የኤች አይቪ የምርመራ ውጤት

ከ 5 ሰአት በፊት

ባለፉት ወራት የኤችአይቪ ኤድስ ምርመራ በከፊል አገልግሎት በተጀመረባት ትግራይ በርካታ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው እየተገኘ መሆኑ እየተነገረ ነው።

ከሆስፒታሎች፣ ከትግራይ ጤና ቢሮ፣ ከፀረ ኤችአይቪ ማኅበራት እና ከሌሎችም በጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚወጡ መረጃዎች በሕብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ስጋት የሚፈጥር “ወረርሽኝ” እንዳለ ያሳያሉ።

ወረርሽኙ ከ25 ዓመት ዕድሜ በታች በሆኑ ወጣቶች ላይ ከፍተኛ እንደሆነ የትግራይ ጤና ቢሮ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

በመቀለ ሆስፒታል ስር የሰደዱ በሽታዎች እና የኤችአይቪ መድኃኒት ተጠቃሚዎች አስተባባሪ ወይዘሮ ሕይወት አረጋዊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ባለፉት ወራት በሆስፒታሉ ከተደረጉት ምርመራዎች መካከል ብዙዎቹ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ይገኛል።

ቢቢሲ ወ/ሮ ሕይወትን በስልክ ያነጋገረው ሰኞ ረፋድ ላይ ነበር። በየቀኑ በአማካኝ ከ20 እስከ 25 ሰዎች የሚመረመሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከልም ቢያንስ ሁለቱ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ ትናግረዋል።

“ከዚህ በፊት በወራት ውስጥ በጥቂት ሰዎች ላይ ነበር ቫይረሱ የሚገኘው። አሁን ግን ከሦስት እስከ አራት እያገኘን ነው። በስልክ እስካወራንበት አስካሁን ድረስ ብቻ ወደ ሦስት የሚጠጉ ሰዎች አግኝተናል” ብለዋል።

ይሁን እንጂ ተመርምረው ራሳቸውን ማወቅ ያለባቸው የሕብረተሰቡ ክፍሎች አሁንም ወደ ምርመራ እየመጡ ነው ብለው አያምኑም።

ለዚህም ምክንያቱ መመርመሪያው ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ መቆየቱ እንዲሁም የሁለተኛ እና የሦስተኛ የኤችአይቪ መመርመሪያ መሳሪያዎች እጥረት በመኖሩ ነው።

በትግራይ ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት በክልሉ የሚገኙ ዋና ዋና ሆስፒታሎች እና የጤና ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። የተቀሩት በመድኃኒት እና በመመርመሪያ መሳርያዎች እጥረት ተጎድተው መቆየታቸው ይነገራል።

በወቅቱ የጤና ባለሙያዎች ጓንት አጥበው ሲጠቀሙ እና ነፍሰ ጡር እናቶችን ለመመርመር ሲቸገሩ ነበር። በነፃ የሚታደል ኮንዶም እና የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቶችን መስጠት አቁመውም ነበር። በርካታ ባለሙያዎች ደግሞ ክልሉን ለቅቀው ወጥተዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ከፍተኛ የሆነ የመመርመሪያ እና የመድኃኒት እጥረት እንዳለ እና በውስን አቅርቦቶች እየተደረጉ ያሉ ምርመራዎች የቫይረሱ ሥርጭት “በጣም ሰፊ” መሆኑን የሚያሳዩ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልጿል።

“በ37 የጤና ተቋማት በተደረገው ሙከራ የኤችአይቪ ሥርጭት ከ1.8 እስከ 10.5 በመቶ መሆኑን ያሳያል” የሚሉት በቢሮው የኤችአይቪ አጠቃላይ መከላከል እና መቆጣጠር አስተባባሪ አቶ ፍስሐ ብርሃኔ፣ ኮንዶም እና ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ለመከላከል ለነፍሰ ጡር እናቶች የሚሰጥ መድኃኒት አለመኖሩን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሕክምና ባለሙያዎች እና ባለሥልጣናት እንደሚሉት በጦርነቱ ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ወሲባዊ ጥቃቶች ለቫይረሱ መስፋፋት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

“[በክልሉ] ከ120,000 በላይ ሴቶች ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ አምስት በመቶው የኤችአይቪ ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል” ይላሉ አቶ ፍስሐ።

ይህም የቫይረሱ ሥርጭት በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ይታያል የሚሉት ወይዘሮ ሕይወት “ተገቢው ጥናት ተደርጎ ቫይረሱ ያለበትን ደረጃ ለማወቅ በተደጋጋሚ እየጠየቅን እንገኛለን፤ ነገር ግን በፊት እንደነበረው መርጣችሁ መርምሩ [‘ታርጌት ቴስቲንግ] ነው የሚባለው። ነገር ግን መላው ሕብረተሰብ መመርመር አለበት” ብለዋል።

“ታርጌት ቴስቲንግ” ማለት ተጋላጭ በሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ብቻ የሚያተኩር የኤችአይቪ ምርመራ ሲሆን፣ እነዚህም በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች፣ የረዥም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ ኤችአይቪ በደማቸው ካለባቸው ወላጆች የተወለዱ ህጻናት፣ ነፍሰ ጡር እናቶች እና በተፈናቃይ ማዕከላት የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው።

የተለፋበት የኤችአይቪ መከላከል ወደ ኋላ ይመለስ ይሆን?

ከ20 ዓመታት በላይ የኤችአይቪ/ኤድስን ሥርጭት ባለበት እንዲቆም እና አዳዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ለመታደግ ስትሠራ የቆየችው ወይዘሮ መልከአ አስገዶም አሁንም እንደገና ‘ራሳችሁን አድኑ’ የሚል ዘመቻ ላይ ትገኛለች።

በ1993 በደሟ ውስጥ ቫይረሱ እንዳለ ካወቀች ጀምሮ በማስተማር እና ከሌሎች ቫይረሱ በደማቸው ከሚገኝ ሰዎች ጋር በመሆን ተጎጂዎችን ስትንከባከብ እና ስታስተምር ቆይታለች፤ አሁንም እያስተማረችም ነው።

ላለፉት ሁለት ዓመታት እርሷ እና ሌሎች ቫይረሱ በደማቸው ያለ ሰዎች በትግራይ ክልል ውስጥ ባጋጠመው የመድኃኒት እና የገንዘብ እጥረት ምክንያት በቂ መድኃኒት ሳያገኙ ቆይተዋል።

ተስፋ ሕይወት የትግራይ ሴቶች ኤችአይቪ/ኤድስ ማኅበር ዋና ዳይሬክተር መልከአ አስገዶም፣ በአሁኑ ወቅት በትግራይ እየታየ ያለው መዘናጋት እና ሥርጭት ከ20 ዓመታት በፊት የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳታል።

“በጣም የደከምንበት ሥራ ወደ ዜሮ እየተመለሰ ይሆን?” ብላ ትጨነቃለች።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በተለይም ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ሴቶች ቤት ውስጥ መዋል ሲጀምሩ “ያኔ ሴቶች ላይ የተለያዩ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። በዚህ ምክንያት ለኤችአይቪ፣ ለፊስቱላ እና ለመሳሰሉት የጤና ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ነበሩ” ትላለች።

የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ያጠፋው ጦርነትን ተከትሎ ብዙ ወጣቶች እና ጎልማሶች ወደ ጦር ሜዳ ሄደዋል፤ ሚሊዮኖችም ተፈናቅለዋል።

“በመድኃኒት እጦት ተጎድተው የቆዩት በአስገድዶ መድፈር እና በድብደባ ለተለያዩ ችግሮች እና ሞት ተጋልጠዋል። ወደ ሜዳ የወጣው ደግሞ ‘ነገ መሞቴ ለማይቀር’ የሚል መንፈስ ስለነበረ ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሲፈጽም ቆይቷል” ስትል ትናግራለች።

እነዚህም የቫይረሱ ሥርጭት እንዲባባስ ካደረጉት እና ስርጭቱ በትክክል እስከማይታወቅ ደረጃ ድረስ ለመድረሱ ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል ሊሆኑ እንደሚችሉ ትጠቁማለች።

ተስፋ ሕይወት የትግራይ ሴቶች ኤችአይቪ/ኤድስ ማኅበር በመቀሌ እና አካባቢው 1017 አባላት ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህም 54ቱ ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ ናቸው።

ኤችአይቪ በኢትዮጵያ ከሦስት ክልሎች በስተቀር አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የፌደራል ኤችአይቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ይፋዊ መረጃ ያሳያል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህም ጋምቤላ፣ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ አፋር፣ ትግራይ፣ አማራ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆናቸውን ገልጾ አስጠንቅቋል።

እ.ኤ.አ. በ2016 የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው በትግራይ የነበረው የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭት 1.24 በመቶ የነበረ ሲሆን አሁኑ ጨምሯል።

በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በ2019 ያደረገው ጥናት በትግራይ የቫይረሱ ስርጭት 1.3 በመቶ እንደነበር ያመለክታል።

በዓለም ጤና ድርጅት ሕግ መሠረት ከጠቅላላው ሕዝብ ከአንድ በመቶ በላይ የሚሆነው በበሽታው ከተያዘ እንደ ወረርሽኝ ይቆጠራል። ምንም እንኳን ብሔራዊ የሥርጭት መጠኑ ወረርሽኝ ባይባልም ሰፊ የቫይረሱ ሥርጭት እንዳለ አያጠራጥርም።

ከጦርነት በፊት በትግራይ የኤችአይቪ ሥርጭት መጠን 1.43 በመቶ እንደነበር የሚጠቅሱት በክልሉ ጤና ቢሮ የአጠቃላይ ኤችአይቪ መከላከል እና መቆጣጠር ዋና አስተባባሪ አቶ ፍስሐ ብርሃኔ፣ በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ “በስፋት እየተሰራጨ” እንደሆነ ይገልጻሉ።

ከጦርነቱ በፊት በትግራይ ቫይረሱ በደማቸው የነበረ ከ43,000 በላይ ጎልማሶች እና ከ3,000 በላይ ህጻናት ነበሩ የሚሉት አቶ ፍስሃ “ከጦርነቱ በኋላ ባደረግነው ቅኝት ወደ 33,000 የሚደርሱ የመድኃኒት ተጠቃሚዎች አሉን” በማለት የተቀሩት ሞተው ወይም ወደሌላ አካባቢ ሄደው ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።

በምዕራብ እና ደቡብ ዞን አካባቢ እንዲሁም ኢሮብ የሚኖሩ ተጠቃሚዎችም በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንደማያውቁ የሚናገሩት አቶ ፍስሐ “ኤችአይቪ በቀን እስከ 1,000 ሰዎች የሚገድልበት ጊዜ ነበር። እስከ 40 ዓመት ድረስ የማይኖርበት ጊዜ ነበር። የዘመናችን ወጣቶች ይህን አያውቁም” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የኤች አይቪ መመርመርያ

“ኮንዶም ወዴት አለህ. . .”

አቶ ርእሶም ወረደ በሽሬ እንዳ ሥላሴ ከተማ የጤና ቁጥጥር ኃላፊ ነው። በአካባቢው የመመርመሪያ መሳሪያዎች ባለመኖራቸው የቫይረሱ ትክክለኛ ሥርጭት እስካሁን አለመረጋገጡን ይናገራል።

“የኮንዶም እጥረት አለ። ሰዎች ሳይመረመሩ እየተጋቡ ነው። ልቅ የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዳለም እንጠረጥራልን። ጠፍተው የነበሩ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች ሳይቀር እየታዩ ነው። እነዚህ ለኤችአይቪ ሥርጭት ዋና አስተዋፅዖ ያበረክታሉ” ይላል።

በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላት የመመርመሪያ ኪት እና ኮንዶም በአፋጣኝ በማቅረብ ተጨማሪ ምርመራዎችን ማድረግ እንደሚገባ ተናግሯል።

ትግራይ ውስጥ ካሉት ምክንያቶች በተጨማሪ የወጣቶች የኤችአይቪ ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን እና ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ እንደ ቡና ቤቶች፣ ጫት እና አደንዛዥ እጽ ተጠቃሚዎች መበራከታቸው ለሥርጭቱ ምክንያት መሆናቸውን አስተያየት ሰጪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለምሳሌ ቢቢሲ ከትግራይ ክልል ንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት በመቀለ 1,998 ቡና ቤቶች እና የምሽት ክለቦች እንዲሁም 111 የጫት ፍቃድ የወሰዱ ነበሩ። በአሁኑ ወቅት ግን ቁጥራቸው እንደጨመረ የጤና ቢሮው መረጃ ያሳያል።

የትግራይ የኦሳድ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ይርጋ ገብረእግዚአብሄርም በተፈጠረው ግጭት የጤና መዋቅሮች፣ ፀረ ኤድስ ክበቦች እና ድርጅቶች እንዲሁም የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያዎች ሰንሰለት ፈርሷል ይላል።

“እነዚህ የሉም ማለት ምርመራ የለም ማለት ነው” ሲልም ሃሳቡን ያጠናክራል።

በተጨማሪም በጦርነቱ ምክንያት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በመዘጋታቸው ከባድ ችgእሮች እንዳሉ ይጠቅሳል።

የእነዚህ ችግሮች ጥምር ተጽእኖ ብዙ ሰዎች ራሳቸውን ወደ አሉታዊ ችግሩን የመቋቋሚያ ዘዴዎች ለምሳሌ ወደ ወሲብ ንግድ እንዲገቡ አድርጓቸዋል ይላል አቶ ይርጋ።

በወቅቱ የበሽታው መከላከያ ዘዴ፣ የመመርመሪያ መሳሪያ አልነበረም፤ በጦርነቱ ወቅት የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከል ትምህርት ቆሞ ነበር። “በአጠቃላይ በክልሉ ኤችአይቪ እንዲጨምር እንጂ እንዲቀንስ የሚያደርግ ሁኔታ አልነበረም” ሲል ያስረዳል።

ይህንንም መነሻ በማድረግ ከአንድ ወር ተኩል በፊት የኤችአይቪ ኮንፈረንስ በትግራይ የተካሄደ ሲሆን የመድረኩ ተሳታፊዎች ሁለት ዋና ዋና የውሳኔ ሃሳቦች እንዲተገበሩ ጠይቀዋል።

አንደኛው ኤችአይቪ በመንግሥት ደረጃ ትልቅ ስጋት መሆኑን ማወጅ ሲሆን፣ ሁለተኛው ለዚህ የሚረዳ ግብዓት እንዲዘጋጅ ጥሪ ቀርቧል።

“የቫይረሱን ሥርጭት ለመቀነስ እና የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ለ28 ዓመታት ደክመናል” የሚለው አቶ ይርጋ፣ ይህ ሁኔታ ወደ ኋላ ተመልሶ ሰዎች ሁኔታውን የማያውቁበት ደረጃ ላይ እንደተደረሰ ይገልጻል።

“ይህ ደግሞ ሰው ሰራሽ የሆነ የፖለቲካ ስህተት ውጤት መሆኑን ሳስብ ያሳዝነኛል። ያለፉት ሁለት ዓመታት ጦርነት መቅረት የሚችል አሳዛኝ ክስተት ነው። በዚህም ምክንያት ሰዎች በመድኃኒት እጦት ሲሞቱ. . . አይተናል” ብሏል።

በተባበረ ክንድ መከላከል

ኤችአይቪ አሁንም የጤና ስጋት መሆኑን የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃም በዓለም ላይ እስካሁን ከ40 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መሞታቸውን ያመለክታል።

ይህ ቫይረስ ገና መድኃኒት ባይገኝለትም መከላከል የሚቻል በሽታ ነው።

ወይዘሮ ሕይወት አረጋዊ አሁን እየታዩ ያሉ ውጤቶችን መሠረት በማድረግ ሕብረተሰቡን በበቂ ሁኔታ ማስተማር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

“በሚገባ ሕብረተሰቡን ለመጠበቅ መደበኛ ጥናት እና ምርምር መደረግ አለበት። የመከላከያ እርምጃዎችም መወሰድ አለባቸው። ይህ ካልተደረገ ምን ያህሉ በቫይረሱ መያዙ እና ሥርጭቱ በመቶኛ ምን ያህል እንደሚሆን አይታወቅም። በዝምታ እና በቸልታ ሕዝቡን ይጨርሳል ብለን ነው የምንሰጋው” ብለዋል።

በተጨማሪም የመመርመሪያ መሳሪያዎች፣ ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቶች፣ ኮንዶም እና ሌሎች የመከላከያ እርምጃዎች እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።

“ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ መድኃኒት የተላመደ ቫይረስ ይስፋፋል። ካለው ችግር አንፃር የተለየ ትኩረት እንደሚያስፈልግ መታሰብ አለበት። እኛ ከባድ አደጋ ላይ ነን፤ መንግሥት ግን እንደ ሥርጭቱ መጠን እየሠራ አይደለም። ባለው ነገር እየታገለ ያለው ባለሙያ ብቻ ነው” ይላሉ።

አቶ ይርጋ ገብረእግዚአብሔር በዚህ ጉዳዩ ላይ ይስማማል፤ የፖለቲካ አመራሩ ሁኔታውን እንደ ስጋት በመውሰድ የፖለቲካ ቁርጠኝነትን ማሳየት እንዳለበት ያምናል። ይህንን የሚያግዙ አገራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማትም ጥሪ ሊደረግላቸው ይገባል ባይ ነው።

እሱ እንደሚለው እየታየ ያለውን አስደንጋጭ የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት፤ የመመርመሪያ መሳሪያዎች፣ መድኃኒቶች፣ በበሽታው ከተያዙ እናቶች የሚወለዱ ጨቅላ ህጻናት ምርመራ እና የመከላከል ሥራ ሊሰራ ይገባል።

ይሁን እንጂ የፌደራል ባለሥልጣናት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመጥቀስ በቂ አቅርቦቶችን እየላኩ አይደለም ይላል።

እስካሁን 72,000 ሰዎችን መመርመር የሚያስችል መሳሪያዎች እንደመጣላቸው በመጥቀስ “መርምራችሁ ውጤቱን አሳዩን እና አማራጭ እንፈልጋለን” እንደተባሉ ለቢቢሲ ገልጿል። “የሚመጣው መድኃኒትም ውስን ነው” ይላል።

“ከቀሪው ዓለም ተለይተን ለሦስት ዓመታት ቆይተናል። የምርመራው ሂደት ተለውጧል። ለዚህም ሥልጠና ያስፈልጋል። የገንዘብ ድጋፍም ያስፈልጋል። የነበሩን መኪኖች በሙሉ ተወሰደዋል። የትራንስፖርት ችግር አለ”

አክሎም ቢሮው ባሉ አቅርቦቶች ተሯሩጦ ለመሥራት የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አቶ ፍስሐ ያስረዳሉ።