መፈንቅለ መንግሥት የፈጸሙት የጦር አመራሮች

ከ 4 ሰአት በፊት

በጋቦን ያሳለፍነው ቅዳሜ የተካሄደውን ምርጫ ውጤት በመሻር ወታደራዊ አመራሮች ፕሬዝዳንት አሊ ቦንጎን ከሥልጣን አንስተው መንበሩን መቆጣጠራቸውን አሳወቁ።

በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ወታደራዊ አመራሮች ባስተላለፉት መልዕክት የጋቦንን አስተዳደር ይዘናል ብለዋል።

ጋቦን 24 በተባለው ጣቢያ ከቀረቡት ወታደሮች አንደኛው “ይሄንን ሙሰኛ አስተዳደር በማስወገድ ሰላምን ለማስፈን ወስነናል” ብሏል።

“አስተዳደሩ ኃላፊነት የጎደለውና ወዴት እንደሚሄድ የማይታወቅ ስለሆነ የአገሪቱን ማኅበራዊ ኑሮ በማመሳቀል ወደ ቀውስ ከቶናል” ሲልም አክሏል።

በብሔራዊ ቴሌቭዥኑ የቀረቡት 12 ወታደሮች የምርጫውን ውጤት እንደሰረዙት ገልጸዋል።

በምርጫው ፕሬዝዳንት አሊ ቦንጎ ማሸነፋቸው ተገልጾ ነበር።

የምርጫ ኮሚሽን እንዳለው ፕሬዝዳንት አሊ ቦንጎ ሁለት ሦስተኛ ድምጽ አግኝተው ምርጫውን አሸንፈዋል።

ተቃዋሚዎች በተቃራኒው ምርጫው ተጭበርብሯል ብለዋል።

በወታደራዊ አመራሮች ከሥልጣን ተወግዷል የተባለው የአሊ ቦንጎ ቤተሰብ ጋቦንን ለ53 ዓመታት መርቷል።

ፕሬዝዳንት አሊ ቦንጎ ምርጫውን ማሸነፋቸውን ቢገልጹም ከጋቦን ተቃዋሚዎች በተጨማሪ ሲቪል ማኅብረት በምርጫው ላይ ጥያቄ አንስተዋል።

በተለይም ዋነኛው ተቃዋሚ አልበርት ኦንዶ ኦሳ እንዳሉት በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ የእሳቸው ስም አልተጻፈም።

የተቃዋሚዎች ጥምር የሆነው ‘አሊያንስ 2023’ እንዳለው ደግሞ አልበርት ኦንዶ ኦሳን በመደግፍ ከፕሬዝዳንታዊ ውድድሩ ራሳቸውን ያገለሉ እጩዎች ስማቸው በድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ ታትሞ ተገኝቷል።

አሊ ቦንጎ
የምስሉ መግለጫ,መፈንቅለ መንግሥት የተፈጸመባቸው አሊ ቦንጎ

የ64 ዓመቱ አሊ ቦንጎ ለሦስተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንት ለመሆን ባደረጉት የምርጫ ውድድር የ69 ዓመቱ አልበርት ኦንዶ ኦሳ ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ነበሩ።

የምርጫ ታዛቢዎች እንዲሁም ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ምርጫው ላይ ክፍተቶች እንደነበሩ ገልጸዋል።

የሲቪል ማኅበራት፣ የማዕከላዊ አፍሪካ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማኅበር ምርጫው ላይ ጥያቄ አንስተዋል።

አሊ ቦንጎ ጋቦንን ለ14 ዓመታት መርተዋል። አባታቸው ኦማር ቦንጎ እአአ 2009 ሲሞቱ ነው ሥልጣን የጨበጡት።

ዋነኛው ተቀናቃኝ አልበርት ኦንዶ ኦሳ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያደርጉ “ጋቦን የቦንጎ ቤተሰብ የግል ንብረት አይደለችም” ብለው ተችተው ነበር።

አሊ ቦንጎ እአአ 2018 ላይ የጤና መቃወስ አጋጥሟቸው ለአንድ ዓመት ያህል ከአመራር ርቀው ቆይተዋል። በወቅቱ ሥልጣን እንዲለቁ ጫና ሲደረግባቸውም ነበር።

ይህ በሆነ በዓመቱ ደግሞ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተደርጎባቸዋል። ከከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት ጀርባ የነበሩ ወታደሮች መታሰራቸውም ይታወሳል።