መርፌ

ከ 33 ደቂቃዎች በፊት

በዩናይትድ ኪንግደም የሰውነት ክብደት ለመቀነስ የሚያስችል ዌጎቪ (Wegovy) የተባለ መድኃኒት ሊሰጥ ነው።

የአገሪቱ ብሔራዊ የጤና ተቋም ይህን መድኃኒት በተወሰነ መጠን ማስገባቱን ተከትሎ ለሕሙማን ሊታዘዝ እንደሚችል ተገልጿል።

በመርፌ የሚሰጠው መድኃኒቱ በአገር አቀፍ ተቋሙ በኩል ወይም በግል ሕክምና መስጫዎችም ሊሰጥ ይችላል።

በአገሪቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሕሙማንን እንደሚረዳ ተገልጿል።

በዓለም የዚህ መድኃኒት እጥረት ስላለ ዋጋው መወደዱ ተዘግቧል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት መርፌው ከ10% በላይ ክብደት ለመቀነስ ያስችላል። ይህ የሚሆነውም ሰዎች ምግብ በልተው እንደጠገቡ እንዲሰማቸው አድርጎ ምግብ እንዳይበሉ በማስቻል ነው።

በአሜሪካና በሌሎች አገራት ታዋቂ ሰዎች ይህንን መርፌ ይወስዳሉ። ባለሙያዎች እንደሚሉት መድኃኒቱ ጤናማ አመጋገብና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አይተካም።

ሙከራ ሲደረግ መድኃኒቱን የወሰዱ ሰዎች መድኃኒቱን ሲያቆሙ ተመልሰው ክብደት ይጨምራሉ።

በዩኬ በምን ያህል ዋጋ እንደሚሸጥ እስካሁን ባይታወቅም በመደበኛነት አራት መርፌ በ73.25 ዩሮ ሲሸጥ ቆይቷል።

ተጠቃሚዎች በሳምንት አንዴ መርፌውን ይወስዳሉ።

ይህንን መርፌ የሠራው የዴንማርክ ድርጅት ኖቮ ኖርዲስክ ሲሆን፣ ምርቱን በስፋት እስኪያጠናቅቅ ድረስ ዓለም አቀፍ ማከፋፈል ላይ ገደቦች እንደሚኖሩ አሳውቋል።

“ለተወሰነ ጊዜ ምርቱ እንደሚቀንስ እንጠብቃለን። የተወሰነ ምርት ግን በዩኬ ገበያ ይቀርባል” ሲል መግለጫ አውጥቷል።

መርፌውን በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈልጉ ሕሙማን ቅድሚያ እንዲያገኙ ለማድረግ ከጤና ባለሙያዎች ጋር በቅርበት እንደሚሠራም ገልጿል።

ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው ሰዎች ሕክምናውን እንዲያገኙም እንደሚሠራ አክሏል።

በዩኬ መድኃኒቱን መውሰድ የሚችሉት ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸውና በሰውነት ክብደታቸው ምክንያት ለሕመም የተጋለጡ ሰዎች ናቸው።

ከተመጣጠነ ምግብና ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጋር ተደምሮ መድኃኒቱ ለሁለት ዓመታት ይሰጣል።

አሁን በዩኬ ሆስፒታሎች በኩል መርፌውን ማግኘት የሚችሉት ወደ 35,000 ሰዎች ሲሆኑ በቀጣይ ተጨማሪ ቁጥር ላላቸው ዜጎች እንደሚዳረስ ተገልጿል።

የተቋሙ ቃል አቀባይ እንዳሉት የመድኃኒቱን ዓለም አቀፍ እጥረት ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

ወደ 50,000 ሕሙማን መድኃኒቱን ማግኘት እንደሚችሉም ተናግረዋል።