
August 23, 2023 – EthiopianReporter.com

ኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዓመታዊ ጉባዔ
ዜና ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አፈንግጠው የነበሩ ፓርቲዎች ጉዳይ በዕርቅ እንዲፈታ መደረጉ…
ቀን: August 23, 2023
- ምክር ቤቱ አዲስ ሥራ አስፈጻሚ ሰይሟል
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአገሪቱ የሰላም ሁኔታ የከፋ ቀውስ ውስጥ መሆኑንና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስመልክቶ የሰጠውን ጋዜጣዊ መግለጫ በመቃወም፣ የራሳቸውን መግለጫ ያወጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ጀምሮት የነበረው ምርመራ ተጠናቆ በዕርቅ እንዲፈታ መደረጉ ተገለጸ፡፡
የምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ ሰኔ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. የሰጠውን ጋዜጣዊ መግለጫ የምክር ቤቱ የአባላትን እምነት የሚሸረሽር መሆኑን፣ የተሰጠውን ኃላፊነት ባለመወጣት በፓርቲዎች መካከል አለመግባባትን የሚፈጥር፣ እንዲሁም ግንኙነቶችን የሚሸረሽር መሆኑን ጠቅሰው የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች መግለጫ ማውጣታቸው ይታወሳል፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ ግጭቶች፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የዜጎች ሞት፣ መፈናቀል፣ እስር፣ የሀብት ውድመት፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር፣ የዜጎች የደኅንነት ሥጋት፣ የእምነት ተቋማት ነፃነት ማጣት፣ የኑሮ ውድነትና አፈናን አስመልክቶ የጋራ ምክር ቤቱ መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡ ይህንን ተቃውመው ሌላ መግለጫ ካወጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የአገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ የትግራይ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባርና የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ይገኙበታል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ በእነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ያስቸለኛል ያለውን ምርመራ በምክር ቤቱ የሕግ ቋሚ ኮሚቴ አማካይነት በፓርቲዎቹ ላይ ጀምሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በምክር ቤቱ ውስጥ መከፋፈልን ላለመፍጠር በሚል ዕሳቤ ችግሩ በዕርቅ መፈታቱን፣ አዲሱ የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ሰብሳቢው ባለፉት ሁለት ቀናት በተካሄደው ጉባዔ በአመዛኙ በዚሁ ጉዳይ ጠንካራ ውይይትና ክርክር የተካሄደ መሆኑን፣ ፓርቲዎቹ በሰጡት መግለጫ በፈጸሙት ጥፋት ላይ ምክክር ተደርጎበትና ይቅርታ ተጠይቆ በቀጣይ አስተማሪ ይሆናል የተባለለት ዕርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ በምክር ቤቱ ውስጥ ክፍፍል የሚፈጥሩ ጉዳዮችን ሊፈታ የሚችል ረቂቅ ሕግ እየተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢው፣ በቀጣይ መሰል ጉዳዮች በሕግ እንዲመለሱ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ነሐሴ 12 እና 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ዓመታዊ ጉባዔውን ያካሄደው ምክር ቤቱ የ2015 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የገመገመ ሲሆን፣ አዲስ ሥራ አስፈጻሚ መርጧል፡፡ በዚህም መሠረት አቶ ደስታ ዲንቃ ከመድረክ ፓርቲ ሰብሳቢ፣ አቶ መለሰ ዓለሙ ከብልፅግና ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ፣ ወ/ሮ ደስታ ጥላሁን ከኢሕአፓ ጸሐፊ፣ መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) ከቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አቶ ሙሳ አደም ከአፋር ሕዝቦች ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ አባል ሆነው ተመርጠዋል፡፡ የአዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ጎላ ብለው በሚታዩ አገራዊ ችግሮች ላይ ምክክር በማድረግ፣ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊያስማማ የሚችል ሥራ ላይ እንደሚያተኩር አቶ ደስታ ተናግረዋል፡፡