የተወሰነ ቢሮ ሸካ፣ የተወሰነ ቢሮ ደግሞ ከፋ፣ የተወሰነው ቤንች፣ የተወሰነውን ማሻ፣ እንዲሁም የተወሰነውን ቴፒ በማድረግ አስተዳደራዊ መዋቅርን የማቃመስ ሥራ ነው የተሠራው፡፡ እንደዚያ ዓይነት አደረጃጀት መሆን የለበትም፡፡ ይህ ውጤታማ ሆኖ ይቀጥላል ብዬም አልጠብቅም፡፡
ሪፖርተር፡- የአስተዳደር መዋቅሮችን በተለያዩ ቦታዎች መዘርጋቱ ለኢኮኖሚ ዕድገትም ሆነ ለማኅበራዊ መስተጋብር ጠቀሜታ ያለው አይደለም?
አቶ ታረቀኝ፡– እንኳን በደቡብ ኢትዮጵያ ያሉ ሕዝቦች ቀርቶ በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ሕዝቦች ተመሳሳይ ነው ፍላጎታቸው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚመሠረቱ ዋና መቀመጫዎች ሊኖሩን ይገባል፡፡ አሁን ያለውን አካሄድና አስተሳሰብ መቀየር አስፈላጊ ነው፡፡ ሁሉ ነገር አዲስ አበባ መሆን አለበት የሚለው አስተሳሰብ መቀየር አለበት፡፡ እነ ናይጄሪያ ከታች ከባዶ ተነስተው ነው እነ አቡጃን የመሠረቱት፡፡ ግብፅ አሁን ከካይሮ ውጪ ትልቅ ከተማ እየሠራች ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ብንሄድ ከጆሀንስበርግ በተጨማሪ፣ ኬፕታውን፣ ሶፊያ ታውን፣ ደርባን አማራጭ ይሆናሉ፡፡ ህንድ ከሙምባይ በተጨማሪ እንደ ሀይድራባድ ያሉ ከተሞች አሉ፡፡ ዋና ከተማ ወይም የፖለቲካ ከተማ ይሁን እንጂ ኒውደልሂ ከሌሎች የህንድ ከተሞች አንፃር ገጠር ነው፡፡ አውሮፓም ሆነ አሜሪካና ሌላ አካባቢ የከተማ ማዕከላት ግንባታ ሰፋ ባለ መንገድ የሚታይ ጉዳይ እንጂ በጎሳና ብሔር የሚለካ አይደለም፡፡ እንዴት አድርገን የጋራ ከተሞችን እናምጣ የሚል አስተሳሰብ ነው መምጣት ያለበት፡፡ ዝም ብሎ በብሔርና በጎሳ ቢሮዎችን የሚቀራመት አደረጃጀት ዘላቂነት የለወም፡፡
በክልሎችም በፌደራልም ደረጃ የማዕከል ከተሞች መስፋፋት አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ በርከት ያሉ ተፎካካሪ ከተሞች መፈጠር አለባቸው፡፡ የፖለቲካ ከተማ አንዱን ካደረግከው የንግድ ማዕከል ከተማ ብለህ ደግሞ ሌላ ቦታ መመሥረት አለብህ፡፡ አንዳንዴም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ብለህ ልትመሠርት ትችላለህ፡፡ ምንም ጥቅም በሌለው ሁኔታ ይህ ቢሮ ለእከሌ፣ እንዲሁም ይህ ቢሮ ለእንትና እያሉ በብሔርና በጎሳ መዋቅር መከፋፈል የሕዝቡን ስሜት ለጊዜው ያስታግስ ይሆናል እንጂ ዘለቄታዊ ጠቀሜታ የለውም፡፡
ሪፖርተር፡- አዲስ የሚፈጠሩ ክልሎች ብዙ የማዕከል ከተሞች እንዲኖራቸው መደረጉ ችግር ነው ይላሉ?
አቶ ታረቀኝ፡– ይህ ዓይነቱ አደረጃጀት ለከተሞች ዕድገትም አይጠቅምም፣ ለመልካም አስተዳደርም አይጠቅምም፣ እንዲሁም ተመልሶ ሕዝቡን የሚለያይ ሁኔታ ፈጣሪ ነው፡፡ ሕዝቡ አርባ ምንጭ የእኔ ነው፣ ሶዶ የእኔ ነው፣ ቦንጋ የእኔ ነው፣ ወዘተ የሚል የእኔነት ስሜት ሊያሳድር የሚችለው ሁሉንም ሕዝብ ባሳተፈ መንገድ የማዕከል ከተሞችን ስትገነባ ነው፡፡ ሁሉንም በሚያገናኙ እሴቶች ከተሞችን ስትገነባና ስታሳድግ ነው ይህ የሚፈጠረው፡፡ በአንድ በኩል ጥሩ የአደረጃጀት ለውጥ የመጣበት ሁኔታ ቢታይም፣ ነገር ግን አሁንም ቢሆን የጋራ ከተሞችን ከመገንባት ይልቅ አንዱ ከሌላው የልዩነት ሰበዝ እየመዘዘ በመካከሉ ድንበር ለማስመር ያለው ፍላጎትና አስተሳሰብ ገና አልተሰበረም፡፡ ያ ለከተሞች ዕድገት ጥሩ አይደለም፡፡ ከተሞች ተደጋጋፊና ተመጋጋቢ ዕድገት ነው ያላቸው፡፡ የሌሎች አገሮች ከተሞች ዕድገት የሚያሳየው አንዱ ከሌላው ተደጋጋፊ ነው፡፡
የከተሞች ባለቤትነትም ቢሆን የሁሉም ነው መሆን ያለበት፡፡ የአንድ ወገን፣ ብሔር ወይም ቦታ መሆን የለበትም፡፡ ይህን ያማከለ ለውጥ አሁን ላይ በሚተገበረው የመዋቅር ለውጥ እየመጣ አይደለም፡፡ ተመልሶ እርስ በእርስ ወደ ግጭትና ወደ ሌላ ቀውስ የሚያመራ አሠራር እየተከተሉ መሆኑ ይሰማል፡፡ በአጠቃላይ የመጣው የአደረጃጀት ለውጥ በጎ ቢሆን እንኳን መዋቅር አገነባቡ ግን በአግባቡ እየተመራ አይደለም የሚል ነው የእኔ ግምገማ፡፡ ለዳግም ግጭትና መንደርተኝነት የሚዳርግ እንጂ፣ ለመልካም አስተዳደርም ሆነ ለከተሞች ዕድገት የሚጠቅም አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ያኔ ደቡብ ክልል ሲመሠረት ከሐዋሳ በተጨማሪ እንደ አርባምንጭ፣ ሆሳዕና፣ ሶዶና የመሳሰሉ ሌሎች ከተሞችም እኩል ጠቀሜታ እንዲኖራቸው ጥረት አልተደረገም?
አቶ ታረቀኝ፡- የከተሞች ዕድገት የተመጣጠነ አልነበረም፡፡ ሐዋሳና አርባ ምንጭ ሲመሠረቱም በኃይለ ሥላሴ ጊዜ በተቀራራቢ ዘመን ላይ የተመሠረቱና ተቀራራቢ ዕድገት ነበራቸው፡፡ ደቡብ ክልል የሚባለው መዋቅር እስኪመጣ ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ያሉ ከተሞች ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ላይ ያሉበት ደረጃ ሰፊ ልዩነት የሚታይበት ነው፡፡ ይህ በከተሞች መካከል ተመጣጣኝም ፍትሐዊም ዕድገት እንዳልነበረ አንድ ማሳያ ነው፡፡ አርባ ምንጭን የቱሪስት ከተማ አድርጎ በዘርፉ ብዙ ማሳደግ ይቻላል፡፡ አርባ ምንጭ ለማደግ የግድ የፖለቲካ ከተማ መሆን አያስፈልገውም፡፡ በቱሪዝም ላይ በሰፊው ኢንቨስት በማድረግ አርባ ምንጭን ከፍ ወዳለ የማዕከል ከተማ ደረጃ ማሸጋገር ይቻላል፡፡ ነገር ግን እኛ አገር የአስተሳሰብ ችግር አለ፡፡ ሁሉ ነገራችን ከፖለቲካ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ የሌሎች አገሮች የፖለቲካ ከተሞች እኮ በአመዛኙ ገጠሮች ናቸው፡፡ የህንድ መዲና ኒውደልሂ ከሌሎቹ አንፃር ገጠር ነው፡፡ ሆላንድ ብዙ የፖለቲካ መዋቅር ያለው ዴንሀግ ቢሆንም፣ ዋና ከተሞች የሚባሉት ግን እነ አምስተርዳምና ሮተርዳም ናቸው፡፡
የመንግሥት ከተማ እንዴት ይደግ በሚለው ላይ የሚከተለው ፖሊሲ ለዚህ ወሳኝ ነው፡፡ ከመንግሥት የኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ግንባታ ጋር የተያያዘ ነው የከተሞች ዕድገት፡፡ በገጠር አካባቢ አግሮ ኢንዱስትሪዎችን ከማስፋፋት ፖሊሲ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ኢንዱስትሪዎች ሲስፋፉ ከተሞች ያድጋሉ፡፡ ከተሞች ደግሞ ብዙ ዓይነት የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡ ነገርዬው የመንግሥትን ፖሊሲም ይደግፋል፡፡ አዲስ አበባን ብናይ ዕድገቱም ሆነ ሁሉ ነገሩ በአንድ አካባቢ መሆኑ ጤናማ አይደለም፡፡ እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች መፍጠርን መንግሥት ታሳቢ ማድረግ አለበት፡፡ እንደ ሸገር ከተማ ዓይነት አፓርታይዳዊ ከተሞችን ሳይሆን፣ ፍትሐዊ ዕድገትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚጠቅሙ ከተሞችን ከታች ከምንም ተነስቶ መፍጠርን ታሳቢ ሊያደርግ ይገባል፡፡
የናይጄሪያ አቡጃን፣ እንዲሁም የግብፅ አዲስ ዋና ከተማን ምሳሌ ማድረግ እንችላለን፡፡ ከተሞች ከታች ተነስተው በጤናማ ሁኔታ ቢያድጉ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያላቸው አስተዋጽኦ ትልቅ ነው፡፡ የዓለም አስተሳሰብና አካሄድም ይህንኑ የተከተለ መሆኑን መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ተፎካካሪ የሆኑ ከተሞች መፈጠር አለባቸው፡፡ የአካባቢህ ከተማ ሲያድግ ነው ብዙ ዕድሎችን የምታገኘውና ጤናማ ዕድገት የሚፈጠረው፡፡ ይህ ግን ብቅ ብቅ ያሉ ከተሞችን እየሸነሸኑ በአንድ ብሔረሰብ፣ ጎሳ ወይም ቡድን ሥር እንዲጠቀለሉ በማድረግ አይመጣም፡፡ መላው ኢትዮጵያዊያን የጋራችን ነው ብለው በሙሉ መተማመን ኢንቨስት የሚያደርጉበትና የሚያሳድጉት አገነባብ በተለያዩ ቦታዎች መምጣት አለበት፡፡ አሁን ያለው አደረጃጀት ግብም ይህ ነው መሆን ያለበት፡፡
ሪፖርተር፡- በዚያን ጊዜ በነበረው ደቡብ ክልል ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ወይም አሠራር አልተሞከረም?
አቶ ታረቀኝ፡- ይህ ነበር ትልቁ የቅሬታ ምንጭ፡፡ ሲጀመር የክልሉ አፈጣጠር በሕዝቡ ፍላጎት አልነበረም፡፡ በአንድ ጀንበር በአፈሙዝ ነው ጥናትም ሳይደረግ በአንድ ጀንበር ነው ክልሉ የተፈጠረው፡፡ ለምሳሌ እኔ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን አራት ቦታዎች እንዲዋቀር ለማድረግ ስነሳ የደረሰብኝ ውርጅብኝ ቀላል አልነበረም፡፡ ተቋሙን ሊገነጣጥለው ነው በሚል ክፉኛ ተቃውሞ ደርሶብኛል፡፡ አንድ ሰው ከካፋ መጥቶ ሐዋሳ ከተማ መዳኘት አለበት ማለት በራሱ በእኔ ዕይታ ጭካኔያዊና ኢፍትሐዊ ፍርድ ነው፡፡ ያለ የሌለ ሀብቱን፣ ገንዘቡን፣ ጊዜውን ጨርሶ አዲስ አበባን ሁሉ አልፎ ነው ከካፋ ሐዋሳ የሚመጣው፡፡ የመንግሥት ሥራ እንኳን ቢሆን ብዙ ነዳጅና ወጪ አፍስሶ ነው የሚደርሰው፡፡ አሁን የተሠሩ ሌሎች አቋራጭ መንገዶች ከሌሉ በስተቀር ሐዋሳና ከካፋ ፍፁም የተራራቁ ናቸው፡፡ ሐዋሳ ላይ ያለ የሌለ ሀብት ከማፍሰስ ውጪ የኅብረተሰቡን አገልግሎት ፍላጎት ባማከለና ፍትሐዊ ተተቃሚነትን በሚያረጋግጥ መንገድ ልማት ለማምጣት የሚደረግ ጥረት የለም፡፡ ሕዝቡም ይኸው የመንግሥት አንድ አቅጣጫ የተከተለ አስተሳሰብ የተጋባበት በመሆኑ፣ ሥራውም ኢንቨስትመንቱም በአንድ አካባቢ ብቻ የተወሰነ ነው፡፡ ዕለታዊ ገቢውን ባማከለ መንገድ እንጂ ሌሎች አካባቢዎች ብሠራና ሀብት ባፈስ ወደፊት ዕድገት ይመጣል፣ በሒደት አተርፋለሁ የሚል አመለካከት ለመያዝ የሚያስችል ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ ሕዝባዊ ኮንፍረንሶችና ስብሰባዎች እንኳን ከዚህ አካባቢ ወጣ ባለ ቦታ ላካሂድ ስትል በጥሩ ሁኔታ አይታይም ነበር፡፡ ሁሉም ነገር አንድ አካባቢ ካልሆነ የሚለው አስተሳሰብ የፀና ነበር፡፡ ሁሉም የእኔ የሚላቸውን ከተሞች ማቋቋም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የነበረው ልምድ ያሳየናል፡፡
ሪፖርተር፡- በደቡብ ክልል አደረጃጀት ወቅት ተሠርተዋል የሚሏቸው በአዳዲሶቹ ክልሎችም ሆነ በአገር ደረጃ እንዳይደገም ምን ቢደረግ ይበጃል ይላሉ?
አቶ ታረቀኝ፡- ለምሳሌ አሁን በሚቋቋሙት ክልሎች ሦስትና አራት ከተሞች በተለያዩ ቦታዎችና በተለያዩ ዘርፍ በማተኮር ማልማት ቢቻል ውጤታማ መሆን ይቻላል፡፡ በፖለቲካ ከተማነት ብቻ ሳይሆን፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ ወይም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በማተኮር ከተሞችን ብትመሠርት ሁሉም የእኔ ናቸው ብሎ የሚይዛቸውና በባለቤትነት የሚያለማቸው ማዕከላትን መፍጠር ትችላለህ፡፡ ደቡብ በአብዛኛው በአማርኛ ቋንቋ ነው የሚሠራው፡፡ ነገር ግን ከሁሉም ማኅበረሰብ ቢመጣ ተሰጥኦውና ክህሎቱ እስካለው ድረስ ውጤታማ የሆነ ሠራተኛን መልምሎ ማሠራት ቢቻል ለሚፈለገው ዕድገት አስተዋጽኦው ትልቅ ነው፡፡ የእኔ ብሔር ካልሆንክ፣ የእኔን ቋንቋ ካልተናገርክ ወይም ከእኔ ቡድን ካልመጣህ እያሉ ብቻ ዝም ብሎ ብቃት የሌለው ሰው እየመደቡ ማሠራት ወደ ጥፋት፣ ወደ ሙስናና ምዝበራ ነው የሚያመራው፡፡ በታሪክ ብናይ ደቡብን አማራ ብቻ አላስተዳደረውም፡፡ ከኦሮሞውም ሆነ ከሁሉም ብሔር የወጡ ሰዎች አስተዳድረውታል፡፡ አንዳንድ ነገሮች ከአስተሳሰብ ጀምሮ መሰበር አለባቸው፡፡ የእኛ ብሔር የእኛ አካባቢ ቢባልም ትክክለኛ አሠራር ግን ሁሌም ቢሆን ያሸንፋል፡፡ አሁን ያለው መንግሥት ከፍተኛ ችግር ውስጥ የወደቀበት ምክንያት መመልከት ካላቃተው በስተቀር ከመሠረታዊ ችግሮቹ አንዱ ይህ ነው፡፡ በማያባራ ጦርነትና ግጭቶች ውስጥ የገባው አንዱ በዚህ የተነሳ ነው፡፡
መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ የፖለቲካ ልሂቃንን ጥያቄ እያከኩ መኖር የመረጠ ይመስላል፡፡ አገሪቱ በማፊያ ቡድኖች እንድትተዳደር፣ ከተሞችም በማፊያ ቡድኖች እንዲመሩ ማድረግ ተገቢነት የለውም፡፡ የከተማ ባለሥልጣናት ኃላፊነታቸውን መሬት ለመውረር ነው እየተጠቀሙበት ያለው፡፡ በጎሳ ተደራጅቶ መሬት መዝረፍ በየትም ከተማ ቢኬድ ያለ ችግር ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ጀምሮ እስከ ትንንሽ ከተሞች የሚታየው ይኸው ነው፡፡ ትልልቆቹ የበለጠ እየፈረጠሙ ትንንሾቹ ደግሞ የገጠር ዝሆኖች እየሆኑ ሄደዋል፡፡ ከተሞቻችን በዚህ አካሄድ የማፊያ ቡድን እየፈጠሩ ሲሆን፣ እነዚህ ኃይሎች ደግሞ የባለሥልጣናትን እጅ የሚጠመዝዙ፣ ከመንግሥትና ከሕግ በላይ እየሆኑ ነው የሄዱት፡፡ ይህ ዓይነቱ የከተማ አመራርና አስተዳደር ደግሞ ለኦሮሞ አርሶ አደር የፈየደው ነገር የለም፡፡ ለአማራ አርሶ አደር የሚበጀው ነገርም የለም፡፡ ለሲዳማ አርሶ አደርና በአጠቃላይ ለተጨቆነው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ አሁንም ቢሆን ሕዝቡ ደሃ ነው፡፡ የክልልም ሆነ የከተማ አደረጃጀት ለውጥ እየተባለ የመጣው የመዋቅር ለውጥ የፈጠረው የተለየ ነገር የለም፡፡ የተወሰኑ የፖለቲካ ልሂቃን በሚገርም ሁኔታ የሕዝቡን ሀብት ሰብስበው እያግበሰበሱት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በቶሎ ካልተለወጠ በስተቀር በአጭር ጊዜ ልክ ዴሞክራቲክ ኮንጎን እንዳወደሟት ማፊያ ቡድኖች ዓይነት በወሮበሎች ሙሉ ለሙሉ የተያዘ ሥርዓት ነው በአገራችን የሚፈጠረው፡፡
የመንግሥት መዋቅርና አስተዳደርን የተቆጣጠሩ ማፊያ ቡድኖች መፈጠር ደግሞ የሕግ የበላይነትን ፍፁም የሚሸረሽርና ሥርዓተ አልበኝነትን የሚያነግሥ ነው፡፡ እኩልነትና ፍትሕ የሚባል ነገርም አይኖርም፡፡ አሁን እየተፈጠሩ ያሉ የክልል መዋቅሮችና አደረጃጀቶች ጥቂት ጮሌዎች የሚከብሩበት ሳይሆን የሕዝቡን ተጠቃሚነት፣ እንዲሁም ተመጣጣኝ አካባቢያዊ ዕድገትን ለማሳካት የሚረዱ መሆን አለባቸው፡፡ እስካሁን የተከተልነው የከተማ፣ የክልል ወይ ሌላ መዋቅር አደረጃጀት የመፍጠር መንገድ በዚህ ረገድ ጉድለት ያለበት መሆኑን በመረዳት ከተለመደው አስተሳሰብ ወጣ ያለ፣ የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ያማከለ ብቻ ሳይሆን የሌሎችን አገሮች ውጤታማ ተሞክሮ የቀመረ መንገድ መከተል ይኖርብናል፡፡
ሪፖርተር፡– ከምባታ አካባቢን ጨምሮ በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክላስተር ክልል አደረጃጀት ላይ በተለያዩ ቦታዎች ቅሬታ እየቀረበ ነው፡፡ የአሁኑ አደረጃጀት የሳተው ነገር ወይም ያልመለሰው ችግር ምንድነው ይላሉ?
አቶ ታረቀኝ፡- በግሌ በመርህ ደረጃ ክላስተር ክልሎች መፈጠራቸው ምንም ችግር አልነበረውም፡፡ ወደ ውስጥ ሲገባ ግን በጥሩ መርህ ላይ ተመሥርተው አይደለም ከተሞችንና ቢሮዎችን እያደራጁ ያሉት፡፡ ለምሳሌ አንዱ ይህን፣ ሌላው ያንን በማለት ቢሮዎችን በብሔር ብሔረሰቦች እያከፋፈሉ ነው ያሉት፡፡ ይህ ፈታኝ ችግር ሆኗል፡፡ ሰው ካነሳው የልማትና የአገልግሎት ተደራሽነት አንፃር አጥጋቢ አደረጃጀት መፍጠር የተቻለ አይመስለኝም፡፡ ከተሞችን ካላቸው ዕምቅ አቅም አንፃር እንዴት እናሳድግ የሚል መንገድንም መከተል አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ የአዲሱ ክልል አደረጃጀት ሒደት ጤናማ ቀመር ያገኘ አይመስልም፡፡ አስተዳደሩ የት ይሁን፣ ምክር ቤቱ የት ይሁን፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የት ይመሥረት የሚሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ የተከተሉት ቀመር ሕዝብ ብዛትና ጥቂት መሥፈርቶችን ባማከለ መንገድ ነው፡፡ ከተሞችን ከባዶ ሜዳ ተነስቶ ማደራጀትም እኮ ይቻላል፡፡ የአደረጃጀት እንበለው የመዋቅር ጥያቄ ሄዶ ሄዶ በመጨረሻ የማዕከል ከተሞችን መገንባት/ማልማት ጉዳይ ይመለከታል፡፡ አሁን በደቡብ የሚሆነው ነገር ግን የጋራ ማዕከል የሆኑ ከተሞችን ማልማት ላይ ያተኮረ ሳይሆን ቢሮዎችን በጎሳና በብሔር ማከፋፈል ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ይህ ዓይነቱ በጣም ራስ ወዳድ አስተሳሰብ ካልተሰበረ ደግሞ ከመዋቅር አልፎ ወደ ቤተሰብ ጭምር የሚገባ ነቀርሳ ነው፡፡ በተለያየ አካባቢ ግጭት እየፈጠረ ያለው ይህ ነው፡፡ ሰሞኑን አርባ ምንጭ ከርሜ ነው የመጣሁት፡፡ በሕዝቡ ውስጥ የሚታየው ስሜት ቅሬታን ያዘለና የመከፋት ነው፡፡ በከምባታ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ቦታዎች የተፈጠሩ ችግሮች ምንጩ ይህ ነው፡፡ ያለፈው የፖለቲካ ሥርዓት ያወረሰው በብሔር ነገሮችን መከፋፈል፣ ከዚያ ውጪ ነገሮችን አለመመልከት፣ ሁሉን ነገር በዘርና በቡድን መነጽር የመመልከት አስተሳሰብ ገና አልጠፋም፡፡ ጎሰኝነትና ዘረኝነትን ያስቀደመው ይህ አስተሳሰብ ላለፉት 30 ዓመታት አገር ለመምራት የተሞከረ ቢሆንም አልተሳካም፡፡ እንዲያውም ሰላማዊ የነበሩ ነገሮችን እያናጋና ተሰምተው የማይታወቁ ችግሮችን እየፈጠረ ነው የሚገኘው፡፡ ስንት ጊዜ ነው ይህን ይዘን የምንቀጥለው፡፡ ወጣ ማለትን ከተለመደው ውጪ መመልከት አለብን፡፡ በኢትዮጵያ አዲስ ወይም የተለየ አደረጃጀትን የመሞከር ነገር አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የ3,000 ዓመታት ታሪክ ያላት አገር ናት፡፡ ሕዝቡ በሰላም፣ ተከባብሮ፣ ሁሉም የአገር ባለቤት ሆኖ፣ ከቦታ ወደ ቦታ ከክልል ወደ ክልል ተንቀሳቅሶና ሠርቶ መብላት የሚችልበት አደረጃጀት ለማምጣት መሞከር አስፈላጊ ነው፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ መሰበር ያለበት ነገር መሰበር አለበት፡፡ ፌዴራሉ ላይ ያለው አስተሳሰብ ሲሰበር ነው ወደ ታች ወደ ክልሎችም ሆነ ወደ ዞኖች መውረድ የሚቻለው፡፡ ይህ በቀጣይ በአገራዊ ምክክሩ ሒደት ተነስቶ በውይይት የሚስተካከል ይሆናል ብዬ ነው ምገምተው፡፡
ሪፖርተር፡- አንድ የደቡብ ምሁር ‹‹አባቶቻችን በቲቲአይ ዕውቀት የፈጠሩትን ትልቅ ክልል እኛ በፒኤችዲ አፈረስነው›› ብለው ነበር፡፡ ትልቅ የነበረው ደቡብ ክልል በነበረው አንድነት ቢቀጥል ይሻል ነበር የሚሉ ሙግቶች አሁንም ይነሳሉ፡፡ ክልሉ ወደ ትንንሽ ክልሎች በመከፋፈሉ በክልሉ ብቻ ሳይሆን በአገር ደረጃም የሚያጣው ነገር የለም ይላሉ?
አቶ ታረቀኝ፡- መከፋፈሉ ላይ ብዙ ተቃውሞ የለኝም፡፡ አንድነቱ ራሱ በአንድ ጀንበር በአፈሙዝ ነው የተፈጠረው፡፡ ለ30 ዓመታት ቆይቶም ቢሆን በመከፋፈሉ ብዙ ችግር ያለው አይመስለኝም፡፡ ክልሎቹ ሲደራጁ ግን የሚደራጁበት ቀመር ነው በጥንቃቄ መሆን ያለበት፡፡ የሕዝቡ የልማት ጥያቄ ምንድነው? ከሕዝቡ ፍላጎት በተጨማሪ የየአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ ያማከለ ልማትን ለማስፋፋት ማቀድ ያስፈልጋል፡፡ የሰላም፣ የቱሪዝም፣ የኢንዱስትሪ፣ የአይሲቲና ሌላም ዓይነት ልማቶችን ማዕከል ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ አሁን በደቡብ አካባቢ እየተፈጠሩ ባሉ አዳዲስ አደረጃጀቶች እየታየ አይደለም፡፡ ያው የቀደመው የተለመደው ጎሳን ማዕከል ያደረገ የመዋቅር ክፍፍል ነው የሚታየው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ነው መቅረት ያለበት፡፡ የብሔር ክፍፍሉ ከ30 ዓመታት በላይ የተሞከረና እንደ አገር ከግጭትና መቆራቆዝ ውጪ አንዳችም ውጤት ያላገኘንበት መንገድ ነው፡፡ ደቡብ ክልል መከፋፈሉ ጠንካራ ክልልን ማፍረስ ነበር የሚለው አመክንዮ በሁለት ጎኑ ሊታይ የሚችል ነው፡፡ በአንድ ወገን የቀደሙ አባቶች እጅ/ጥረት ባይኖርበት ኖሮ እስካሁንስ ክልሉ በአንድነት ሊቆይ ይችል ነበር ወይ ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ ያለንበት ሁኔታ እንደሚታየው ከድጡ ወደ ማጡ እየገባ ነው ያለው፡፡ ደቡብን ብቻ ሳይሆን አገሪቱንም በየትውልዱ የገነቡ ሰዎች ጠንካራ አድርገው ባይገነቡት ኖሮ እስካሁን እንደ አገር ሳንፈረካከስ መቀጠል ከባድ ይሆንብን ነበር የሚያሰኝ ነው፡፡
በየጊዜው የማይሆኑ ትርክቶች እየተፈጠሩ አብሮ የመኖር ጠንካራ እሴት ፈጥሮ የቆየውን ሕዝብ ሲከፋፍሉና ሲያጫርሱ ቢቆዩም፣ ኢትዮጵያ እንደ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ሰፊ መሠረት አባቶቻችን በመጣላቸው እስካሁን ቆይተናል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥል ለማድረግ አቅም አልጠፋም፣ ሀብቱም አልጠፋም፣ ችሎታው ያላቸው ሰዎችም አልጠፉም፡፡ አገሪቱ ግን በብሔረሰብ ተደራጅተው በሚንቀሳቀሱ ማፊያ ቡድኖች ታንቃ ተይዛለች፡፡ መንግሥት ለዚህ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሙስናና ንቅዘትን በመከላከል ብቻ ሳይሆን በጠንካራ አመራር ትልቅ ሚና አለው፡፡ በእኔ ግምት አሁንም አልረፈደም፣ አገርን አንድ አድርጎ የማስቀጠል ጉዳይ የሁላችንም ነው፡፡