
ከ 5 ሰአት በፊት
ለሁለት ዓመት ያህል ተቋርጦ የቆየው በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብፅ መካከል ሲደረግ የነበረው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ድርድር ካይሮ ላይ መጀመሩ ተገለጸ።
የሦስቱ አገራት ተወካዮች ኢትዮጵያ ወደማጠናቀቁ በተቃረበችው በአወዛጋቢው ግድብ ላይ የሚያደርጉትን ድርድር ከረጅም ጊዜ በኋላ እሁድ ነሐሴ 21/2015 ዓ.ም. መጀመራቸውን የኢትዮጵያ እና የግብፅ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
ይህ ድርድር የተጀመረው ባለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ በሱዳን ጉዳይ ላይ በተደረገ ስብሰባ ወቅት ተገናኝተው ንግግሩን ለማስቀጠል ከተስማሙ በኋላ ነው።
ሁለቱ መሪዎች በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት፣ የውሃ አለቃቅ ደንቦች እና መመሪያዎች ላይ ውይይት አድርገው መደበኛው ድርድር በፍጥነት ተጀምሮ በአራት ወራት ውስጥ ከመግባባት ላይ ለመድረስ ጥረት እንዲደረግ ተስማምተው ነበር።
በዚህም መሠረት ከሁለት ዓመታት በኋላ በተጀመረው የሦስትዮሽ የቀጥታ ንግግር በአገራቱ መካከል ስምምነት እንዳይደረስ ምክንያት በሆኑ የግድቡ የውሃ ሙሌት እና አጠቃላይ ሥራ ላይ በመነጋገር ከስምምነት ለመድረስ ታስቧል።
በሦስቱ አገራት መካከል ሲካሄድ ለዓመታት የቆየው ድርድር በመጨረሻ የተካሄደው በሚያዚያ 2013 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት ነበር። ይህ ድርድር በመጨረሻ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ዋና ከተማ ኪንሻሳ ውስጥ የተካሄደ ሲሆን ከስምምነት ሳይደረስ መቋረጡ አይዘነጋባም።
አሁን ካይሮ ላይ በተጀመረው ድርድር ላይ የቀድሞው የኢትዮጵያ የውሃ ሚኒስትር እና በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ስለሺ በቀለ (ዶ/ር፣ ኢ/ር) የአገሪቱን ተደራዳሪ ቡድን እንደሚመሩ ታውቋል።
በግብፅ በኩል ደግሞ የመስኖ እና የውሃ ሃብት ሚኒስትሩ ሃኒ ሴዊላም የአገራቸውን ተደራዳሪ ቡድን የሚመሩ ሲሆን፣ አገራቸው በሕዳሴው ግድብ የውሃ አሞላል እና አጠቃላይ ሥራ ላይ ሕጋዊ እና አሳሪ ስምምነት እንዲደረስ ፍላጎት እንዳላት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን መሪ አምባሳደር ስለሺ ባደረጉት ንግግር “የኢትዮጵያን የአሁን እና የወደፊት ትውልድ ጥቅም ለማስጠበቅ በአባይ ውሃ የመጠቀም መብት መሠረታዊ” መሆኑን መግለጻቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
- ኢትዮጵያ እና ግብፅ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ንግግር ለመጀመር እና ከስምምነት ለመድረስ ተስማሙ13 ሀምሌ 2023
- ኢትዮጵያ የግድቡን ውዝግብ “ለጊዜ መግዣነት እየተጠቀመችበት ነው” ስትል ግብፅ ከሰሰች13 ሚያዚያ 2023
- ግብፅ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ “ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው” ማለቷ ኢትዮጵያን አስቆጣ17 መጋቢት 2023
የግብፅ ሚኒስትርም በበኩላቸው በአገራቱ መካከል “ሕጋዊ እና አሳሪ ስምምነት ሳይደረስ” በኢትዮጵያ በኩል የቀጠለውን የግድቡ የውሃ ሙሌት እና ሥራ ቀደም ስል የተደረሰውን የመርሆዎች ስምምነት የሚጥስ መሆኑን በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰው “ሁሉም ወገኖች የተናጠል እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠቡ” የግብፅን ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ በኩልም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ለሦስቱ አገራት የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን አምባሳደር ስለሺ ጠቅሰው፣ “ኢትዮጵያ በፍትሃዊ እና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት መርኅ ላይ የተመሠረተ አቋሟን አጠናክራ እንደምትቀጥል” መግለጻቸው ተዘግቧል።
የኢትዮጵያም ሆነ የግብፅ ባለሥልጣናት ከረጅም ጊዜ መቋረጥ በኋላ መልሶ የተጀመረው ድርድሩ በመግባባት እና በስምምነት እንዲጠናቀቅ ፍላጎት እንዳላቸውን እንዲሁም አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል።
የግብፁ የመስኖ እና የውሃ ሚኒስትር ጨምረውም በአገራቱ መካከል ላሉ አወዛጋቢ ጉዳዮች የሁሉንም ጥቅም የሚያስጠብቁ የቴክኒክ እና የሕግ መፍትሄዎች ለማግኘት ዕድሎች እንዳሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ከአስር ዓመታት በላይ ላስቆጠረው ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ያወጣች ሲሆን፣ በተወሰነ ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩም ይታወቃል።
ሱዳን እና ግብፅ ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለው ግድብ የውሃ አቅርቦታችንን ይጎዳብናል በማለት ተቃውሞ ሲያሰሙ ቆይተዋል። ድርድሮች በሚካሄዱበት ጊዜም ኢትዮጵያ አሳሪ እና ሕጋዊ ስምምነት እንደትፈርም ቢወተውቱም በኢትዮጵያ በኩል በወንዙ የመጠቀም መብቴን የሚጋፋ ነው በሚል ሳትቀበለው ቆይታለች።
ግብፅ ግድቡ ከአባይ ወንዝ የማገኘው የውሃ መጠንን ይቀንስብኛል በማለት በግድቡ ዙሪያ ያላትን ተቃውሞ አስከ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት ወስዳዋለች።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት እየተጠናቀቀ ያለውን የታላቁን ሕዳሴ ግድብ በውሃ የመሙላት ተግባርን በክረምት ወራት የታችኛውን ተፋሰስ አገራት በማይጎዳ መልኩ በተሳካ ሁኔታ አከናውናለች።
አራተኛው በዚህ ዓመት ይከናወናል የተባለው የውሃ ሙሌት የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ፍላጎት ባገናዘበ ሁኔታ አስከ መስከረም ድረስ እንደሚከናወን ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መናገራቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ የግድቡ ግንባታ እና ሙሌት ሳይቋረጥ ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር ንግግር ለማድረግ ፍላጎት እንዳለት በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።
ግብፅ እና ሱዳን ግን ከሁሉ በፊት ሕጋዊ እና አሳሪ ስምምነት መደረግ አለበት በማለት የኢትዮጵያን የንግግር ጥያቄ ሲቃወሙት መቆየታቸው አይዘነጋም።
አሁን በሦስቱ አገራት ተጀመረ የተባለው ስምምነት መቼ እንደሚጠናቀቅ ያልተገለጸ ሲሆን፣ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያለቸው ሱዳን በማን እንደምትወከል እና ስለድርድሩ በይፋ ያለችው ነገር የለም።