
August 23, 2023 – EthiopianReporter.com
ካለፈው ወር መገባደጃ ጀምሮ ነበር በአማራ ክልል ወልዲያ አካባቢ ግጭት ተከሰተ የሚል ዜና መሰማት የጀመረው፡፡ በቀናት ልዩነት ደግሞ በሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች ውጥረት ማየሉ መነገር ጀመረ፡፡ በሒደት ውጥረቱ ቀጥሎ በአንዳንድ ከተሞች ውጊያ መካሄዱ ተሰማ፡፡
የአማራ ክልል ግጭት አሳስቦኛል ያለው መንግሥት ችግሩ በመደበኛ የሕግ ማስከበር መንገድ ስለማይፈታ፣ ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ጀምሮ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ክልሉ በኮማንድ ፖስት ዕዝ ሥር እንዲመራ ስለማድረጉ መንግሥት አስታውቋል፡፡
ከዚያ ወዲህ በክልሉ የተፈጠሩ ለውጦችን በተመለከተ የተጠየቁ የተለያዩ የክልሉ ከተሞች ነዋሪዎች፣ በክልሉ በአንፃራዊነት ሰላምና መረጋጋት መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ያም ቢሆን ግን ከአስተዳደር፣ ከመደበኛ አገልግሎት፣ እንዲሁም ከንግድና ግብይት እንቅስቃሴ ዳግም መመለስ ጋር በተገናኘ ነዋሪዎቹ ሥጋታቸው አለመቀረፉን ነው የተናገሩት፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከወጣና ክልሉ በኮማንድ ፖስት ሥር ከሆነ በኋላ በተለያዩ ካባቢዎች የእስራት ቁጥር መጨመሩ እንዳሳሰባቸው፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አተገባበር የሚከታተል ገለልተኛ ወገን ወደ ክልሉ ገብቶ አፈጻጸሙን እንዲከታተል አለመፈቀዱ አግባብ አለመሆኑን ሲያስታውቁ ነበር፡፡
በሌላ በኩል በፍኖተ ሰላም ከተማ የድሮን ጥቃት ተፈጽሟል መባሉ፣ እንዲሁም በመርሳ ከተማ አቅራቢያ በቅርቡ ግጭት አጋጠመ መባሉ፣ በተጨማሪም በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ቢረግቡም ሙሉ ለሙሉ ሰላማዊና የተረጋጋ ሁኔታ ገና አልተፈጠረም ከመባሉ ጋር ተያይዞ፣ ክልሉን ወደ ቀደመ ሁኔታው ለመመለስ ገና ብዙ ይቀረዋል የሚለውን ሥጋት አጉልቶታል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ በክልሉ ስላለው ተጨባጭ ሁኔታ መረጃ የሚሰጡ ከመንግሥት ወገን ባይገኙም፣ በተለያዩ አካባቢዎች ከተሞች ያሉ ነዋሪዎች ግን ከእነ ሥጋቱ መደበኛ እንቅስቃሴ ስለመጀመሩ ተናግረዋል፡፡
የመርሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ኑርአዲስ አብዱ አሁን በአካባቢው ፍፁም መረጋጋት እንዳለ ይናገራሉ፡፡ የንግድ እንቅስቃሴ መኖሩን፣ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት መጀመራቸውን፣ እንዲሁም የሕዝቡ እንቅስቃሴ መመለሱን ያስረዳሉ፡፡
‹‹መርሳ ከተማ በወልዲያና በውጫሌ መካከል ነው የምትገኘው፡፡ ወደ ወልዲያ በሚወስደው መንገድ ላይ ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች ባሳለፍነው ቅድሜ ግጭት መከሰቱን ሰምተናል፤›› ያሉት ኑርአዲስ፣ ይሁን እንጂ ግጭቱ ወደ ከተማ አለመስፋፋቱን አረጋግጠዋል፡፡
በመርሳ ከተማና በዙሪያዋ በአንፃራዊነት የተረጋጋ ሁኔታ መኖሩን የተናገሩት ኑርአዲስ፣ በተለይ ከደሴ ወደ መርሳ የሚወስደው ዋና የንግድ መተላለፊያ መንገድ ችግር ያላጋጠመው መሆኑ የከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ የተረጋጋ ሆኖ እንዲቀጥል እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡ ያም ቢሆን ግን በሰው ሠራሽ ችግር እየተፈጠረ ካለው የዋጋ ንረትና የገበያ አለመረጋጋት በስተቀር፣ ንግድም ሆነ ሌላው የከተማ እንቅስቃሴ የተመለሰ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በሌሎች አካባቢ ስላለው ሁኔታ ሪፖርተር የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎችን በስልክ በማነጋገር ለማጣራት ጥረት አድርጓል፡፡ የወልዲያው ሐኪም ዶ/ር አሸናፊ ግርማ አካባቢያቸው ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለሱን ተናግረዋል፡፡ በከተማው መደበኛ የሥራ እንቅስቃሴ መጀመሩን የተናገሩት የሕክምና ባለሙያው፣ የኑሮ ሁኔታው ግን ብዙዎችን ለጉዳት እየዳረገ መሆኑን አክለዋል፡፡
‹‹የመንግሥት ሠራተኛውና አነስተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል በእጥፍና በሁለት እጥፍ እያሻቀበ ባለው የሸቀጦች ዋጋ የተነሳ በኑሮ እየተፈተነ ነው፡፡ ያም ቢሆን ግን የሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ የነበረው ግጭት በመቆሙ በአካባቢያችን የተረጋጋ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ዶ/ር አሸናፊ አክለውም የሐምሌ ወር ደመወዝ ለመንግሥት ሠራተኞች እንደተከፈለ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከሰሞኑ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ላይከፈላቸው ይችላል የሚል ወሬ እየተናፈሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ደመወዝ አይከፈለንም የሚለው ሥጋት በአካባቢው መኖሩን በመጥቀስ፣ ይህ ግን በወሬ ደረጃ ያለ ሥጋት እንጂ የተጨበጠ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከሳምንት በኋላ የነሐሴ ወር ደመወዝ ስለሚወጣ ይህን ሥጋት ያኔ ተጨባጭ መሆን/አለመሆኑን ማየት ይቻላል፤›› በማለት አክለዋል፡፡
የጎንደር ነዋሪዋ ወ/ሮ ሻሼ [የአባታቸው ስም አልተጠቀሰም] በበኩላቸው፣ ‹‹እግዚአብሔር ይመስገን አንፃራዊ ሰላምና እንቅስቃሴ አለ፤›› ሲሉ ነበር ምላሽ የሰጡት፡፡ ቢሮዎችም መከፈታቸውንና ገበያም መኖሩን የተናገሩት አስተያየት ሰጪዋ፣ ‹‹ቀጥሎ ምን ይመጣል የሚለው ሥጋት ካልሆነ በስተቀር አሁን ደህና ነን፤›› በማለት የአካባቢያቸውን ሰሞነኛ ሁኔታ ገልጸውታል፡፡ ወ/ሮ ሻሼ የሸቀጦች መገኘትና ገበያ መመለሱ ትልቅ ነገር ቢሆንም፣ በአካባቢያቸው የተከሰተው የዋጋ መናር ጉዳይ እንዲታሰብበት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ብርሃኑ ዝናቡ በበኩላቸው፣ ‹‹ትራንስፖርትም አለ፣ የመንግሥት ሥራም ከተመለሰ ሳምንት ሆኖታል፤›› ብለዋል፡፡ እሳቸው በሚሠሩበትና በሚኖሩበት አካባቢ ደመወዝ ላይከፈለን ይችላል የሚል ሥጋት አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ሰላምና መረጋጋቱ እንዲመለስ የተሠራው ጠንካራ ሥራ፣ የዋጋና የገበያ መረጋጋት በመፍጠር በኩልም እንዲደገም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት እንደገና መፈጠሩን የሚጠቁሙ ብቻ ሳይሆን፣ አሥጊ ሁኔታ ስለመኖሩ የሚጠቁሙ መረጃዎችም እየተሰሙ ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች መንግሥት ወይም የፀጥታ አካላት የከተማ አካባቢዎችን ብቻ እንጂ፣ ወጣ ያሉና ገጠራማ አካባቢዎችን ሙሉ ለሙሉ በእጃቸው አለማስገባታቸው እየተነገረ ነው፡፡
በተለይ በምሥራቅና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች ከተሞች አለመረጋጋቱ አሁንም መቀጠሉን የአካባቢው ምንጮች ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ በፍኖተ ሰላም፣ በደምበጫ፣ በአማኑኤል፣ በቡሬ፣ በጂጋ፣ በቋሪትና በሌሎች የጎጃም ዞን ከተሞችና የወረዳ ማዕከላት ሙሉ ለሙሉ መረጋጋት አለመፈጠሩን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
በአገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማኅበራትን ጨምሮ በውጭ ያሉ የሲቪክ ማኅበራትና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ በአማራ ክልል እየተፈጠረ ያለው የፀጥታ መደፍረስ እንደሚያሳስባቸው ደጋግመው በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ የአማራ ክልል ግጭት ወደ ለየለት ጦርነት እንዳያመራ ሥጋታቸውን ከሚያጋሩ ወገኖች ጀምሮ፣ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግሥት ጥረት ያድርግ የሚሉ ወገኖች በርካታ ናቸው፡፡
ግጭቱን ተከትሎ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች የንፁኃን ዜጎችን መብቶችና ነፃነቶች አደጋ ላይ እንዳይጥሉ የሚደረገው ውትወታም ከፍተኛ ነው፡፡
ያም ቢሆን ግን የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ፣ የምሥራቅ አማራ ኮማንድ ፖስትና የመከላከያ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም የአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በክልሉ ስላለው የፀጥታ ሁኔታ በቅርቡ መግለጫ በሰጡበት ወቅት የተረጋጋ ሁኔታ መፈጠሩን አስታውቀው ነበር፡፡ ለሰላምና አለመረጋጋት ምንጭ የሆኑ ያሏቸው ኃይሎች በክልሉ አለመረጋጋት ከመፍጠር ባለፈ፣ የአገሪቱን ደኅንነት አደጋ ላይ እየጣሉ መሆናቸውን መግለጫውን የሰጡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡
በዚህ መግለጫ በዋናነት የአማራ ክልል ውስጥ ለፀጥታ መደፍረስ ምንጭ የሆኑ ኃይሎች ደቅነውት የነበረው የደኅንነት አደጋ ሙሉ ለሙሉ ስለመቀልበሱ ተብራርቷል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ የኮማንድ ፖስቱ ሁሉንም የአማራ ክልል ቀጣናዎች በቁጥጥር ሥር ማስገባቱ፣ አንዲሁም የአካባቢዎቹ ሰላም ወደ ቀደመ ሁኔታው መመለሱ ተያይዞ ተገልጿል፡፡
ከአማራ ክልል የሚወጡ መረጃዎች በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች በተጨባጭ በሰላምና መረጋጋቱ ላይ የመጣ ለውጥ አለመኖሩን ያመለክታሉ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የመንግሥት መዋቅርም ሆነ የመንግሥት የፀጥታ ተቋማት ሽፋን አለመኖሩ ጭምር እየተነገረ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከመንግሥት ወገን ክልሉ በኮማንድ ፖስቱ ሥር ሙሉ ለሙሉ መግባቱና ፀጥታውም ወደ ቀደመ ሁኔታ መመለሱ ይነገራል፡፡
አማራ ክልል በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ወዴት ሊያመራ ይችላል የሚለው ጉዳይ እርግጠኝነት ባጣበት በአሁኑ ወቅት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እስከ መቼ በሥራ ላይ ይቀጥላል የሚለው ጥያቄም ገና መልስ ያገኘ አይመስልም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን የተመለከቱ ሕዝባዊ ውይይቶች በክልሉ ለማካሄድ መታቀዱ እየተነገረ ነው፡፡ ሕዝባዊ ውይይቱ ይመራበታል የተባለ ባለ 36 ገጽ የመንግሥት ሰነድ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ እየተሠራጨ ሲሆን፣ ክልሉ ያጋጠመውን ወቅታዊ ችግር ስለመፍታትና ስለአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች በሰነዱ ሰፊ ማብራሪያ መሰጠቱ ተነግሯል፡፡
በዚህ ሰነድ ገጽ ሰባት ላይ፣ ‹‹የክልሉን ሁኔታ በመሠረታዊነት ለውጥ በሚያመጣ አኳኋን ታስቦና እውነቱን ተጋፍጦ በተለይ ከሕዝቡ ጋር በመነጋገር፣ ካልተቻለ ነገም በተመሳሳይ ሽክርክሪት (Vicious Circle) ውስጥ እንደምንገኝ መተንበይ የተለየ ተሰጥኦ አይጠይቅም፤›› በማለት ለሁኔታው አፈታት ትንተና መሰጠቱ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
በአገሪቱ የተፈጠረውን የፖለቲካ ለውጥ በማምጣት የአማራ ሕዝብ የነበረውን ድርሻ፣ እንዲሁም የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ሰነዱ ይዘረዝራል፡፡ ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ልማት ጥያቄ፣ የዴሞክራሲ ጥያቄ፣ ራስን የማስተዳደር ጥያቄ፣ የአከላለል ጥያቄ፣ የሰብዓዊ መብት ጥያቄ እንዲሁም በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ጥያቄ፣ በሚል ሰነዱ የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች ይዘርዝራቸዋል፡፡ ምንም እንኳ ሰነዱ በይፋ ስለመሠራጨቱ ማረጋገጫ ባይሰጥም፡፡