የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የያዙ ሰዎች

ከ 9 ሰአት በፊት

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት አገሪቷን ለፀጥታ እና ደኅንነት ስጋት አጋልጧታል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት የዘለቀው ጦርነት፣ በኦሮሚያ እንዲሁም ከቅርብ ወራት ወዲህ በአማራ ክልሎች የሚካሄዱት ግጭቶች በአገሪቱ ውስጥ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ተደምሮ ኢትዮጵያን ከገጠሟት ችግሮች የተወሰኑት ናቸው።

በተለያዩ ስፍራዎች የተከሰቱት ግጭቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንዲሞቱ፣ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አንዲሁም ንብረታቸው እንዲወድም አድርጓል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ጦርነት በሰላም ስምምነት ቢቋጭም፣ በኦሮሚያ ያለው ግጭት ያለምንም መፍትሄ እንደቀጠለ ይገኛል። ይህ በእንዲህ እያለ ነው በአማራ ክልልም አዲስ ግጭት የተቀሰቀሰው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የተለያዩ የፖለቲካ ለውጦች ቢወደሱም፣ በተለያየ ጊዜ በተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ እና እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶችን በፍጥነት መፍታት አለመቻላቸው ግን አገሪቱን የፀጥታ ስጋት ውስጥ ጥሎታል።

ለመሆኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አንኳር ችግሮች ምንድን ናቸው?

አሁን ኢትዮጵያ ላለችበት የፖለቲካ ችግር መንስዔው ዘርፈ ብዙ እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።

በበርኒንግሃም ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት ብዙነህ ጌታቸው (ዶ/ር) መሠረታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጥያቄ በሁለት ዓለም የፖለቲካ ዕይታ መካከል ያለ ግጭት ነው ይላሉ።

እኚህ ምሁር አገሪቷ ብሔር ተኮር ፌደራሊዝም በሚከተሉ እና አሃዳዊነትን በሚያቀነቅኑ መካከል መወጠሯን ያስረዳሉ።

የኢህአዴግ መንግሥት ከሥልጣን ከወረደ በኋላ የፌደራሊዝም ሥርዓትን የሚያቀነቅኑ እና መቀጠል አለበት ብለው የሚያምኑ ቡድኖች “ራሳችንን በራሳችን እናስተዳድር” የሚል ጥያቄያቸው እንደጨመረ የደቡብ ክልልን በአስረጅነት በማንሳት ብዙነህ (ዶ/ር) ይናገራሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን የፌደራሊዝም ሥርዓት የሚቃወሙ እና “አገሪቱን ይከፋፍላታል፣ ያዳክማታል” የሚሉ ወገኖች ድምጻቸውን ማሰማት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በዚህ የሐሳብ ፍጭት መካከል ችግር እየተፈጠረ እንደሆነ ብዙነህ (ዶ/ር) ያስረዳሉ።

በአገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየት በመስጠት የሚታወቀው እያስፔድ ተስፋዬ ደግሞ፣ መሠረታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር “በአገሪቱ ውስጥ ተቃራኒ ጫፍ የቆሙ ሐሳቦች እና እነዚህን ሐሳቦችን አስማምቶ አለማስኬድ ነው” ይላል።

“ኢትዮጵያ አገረ ግንባታ ያላለቀባት አገር ናት” የሚለው እያስፔድ፣ ከ2011 ዓ. ም. ወዲህ እነዚህ ጫፍ የረገጡ ሐሳቦች ያለውን ችግር የበለጠ እንዳባባሱት ይጠቅሳል።

እያስፔድ እንደሚለው መንግሥት እነዚህን ሐሳቦችን አስማምቶ ለአገር ግንባታ ከማዋል ይልቅ፣ “ከግጭቶቹ በሚያገኘው ጥቅም ላይ አትኩሯል” ይላል።

በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ በግጭት እና ግጭት አፈታት ላይ ጥናት የሚሰሩት ዶ/ር መብራቱ ከለቻ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ እና የነበሩ የፖለቲካ ችግሮች ከአገሪቷ አመሠራረት ጋር ተያይዘው የመጡ የብዙ ምክንያቶች ድምር ውጤት መሆኑን ይናገራሉ።

ይህንንም ሲያብራሩ፣ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር መሆኗን በማስታወስ፣ በንጉሣዊ እና በወታደራዊ አገዛዝ ውስጥ ያለፈች መሆኗ እንዲሁም ባለፉት ሥርዓቶች ውስጥ የተፈፀሙ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች እና ወንጀሎች መፍትሄ አለማግኘታቸው አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ይጠቅሳሉ።

አክለውም እነዚህ በታሪክ ውስጥ የተፈጠሩ ቅራኔዎች ሳይፈቱ እዚህ መድረሳቸው አገሪቱ ላለችበት የግጭት አዙሪት ምክንያት መሆናቸውን ይናገራሉ።

“ግልጽ የፖለቲካ መስመር አለመኖር”

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭትን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ በአገሪቱ ውስጥ የሰላም እጦት እና ቀውስ የተፈጠረው በብልጽግና አስተዳደር “ግልጽ የሆነ የፖለቲካ መስመር ካለመኖሩ የተነሳ ነው” ሲል ገልጾ ነበር።

ፓርቲው በዚህ መግለጫው “ለተፈጠረው አለመረጋጋት መንስዔ የብልጽግና መሪዎች ግልጽ የሆነ የፖለቲካ መስመር ላይ አለመቆማቸው እና አቋምም ሆነ አቅም የላቸውም” በማለት ይወቅሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከወሰዷቸው እርምጃዎች መካከል በአራት ፓርቲዎች ግንባርነት ይመራ የነበረውን የኢህአዴግ ፓርቲ አፍርሶ ሁሉን ያቀፈውን ብልጽግናን መመሥረት ነው።

ከዚህ አኳያ ፓርቲው ይቋቋም እንጂ መጥፎም ይሁን ጥሩ እንደ ኢህአዴግ ጊዜ ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ፕሮግራም እንደሌለው እያስፔድ ይተቻል።

“ኢህአዴግ ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ፕሮግራም፣ ድሃን ማዕከል ያደረገ ስትራቴጂ ነበረው። ልማታዊ ስትራቴጂን ይከተል ነበር። ውጤታማ ነው ወይስ አይደለም የሚለው አንዳለ ሆኖ ማለት ነው።

አህሎም “ብልጽግና ከተመሠረተ ወዲህ ግን እኛ ‘ፕራግማቲስት ነን። በሁኔታ ላይ ተመሥርተን ነው የምንንቀሳቀሰው እንጂ፣ ቋሚ የሆነ መስመር የለንም።’ ብለው በግልጽ ሲናገሩ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የተወሰነ ወደ ልማታዊ መንግሥት አቅጣጫ እየተመለሱ ነው የሚመስሉት። ቢሆንም ግልጽ የሆነ አቋም የላቸውም” ይላል።

የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የያዙ እናት

የፖለቲካ ምሁሩ ብዙነህ (ዶ/ር) ግን ይህንን ሐሳብ አይደግፉም። አገሪቷን እያስተዳደረ ያለው መንግሥት ከኢህአዴግ የተለየ የፖለቲካ ፕሮግራም እንደሌለው እና የድሮውን አስተዳደር ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ የሚሠራ እንደሆነ ይከራከራሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጣው በኦሮሚያ ውስጥ ብሔር ተኮር ፌደራሊዝምን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ትግል ለማድረግ ተቃውሞ በወጡ ወጣቶች የተነሳ መሆኑን በመግለጽ፣ ከኢህአዴግ የተለየ የፖለቲካ ፕሮግራም ያለው አይደለም ብለዋል።

“የፖለቲካ አመለካከቱ [የዐቢይ መንግሥት] የፌደራሊዝም ሥርዓትን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ይመስለኛል። ይህንን በግልጽ የሚያሳየው ደግሞ ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ ተጨማሪ አራት ክልሎች መፈጠራቸው ነው።

“ይህ ማለት ፌደራሊዝምን ያቀነቅናል ማለት ነው። ተጽፎ ሥራ ላይ ሳይውል የነበረው ሕገ መንግሥት ለብዙ ዓመታት ይነሳ የነበረውን የሕዝብ ጥያቄ መልሷል። ይህ መንግሥት ፌደራሊዝምን ማስቀጠል ይፈልጋል። በዚህ ላይ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለም” ይላሉ።

“ከኃይል እርምጃ በፊት መነጋገር ይቅደም”

ኢትዮጵያ “ትንንሽ አገራት ያቀፈች አገር ናት” የሚለው እያስፔድ፣ ጫፍ የረገጡ የፖለቲካ አመለካከቶችን አንድ ላይ ለማምጣት ከመንግሥት ብዙ እርምጃ መሄድ ይጠበቃል ሲል ያክላል።

“የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶችን እንደ ዕድል በመጠቀም ለራሱ የፖለቲካ ፍላጎት ለማዋል መሥራቱን ትቶ እንደ ብሔራዊ ምክክር ያሉ ነገሮችን በመጠቀም እነዚህን ችግሮች መፍታት ይችላል።”

በሌላ በኩል እንደ ኢዜማ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሁን ያለው መንግሥት ግልጽ የሆነ የፖለቲካ መስመር የለውም በማለት የወደፊት የአገሪቱ ፖለቲካ ዕጣ ፈንታ አስጊ መሆኑን ያስቀምጣሉ።

ብዙነህ (ዶ/ር) ደግሞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች፣ ለአገሪቱ ሰላም አስጊ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ አሁን ያለው ችግር በቅርብ ጊዜ ይፈታል ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ።

ያሉትን ችግሮች በኃይል ብቻ መፍታት ሳይሆን የምክክር እና የፖለቲካውን ዐውድ በማስፋት አገሪቷን ማረጋጋት ወሳኝ እንደሆነ ይመክራሉ።

በሰሜን ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመታት ደም አፋሳሽ ግጭት በኋላ በስምምነት የተቋጨው ጦርነት፣ ለአገሪቷ አደጋ ሆኖ እንደነበር የሚናገሩት ምሁሩ “የትግራይ ጦርነት በሰላም መጠናቀቁ አገሪቷ በተወሰነ መልኩ እንድትረጋጋ ረድቷታል” ብለዋል።

አክለውም በአገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ልዩነቶችን ሁሉ ኃይል በመጠቀም ብቻ መፍታት እና ሰላም ማምጣት ስለማይቻል፣ በተቻለ መጠን ችግሮችን በንግግር እና በውይይት እንዲሁም ደኅንነትን በማጠናከር ወደ መረጋጋት ማምጣት ይቻላል ይላሉ።

እያስፔድ በበኩሉ፣ መንግሥት ለሚነሱ ጥያቄዎች ሁሌም በኃይል እርምጃ ምላሽ ለመስጠት መሞከሩ እንደማያስኬድ ጠቅሶ፣ አሁን ባለው አያያዝ መንግሥት አካሄዱን ካላስተካከለ በቅርብ ጊዜ ወደ ሰላምና መረጋጋት አገሪቱን ማምጣት ከባድ መሆኑን ይናገራል።