ዘውዱ ሃፍቱ

1 መስከረም 2023, 07:48 EAT

በጦርነት ምክንያት ለሁለት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው በአደባባይ የአሻንዳ በዓል ከሳምንት በፊት በትግራይ ክልል በደማቅ ሁኔታ መከበሩ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ ግን በመቀለ ከተማ ውስጥ የተፈጸመው ግድያ በርካቶችን አስደንግጦ አስካሁን ድረስ ዋነኛ መነጋጋሪያ ርዕስ ሆኗል።

የመቀለ ከተማ ነዋሪዋ ዘውዱ ሃፍቱ የናፈቀችውን የአሸንዳ በዓል ለመታደም ተዘጋጅታ እንዲሁም ጓደኛዋን ልደት ለማክበር ነበር ከቤቷ የወጣችው። ነገር ግን የገጠማት ያሰበችው ደስታ አልነበረም በከተማዋ አዲ ሓውሲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ምሽት ላይ አስካሁን ባልታወቁ ሰዎች እና ባልተወቀ ምክንያት ግድያ ተፈጽሞባታል።

ይህ ግድያ ለቤተሰቦቿ ከባድ እና መሪር ሐዘንን ከማስከተሉ ባሻገር በመቀለ ከተማ እና ከዚያም ባሻገር ባለው ሕዝብ ዘንድ ድንጋጤን ፈጥሯል። ክስተቱም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መነጋገሪያ ሆኖ ግድያውን የፈፀመው ማነው? ለምን? የሚሉ ጥያቄዎች በማስከተል ከዚሁ ጋር የተያያዙ የተለያዩ መላ ምቶች እና ግምቶች እየተሰጡ ነው።

ቢቢሲ የሟቿን ወጣት የዘውዱ ሃፍቱ ቤተሰብን፣ የዐይን እማኞችን እና የመቀለ ከተማ ፖሊስን በግድያው ዙሪያ ያላቸውን መረጃ ጠይቋል።

ሁሉን ነገሯን የቤተሰቦቿን ሕይወት ለመለወጥ ሰጥታለች የምትለው ብርትካን ሃፍቱ የሟች ዘውዱ ታናሽ እህት ናት። ዘውዱ ተወልዳ ያደገችው በመቀለ ከተማ ማይ አንበሳ በሚባል አካባቢ ነው። ቤተሰቧ ካሏቸው ሦስት ልጅች መካከልም የበኩር ናት።

አባቷ በጥበቃነት ተቀጥረው እናቷ ደግሞ ጠላ ጠምቀው እየሸጡ ነው ልጆቻቸውን ያሳደጉት። ዘውዱ ከሼባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በአካውንቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛለች።

ከዚያ በኋላ በተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥራ በመሥራት እራሷን እና ወላጆቿን ታስተዳድር ነበር። ዘውዱ በአካባቢዋ በአብዛኛ ዕቁብ በመሰብሰብ ትታወቃለች።

በትግራይ ጦርነት ሲካሄድ ወደ አዲስ አበባ ሄዳ ተመሳሳይ ሥራ ትሰራ ነበር። ጦርነት ቆሞ ሰላም ከወረደ በኋላም ወደ ትግራይ ተመልሳ ከቤተሰቧ ጋር በመሆን ቀደም ሲል ስትሠራ የነበረውን ሥራ መልሳ በመጀመር፣ ቤተሰቦቿን መደገፍ ቀጥላ እንደነበር ቤተሰቦቿ ተናግረዋል።

ብርቱካን ታላቅ እህቷ ስትገልጻት “ዘውዱ ማለት ለእህቶቼ እና ለወላጆቼ እንጂ ለራሴ ብላ ሕይወቷን አልመራችም። እኔ ታናሽ እህቷ ነኝ፤ የራሴን ሕይወት እየመራሁ ነው። አግብቼ ወልጃለሁ። እሷ ግን እህቶቼ ላይ ለውጥ ሳላይ፣ ወላጆቼን ጥግ ሳላስይዝ ትዳር አልመሰርትም ብላ አላገባችም፤ አልወለደችም” ስትል ዘውዱ የቤተሰቡ ተንከባካቢ እንደነበረች በመሪር ሐዘን ትናገራለች።

ቅዳሜ ነሐሴ 13/2015 ዓ.ም. ዘውዱ ለአሸንዳ በዓል ፀጉሯን ተሰርታ፣ የተለመደ ሥራዋ የሆነውን ዕቁብ ሰብስባ ከጓደኛዋ ጋር በመሆን የአንዲት ጓደኛቸውን የልደት በዓል ለማክበር ነበር ልብሷን ቀይራ ከቤቷ ወጣች።

“የጓደኛቸው ልደት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ ነበር፤ ለምን ወደ አዲ ሓውሲ እንደሄዱ አልገባኝም” ትላለች ብርቱካን።

ከዚያ በኋላ በዕለቱ ምሽት ላይ አደጋ አጋጥሟት አይደር ሆስፒታል ውስጥ እንደምትገኝ በስልክ እንደተነገራት እና የመጨረሻ ቃሏን ሳትሰማ እህቷ እንደተለየቻት በተሰበረ ልብ ትገልጻለች።

የወጣቷ ሞት ምክንያት ምን እንደሆነ ሳይታወቅ እንቆቅልሽ መሆኑ ለቤተሰቧ ሌላኛው ጭንቀት ሆኗል። እህቷ ዘውዱ በምን ምክንያት ሕይወቷን እንዳጣች፣ ቤተሰቦቿ የሞቷን ምክንያት መገመትም ሆነ ማወቅ እንዳልቻሉ ትናገራለች።

“ጠላት የላትም” የምትለው የዘውዱ እህት፣ ዘውዱ ከሰዎች ጋር ጥሩ መቀራረብ እና ግንኙነት እንዳላት በመጥቀስ ገዳዮቿ አለመታወቅ እና ሞቷ ከቤተሰብም በላይ በዙሪያዋ ያሉ ሰዎችን ግራ ያጋባ ነው።

“በሰላም ወጥተሽ በሰላም ግቢ ብለው የሚመኙላት እንጂ መጥፎ የሚያስብላት ሰው የለም። ጠላት ሳይኖራት ማንን ልንጠረጥር እንችለን?” በማለት የእህቷ ግድያ እንቆቅልሽ እንደሆነባት ትናገራለች።

የመቀለ ፖሊስ ግድያው ከተፈጸመበት ደቂቃ ጀምሮ የዘውዱ ገዳዮችን ለመያዝ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ የከተማዋ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የጽህፈት ቤቱ አዛዥ ኮማንደር ወልዳይ መውጫ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ግድያውን ለማጣራት ከዞኑ እና ከክፍለ ከተማ የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያካተተ ልዩ ቡድን ተቋቁሟል።

ኮማንደሩ ምርመራው እልባት ባለማግኘቱ እና ዝርዝር አስተያየት መስጠት የምርመራውን አካሄድ ስለሚቃረን ምርመራው የደረሰበትን ደረጃ አስመልክቶ ከመናገር ተቆጥበው “ምርመራውን በማጠናቀቅ እና ወንጀለኛውን በመያዝ ውጤቱን ለሕዝብ የምናሳውቅበት ዕድል እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

በማኅበራዊ ሚድያ ላይ ከሚገለጸው ሌላ ሕብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር ትብብር እያደረገ እንደሆነ የገለጹት ኮማንደሩ፣ በሂደቱ የአካባቢው ሕብረተሰብ ተሳትፎ አሁን ካለው በላይ መሆን አለበት ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ግድያው ተፈጽሞበታል የተባለው የአዲ ሓውሲ አካባቢ መንገድ ከደስታ ሆቴል እስከ ሊባኖስ ሆቴል የሚወስደው ሲሆን በተለምዶ በርካታ ሰው የሚንሳቀስበት ነው።

አቶ ኮኸብ አስፋሃ የሚኖሩት ወንጀሉ በተፈጸመበት ዓዲ ሓቂ ክፍለ ከተማ ነው። እንደ አጋጣሚ ሆኖ መንገዱን ሊያቋርጥ ሲል የፊት የሩቅ መብራት ያበራ ፒክ አፕ መኪና እየበረረ ሲያልፍ ተመልክተዋል። በዚያው ቅጽበት የሰዎች ጩኽት ወደ አሰሙበት ቦታ ሲደርሱ አስከሬን ማየታቸውን ተናግረዋል።

“ሁኔታው የተከሰተው ለሁለት ሰዓት ሩብ ጉዳይ ላይ ነው። ዘረፋ ተፈጸመ አልን እንጂ እንዲህ የሚዘገንን ወንጀል የተፈጸመ አልመሰለንም ነበር። መኪናው ከመጠን በላይ ሲበር እኔንም አስግቶኝ ነበር። ድንገት ሰዎች እሪታ እያሰሙ ወደተሰበሰቡበት ስጠጋ ደግሞ ሬሳ ወድቆ አየሁ” ሲል ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ከዚህ ክስተት በኋላ አስከሬኗ ተነስቶ ከሟች ጋር ከነበሩት ሴቶች ጋር በአምቡላንስ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እና ሆስፒታል እንዲሄድ መደረጉን የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“ስርቆት ይሁን ወይም ሌላ ዓላማ ያለው ነገር ግልጽ አይደለም፤ ጥቃት መሆኑን ግን መገመት አያስቸግርም። ከጎኗ የነበረች የሟች ጓደኛ ነገሩን ግልጽ ታደርገዋለች ብለን እንጠብቃለን” ይላሉ አቶ ኮኸብ።

ከድርጊቱ በኋላ የአካባቢው ሕብረተሰብ ከፖሊስ ጋር በመሆን ከግድያው ጋር ግንኙነት ያላትን መኪና በመከተል እና በማፈላለግ ሌሊቱን ሙሉ ጥረት ሲያደርጉ እንዳደሩ ነዋሪው ተናግረዋል።

ይህ የወጣቷ ግድያ የመቀለ ከተማ ነዋሪን በእጅጉ ያስደነገጠ ነው። ከክስተቱ ጋርተያይዞ ሰዎች የተለያየ መላምቶችን እየሰነዘሩ ነው። እስካሁን ግን የተገኘ ተጨባጭ ነገር የለም። ሁሉም የግድያውን ምክንያት እና የገዳዮቹን ማንነት ለማወቅ በጉጉት እየጠበቀ ይገኛል።

በተጨማሪም የሟች ዘውዱ ሃፍቱ ቤተሰቦችም የልጃቸው ደም በከንቱ ፈሶ እንዳይቀር የገዳዮቿን ማንነት ለማወቅ እና የልጃቸው ገዳዮች በፍትህ የእጃቸውን እንዲያገኙ ይሻሉ።

የሟች እህት ብርቱካን “በርካታ ወጣቶች በየበረሃው ቀርተዋል። ነገር ግን እህቴ ከተማ ውስጥ በሰላም በወጣችበት መቅረቷ በጣም ይከብዳል። ይህ በሌሎች እህቶቻችን ላይ እንዳይደገም ፍትህ መሰጠት አለበት” በማለት ሕዝብን እና መንግሥትን ተማጽናለች።