ሲሳይ ሳህሉ

August 20, 2023

ቆይታ

ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን መመረት መነሻ እንደነበር የሚነገርለት ዴስቲኒ ኢትዮጵያ፣ 2012 .ከተለያዩ ከማኅበረሰብ ክፍሎች የተወጣጡና በኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ሚና ይኖራቸዋል የተባሉ ሃምሳ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ አክቲቪስቶች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች የተሳተፉበት ውይይትና ምክክር ሒደት ውስጥ ከፍተኛ የመሪነት ሚና ከነበራቸው ግለሰቦች አንዱ፣ የማይንድ ኢትዮጵያ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና በአካባቢ ጥበቃ ተሟጋችነት የሚታወቁት ንጉሡ አክሊሉ (ዶ/ር) ነበሩ፡፡ በወቅቱ የነበረው ውይይት አገሪቱ አሁን ለደረሰችበት ቁመና ስላበረከተው አስተዋኦና የቀጣይ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ሲሳይ ሳህሉ ከንጉሡ (ዶ/ር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡– ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ከዓመታት በፊት ሲያከናውን የነበረው ውይይት ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን መመሥረት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉ ይነገራል፡፡ ጀምራችሁት የነበረው ውይይት አሁን ምን ላይ ይገኛል?

ዶ/ር ንጉሡ፡- ያኔ እንግዲህ ይህንን ሥራ ስንጀምር ጀማሪዎቹ የሰላም ግንባታ ላይ የነበርን ሰዎች አይደለንም፡፡ ከተለያዩ ሙያዎች ተሰባስበን አገሪቱ ውስጥ ያለውን ችግር እንዴት መፍታት ይቻላል በሚል የዜግነት አስተዋጽኦ እናድርግ ብለን ነው የጀመርነው፡፡ እኔ ለረዥም ጊዜ የቆየሁበት ዘርፍ ሌላ ነው፡፡ በአካባቢ ጥበቃና በአየር ንብረት ለውጥ ነው ለብዙ ዓመታት የሠራሁት፡፡ ሌሎች አብረውኝ የነበሩ ጓደኞቼም እንዲሁ ነበሩ፡፡ እና ያኔ በጣም የገረመኝ ነገር ቢኖር አገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ ሥርዓቱ በአጠቃላይ ውይይትን ባህሉ አለማድረጉ፣ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በጠመንጃ አፈሙዝ በጉልበት፣ በኃይል ፍላጎጎትን የመጫን አባዜ የተጠናወተው መሆኑን ነው፡፡ በዚህም መሠረት የፖለቲካ ባህላችን ውስጥ ውይይት አለመኖሩን ተረድተናል፡፡ ያንን ስንረዳ 50 ሰዎች ካወያየን በኋላ ‹‹አፄ በጉልበቱ፣ የፉክክር ቤት፣ ንጋት፣ ሰባራ ወንበር›› በሚል አራቱን ዕሳቤዎች በውይይት የተሳተፉ ሰዎች ሪፖርቱን ለሕዝብ ይፋ ሲያደርጉ ‹‹ንጋትን እንፈልጋለን፣ ለንጋት እንሠራለን›› የሚል መግለጫ አውጥተው ራሳቸው አነበቡት፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት የአዘጋጆች ሚና በጣም ውስን ነበር፡፡ ከማቀላጠፍና ከማስተባበር ውጪ ያደረግነው ነገር አልነበረም፡፡ ይህን ተከትሎ እኛ ምንድነው ያደረግነው? ንጋትን ከተመኛችሁ ንጋት እንዴት ይመጣል ብላችሁ ታስባላችሁ ብለን ስንጠይቅ፣ ተሳታፊዎቹ ሦስት የንጋት መንገዶችን አስቀምጠው ነበር፡፡ በዚህ መሠረት የመጀመርያው ገለልተኛ ተቋማትን መገንባት፣ ሁለተኛው ዕርቅና ይቅርታ ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ለረዥም ጊዜ ዕርቅ ዕርቅ ባለመካሄዱ አሁን መካሄድ አለበት በማለት በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሲያጋጥም የነበረው ግጭት በዕርቅና በይቅርታ እየፈታን መሄድ፣ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መምጣት አለብን በሚል የችግር መፍቻ መንገዶችን ከጦር መሣሪያ አፈሙዝ ወደ ውይይት መሆን አለበት ብለው አስቀመጡ፡፡ ይህን ከተረዳን በኋላ ዕርቅና ይቅርታን በሚመለከት መንግሥት ባቋቋመው የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አማካይነት፣ ወይም ተቋማትን መገንባት የዕኛ ሚና ባለመሆኑ ለመንግሥት ሰጠነው፡፡

የጠረጴዛ ውይይት የሚለውን ግን እኛ ገፋ እናድርገው በሚል፣ ከሰላም ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር በመሆን አንድ ቡድን አቋቋምን፡፡ ያ የተቋቋመው ቡድን ሌሎችም መሰል ጉዳዮችን በምክክርና በውይይት የሚፈቱ ተቋማን አንድ ላይ አቀናጅነተን ብንሠራ ጥሩ ነው በሚል አምስት ሌሎች ድርጅቶችን፣ በተለይም የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን፣ የሐሳብ ማዕድ የተባለ ድርጅት፣ ኢትዮጵያውያን ለአካታች ምክክር የተሰኘ ትብብር፣ ኢንሸቲስ ፎር ቼንጅና ጀስቲስ ፎር ኦል የተሰኙ ተቋማትን አንድ ላይ አድርገን ማይንድ ኢትዮጵያ (Multi Stakeholders Initative for National Dialogue) የሚባለው ስብስብ ሁሉን አካታች አገራዊ የምክክር ውጥን ይዘን ውይይት ጀመርን፡፡ በዚህ ሒደት ስምንት ድርጅቶች ሆነን ለ18 ወራት በትጋት ስንሠራ ቆየን፣ በዚህ ሁሉ ጊዜ በእርስ በርስ መቀራረብ ለሚከናወነው ሥልጠና ፕሮግራም ማውጣት፣ የሌሎች አገሮችን ልምድ መዳሰስና እንዴት እንሂድበት የሚለውን ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት የመሳሰሉትን ሠራን፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የአገራዊ ምክክር የዝግጅት ምዕራፍ ላይ ስንሠራ ቆየን፡፡ በዚህም በምክክሩ ማን ይሳተፍ፣ ተሳታፊው እንዴት ይመረጥ፣ ምክክሩ እንዴት ይካሄድና አጀንዳ እንዴት ይሰበሳባል የሚሉትን ነገሮች እየሠራን በአገሪቱ ውስጥ ሁሉን ባካተተ መንገድ ማን ይሳተፍ በሚል የተለዩ ተሳታፊዎችን በሚገባ እየመረጥን ሁሉንም እያዳረስናቸውና እያናገርናቸው ቆየን፡፡ ሌላው ለምክክር ሒደቱ ሀብት ስለሚያስፈልግ ሀብት ማፈላለጉንም ስንሠራ ቆየን፡፡ በሒደት እየሠራን ስንሄድ ሥራው መሀል ላይ ደርሶ ጥሩ እየሄድን ቆየን፡፡ በኋላ ግን የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የማቋቋም ውጥን በመንግሥት ዘንድ እንደተጀመረ የመንግሥት አካላት ነገሩን፡፡ መንግሥት ይህንን ነገር ቁርጠኛ ሆነን ልንወስደውና ትኩረት ልንሰጠው ይገባል በሚል ኮሚሽን ተቋቁሞለት፣ በአዋጅ ኮሚሽነሮች ተመድቦ መሠራት አለበት በሚል ከእኛም ጋር ውይይት ተጀመረ፡፡ ኮሚሽኑ ይቋቋም የሚለውን ሐሳብ ስንሰማ ለጉዳዩ ትኩረት እንደተሰጠ ቆጠርነው፡፡ በዚህም ኮሚሽኑ እንዲቋቋም በእኛ በኩል መስጠት ያለብንን ምክርና ሐሳብ  ሰጥተን ኮሚሽን ተቋቁሞ ኮሚሽነሮች ተሰየሙ፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት እንግዲህ ያ ኮሚሽን  ከተቋቋመ 18 ወራት ሆኖ ሥራ ላይ ይገኛል፡፡ እንግዲህ የማይንድ ኢትዮጵያ ስብስብና ውጥን አሁን ላለው አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አንድ መሠረት የጣለ ውጥን ነው፡፡ ሁለተኛው ነገር ምርጫ ሲካሄድ ምርጫው ላይ ብጥብጥና ሁከት ይፈጠርና አገር ሊበጠበጥ ይችላል በሚል ቅድመ ምክክር እናድርግ በማለት፣ ማይንድ በሚባለው ስብስብ አማካይነት ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራሮች ጋር ለአራት ጊዜ በዝግ ውይይት አካሂደናል፡፡

ይህ በዝግ የነበረ ስብሰባ ማንም አያውቀውም፡፡ ምክንያቱም ስንሠራ ሥራው  እንዲታይ እንጂ በቅድሚያ ዕወቁልን አንልም፡፡ ስለዚህ በዚህ አገራዊ ምርጫ ቅድመ ውይይት በመደረጉ ምክንያት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ምርጫው መቶ በመቶ ገለልተኛ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ነበር በሚለው ላይ አልተስማሙም፡፡ ነገር ግን ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ወደ ግጭት አልገቡም፡፡ ነገር ግን ምርጫውን ገለልተኛ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ያላሰኙት ጉዳዮች ምንድን ናቸው የሚለው ላይ ዝርዝር ጉዳዮች ተነስተው ውይይት እየተደረገ ለሚነሱ ጥያቄዎች ደግሞ ምላሽ እየተሰጣቸው፣ ከመጀመርያው ውይይት እየተዳመረ ቀጣይ ውይይት እየተካሄደ፣ በአራቱም ውይይቶች ጥሩ ውጤቶች እየተገኘበት፣ በዚህ ውይይት ምክንያት ሥጋቶችንና ጉድለቶችን መቀነስ ተችሏል፡፡ በዚህም ምርጫው ፍትሐዊ፣ ተዓማኒና ገለልተኛ ባይሆንም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን አስተዋጽኦ አድርገናል፡፡ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን ሲባል በምርጫ ሒደቱ ችግር ቢያጋጥም እንኳ ችግሩን ወደ ምርጫ ቦርድ፣ ወይም ይህን የምርጫ ጉዳይ እንዲዳኙ ወደ ተቋቋሙ ፍርድ ቤቶች እንሄዳለን እንጂ ወደ አደባባይና አመፅ አንሄድም በማለት ተስማሙ፡፡ ፓርቲዎቹም ያንን ስምምነት ሥራ ላይ አዋሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ያለፈው ምርጫ ሰላማዊ የሆነው በተደረጉ ዝግ ምክክሮችና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በወሰዱት መልካም ውሳኔ የተነሳ በመሆኑ ለዚህም ምሥጋና ይገባቸዋል፡፡ ሌላኛው ጉዳይ የታሪክ ባለሙያዎችን ያሰባሰብንበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ዜጎችን የሚያከራክሩን አልፎ አልፎም ከሚያጣሉን፣ ከሚያጋጩንና ከሚያገዳድሉን ነገሮች አንዱ የታሪክ አረዳዳችን ነው፡፡

በዚህ የታሪክ አረዳዳችንና ትርክታ የተነሳ በዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎች የመጀመርያ ዓመታቸው ላይ የሚሰጠው የጋራ ትምህርት (Common Course)፣ በሚነሳው ከፍተኛ ውዝግብ የተነሳ ከ1990ዎቹ ጀምሮ መሰጠት አቁሟል፡፡ በዚህም የተነሳ የታሪክ ባለሙያዎች በዚያው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ራሳቸው እርስ በርስ በከፍተኛ አለመግባባት ውሰጥ ገብተዋል፡፡ ምክንያቱም ደግሞ አንዳንድ የታሪክ ባለሙያዎች ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፣ መጻሕፍቶቻቸው ተቃጥለዋል፡፡ የሚያዋርድ ነገር ደርሶባቸዋል፡፡ ይህን የሰማነው ከምሁራኑ ጋር ውይይት ስናደርግ ነው፡፡ ይህም ከሆነ በኋላ ከ60 በላይ የሚጠጉ የታሪክና ተጓዳኝ ባለሙያዎችን ከሰላም ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ጋር ሆነን ሰብስበናቸው፡፡ ለተወሰነ ጊዜ በጋራ ውይይት አካሄዱ፡፡ ከዚያም ከምክክሩ ሁለት መሠረታዊ ውሳኔዎችን አስተላለፉ፡፡ የመጀመርያው የታሪክ አረዳድና አተራረክ ችግር ውስጥ የምንገባው ታሪክ የፖለቲካ መሣሪያ እየሆነ ስለተቸገርን ነው የሚል ነበር፡፡ ታሪክ ግን ሳይንስ ነው፡፡ ይህ  ሳይንስ ሲተረክም ሆነ ሲጻፍ መሟላት የሚገባቸው መመዘኛዎችና ደረጃዎች አሉት፡፡  እነዚህ መመዘኛ ደረጃዎችን ማውጣት የሚቻለው ደግሞ የባለሙያዎች ስብስብና ማኅበር ሲኖር ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የባለሙያዎች ማኅበር አለመኖሩ አንዱ ችግሩ በመሆኑ፣ በዚህ ምክክር የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር እንዲመሠረት መቋጫ አግኝቶ ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ ሁለተኛው ተማሪዎች የታሪክ ትምህርት መማር ያለባቸው ቢሆንም፣ በታሪክ ትምህርት መጻሕፍት ውስጥ ያሉ ጉዳዮች ተማሪዎችንም ሆነ የታሪክ ባለሙያዎችን የማያግባቡ ነገሮች አሉባቸው የሚል ነበር፡፡

በመሆኑም እነዚህን አጨቃጫቂና አከራካሪ ጉዳዮች ለመፍታት የታሪክ ባለሙያዎች ለተወሰነ ጊዜ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ብዙም ውጤት ባለማፍራቱ የታሪክ ባለሙያዎቹ በውይይት የተስማሙት የሚያከራክሯቸውን ነገሮች አንስተው እንዴት እናድርግ የሚለው ላይ ተወያይተው፣ እንዴት መቅረብ አለበት በሚለው ጉዳይና በሚያከራክረው ነጥብ ላይ ከስምምነት ደረሱ፡፡ ከዚያ አሥራ ሁለት አባላት ያሉት የባለሙያዎች ግብረ ኃይል አቋቁመው ነበር፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ያ ግብረ ኃይል ሥራውን ጨርሶ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ተመሠረተ፡፡  

በዚህ ማኅበር አማካይነት ከረዥም ጊዜ ውይይትና ንግግር በኋላ በትምህርት ሚኒስቴር አማካይነት ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ የታሪክ ትምህርት እየተሰጠ ነው ያለው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በአገራዊ የወጣቶች ውይይት በተለይም ውጣቶችን ለማቀራረብ፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን፣ በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ ውሰጥ ያሉትን ጭምር ጋብዘን ጥሩ ምክክር ስናደርግ ቆይተናል፡፡ በተመሳሳይ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃንን ጭምር ሰብስበን ውይይት አድርገናል፡፡ ወደ 40 ለሚጠጉ የመገናኛ ብዙኃን በሰላምና በግጭት አፈታት ጉዳይ የሚዘግቡ ባለሙያዎችን በአገራዊ ምክክርና በሰላም ሒደቶች ላይ አሠልጥነናቸው፣ የሰላም ነክና የግጭት አፈታት ነክ ጉዳዮች ላይ ቋሚ ዘጋቢ እንዲሆኑ ስንሠራ ቆይተናል፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት ያገኘነው ነገር ምክክር በጣም ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ዓይተናል፡፡ በተለይ በሒደት ቡድን ውስጥ ያሉ ሰዎችን በማቀራረብ ሰዎች የሌሎችን ሰዎች ሐሳብ እንዲያዳምጡ በማድረግ፣ አንዱ ሌላውን ለመረዳት ዕድል ይሰጣል የሚለውን ተረድተናል፡፡

ስለዚህ አሁን የጠቀስኳቸው ውይይቶችና ምክክሮች ወደ ድርጊትና ተግባር የተቀየሩት፣ ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ከመጀመርያ ሒደት ጀምሮ የተለያዩ አቋም ያላቸውን  የተቃረኑ ሰዎች አንድ ላይ መጥተው በጠረጴዛ ዙሪያ ሲነጋገሩ መሆኑን ተረድቷል፡፡ በዚህም እነዚህ ሰዎች ብዙ የሚጋሩት ነገር እንዳለና የማያግባቧቸው ነገሮች ላይ እየተነጋገሩ መሄድ እንደሚችሉ፣ አንዱ ሌላውን የተረዳበት መንገድ ስህተት እንጂ አንዳሰበው አለመሆኑንና የበለጠ ወደፊት መጓጓዝና መደማመጥ እንዳለባቸው የተረዱበትን መንገድ ያሳየ ነው፡፡ ይሁንና አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ከበፊትም ጀምሮ የፖለቲካ ባህላችን ውይይትን ባህሉ አላደረገም፡፡ የሚሰጠው ምላሽ ኃይል አዘል ነው፡፡ በዴሞክራሲ ወደፊት የተራመዱ ናቸው የምንላቸውና ራሳቸውን የዴሞክራሲ አራማጅ ነን ብለው የሚጠሩ የፖለቲካ አደረጃጀቶች እንኳ ዴሞክራሲን አልተለማመዱትም፡፡ ውጭ ያለን አካል ዴሞክራሲን ያለ ገደብ ይስጠን ይላሉ፡፡ ነገር ግን በውስጣቸው ዴሞክራሲን አልተለማመዱትም፡፡ ይህ የሚያሳየው በውስጣቸው ያሉ የሐሳብ ልዩነቶችን የማስተናገድ አቅማቸው ደካማ መሆኑን ነው፡፡ ይህ በአጠቃላይ እንደ አገር ያለብን መሠረታዊ ክፍተት መሆኑን ስለተረዳን፣ ይህንን የምክክር ሥራ እየቀጠሉ መሄድ ምንም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነበር፡፡ ምክክሩ የአገሪቱ የፖለቲካ ባህል ማዕከል እስኪሆን ድረስ መሥራት እንዳለብን፣ ሰዎች በጠመንጃ አፈሙዝ ወይም በጉልበት አንድ ችግር መፍታት እንችላለን ብለው ሲያስቡ፣ ወደ ጠረጴዛ እንዲመለሱ የማበረታታት ሥራ ስንሠራ ቆየን፡፡ አሁንም ይህንን እየሠራን ነው ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከማይንድ ኢትዮጵያ ጅምር ሥራዎች አንዱ ለመቀራረብና ለመተያየት የማይፈልጉ አካላትን በአንድ መድረክ ማወያየት መቻሉ አንድ ትልቅ ስኬት ነበር ይባላል፡፡ ይህ እንዴት ተሳካላችሁ? አሁንስ በዚያ የማቀራረብ መንገድ እየተሄደ ነው ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ንጉሡ፡- በአገራችን እኮ ብዙ ባህላዊ ሥርዓቶች አሉ፡፡ ፖለቲካው ያን መኮረጅ አልቻለም እንጂ፣ ብዙ በሕዝባችንና በግለሰቦች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች  በዛፍ ጥግና በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች የሚፈቱ ናቸው፡፡ ምክክር ወደድንም ጠላንም ባህላዊ ተቋም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውሰጥ ለምሳሌ የፍትሕ ተቋማት ማለትም ፖሊስ፣ ፍርድ ቤትና ማረሚያ ቤት የመሳሰሉት እንዳሉ ሆነው ብዙዎቹ የኅብረተሰቡ የፍትሕ ፍላጎቶች የሚሟሉት በተለይም 50 በመቶ ገደማ በባህላዊ የሽምግልናና የዕርቅ መንገዶች ነው፡፡ በየክልሉ ብንሄድ በሰዎች መካከል ያለን አለመግባባትና ቅራኔ መፍታት የሚቻልባቸው የተለያዩ ባህላዊ ሥርዓቶች አሉ፡፡ እነዚህ ባህላዊ ሥርዓቶች ተከራካሪ ወገኖች መጥተውና ያላቸውን ሐሳብ አቅርበው፣ የሚዳኛቸው ሥርዓት ቁጭ ብሎ በሚሰጠው ብያኔ መሠረት የሚፈጸሙ ናቸው፡፡ እኛ ባህሉ አለን፣ ለዚህም አክብሮት አለን፡፡ ነገር ግን ፖለቲካው እንደዚህ አይደለም፡፡ ፖለቲካው ከውጭ የተኮረጀ እንጂ ኢትዮጵያዊ አይደለም፡፡ በዚያ ምክንያት ፖለቲካችን ውስጥ ሥር የሰደደ ነቀርሳ ነው ያለው፡፡ የፖለቲካ ሥርዓታችን ለረዥም ጊዜ መወያየትን ባህል ባለማድረጉ የዘራነውን እያጨድን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ውይይትን እንደ አንድ የችግር መፍቻ ባህል እየዘራነውና እየተጠቀምንበት ከሄድን ለሚቀጥሉት ጊዜያት ዕድል አለ፡፡ በማይንድ ኢትዮጵያ ያወያየናቸው ሰዎች ይህን የንጋት አማራጭ ለማምጣት 20 ዓመት ነው የሰጡት፡፡ ያኔ በጣም ክርክር ነበር፡፡ በአምስት ዓመት ለምን አናመጣውም ሲሉ የተወሰኑት፣ ሌሎች ደግሞ አይ ችግሩ ጥልቅና ውስብስብ በመሆኑ እንዲሁ ንቀንና አሳንሰን ከገባን ብዙ ዋጋ የሚያስከፍለን ነገር ስላለ 20 ዓመት ዕድል እንስጠው በሚል ነበር  ውል የገቡት፡፡ አሁን እንግዲህ በማይንድ ኢትዮጵያ አማካይነት በተደረገው ውይይት እነዚያ አራት ዕሳቤዎች ከወጡ አራተኛ ዓመት ይዘዋል፡፡ በመጣንበት አራት ዓመት ውስጥ ሰባራ ወንበርም፣ አፄ በጉልበቱም፣ የፉክክር ቤትንም ንጋትንም የሚመስሉ ነገሮችን ዓይተናል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ተወያዮቹ ንጋት የሚመጣበትን ለይተዋል፡፡ በእነዚያ መንገዶች ላይ በተገቢው መንገድ ርብርብ ከተደረገ ሌሎቹ እየቀነሱ ወደ ንጋት መሄድ እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከአራቱ መንገዶች አሁን ያለንበት ወቅታዊ ሁኔታ የትኛው ላይ ያመዝናል?

ዶ/ር ንጉሡ፡- አሁን እንዲህ ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ ሁኔታው በጣም ይዋዥቃል፡፡ እንደሚታወቀው ባለፉት አምስት ዓመታት ብዙ የሚዋዥቁ ነገሮች ታይተዋል፡፡ ብዙ ፖለቲከኞች ሲጠየቁ ንጋት የሚባል ነገር የለም ይላሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ሲጠየቁ ንጋትን የሚያመላክቱ ነገሮች አሉ ይላሉ፡፡ ለምሳሌ ቅድም እንደጠቀስነው ተቋማትን ሙሉ ለሙሉ መገንባት ብዙ ቢቀረንም፣ ግን ተዓማኒነት ያላቸው ተቋማት እየተገነቡ እንደሆነ ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የዕንባ ጠባቂና ዋና ኦዲተር በጣም የሚገርም ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስህተት ሲፈጽሙ ወጥተው ሲሞግቱ እየታዩ ነው፡፡ ይህ አመላካች ጅማሮ ነው፡፡ እነዚህ ጅማሮዎች ተጠናክረው መሄድ አለባቸው፡፡ ነገር ግን ብዙ ይቀረናል፡፡ ለምሳሌ የመገናኛ ብዙኃን ገና ብዙ ዕርምጃ መሄድ አለባቸው፡፡ በፍርድ ቤቶች የተጀመሩ መልካም ጥረቶች አሉ፡፡ እሱ መስመር ከያዘ እሱም አንድ ጥረት ነው፡፡ በተመሳሳይ የሃይማኖትና የባህላዊ ተቋማት ካለፈው ስህተት እየተማሩ መቀጠል አለባቸው፡፡ ምምክርን በተመለከተ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አለ፡፡ እስካሁን ድረስ ዓይተነው የማናውቀው እንደ አገር ምክክር ያስፈልገናል ተብሎ፣ አብዛኞቹ ባለድርሻ አካላት ተስማምተው የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ በሙሉ ጊዜው እየሠራ እዚህ ደረጃ ደርሷል፡፡ ይህ ተቋም ሥራውን እየሠራ ነው፣ ፍሬው ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ አሁን ገና በዘር ደረጃ ነው ያለው፡፡ እኔ አንድ ትልቅ በጣም የሚያሳስበኝ ነገር ግን እዚህ አገር ዕርቅ የሚባል ነገር እየተካሄደ አይደለም፡፡ ይቅርታ እየተካሄደ አይደለም፡፡ ትናንትና ስንቆጥራቸው የነበሩ በደሎች ሳይዘጉ ሌላ በደል ይፈጠራል፡፡ ትናንት በድሏል የተባለው ዛሬ እየተበደለ፣ ትናንት ተበድሏል የተባለው ዛሬ እየበደለ፣ የበደል አዙሪትና የቂም በቀል አዙሪት ውስጥ ነን፡፡ ይህ የበደልና የቂም አዙሪት መፍታት ይቻላል ብዙ የተወሳሰበ ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህን የበደል አዙሪት የምንፈታው ለዕርቅ ዕድል ስንሰጥና በተለይ ፖለቲካ ውስጥ ያሉ መሪዎች ይህን ተቀብለው ዕርምጃ ሲወስዱ ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ተግባር እያየን አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት ይህን ሊፈጽም የሚችል የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ነበር፡፡ አሁን ግን የለም፡፡ ምናልባት ምክክሩ አንድ ደረጃ ሊያደርሰን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ዕርቅንና ይቅርታን በሚገባ ሊያካሂድ የሚችል ምንም ዓይነት ተቋምና አደረጃጀት፣ ምንም ዓይነት የፖሊሲ ማዕቀፍ የለንም፡፡ ይህ በአስቸኳይ መደረግ አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በዴስቲኒ ኢትዮጵያ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ 50 ግለሰቦች፣ የአገሪቱ የወደፊት አጣዳፊነት በሚል አራት ዕሳቤዎችን ያወጡት ግለሰቦችና የማይንድ ኢትዮጵያ አሁናዊ ቁመና ምን ላይ ነው? በየጊዜው በመገናኘት ሁኔታውን ትገመግማላችሁ ወይስ አበቃ?

ዶ/ር ንጉሡ፡- በ2016 ዓ.ም. እነዚያን ተሳታፊዎች እንደገና ለማሰባሰብ ዕቅድ አለን፡፡ በእርግጥ ብዙ ጉዳዮች ተለዋውጠዋል፡፡ እነሱን አሰባስበን እንደገና ነገሮችን እንዲገመግሙ ዕቅድ አለ፡፡ ነገር ግን ማይንድ ኢትዮጵያ የብዙ ተቋማት ስብስብ ነው፡፡ ከጅምሩ የተቋቋመበት ዓላማም አገራዊ ምክክር ለማድረግ ነበር፡፡ ነገር ግን አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስለተቋቋመ ማይንድ ተሰብስቦ ሌላ ትይዩ ምክክር ማድረግ አይችልም፡፡ ስለዚህ እንደ አንድ አካል ማይንድ የሚባል ስብስብ አሁን የለም፡፡ ነገር ግን በዚህ ውስጥ ተሰብስበው የነበሩ ተቋማትና ድርጅቶች በየግል እየተገናኘን እናወራለን፣ እንነጋገራለን ሁሉም ተቋም በየራሱ ይሠራል፡፡

ሪፖርተር፡- አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ትልቅ ሚና የተሰጠውና ተስፋ የጠጣለበት ተቋም ነው፡፡ ነገር ግን ዘገየ የሚል ወቀሳ እየተሰማበት ነው፡፡ ኮሚሽኑ በሚጠበቅበትና በሚፈለገው ልክ እየተራመደ ነው ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ንጉሡ፡- አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከተቋቋመ የ18 ወራት ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ እንደተባለው ሁለት የሰሉ ትችቶች እየቀረቡበት ነው፡፡ አንዱ ትችት ዘገየ የሚለው ነው፡፡ ለዚህም ኮሚሽነሮቹ ይህንን ትችት ሰምተው ማስተካከያ እያደረጉ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ ሁለተኛው ትችት አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሕዝቡ በሚገባ እንዲያውቀው የሚረዳ ጠንካራ የሆነ የኮሙዩኒኬሽን ሥልት የለውም ነው፡፡ ሕዝቡም በበቂ ሁኔታ መረጃ እያገኘ አይደለም የሚል ነው፡፡ ግብዓትም እየሰጠ አይደለም የሚል ሲሆን፣ ለዚህም ማስተካከያ እየተደረገ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ እነዚህ አስተያየቶች ኮሚሽኑ ሊሠራ የሚገባውን ጉዳይ በመገንዘብ በኮሚሽኑ ላይ የተጣለበት መልካም ተስፋ መኖሩን ማሳያ ናቸው፡፡ በምክክር ኮሚሽኑ ላይ  ተስፋ ባይኖር ግን ይህ አስተያየትና ትችት አይሰጥም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- አገራዊ  የምክክር ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ወዲህ አውዳሚ የተባለው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተካሂዷል፣ እሱም በስምምነት ሲቆም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎችና በሌሎች አካባቢዎች የሰላም ዕጦት አለ፡፡ መንግሥት የሚወስደው የኃይል ዕርምጃ ከአገራዊ  የምክክር ኮሚሽን ሥራ ጋር እንዴት ተጣጥሞ መሄድ ይችላል የሚል ጥያቄም ይነሳል፡፡

ዶ/ር ንጉሡ፡ የምክክሩ ቅርፅና ይዘት ምንም ይሁን ምን በአዎንታዊ ጎኑ ማየት ያለብን ነገር ቢኖር፣ ምክክር ያዋጣናል የሚለው ሐሳብ ከብዙ አካላት እየመጣ መሆኑ ነው፡፡ በፊት እንደዚህ ዓይነት ነገር አይታይም ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ አመራሮችም ሆነ የገዥው ፓርቲ ባለሥልጣናት በዚህ ጉዳይ ላይ ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ ይህ በጣም አበረታች ነገር ነው፡፡ ለምክክር ፈተና የሆነው ነገር፣ ወደ ምክክር ሲጠሩ ደካማነት የሚመስላቸው ሰዎች አሉ፡፡ መሣሪያ አስቀምጠህ በጠረጴዛ ዙሪያ ችግራችን እንፍታ ሲባል መሸነፍ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ነገር ግን ምክክር ሥልጡንነትና ትልቅነት ነው፡፡ ሌሎችንም ለማዳመጥ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ ለረዥም ጊዜ የቆየ ችግር ነበር፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ከ27 ዓመታት እስር ሲፈቱ በዚያን ጊዜ የነበረው በነጮች፣ በጥቁሮችና በህንዶቹ መካከል የነበረው የዘር ግጭትና በደል በጣም ከባድ ነበር፡፡ ሥርዓታዊ መልክ ሁሉ የያዘ በደል ነበር ጥቁሮቹ ሲያስተናግዱ የነበረው፡፡ ሌላው ቀርቶ ኔልሰን ማንዴላም 27 ዓመታት ነበር የታሰሩት፡፡ ለ27 ዓመታት ታስሮ ሲወጣ አንድ ሰው ምን ነበር ማድረግ የነበረበት ብለን ስናስብ፣ ነጮችን ማስወጣትና ኃይል አዘል ውሳኔ ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ነገሩ ሰከን ተብሎ ባይታሰብበት ኖሮ ነጮችም ሀብት ያፈራንበትና የኖርንበት በሚል እነሱም ኃይል አደራጅተውና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተባባሪዎቻቸውን አደራጅተው በህቡዕ ሲጠብቁ ነበር፡፡ ያ ጊዜ ደቡብ አፍሪካን ወደ የማያበራ ዓለም አቀፍ የጦርነት ቀጣና ይከታት ነበር፡፡ ማንዴላም ሲፈቱ ጠላቶቼ ነጮች ሳይሆኑ ሥርዓቱ ነው፣ ስለዚህ ሥርዓቱ ከተስተካከለ ከነጮች ጋር መኖር እንችላለን ብለው ሲናገሩ ያን ጊዜ የነበረው የጥቁሮች ቁጣ ረገበ፡፡ መሪ ስትሆን ይህ ቁመና ነው ሊኖርህ የሚገባው፡፡ እሳቸውም መሪ ሲሆኑ 27 ዓመታት የበደላቸውን መበቀል ሳይፈልጉ ቀሩ፡፡ አየህ መሪ ስትሆን የምትወስናቸው ጥበብ የሞላባቸውና አገርን የሚታደጉ ናቸው፡፡

በደቡብ አፍሪካ ከዚያ በኋላ በቀጥታ ወደ ውይይት ገባች፡፡ ውይይቱ እስካሁን ችግሩም አልቆመም፣ ውይይቱም አልቆመም፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር የኢትዮጵያና የታዳጊ አገሮች ብቻ አይደለም፡፡ አየርላንድም እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ነበሩ፡፡ በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች መካከል ሲደረግ የነበረና በጣም ብዙ ዘመን የቆየ ችግር ነበር፡፡ ሁለቱ ወገኖች ለ30 ዓመታት ተዋግተው ነበር፡፡ በሰሜን አየርላንድ ቦታ ማለት ነው፡፡ የዛሬ 25 ዓመታት የጉድ ፍላይ ዴይ ስምምነት ተፈራረሙና ችግሮቻቸውን በጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ በምክክር እንፈታለን ብለው ተቋማት አቋቋሙ፡፡ ብዙ የተበዳደሉ አካላት እየተገናኙ መነጋገር ጀመሩ፣ መገናኛ ብዙኃኑም እነዚህን አካላት እያገናኙና እያነጋገሩ የድልድይ ሥራ መሥራት ጀመሩ፡፡ ፅንፍ ይዘው ሲከራከሩ የነበሩ ሰዎች በጠረጴዛ ዙሪያ እውነተኛ ምክክር ማድረግ ጀመሩ፣ መቀራረብም ተፈጠረ፡፡ መተማመን እያደገ መጣ፡፡ አሁንም በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች መካከል ልዩነት እንዳለ ነው፡፡ 25ኛ ዓመት ሲከበር በአጋጣሚ አንድ መርሐ ግብር ላይ ተሳትፌ ነበር፣ እናም አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች አሉ፡፡ ግን አንድ የተስማሙበት ነገር ቢኖር በፍፁም ጠመንጃ ይዘው ላለመዋጋት ነው፡፡

በግብፅና በእስራኤል መካከል ለረዥም ጊዜ የቆየ ችግር እንዲሁ ተከታታይ በሆኑ ምክክክሮች ነው የተፈታው፡፡ የግብፅና የእስራኤል የሚባልና ከእሱ በፊትም የካምፕ ዴቪድ የሚባል በአሜሪካ የተደረገ ስምምነት አካሂደዋል፡፡ ያንን ስምምነት ሲያመቻቹና ሲያካሂዱ የነበሩት ሰዎች የተናገሩት ነገር ቢኖር፣ ምክክር በአንድ ጊዜ የምንፈልገውን ነገር የምናገኝበት እንዳልሆነ ነው፡፡ ምክክር በምዕራፍ እየተከፋፈለ፣ ብዙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበትና የማያቋርጥ ሒደት እያደረግን፣ ቀስ በቀስ ዛሬ ያጣነውን እየተመካከርን ነገ እየተቀበልን፣ ዛሬ እኛ ለሌሎች የነፈግነውን ለሌሎች እየሰጠን ወደ መቻቻልና መቀባበል የምንመጣበት ሒደት ነው፡፡ ያንን ሁሉ ያስነሳው የስድስት ቀናት ጦርነት የሚባለው ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሁለቱ አገሮች ጦርነት ውስጥ ገብተው አያውቁም፡፡ በዓለማችን ዙሪያ ያሉና ሥር የሰደዱ ችግሮች በማንነት፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋና በመሳሰሉት ላይ ያተኮሩ በርካታ ግጭቶች አሉ፡፡ እነዚህ ግጭቶች የተፈቱባቸውና መስመር የያዙባቸውን ቦታዎች ብንመለከት ምክክር ነው እዚያ ያደረሳቸው፡፡ ሌላው ቢቀር ለችግሩ ሲባል ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳይገብሩ ያደረጋቸው ምክክር ነው፡፡ አሁንም የፖለቲካና የሚዲያ አመራሮች፣ ሌሎች ኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉ አደረጃጀቶች፣ በአንድም ሆነ በሌላ አጋጣሚ የፖለቲካ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ይህንን ነገር የመወሰን ሥልጣን አላቸው፡፡ እያንዳንዷ የምንናጋራት ነገር መሬት ላይ ስትወርድ ሰው ትገድላለች፡፡ የምናየው ነገርም ይህንን ነው፡፡ ላይ ሆነን የምናደርገው ነገር እንዴት አድርጎ መሬት ላይ ሰላም ሊያመጣ እንደሚችል መነጋገር ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ለረዥም ዓመታት አልተግባቡም ነበር፡፡ ኤርትራ ከመንገጠሏ በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ ብዙ ጦርነት ይካሄድ ነበር፡፡ በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወይ ሞተዋል ወይ ቆስለዋል፡፡ ከዚያም በኋላ ኤርትራ ነፃነቷን አውጃ ከሄደች በኋላ እንደገና ጦርነት ውስጥ ገብተናል፡፡ የቂምና የበቀል አዙሪት ውስጥ ነበርን፡፡ ይህንን የቂምና የበቀል አዙሪት ምን ሰበረው? አንድ መሪ የተናገሩት ነው የሰበረው፡፡ ውስጥ ውስጡን የሚካሄዱ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንድ ቀን ተነስተው ኢትዮጵያና ኤርትራ ካሁን በኋላ በሰላም መኖር ይችላሉ፣ የሰላም በር እንዲከፈትልን እንጠይቃለን፣ እንነጋገር አሉ፡፡ ከዚያ በኋላ በኤርትራውያንና በኢትዮጵያውያን መካከል የነበረው ጥርጣሬ፣ ጥላቻ ፍርኃትና ሥጋት ቀርቶ ከኢትዮጵያ ውጪ ስንገናኝ በጎን የምንተያይ ሰዎች አሁን መንፈሱ ታድሷል፡፡ እናም መሪ ሲኮን ሰክነን፣ አውጥተንና አውርደን የምናደርገውን ነገር ሕዝብ ይቀበለዋል፡፡ መሪ ፀጋ አለው፡፡ የሚናገረውም ጉልበት አለው፡፡ መሪ ተኩኖ እንደ ልብ መናገርና እንደ ልብ ማሰብ አይቻልም፡፡ መሬት ላይ የምናያቸው ግጭቶች፣ ግድያዎችና ጦርነቶች በጠቅላላ መጀመሪያ የሚነሱት አሁን በምናያቸው የአንደበት ችግሮች ነው፡፡

አሁን እንደምናየው አሁንም ግጭት አለ፡፡ በተለያየ ሁኔታ አንዳንዴ በቁስ ላይ የተመሠረተ ግጭት አለ፡፡ የግጦሽ ምናምን ሊባል ይችላል፡፡ ሌላ ጊዜ በቁስ ላይ ላይሆን ይችላል ማንነት ላይ ያተኮረ ማለትም ከሃይማኖትና ከብሔር ብሔረሰቦች ጋር የተያያዘ ግጭቶች አለ፡፡ ከባድ ጦርነት በሚካሄድባቸው ቦታዎች ብቻ እንላለን እንጂ ከሰሞኑ እንደሚታየውም አዳዲስ ክልሎች ሲመሠረቱ የሚፈጠሩ/የተፈጠሩ ጭቅጭቆች አሉ፡፡ አዲስ ክልል ሲመሠረት ወዲያወኑ ግጭቶች ይከሰታሉ፡፡ የክልሉ መቀመጫ ማን ይሁን? የክልሉ ፕሬዚዳንት ማን ይሁን? የሚሉትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ይህ የማይበራ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ውሳኔዎች በሚወሰኑበት ጊዜ ምክክርን መሠረታዊ በማድረግ ውዝግብንና ችግርን የምንፈታበት መንገድ አድርጎ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ፖለቲካችን ይኼንን ነገር ካላስገባ በስተቀር ሁሉም የማንነት ቡድን የራሱን መብት ለማስከበር ይነሳል፡፡ የራሱ መብት እንዲከበርለት ደግሞ የአንተ መብት ተደፈጠጠ፣ ጠፋ የሚለው ጉዳዩ አይደለም፡፡ በጣም ግል ተኮር ፍላጎት ውስጥ እንገባለን፣ እናም አያባራም፡፡

ሪፖርተር፡- በአገር አቀፍ ደረጃ  በአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አማካይነት ውይይት ተጀምሯል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በየመሀሉ በፖለቲካም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ግጭቶች ቀጥለዋል፡፡ ይህን ነገር እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?

ዶ/ር ንጉሡ፡- አንድ ነገር ስትጀመርው ከባድ ነው፡፡ የትም አገር ምክክር የሚባለው ሲጀመር በቀላሉ አይደለም የተጀመረው፡፡ ምክክር በመሠረቱ ሰዎች በቀላሉ የሚቀበሉት ጽንሰ ሐሳብ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሁለት አካላት ይመካከሩ ሲባል አንዱ በለጥ ይላል፣ ለውይይቱም ራሱን ያዘጋጃል፡፡ በሌላ በኩል ያለው አካል ደግሞ መጀመርያ ለመደራደር እኩል መሆን አለብን ይላል፡፡ ነገሮች እየተለዋወጡ ይሄዳሉ፡፡ አንድ ነጥብ ላይ ቆመን ምክክር ካልጀመርን ችግር ይከሰታል፡፡ ምክክሩ ለአንድ ቡድን ያደላል ተብሎ ከታሰበና ጎሎብኛል (ተዳልቶብኛል) የሚለው አካል እኔ ወደዚያ ተመሳሳይ አቅም እስክመጣ ድረስ ውይይት ማድረግ አልፈልግም ይላል፡፡ ካለበለዚያ ጥቅሜ ይወሰድብኛል እጎድላለሁ ብሎ ካሰበ ወደ ጠመንጃ ይሄዳል፡፡ አንድ ቀን ሌላው ይቀየራል፣ ሌላው ደግሞ ጠመንጃ ይዞ ይገኛል፡፡ ምክክር ነባራዊ ሁኔታችንን ከግምት ውስጥ አስገብተን የምናደርገው መሆን የለበትም፡፡ እንደዚያ ቢሆን ኔልሰን ማንዴላ በፍፁም ምክክርን አይፈልጉም ነበር፡፡ ቁስል አለው፣ ሕመም አለው፡፡ ግን እንደዚያ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- እንቢተኛ ፖለቲከኞችን እንዴት ማቀራረብ ይቻላል?

ዶ/ር ንጉሡ፡- ከፖለቲከኞች ጋር አያይዘን የምንመለከተው ከሆነ ጉዳዩን ሁለት ቦታ ከፍሎ ማየት ይገባል፡፡ አንደኛው ፖለቲካው ራሱ በአብዛኛው ማንነትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ስለሆነም አንድ የማንነት ቡድን ያለው ጥቅም ጎድሎብኛል፣ በደል ደርሶብኛል ብሎ ካሰበ ያንን ነገር ነው ይዞ የሚሄደው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ አደረጃጀታችን በማንነት ላይ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ግጭቶች ብዙውን ጊዜ የሚሽከረከሩት በማንነት ጥቅምና ጉዳት ዙሪያ ስለሆነ፣ የፖለቲካ አደረጃጀት እስካልተቀየረ ድረስ ይኼ ነገር ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ይቀጥላል፡፡ በሌላ በኩል ይኼንን በማድረግ ትርፍ የሚያገኙ ፖለቲከኞች የሉም ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም ሁሉም ላይ መደፍደፍ ደግሞ አይቻልም፡፡ ፖለቲከኛ እንኳን ባይኖር አንዳንዴ ፖለቲካ በሌለበት ለምሳሌ ሃይማኖት ውስጥ ያሉ የተለያየ አካላት ይጣላሉ፡፡ ነገር ግን አሁን ስታስበው ሃይማኖት ውስጥ ምን ፖለቲካ አለ? አንዳንዴ ደግሞ ሃይማኖቶች ራሳቸው የፖለቲካ መሣሪያ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ ሃይማኖቶች ገለልተኛ ሆነው ሲሠሩ ለሌሎች ሃይማኖቶች የሚሰጡ ክብርና ዕውቅና ሳይነፈጉ መሄድ አለባቸው፡፡ ላለፉት 100 ዓመታት በጣም የበረታው ግጭት ከዚህ ቀደም እንደነበሩት ጊዜያት የወሰን ሳይሆን ማንነት ተኮር ነው፡፡ እናም ይኼ ወደፊትም ላይቆም ይችላል፡፡ ግን የአፈታት መንገዱ ላይ ልንስማማ እንችላለን፡፡ ዛሬ በተለያየ ምክንያት የተገነቡ አቋሞች ካሉ፣ አመለካከቶች አሉ፡፡ ምክክር ማለት አቋማችንን አሽቀንጥረን እንጣል ማለት አይደለም፡፡ ምክክር ማለት አቋማችንን ይዘን ግን በጠረጴዛ ዙሪያ ይዘነው መጥተን እናስረዳ፣ የሌሎችንም እናዳምጥ ማለት ነው፡፡ ምክክር ማለት ሦስት ነገሮች ነው፡፡ በመሠረታዊነት አንዱ ማዳመጥ ነው፡፡ ሁለተኛው እርስ በርስ ተነጋገሮ ለመግባባት መሞከር ነው፡፡ ሦስተኛው ቅርርብ መፍጠር ነው፡፡ ቅርርብ መፍጠር ስንችል እርስ በርስ ብዙ በውስጣችን ያሉ ወገንተኝነት፣ አንዱ ስለአንዱ ያለው የተሳሳተ ግምት እየቀነሰ ይመጣል፡፡ የተሳሳቱ ግምቶች እየቀነሱ ሲመጡና የያዙትን  አቋም እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ ትከሻ መለካካት ይኖራል፡፡ ትከሻ መለካካት በጦርነት ብቻ አይደለም፡፡ በጠረጴዛ ዙሪያም ትክሻ መለካካት አለ፡፡ አቋም ተይዞ ጠረጴዛ ዙሪያ ሲቀረብ አንዱ የሌላኛውን ቁጣ፣ በደልና ቅሬታ ይረዳል፡፡ ስለዚህ ይህን በደል አልሰማም ብዬ ብቆይ ነገ ሌላ ነገር ይመጣል የሚል ሐሳብ ይመጣል፡፡ አሁን ባለፉት 30 ዓመታት የሠራናቸው ነገሮች ናቸው እንደገና አገርሽተው ሰሜን ኢትዮጵያ ላይ ያንን ሁሉ ነገር የፈጠሩት፡፡ የኃይል አማራጮችን እንደ ዋነኛ ችግር መፍቻ በመጠቀማችን አይደለም እንዴ ደርግ ሥርዓት 17 ዓመታት ገዝቶ ከሥልጣን ሊወርድ አንድ ወር ሲቀረው የሰላም ኮሚሽን አቋቁሞ የነበረው? ምክክርን የመጨረሻ አማራጫችን አድርገን ማየት የለብንም፡፡ ከአሁኑ ኃይላችን ምንም ይሁን፣ ሥልጣናችን ምንም ይሁን፣ አቅማችንም ሆነ በደላችን ምንም ይሁን ምክክርን ተቀብሎ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መምጣት ይገባል፡፡ ከዚያ በኋላ ምክክርን እንደ ሒደት መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ ምክክር ድርድር አይደለም፡፡ ምክክር አንዱ ሌላኛውን የሚያዳምጥበት፣ የሚረዳበትና መተማመን እየተፈጠረ የሚኬድበት ሒደት እንጂ ድርድር አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ጫፍና ጫፍ ለረገጡ ፖለቲከኞች የሚሆነው አማራጭ ምንድነው? እነሱስ ምን ዓይነት ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ?

ዶ/ር ንጉሡ፡- የያዙትን ምክክር መቀጠል፣ ያዋጣል የሚሉትን ሐሳብ ተቀብለው መሄድ ነው፡፡ ከዚያ ምክክርን ተቋማዊ ቅርፅ መስጠት፡፡ አሁን አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሦስት ዓመት ተሰጥቶት ከሦስት ዓመት በኋላ ችግራችንን በሙሉ ፈተን ኢትዮጵያ አለፈላት ብለን የምናቆመው ነገር አይደለም፡፡ አሁንም፣ ወደፊትም ግጭት ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ማንነት ተኮር ግጭቶች ደግሞ እየቀጠሉ ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ቢያንስ ተቋማዊና ሕጋዊ ማዕቀፍ ካለ የማያቋርጥ ተከታታይ ውይይት ማድረግ ይቻላል፡፡ ያንን ውይይትና ምክክር እያካሄድን እንሄዳለን፡፡ ለሚፈጠሩ፣ ወደፊትም ሊመጡ ለሚችሉ ግጭቶች መሠረት ጥለን ለካ በምክክር ችግራችንን ልንፈታ የምንችልበት ጥሩ መንገድ ነው ብለን ልንሄድ እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡-  አሁንም ግጭት ቀጥሏል፡፡ ባለፈው ፓርላማው ባደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስብሰባ ወቅት መንግሥት አሁንም ግጭትን በጦርነት ለመፍታት አየሄደ ነው፣ ይህ አካሄድ የትም አያደርስም የሚሉ አስተያየቶች ተደምጠዋል፡፡ በዚህ ግጭት በቀጠለበት ሒደት ወደ መፍትሔው አይርቅም ወይ? ግጭት ሳይበርድ እንዴት መነጋገር ይቻላል?

ዶ/ር ንጉሡ፡- የሌሎች አገሮችን ልምዶች ወስጄ ነው የምነግርህ፡፡ ግጭትማ ካለቀ ምን መነጋገር ያስፈልጋል? ግጭቱ ሳይበርድ እንዴት እንነጋገራለን ከተባለ፣ ግጭት ከበረደ የመነጋገር ምክክር አይኖርም፡፡ አሁን ነው ንግግር የሚያስፈልገው፣ ግጭቱ አጀንዳ ሆኖ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ይምጣ፡፡ ለምሳሌ ትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት እስኪያልቅ ድረስ  ምክክር ለማድረግ እንጠብቅ ቢባል ብዙ ሕዝብ አለቀ አይደል እንዴ? አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች እስኪበርዱ ልንጠብቅ ነው? ምን ዋስትና አለ? ለዚህ ማስተማመኛችን ምንድነው? ምንም ማስተማማኛ የለም፡፡ ዛሬ ሰላማዊ ናቸው በምንላቸው ቦታዎች ግጭት እንደማይፈጠር ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ እኔ የምለው የትም አገር በግጭቶች መካከል ነው ውይይት የተጀመረው፣ ግጭቶች ሳይበርዱ ነው ውይይት የተጀመረው፡፡ ለምሳሌ የተኩስ አቁም ስምምነት ልታደርግ ትችላለህ፡፡ ለእሱም ግን ውይይት ያስፈልጋል፡፡ ተኩስ እናቁም ብለህ መነጋገር አለብህ፡፡ ምክንያቱም ተኩስ ማቆም የአንድ አካል ውሳኔ ብቻ አይደለም፡፡ ስለዚህ ምንም ወደኋላ ሳንል ዛሬ ያለንበት ሁኔታ ለእኛ ያድላም፣ አያደላም ምክክርን እንደ አንድ ዋና አማራጭ ይዘን መቀጠል አለብን፡፡ ቅድም እንዳልኩት ምክክር ዘላቂ ነው፡፡ ይህ ማለት በየጊዜው እየተደረገ፣ ዛሬ ምክክር ያላሳካውን ነገ እያረምነው፣ ነገ ያልታረመውን ከነገ ወዲያ እያረምን የሚሄድ ነገር ነው (ባህላችን ሲሆን)፡፡ ግጭት እስኪቆም እንጠብቅ የሚለው ነገር ለእኔም ዓለም አቀፍ ልምዱም ያን አያሳይም፣ ተጨባጭ ነገርም አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የሃይማኖት ተቋማት ለሰላም ተምሳሌት ይሆናሉ ተብለው ይታሰባል፡፡ ነገር ግን በእነሱም መካከል ግጭት እየተፈጠረ ነው፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ከፖለቲካ የፀዱ ሆነው መቀጠል ይችላሉ ወይ?

ዶ/ር ንጉሡ፡- ይቻላል፡፡ ወደ ታሪካችን ስንመለስ ያሉት ነገሮች የሚያሳዩት መንግሥታት በጠቅላላ ከድሮ ጀምሮ፣ እነዚህን በጣም ጠንካራ ተቋማት የራሳቸው መሣሪያ የማድረግ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ የራሳቸው መሣሪያ ያደርጓቸዋል፡፡ ልክ አንድ ተቋም በድንገት መጥቶ ገለልተኛ ይሆንልኛል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ሌላው ይቅርና ባህላዊ የሽምግልና ሥርዓቶች በፖለቲካ ሊጠለፉ ይችላሉ፡፡ የፖለቲካ አገልጋዮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ግን ይኼ ሁሉ እየሆነ እያለ ደግሞ በእምነቱም፣ በባህላዊ ሥርዓቱም ውስጥ ገለልተኛ የሆኑ የተከበሩ ሰዎች አሉ፡፡ በየቦታው የምንጠራቸው ትልልቅ ሰዎች አሉ፡፡ ለእኔ እነዚያ ሰዎች ትልልቅ ተቋማት ናቸው፡፡ ቀስ እያልን የችግሮቻችንን ሥረ መሠረት ወደ ታች እየሄድን እየፈታን ስንሄድ ይኼም ነገር እየተፈታ ይሄዳል ብዬ ነው የማምነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን በሃይማኖት ተቋማት ላይ ምንም ዓይነት አተያይ ቢኖረንም፣ ምክክር የእነሱንም ጉዳይ ሊፈታ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በሃይማኖት ተቋማት መካከል ምክክር አድርገን ነበር፡፡ የፖለቲካ ሥርዓቶች በተከታታይ እምነትን መጠቀም እንደሚፈልጉ ራሳቸውም በይፋ የተናገሩት ነገር ነው፡፡ ያ ነገር ትክክል ነው መቀጠል አለበት ብለው ሁሉም አያምኑም፣ የሚያምኑ ግን አሉ፡፡ እናም ያንን ነገር እንዴት ነው የምታስተካክለው? እሱን ቀስ እያልክ የምታስተካክለው ነገር ነው፡፡ በድንገት ወይም በአስቸኳይ የምታደርገው ነገር አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ባህላዊ የችግር መፍቻዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ክልሎች አሉ ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን እነዚህን የግጭት መፍቻ መንገዶች በመጠቀም ችግር ለመፍታት በሚሞከርበት ወቅት የፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነት ይታያል፡፡ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በሌለበት ባህላዊ መንገዶች ፍቱን ስለሆኑ ሁለቱ ሳይጠላለፉ እንዲሄዱ እንዴት ማካሄድ ይቻላል?

ዶ/ር ንጉሡ፡- ባለፉት ጊዜያት ኢትዮጵያን ሲመሩ የነበሩ ነገሥታት በሙሉ የነበረባቸው ትልቅ ፈተና፣ የሃይማኖት ተቋማትን ካልተጠቀሙ ሕዝቡን መቆጣጠር  እንደማይችሉ ነው፡፡ ስለዚህ የሃይማኖት ተቋማትን የመቆጣጠር ፍላጎት ነበራቸው፡፡ ይህን ደግሞ እነሱም ራሳቸው ሆኑ ሕዝቡ በግልጽ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ የባህላዊ ሥርዓቱም ቢሆን ከዚያ ነፃ ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በማንኛውም ባህላዊም ይሁን የሃይማኖት ሥርዓት ውስጥ በጣም ጠንካራ የሆኑ፣ ከምንም ነገር በላይ እምነታቸውን የሚያስቀድሙ፣ ለባህላዊ ሥርዓታቸው ቅድሚያ የሚሰጡ በጣም የተከበሩና አንቱ ተብለው የሚጠሩ ግለሰቦች በየቦታው አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች እስካሉ ድረስ ተቋማቱም እየተለወጡ መሄዳቸው አይቀርም፡፡ እነዚህን መልካም ዝና ያላቸውና አንቱ የተባሉ ሰብዕናዎችን እንዴት እናስቀጥላቸው የሚለው ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ የሃይማኖትና የባህላዊ መሪዎቻችን እንደ ፖለቲከኞች በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠውና ተነጋግረው ማረም ያለባቸው ነገር አለ፡፡ ይህ በራሱ ምክክር ሲባል ፖለቲከኛው ብቻ አይደለም፡፡ ዘላቂ ምክክር ሲባል በሃይማኖት መሪዎች፣ በመገናኛ ብዙኃን መሪዎች፣ በሴቶችና በወጣቶች መካከል ምክክር ይደረጋል ማለት ነው፡፡

በመጨረሻ ልናገር የምችለው ኢትዮጵያውያን ብዙ የምናልፍባቸው ፈተናዎች አሉ፡፡ በየጊዜው የማንግባባቸው የእርስ በርስ ቅራኔዎች፣ ግጭቶችና መገዳደሎች ውስጥ ስንገባ ቆይተናል፡፡ አሁንም እዚያው ውስጥ ነን፡፡ ነገር ግን በታሪካችን ውስጥ ዕድል ያልሰጠነው ብቸኛው ነገር ምክክር ብቻ ነው፡፡ ሁሉንም ሞክረነዋል፡፡ በረሃ ገብተን አሸንፈን ተመልሰናል፡፡ መፈንቅለ መንግሥት አድርገን መንግሥት ገልብጠናል፡፡ አንድ ፖለቲከኛ ሌላውን አስሯል፣ ገድሏል፡፡ አንዱ ሌላውን ዘርፏል፡፡ አቅም ያለው አቅም የሌለውን ብዙ ነገር ሲያደርግ ዓይተናል፡፡ መንግሥታዊ ሥልጣን ባይኖረውም የታጠቀ አካል ያልታጠቀውን አንገላቷል፡፡ ስለዚህ በታሪካችን ብዙ ነገር አድርገናል፡፡ ነገር ግን በታሪካችን ያላደረግነው ዘላቂና ፍቱን መድኃኒት ሊሆነን የሚችለው ምክክር ብቻ ነው፡፡ እነዚህ አሁን የሚታዩት ኃይል የተሞላባቸው መንገዶች ለጊዜው ዕረፍት የሰጡን ይመስላሉ፡፡ ነገር ግን የረዥም ጊዜ ውድቀት ናቸው፣ ክሽፈት ናቸው፡፡ በረዥም ጊዜ ራስን በራስ የማጥፋት ዓይነት ሒደቶች ናቸው፡፡ በታሪካችንም ዘላቂና ፍቱን የሆነ መድኃኒት ከፈለግን ምክክር ብቻ ነው ያላደረግነው፡፡ ግን እሱን ማድረግ በጀመርን ጊዜ እንደ ኢትዮጵያውያን የሚያስተሳስሩን ገመዶች ላይ እናተኩራለን፡፡ እንደ ኢትዮጵያውያን ከመፈራረጅ ወጥተን መደማመጥ እንችላለን፡፡ እኛም ውስጣችን ያለውን ሥጋት ለሌሎች በማቅረብ የሌሎችንም ከልብ በማድመጥ መተማመን እንፈጥራለን፡፡ መተማመን መፍጠር የምንችለው በመነጋገር እንጂ፣ በጠመንጃ አፈሙዝ ሰውን አስገድዶ ማሳመን አይቻልም፡፡ መንግሥትም ይሁን ሌላ የታጠቀ ኃይል ለጊዜው ጨቁኖ ሊይዝ ይችላል፡፡ ነገር ግን ምክክር ሲደረግ ነው ነገሮች እየተቀየሩ የሚሄዱት፡፡ በሽታ ጊዜያዊና የረዥም ጊዜ ተብሎ መድኃኒቱም በዚያው ልክ እንደሚወሰደው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ችግሮች ጊዜያዊና የረዥም ጊዜ ናቸው፡፡ የረዥም ጊዜ ችግሮቻችን ለመፍታትና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ዘላቂ የምክክር ሒደት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ምክክር ለረዥም ጊዜ የሚወሰድ እንጂ እንደ ጉንፋን መድኃኒት ለአጭር ጊዜ የሚወሰድ አይደለም፡፡ ለረዥም  ጊዜ እንደ ልብ ሕመም ሳናቋርጥ የምንወስደው ነው፡፡ ፀብን እየመገብን ሰላምን ማምጣት አንችልም፡፡ ምክክርን እንደ ትልቅነትና መልካም ሰብዕና ማየት ያስፈልጋል፡፡ ምክክር መሸነፍ አይደለም፡፡ ምክክር ውርደት አይደለም፡፡ ምክክር መከባበር ነው፡፡ ይህን ማድረግ እንችላለን፡፡ ስለዚህ ተስፋ አንቁረጥ የሚል መልዕክት አለኝ፡፡