በደቡብ ኢትዮጵያ ጨንቻ ውስጥ በአንድ ገበያ ነጋዴ የሆኑ ሴቶች
የምስሉ መግለጫ,በደቡብ ኢትዮጵያ ጨንቻ ውስጥ በአንድ ገበያ ነጋዴ የሆኑ ሴቶች

ከ 5 ሰአት በፊት

ኢትዮጵያ እና ፌደራሊዝም ከተዋወቁ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል።

በአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47 መሠረት የፌደራላዊ መንግሥቱ አባላት ዘጠኝ ክልሎች መሆናቸውን ያትታል።

ሕገ መንግሥቱ በዚህ ሳያበቃ በእነዚህ “ክልሎች ውስጥ የተካተቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው” ይላል።

በሕገ መንግሥቱ ከተጠቀሱት ዘጠኝ ክልሎች የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ህልውናው በይፋ አክትሟል። ለዓመታት በዚህ ስም ሲጠራ የቆየው ክልል በአራት ክልሎች እንዲዋቀር ሆኗል።

ከክልሉ ቀድሞ የወጣው የሲዳማ ክልል ነበር፤ በመቀጠልም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በተመሳሳይ አዲስ ክልል ሆኖ ተቋቁሟል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ደግሞ ሦስተኛው ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተመሠረተ ሲሆን፣ አራተኛው ደግሞ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተብሎ ተዋቅሯል።

ከሲዳማ ክልል በስተቀር አዲስ የተመሠረቱት ክልሎች በውስጣቸው የየራሳቸውን ክልል ለማቋቋም ጥያቄ ያቀረቡ የተለያዩ ብሔሮችን በውስጣቸው ይዘዋል።

ተደጋጋሚ የክልልነት ጥያቄ

የተለያዩ ክልሎችን ለመመሥረት ለረዥም ጊዜ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቷል።

በቀድሞው ደቡብ ክልል የሚገኙ ሁሉም ዞኖች፣ ክልል የመሆን ጥያቄ አቅርበው ነበር።

የፌደራሊዝም ባለሙያው ቀነኒ ጅባት (ዶ/ር) አገሪቱ ብሔር ተኮር ፌደራሊዝምን መከተል ከጀመረች ማግስት አንስቶ በቀድሞው ደቡብ ክልል የክልልነት ጥያቄዎች ተደጋግመው መነሳታቸውን ይጠቅሳሉ።

“በደቡብ የአገሪቱ ክልል የሚገኙ ብሔሮች አንድ ላይ እንዲሆኑ ቢደረጉም ወረቀት ላይ የሰፈረው ፌደራሊዝም ግን ለዓመታት ተግባራዊ አልሆነም። እነዚህ ብሔሮች የተለያየ ማንነት እና ቋንቋ ነው ያላቸው” ይላሉ።

የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ያጠኑት እና በቀድሞው ደቡብ ክልል ኮሙኒኬሽን የሠሩት አቶ ደያሞ ዳሌ ደግሞ በቀድሞ ክልል የነበሩ ፖለቲከኞች አብረው መቆየት ባለመቻላቸው ከየአካባቢያቸው ጥያቄ መቅረቡን ይገልጻሉ።

ጥያቄው ከተነሳ በኋላ ደግሞ መንግሥት መመለስ የሚችለው አሁን በተካሄደው መልኩ መሆኑን ማስታወቁን ገልጸዋል።

“ዋናው ችግር የቀድሞው ክልል ውጤታማ መሆን አለመቻሉ ነው። የድሮውን ክልል ለማስቀጠል ፖለቲከኞቹ መስማማት አልቻሉም” በማለት ዋነኛው ያሉትን የአዳዲሶቹን ክልሎች ምሥረታ ምክንያት ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ለክልልነት የሚያስፈልገውን መስፈርት ስለምናሟላ ምላሽ እንፈልጋለን የሚሉ ጥያቄዎች መደጋገማቸውን ቀነኒ (ዶ/ር) ያስታውሳሉ።

ገዢው ፓርቲ ዞኖቹ ያቀረቡትን የክልልነት ጥያቄ ካጤነ በኋላ ለሲዳማ የክልልነት ምላሽ ሲሰጥ ሌሎቹ ደግሞ በክላስተር እንዲዋቀሩ ወስኗል።

ክላስተር በተለያዩ ቦታዎች የሚሰጡ አገልግሎቶች ኖረው በማዕከል ደግሞ የማስተባበር ሥራ የሚከናወንበት አደረጃጀት ነው።

ለምሳሌ ያህል ስድስት ቀበሌዎች በጤና ክላስተር ቢዋሃዱ፤ ስድስቱም የጤና ጣቢያ ይኖራቸውና አንደኛው ቀበሌ ላይ ሆስፒታል በማቋቋም ሁሉንም ቀበሌዎች የሚያገለግልበት አሠራር ነው ሲሉ አቶ ደያሞ ያስረዳሉ።

ከሲዳማ ክልል ውጭ ያሉት ክልሎች ዞኖችን በክላስተር አጣምረው፣ ክልሎቹ እንደ አስተባባሪ የሚሆኑበት አሠራር መዘርጋቱን ገልጸዋል።

በቀድሞው ደቡብ ክልል ድምጸ ውሳኔ የተካሄደባቸው አካባቢዎች አሉ።

በቀድሞው ሲዳማ ዞን በደቡብ ክልል ለመቀጠል እና አዲስ ክልል ለመመሥረት በቀረበ ሃሳብ ላይ ሕዝበ ውሳኔ ተሰጥቷል።

በክላስተር አደረጃጀት ክልል ለመመሥረት በሕዝበ ውሳኔ ይሁንታ የሰጡት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልን መሠረቱ።

በቀድሞው ደቡብ ክልል ሥር የቀሩት ሌሎች ዞኖች ግን ሕዝበ ውሳኔ አላካሄዱም። ባሉበት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚል አዲስ ክልል ሆነዋል።

በሕዝቦች ያልተዋጠው ምላሽ

ቀነኒ (ዶ/ር) እንደሚሉት ከሆነ በሽግግር መንግሥቱ ወቅት የቀድሞው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልልን በአምስት ክልሎች እንዲዋቀር ተደርጎ ነበር።

ኢህአዴግ ሃሳቡን ወደ ጎን በማለት የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በሚል በአንድ ላይ ማዋቀሩ በክልሉ ሕዝቦች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አይደለም ይላሉ።

ይህም ጥያቄ ለዓመታት ሲንከባለል ቆይቶ በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ገፍቶ መጣ።

አቶ ደያሞ ሕዝቡ አገልግሎት የሚያገኘው በወረዳ እና በቀበሌ መሆኑን በማንሳት ተራው ሕዝብ “የክልልነት ጉዳይ ይህን ያክል የሚያሳስበው ጉዳዩ አድርጎ የሚወስደው አይደለም” በማለት “በሕዝብ ስም ነው [የክልልነት ጥያቄው] የተካሄደው” ብለዋል።

“ለደንቡ ያህል ደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ነው የሕዝብ ፍላጎት ማሳያ ተብሎ ሕዝበ ውሳኔ የተደረገው። [በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል] ሕዝበ ውሳኔ ስላልተካሄደ የሕዝብ ፍላጎት የሚለው ነገር ጭራሽም አይሠራም” በማለት የተለያየ ሂደት ተግባራዊ መደረጉን አመልክተዋል።

የጋሞ ብሔር አባላት

የተራራቁት መሥሪያ ቤቶች

እነዚህ አዳዲስ ክልሎች ከተመሠረቱ በኋላም ግን ጥያቄዎች መነሳታቸውን ቀጥለዋል።

የሚነሳው ጥያቄ ከባለሥልጣናት ሳይሆን ‘ከጀርባቸው ባሉ አክቲቪስቶች’ መሆኑንም ይናገራሉ።

ከሚነሱት ጉዳዮች አንደኛው የአዳዲሶቹ ክልሎች ዋና ከተማ እዚህ ይሁን፣ እዚህ ይሁን የሚሉ ናቸው።

“በፖለቲከኞች ደግሞ በበቂ ሁኔታ የክልል መሥሪያ ቤቶች ለእኛ አልተሰጡንም የሚል በተለይም ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከምባታ ጥያቄ እየተነሳ ነው” ብለዋል – አቶ ደያሞ።

መሥሪያ ቤቶች የተለያዩ ከተሞች መሆናቸውንም እንደ ችግር ይመለከቱታል፤ ከዚህ ጋር ተያይዞም የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ሊኖር ይችላል።

ለምሳሌ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል መሥሪያ ቤቶችን በስድስት ከተሞች ውስጥ አዋቅሯል። አንድ ሰው የኢንቨስትመንት ፈቃድ ቢፈልግ ጽህፈት ቤቱ አርባምንጭ ነው ያለው። የግብርና ቢሮው ያለው ደግሞ ዲላ ነው።

እንግዲህ በግብርና ዘርፍ ኢንቨስትመንት ፈቃድ ለማውጣት የሚፈልግ ሰው ጉዳዩን ለማስፈጸም የተለያዩ ከተሞችን መዞር ይጠይቃል ማለት ነው።

“ይህ አገልግሎት ለሚያገኝ ለተራው ሰው በጣም አስቸጋሪ አደረጃጀት ነው። ስለዚህ ክላስተር ከሕዝብ አንጻር በጣም አስቸጋሪ ነው” ብለዋል።

ሌላው ችግር ይፈጠራል ተብሎ የነበረው የዞን አደረጃጀት መሆኑን ደያሞ አንስተው “ዞን የጠየቁት በእደላ መልክ ለሁሉም ተሰጥቷል። ልዩ ወረዳ የነበረው በሙሉ ዞን በመሆኑ አሁን እሱ ጉዳይ አይደለም” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ለሁሉም ብሔሮች ክልል የመመሥረት መብትን አጎናጽፏል።

የአሁኑ ምላሽ ወደ ፊት ሌላ የክልልነት ጥያቄ ላለመነሳቱ ምንም ማረጋገጫ አይሰጥም ይላሉ አቶ ደያሞ።

በወላይታ እና በጉራጌ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መወስዳቸውንም ጠቁመዋል።

በቅርቡ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የወላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር አቶ ጎበዜ ጎአ በወላይታ የተካሄደውን ሕዝበ ውሳኔ “ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን የሚደፍጠጥ፤ ሕዝቦች የተሰጣቸውን መብት የሚነፍግ፤ ገዢዎች የሚያነሷቸውን ሃሳቦችን ወደፊት ያመጣ፣ የወላይትን ሕዝብ ጥቅም እና ህልውና የሚፈታተን አደገኛ ፕሮጀክት ነው” ብለዋል።

ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ከመውሰድ ባለፈ የወላይታ ሕዝብ የራሱን አስተዳደር እስከሚመሰረት ድረስ “ሠላማዊ እና ሕዝባዊ ትግላችንን አጠናክርን እንቀጥላለን” ብለዋል።

ይህን ከግምት በማስገባት “ጥያቄው ወደፊት እንዳይነሳ ብቻ ሳይሆን አሁንም ጥያቄው ተነስቷል። መንግሥት እንዴት አድርጎ ይመልሰዋል የሚለውን የምናው ነው የሚሆነው” ይላሉ አቶ ደያሞ።

ፖለቲከኞች “ለራሳቸው አልመች ሲላቸው፤ ሥልጣን ክፍፍል አልደረሰንም ሲሉ የሕዝብ ጥያቄ በሚል እንደገና ሊያነሱት ይችላሉ። ስለዚህ ዋስትና የለውም” ብለዋል።

ቀነኒ (ዶ/ር) ደግሞ የክልልነት ጉዳይ ከኢኮኖሚ፣ ከፖለቲካ እና ከአስተዳደር እና ከሌሎችም ጉዳዮች አንጻር መታየት አለበት ይላሉ።

“ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት አላቸው ማለት ግን ሁሉም የየራሳቸውን ክልል መመሥረት ይችላሉ ማለት አይደለም። መንግሥት የራሱን የፖለቲካ ፍላጎት እና የአገሪቷን አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት ክልልነትን ይሰጣል” ብለዋል።

“ለምሳሌ የአገው፣ የቅማንት፣ የወሎ ሕዝቦች የክልልነት ጥያቄ ቢያቀርቡ፤ ይህ የአማራ ክልልን የህልውና ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል። መንግሥት በአንድ በኩል ይህ ስጋት አለበት። በሌላ በኩል ደግሞ [በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ] ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች በሙሉ ክልልነት መስጠቱ ከቀጠለ ከ80 በላይ ክልላዊ መንግሥታት ሊኖሩ ነው። ይህም ደግሞ ለአስተዳደር እና ለበጀት አስቸጋሪ ይሆናል” ይላሉ።

በእርጋታ እና በመግባባት መፍታት

አገሪቱ ብሔር ተኮር ፌደራሊዝምን እስከ ተከተለች ድረስ የሕብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ትስስር ከግምት ውስጥ በማስገባት የክልልነት ጥያቄ እንደሚቀጥልም ቀነኒ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ጉዳዩ ማቆሚያ ያለው አይመስልም ሲሉ አቶ ደያሞም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ።

በቀድሞው ደቡብ ክልል ውጥ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት መጣደፍ አግባብ እንዳልነበርም ጠቁመዋል።

“ምክክር የሚባለው ነገር ተካሂዶ ሕገ መንግሥት ማሻሻያዎች ተደርገው፤ በእርጋታ የብዙ ሰው መግባባት ያለበት ሁሉም ፓርቲዎች የሚስማሙበት ዓይነት አደረጃጀት ለክልሉም ለመላው ኢትዮጵያም ያስፈልጋል” ብለዋል።

ሕጋዊ መሠረቱ ሳይለወጥ አሁን በክላስተር የሚመሠረተው የክልል ጉዳይ “ሌላ ጥያቄ እያበጀ ማቆሚያ የሌለው ሥራ መፍታትን፣ የሕዝብ ጭቅጭቅን እና ሞትንም ሊያስከትል ይችላል” ብለዋል።

“ከዚህ ይልቅ መፍትሄው በእርጋታ ሕገ መንግሥትን መቀየር ነው። ሕገ መንግሥት ለመቀየር ግን መጀመሪያ ሰፊ ንግግር ማድረግ ያስፈልጋል የሚል እምነት አለኝ” ሲሉ የመፍትሄ ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል።