አዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ

25 ነሐሴ 2023, 17:48 EAT

ለስድስት ወራት በሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር የሚገኘው የአማራ ክልል ምክር ቤት በዶክተር ይልቃል ከፋለ ምትክ አቶ አረጋ ከበደን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾመ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ነሐሴ 19/ 2015 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ ባካሄደው 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤው ላይ ነው አዲስ ርዕሰ መስተዳድር እንደሾመ የተዘገበው።

በክልሉ በአምስት ዓመት ውስጥ ስድስተኛ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተሾሙት አቶ አረጋ በሥራ ፈጠራ እና ሥልጠና ቢሮ ኃላፊነትም ሲያገለግሉ ነበር።

ክልሉን ሲያስተዳድሩ የነበሩት ዶክተር ይልቃል ከፋለ የመልቀቂያ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው በምትካቸው አቶ አረጋ ከበደን አዲስ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ምክር ቤቱ መሾሙ ያሳወቀው።

መስከረም 20/2014 ዓ.ም የአማራን ክልል እንዲያስተዳድሩ የተመረጡት የዶክተር ይልቃል የመልቀቂያ ጥያቄ በምክር ቤቱም ተቀባይነት አግኝቷል።

ለ23 ወራት ክልሉን በመምራት ያገለገሉት ዶክተር ይልቃል ለፓርቲያቸው የመልቀቂያ ደብዳቤ ካስገቡ ስምንት ወራት እንደሆናቸው ለምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር ላይ ጠቅሰዋል።

ሆኖም ወቅታዊ ሁኔታዎች ለመቆየት እንዳስገደዳቸው ጠቁመው “በቀውስ ወቅት ወደ ሥልጣን መጥቶ በቀውስ ወቅት ኃላፊነትን መልቀቅ ህመሙን የማውቀው እኔ ብሆንም የምችለውን ሁሉ ግን ሰጥቻለሁ፤ ጥያቄዬንም ፓርቲዬ ተቀብሎኛል” ብለዋል።

“ሕዝብ እና መንግሥት የሰጠኝን ኃላፊነት በገባኝ እና በምችለው ልክ ተወጥቻለሁ” ያሉት ዶክተር ይልቃል ላለፉት ሁለት ዓመታት ማኅበራዊ፣ ቤተሰባዊ እና የጤና ችግሮቻቸውን ተቋቁመው ማገልገላቸውን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ ባደረገው አስቸኳይ ጉባኤ በክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ መምከሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ከሁሉም በላይ መንግሥታዊ ሥርዓት መቅደምም እንዳለበት ተሰናባቹ ርዕሰ መስተዳድር ገልጸዋል።

“ከመንግሥት ውጭ የታጠቀ ኃይል መኖር መጨረሻው እንደ የመን እና ሶማሊያ መሆን ነው። ከሌሎች መማር ካልቻልን ከማን ልንማር እንችላለን” በማለት ተናግረዋል።

ምክር ቤት የክልሉን የጸጥታ ችግር ከገመገመም በኋላ ፈጻሚ አካሉን አደረጃጀት መቀየር እንዳለበት መግባባት ላይ መደረሱም ተነግሯል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ከርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ የተለያዩ ሹመቶችንም በማጽደቅ አስቸኳይ ጉባኤውን አጠናቋል።

በዚህም መሠረት ሹመታቸው የጸደቀላቸው

አዲስ ከተሾሙት ኃላፊዎች ውጪ ያሉ ሌሎቹ የክልሉ ተቋማት ላላፊዎች ባሉበት እንዲቀጥሉ ስለመወሰኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በክልሉም ወጥ የሆነ ማሻሻያ ተግባራዊ ለማድረግ መግባባት ላይ ተደርሷልም ተብሏል።

ክልሉ የገጠሙት ተግዳሮቶች

ሕዝቡን የሚያስከፉ በርካታ ተግዳሮቶች መኖራቸውን የተናገሩት ተሰናባቹ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል፣ አመራሩን ማውረድ እንዲሁም ፓርቲው በምርጫ እንዲቀጣ ማድረግ እንጂ “ኃይል በፍጹም አማራጭ ሊሆን አይገባም” ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ የፖለቲካ ትግል ውስብስብ እንደሆነም ጠቅሰው ወጥ ዓላማ፣ የጋራ ራዕይ፣ በቂ የትግል ስልት እና የሌሎችን አሰላለፍ ያልተረዳ በመሆኑ ፈታኝ አድርጎታል ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲወሰን ጥሪ ያቀረበውም ግጭቱ በጥቂት ቀናት ብቻ ከቁጥጥር ውጭ መሆኑን ተከትሎ እንደነበር አስታውሰዋል።

የአማራ ክልል ከሌሎቹ የአገሪቱ ክልሎች በተለየ ባለፉት ዓመታት በርካታ ርዕሰ መስተዳደሮች የተፈራረቁበት መሆኑ ይታወቃል።

እነዚህም አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ አቶ አገኘሁ ተሻገር እና ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ናቸው።

በዚህም ዛሬ የክልሉን መሪነት መንበር የተረከቡት አቶ አረጋ ከበደ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ስድስተኛው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነዋል።

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በመከላከያ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ሲደረጉ የነበሩ ግጭቶች ተባብሰው መቀጠላቸውን ተከትሎ ከአማራ ክልል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የቀረበለትን ጥያቄ ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ ይታወሳል።

በክልሉ በትጥቅ የተደገፈ ሕገወጥ እንቅስቃሴ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር ወደማይቻልበት ደረጃ የተሸጋገረ በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ ማወጅ አስፈላጊ መሆኑም ነው የተገለጸው።

በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተደረገው ውጊያ የሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት መቅጠፉን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት መገደላቸውን እንዲሁም የተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መንግሥታዊ መዋቅሮች መፍረሳቸው ተገልጿል።

በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት የንጹሃን ሕይወት መጥፋቱን፣ ንብረት መውደሙን እና ዘረፋ መፈጸሙን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ እንዲሁ ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ ይታወሳል።

በአማራ ክልል ዋና ዋና ከተሞችን ጨምሮ ሲካሄድ የነበረው እና ለሳምንታት የዘለቀው ግጭት በአብዛኛው መረጋጋት ማሳየቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) አስታውቋል።